Tuesday 2 February 2021

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፭)

 Please read in PDF

ካለፈው የቀጠለ …

·        እግዚአብሔርን መምሰል

“በርካታ የምዕራብ ክርስቲያኖች የኦርቶዶክስን የቲኦሲስ ወይም እግዚአብሔርን የመምሰል ሥነ ሐሳብ በትክክል ሊረዱት አልቻሉም። በተለይም ‘ሰው አምላክ ይኾን ዘንድ አምላክ ሰው ኾነ’ የተሰኘውን የቅዱስ አትናቴዎስን ጥቅስ ሲያነቡ፣ ይህ የምሥራቃዊ ሂንዱይዝም ወይም የፓንቴይዝም ተጽዕኖ ነው በማለት ያስባሉ።”[1]

“በቅድስና እግዚአብሔርን በመምሰል የማደግ ሂደትም ከእግዚአብሔር ቅድስና የመሳተፍ ሱታፌያዊ ሂደት ነው። … ሐዋርያው፣ ‘ … ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን።’ ያለው የባሕርዩ መገለጫና መታወቂያ የኾኑትን ነገሮች - ኃይላተ እግዚአብሔር ቅድስና፣ ቸርነት፣ ደግነት፣ ጥበብ፣ እውነተኛነት፣ ገዢነት … የመሳሰሉትን ገንዘብ እናደርግ ዘንድ የተሰጠን በመኾኑ ነው። ይህም ከፓንቴይዝም እርሾ የጸዳ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ሐዋርያዊ ትምህርት ነው።”[2]



ያረጋል አበጋዝ ሱታፌ አምላክነት የፓንቴይዝም ተጽዕኖ የለበትም ቢልም፣ ስለ አሥሩ ማዕረጋተ “ቅዱሳን” በገዛ እጁ በጻፈው ሌላኛው መጽሐፉ እንዲህ ይላል፤

“ከዊነ እሳት የመጨረሻው ማዕረግ ሲኾን እዚህ ደረጃ የደረሱ ቅዱሳን ሰውነታቸው ለአጋንንት የሚያቃጥልና የማይቀረብ ይኾናል። … ተሐዋስያን ከሰውነታቸው ሲያርፉ እሳት እንደ ገባ ጅማት እየተኮማተሩና እያረሩ ይወድቃሉ። … ለነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ ይበቃሉ፣ ሥላሴን ያያሉ፣ የጌትነቱ ብርሃን በሕሊናቸው ይገለጽላቸዋል። … ሥጋዊ አኗኗርና አስተሳሰብ ፈጽሞ ይረሳቸዋል፣ ጾር ይጠፋላቸዋል … ”[3]

ያረጋል አበጋዝ፣ ሱታፌ አምላክነትን ወይም የጸጋ አምላክነትን ለመስበክ እንዲረዳው ደግሞ ከተጠቀመባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል፣ ዘጸ. 7፥1 እና 2ጴጥ. 1፥4ን ማዕከል ያደረገ ነው። ነገር ግን እኒህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በትክክል ላስተዋለና እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ላጠና ሰው፣ ሰዎች አድገው፤ አድገው የጸጋ አማልክት ወይም የጸጋ አምላክ መኾናቸውን የሚያመለክቱ አይደሉም።

ዘጸ. 7፥1፦ ቃሉ እንዲህ ይላል፣ “እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል።” በዚህ ክፍል ላይ ሙሴ በፈርዖን ላይ አምላክ መኾኑን ተጠቅሶ እንመለከታለን፤ ቃሉ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ “አምላክ” ተብሎ የተጠቀሰው ቃል፣ “ኤሎሂም” የሚለውን ቃል የሚወክል ነው። “ኤሎሂም” የሚለውን ቃል ደግሞ፣ እንደ አገባቡ ለብዙ አካላት ውሎ እናገኘዋለን፤ ለምሳሌ፦ ኤሎሂም ጣዖታትን (ዘፀአ. 18፥11፤ መዝ. 95፥3፤ 96፥5)፣ መላእክትን (መዝ. 8፥5) እና ሰዎችን ሊያመለክት ይችላል፤ (ዘፀአ. 7፥1፤ 21፥6፤ 22፥8፤ መዝ. 82፥1-6፤ ዮሐ. 10፥34-35)። ኤልና ኤሎሂም እንደ ዐውዱ በአምላክ ወይም በአማልክት ሊተረጐሙ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ ግን ትክክለኛ ትርጕም የሚኾነው እግዚአብሔርን የሚያመለክት ነው።[4]

ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ በእግዚአብሔር አንደበት “እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል።” (ዘፀአ. 7፥1) በማለት ሲነገረው፣ የተነገረበት ዋና ዐላማው ራሱ አምላከ ጸጋ ስለ መኾን አይደለም፤ ምክንያቱም ትኾናለህ እያለ ያለው እግዚአብሔር ነውና፤ ልኹን እንኳ ቢል ሠጪው እግዚአብሔር እንጂ ሙሴ የጸጋ አምላክ የኾነ አይደለም። ይህ የተባለበት  ዋናው ምክንያት ግን ሙሴ በፈርዖን ቤት ላይ ከሰማይ ማለትም፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሰጠው ኃይልና ሥልጣን በሚያደርገው ታላቅ ተአምራትና መቅሰፍት ነው፤ በዚህ ጉዳይ አሮንም “ነቢይ” በመኾን ለፈርዖን መልእክትን ያመጣል። ስለዚህ ኤሎሂምነት ለአንድ ለተላከበት ጉዳይ የተሰጠውን ሥልጣን የሚያመለክት ነው።

ቅዱሳን ሐዋርያት በአንድ ወቅት በልስጥራ “እግሩ የሰለለ፥ ከእናቱም ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የኾነ፥ ከቶም ሄዶ የማያውቅ አንድ ሰው” (ሐዋ. 14፥8) በጌታችን ኃይልና ችሎታ ሲፈውሱ፣ በዙሪያቸው የነበሩት ሰዎች እጅግ አከበሯቸው፤ ከማክበርም አልፈው “አማልክት ሰዎችን መስለው ወደ እኛ ወርደዋል” በማለት እንደ አማልክቶቻቸው ስያሜ ስምን ሰጥተዋቸው፣ መሥዋዕትን ሊያቀርቡላቸው ወደዱ። እንደ አንዳንዶች ግምት ይህ የአገልግሎት ክብር እንደ ኾነ ሊናገሩ የሚደፍሩ ይኖራሉ።

ነገር ግን ሐዋርያት “አማልክት ነን” ብለው ፈቅደው አልተቀበሉም፤ ይልቁን “ … ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥ እንዲህም አሉ፦ እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ኹሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። …ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው።” (ሐዋ. 14፥14-18)። በአይሁድ ልማድ ልብስን መቅደድ ከባድ ሐዘንን ገላጭ ነው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት በተደረገላቸው ነገር ሐዘናቸውን ገልጠው፤ ላለመቀበልም ፊት ለፊት ተጋፈጡ። ሰዎች ብቻ እንጂ አማልክት አይደሉምና።[5]

2ጴጥ. 1፥4፦ እግዚአብሔር አምላክ እንድንመስለው ይፈቅዳል፤ እኛ እርሱን እንድንመስል የፈቀደበት ጠባይ ደግሞ ግልጥና የተብራራ ነው። ከክፍሉ እንደምንረዳው እግዚአብሔርን መምሰል እንደሚገባን ለመናገር እርሱን ለመምሰል የተካፈልነውን ባሕርይ ይገልጣል። እንዲሁም በመቀጠል ይህ ባሕርይ እንዴት ባለ ትጋት ሊገለጥ እንዳለ ይነግረናል፤ ይኸውም ልንመስለው የሚገባን በእውነተኛ መንፈሳዊነት ማለትም እርሱን በማመን፣ በበጐነቱ፣ በእውቀት፣ ራስን በመግዛት፣ በመጽናት፣ በመዋደድ እንጂ መለኮትን በጸጋ አማልክትነት ስለ መኾን አይናገርም።

በቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር፣ አማኞች እግዚአብሔርን የሚመስሉት “ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት በማምለጥ” ነው፤ እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስና ንጹሕ ነው፤ ሰው ግን ቅድስናን ገንዘብ የሚያደርገው ከክፉ ነገር በእግዚአብሔር ጸጋ፤ በክርስቶስ የመስቀል ሥራ በማምለጥ እንጂ ኖሮ፤ ኖሮ ወደ ከዊነ እሳትነት በማደግ የእግዚአብሔር “ብዜት” ኾኖ አይደለም። 1ጴጥ እና ገላ. 5 ላይ የተገለጠውን የመንፈስ ፍሬ የያዘን ወይም እውነተኛ መንፈሳዊነትን የያዘን ሰው የሚያመለክት ነው። ነገር ግን ይህ የጸጋ አምላክ መኾንን የሚያመለክት አይደለም።

በዮሐ. 17፥22-23 ውስጥ እና 1ጴጥ.1፥4 እንደ ተገለጠው እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት አለን። እንዲሁም “የመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች” ነን። ይህ ማለት በክርስቶስ ማንነትና ሥራ በኩል የቅድስና የፍቅር እና የዘለዓለማዊ ሕይወት ተካፋዮች እንኾናለን ማለት እንጂ ኅብረታችንና የመለኮት ባሕርይ ተካፋይ መሆናችን ተፈጥሯዊ (Ontological) ለውጥ ያመጣል ማለት አይደለም።[6]

የመለኮት ባሕርይ ተካፋይ በመኾናችን ወደ ፍጹም እሳትነት አንለወጥም፤ ወይም የሥጋ አኗኗርን ጨርሰው አያውቁትም ወይም ሰውነታቸው አንዳች ኀይልን እንደ ለበሱ ለተሐዋስያን እንኳ የማይመች እሳት ይኾናል የሚል ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ጨርሶ የለም። መቼም ይህ በሰማይ ነው ከተባለ፣ በሰማይ እንዲህ ያለ የተሐዋስያንና የበራሪ ነፍሳት ተረት በዚያ የለም፤ በዚህ ምድር ከኾነ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰ አንድም ምስክር ማቅረብ አይቻልም።  

እውነተኞቹና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የኾኑቱ ኦርቶዶክሳውያን፣ የተሳሳቱ አመለካከቶች ግራ እንዳያጋቡ ለመከላከል የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ማንነትን እና የእግዚአብሔርን ኃይል (ኢነርጊያ) በመለየት ጥንቃቄ ያደርጋሉ። እግዚአብሔር በመለኮታዊ ባሕርዩ (ኡስያ) መታወቅ የማይቻል ነው። ነገር ግን ፍቅር የኾነው እግዚአብሔር በኢነርጊያው አማካይነት እርሱን እንድናውቀው ፈቅዶልናል። በፍጥረቱ አማካይነት በልግስናው እና በመቤዠቱ ለእኛ ራሱን ገልጦልናል። በመለኮታዊው ኢነርጊያው አማካይነት እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር አንድነት እንዲኖረን ፈቃዱ ሆኗል።[7]

በሥጋ በተገለጠው በክርስቶስ ጸጋ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር መተባበርን ወይም ኅብረትን እንለማመዳለን። ቲኦሲስ ወይም “እግዚአብሔርን መምሰል” እውን የሚኾነው በቅድስና፣ ፍጹም በመደረግ፣ ባልተቋረጠና ቀጣይ በኾነ መንፈስ ቅዱስን የመቀበል ሂደት ነው። … እኛ ከፈቀድንለት ወይም ፈቃዱን ከመረጥን ደካማ ቈሻሻ የሆንነውን ሰዎች፣ ልንገምተው ወደማንችለው ደረጃ፣ ምንም እንኳ አኹን በጥቂቱ የምንለማመደው ቢሆንም፣ ወሰን በሌለው ውበት፣ ዘለዓለም ነዋሪ፣ ኀይልን የተሞላን፣ ጥበብና ፍቅር የተሞላን ፍጡራን አድርጎ እርሱን እንድናንጸባርቅ ወደ ራሱ መልክ ይለውጠናል። ይሁን እንጂ ሂደቱ ረጅም እና በከፊል በጣም መከራ የተሞላ ነው። ነገር ግን ይህ የምንኾነው ነገር ነው፤ ጌታ ማለት እንደ ተናገረው እንደ ቃሉ ስለ ኾነ ምንም የሚቀነስ ነገር የለም።[8]

