Monday 22 February 2021

“በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ።” (ዮና. 3፥8)

 Please read in PDF

ጥንተ ታሪክ

ሊመጣ ካለው ቊጣና ፍርድ ታመልጥ ዘንድ፣ የንስሐ ዕድልን ሊሰጥ እግዚአብሔር የአማቴ ልጅ ዮናስን ወደ ነነዌ ላከ። ነገር ግን ነቢዩ ዮናስ እግዚአብሔር ላዘዘው ምላሹ አለመታዘዝና ወደ ራሱ ፈቃድ አዘንብሎ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሸሸ። እግዚአብሔር ግን ሉዓላዊና ኹሉን ሲያደርግ የሚሳነው የሌለ ነውና ዮናስን ወደ ነነዌ በራሱ ማጓጓዣ [በተአምራዊ መንገድ] በዓሳ አንበሪ ሆድ ጭኖ ነነዌ አደረሰው።


የዮናስ ስብከት

ዮናስ ነነዌን ውስጧን ተመላልሶ ካያት በኋላ የሰበከላት ስብከት፣ እጅግ አጭርና ግልጥ ነበር፤ በጩኸት ቃል፣ “በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች” (3፥4) ብሎ ተናገረ። ዮናስ የተናገራት ይህች አጭር ሐረግ፣ ነነዌ ፊቷን ወደ እግዚአብሔር እንድትመለስ አደረገ። አሦር የቀደመ ዘመን ብርታትዋ ተዳክሞ፣ በዙርያዋ ያሉት ጠላቶችዋ እየተነቃቁ ነበርና ለመመለስ ጊዜ አልወሰደባትም። እንደ ዮናስ ዐሳብና አለመታዘዝ ሳይኾን፣ ከእግዚአብሔር ቃል የተነሣ የሕዝቡ ልብ ለዘበ፤ ታዘዘ። የእግዚአብሔር አገልጋይ ለእግዚአብሔር ባይታዘዝ፣ እግዚአብሔር ግን በሉዓላዊነቱ ሥራውን ከመሥራት የሚያግደው የለም። እናም ንጉሡ እንኳ ሳይቀር፣ የነነዌን መገለባበጥ ስብከት ሲሰማ፣ ኹሉም ሰው በሚያየው ሥፍራ ተቀመጠ፤ እንደ ባሪያ ማቅ ለበሰ፤ ዐመድ ነስንሰ፤ ተዋረደ። እውነተኛ ንስሐ ገባ፤ ከዚያም አዋጅን አወጀ!

 

የንጉሡ “ስብከት”

ንጉሡ የወሰደው እርምጃ፣ አንድ እውነተኛ መንፈሳዊ ሰው ሊያደርገው የሚገባውን እውነተኛ ተግባራዊ ምላሽነት ያዘለ እርምጃ ነው። ወዲያው ንስሐ ገባ። ስብከቱ አጭር፣ እርምጃውና ውሳኔው ግን እጅግ አስደማሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አጭር ስብከት ተሰብከው ወዲያው ስለሚመለሱ ሰዎች እጅግ ብዙ ምስክሮች አሉት፤ ለመመለስና ከክፋት ዘወር ለማለት የስብከት መርዘምና ማጠር ሳይኾን የልብና የውስጥ ውሳኔ ነው።

ንጉሡ ካወጃቸው አዋጆች ውስጥ “ከግፍ ተመለሱ” የሚል ጽኑ ቃል አለ። ግፍ ሕግና ምስክር የማይደርስበት፣ ከገዛ ኅሊናና ከእግዚአብሔር ፊት ግን የማናመልጥበት የክፋት ሥራ ነው። አሦራውያን ዓለምን ሲገዙና ግዛታቸውን ሲያስፋፉ፣ እጅግ አያሌ ግፎችን ከእነርሱ በሚያንሱ አገራት፣ ሕዝቦች፣ ጐረቤት በኾኑት አገራት ላይ ጭምር ፈጽመዋል። በዚህም እጅግ በጭካኔ ተሞልተው ርኅራኄና ምሕረትን ጥለው ነበር። ስለዚህም ንጉሡ በግልጥ እንዲህ ተናዘዘ፤ “እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ኾነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ኾነ ማን ያውቃል?”። በማለት በመሐሪው ምሕረት በመታመን ተመለሱ። የነነዌ ሰዎች ከግፋቸው ስለ ተመለሱና ግፋቸውን ስለ ተዉ፣ እግዚአብሔርም በርኅራኄ አዝኖ ተመለሰ።

ምን ቀረልን፤ ምንስ እንማራለን?

“በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት” የነነዌ ጾም ዛሬ ይጀምራል፤ ለሦስት ቀናት ያህል። የሚጾምበትም ምክንያት፣ እግዚአብሔር ለነነዌ ያደረገውን ምሕረትና ርኅራኄ ለእኛም ያደርግ ዘንድ በሚል “መልካም መሻት” ነው፤ ግን ብዙ ጊዜ ከሃይማኖታዊ ሥርዓት የዘለለ ባይኾንም። ምክንያቱም እንደ ቤተ ክርስቲያንም እንደ አገርም የፈጸምናቸው አያሌ ግፍና ዓመጽ በመካከላችን አለ። በዘር፣ በብሔር፣ በጐሣ፣ በቋንቋ፣ መንግሥትን ጨፍነን በመደገፍና በመቃወም … ተቧድነን በጥላቻ ውስጥ ኾነን፣ ከብሔራችን ውጭ ያለውን ሰው እንጀራ የነጠቅን፣ የሰው ደም በግፍ ያፈሰስን፣ ሰውን ያስጨነቅን፣ ድኾችን የነጠቅን፣ ከስውር ያለፈ ሥልጣንን፣ ዘመድን፣ ብሔራችንን፣ መንደራችንን፣ ጐጣችንን … ተገን አድርገን በአደባባይ ግፍን የፈጸምን ቊጥራችን የትየለሌ ነው።

እናም እንደ ነነዌ እውነተኛ ምላሽ የሚኖረን፣ እውነተኛ ንስሐ ስናደርግና ግፋችንን ስንተውና በግፋችን እውነተኛ ብሔራዊ ንስሐ ስንገባ ብቻ ነው፣ እንጂ ሃይማኖታዊ ልማድን ስለ ፈጸምን አይደለም። ጌታ መንፈስ ቅዱስ በትክክል እንደ ቃሉ እንድንኖር እውነተኛ ንባብና ያነበብነውን በመታዘዝ መመለስን ያብዛልን። አሜን።

3 comments:

  1. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come.

    ReplyDelete
  2. I want to say something just it was Amazing. AMAZING

    ReplyDelete
  3. መልካም አገልግሎት ነው በእውነት ለሌሎችም ትምህርት ነው በሁሉም አቅጣጫ 😍😍

    ReplyDelete