ከዚህ ባሻገር አንዳንዶች፣ “እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ታላቅ ነው” በማለት የሚጠቅሱት፣ ቃሉ የተነገረው ለሥጋዌ ይኸውም ለአስተርእዮተ እግዚአብሔር እንጂ ፈጽሞ ለእኛ አይደለም። እንግዲህ የመድሎተ ጽድቅ ጸሐፊ፣ አስቀድሞ የምናስተምረው ብዝሐ አማልክትን አይደለም ብሎ ስጋቱን ቢገልጥም፣ ብዝሐ አማልክት መኾኑን ግን ማስተባበል አይችልም። በክርስቶስ የሚያምኑ የተዘጋጀላቸው ክብር አለ፤ ይኸውም ወደ ተፈጠሩበት ክብር በመመለስ፣ እግዚአብሔርን ይመስላሉ እንጂ ፈጽሞ የጸጋ አማልክት አይኾኑም አልያም የጸጋ አምላክነትን አይቀበሉም!

ይቀጥላል …

 

 



[1] በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ ገጽ 22

[2] መድሎተ ጽድቅ፤ ገጽ 110

[3] ያረጋል አበጋዝ(ዲያቆን)፤ ፍኖተ ቅዱሳን፤ 1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ማተሚያ ቤቱ ያልተጠቀሰ፤ ገጽ 206

[4] ቄስ ኮሊን ማንሰል፤ ትምህርተ እግዚአብሔር፤ 1995 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት። ገጽ 174

[5] አቤንኤዘር ተክሉ፤ የእምነት አንቅስቃሴ የዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ፈተና፤ ገጽ 114-115

[6] በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ 2010 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ኤልያኪም ማተሚያ ቤት፤ ገጽ  23-24

[7] አቤንኤዘር ተክሉ፤ የእምነት አንቅስቃሴ የዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ፈተና፤ ገጽ 114-115

[8] በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ ገጽ  25-26 እና C.S. Lewis, 1952, p. 174

10 comments:

  1. Egziabiher ybarklingn

    ReplyDelete
  2. GOD bless you for sharing. May the SPIRIT be your guide & strength for days to come.

    ReplyDelete
  3. ወደ የትኛው ቃል ለማንም ያልተረዳው አረዳድ ተረዳውት ከዚህ ላይ ይህ ጎሎታል ብሎ የተጨመረበት የተኩላው መንገድ ለማያውቅሽ ታጠኝ

    ReplyDelete
  4. ወንበዴ መናፍቅ

    ReplyDelete
  5. እስኪ ዝም ብለህ የራስህን አጥብቅ!!! በመጀመሪያ አንተ አይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣና ከዚያ የሌላውን ጉድፍ ማየት ትችላለህ

    ReplyDelete
  6. መንገድ የጠፋህ መናፍቅ

    ReplyDelete
  7. 2ኛተሰ2:1---10 የመናፍቁ ሸሱሴ

    ReplyDelete
  8. አየ አለማወቅ ደጉ!!!! ዱልዱሞች ግን ምን አለባችሁ

    ReplyDelete
  9. ወተት ጠጣ መጀመርያ

    ReplyDelete
  10. አቤኔዜር የስምህን ትርጓሜ
    ድንጋይ ማለት መሆኑን ስነግርህ ስሙ ይመርሖ ኀበ ግብሩ እንደተባለ ትልቅ ቋጥኝ ነህ
    አቤቤነዜር

    ReplyDelete