Sunday 24 January 2021

የማርያም ምስልና የሚካኤል ክንፍ!

 Please read in PDF

መግቢያ

በብዙዎች ዘንድ ከምንከሰስበት ነገር አንዱ፣ “ስለ ማርያም አትሰብኩም፤ ስለ ቅዱሳንም አትመሰክሩም” የሚል ክስ ነው።  ይህን የሚሉ አካላት እያወቁም ይኹን በጽንፈኝነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ተቃራኒ በመኾን ዘመናቸውን ስለ ማርያምና ስለ ቅዱሳን “በመስበክ” ይከስራሉ። ከዚህም የተነሣ አያሌዎች ማርያምን በመስበክ የታወቁ ናቸው። ከሰሞኑ እንኳ ካየነው የዘበነ ለማን ዓይን ያወጣ ግብዝነት ማንሳት እንችላለን። ይህን ሳሰላስል የመጣልኝ አንድ አስቂ ታሪክ አለ። መልአኩ ሚካኤል አንድ ክንፉ ያዘቀዘቀበት ምክንያትና የማርያም ከፍጥረተ ዓለሙ በፊት መታየት።



የተረቱ ተራቾች ታሪክ

በአንዳንዶች ዘንድ መልአኩ ሚካኤል ከተሰጡት ስሞች መካከል አንዱ፣ “መልአከ ምክሩ” የሚል ነው። ይህንም ስያሜ ሊያገኝ የቻለው እንዲህ ነው በማለት ይተርታሉ፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ መላእክትን ፈጠረ፣ ከመላእክትም መልዐከ ምክሩ የተባለውን ሚካኤልን አቀረበው፤ ከዚያም በወደቀው በሳጥናኤል ፈንታ ሰውን ፈጠረ፤ ወደ ሚካኤልም አመጣው፤ ሚካኤልና ነገዱም ደስ አላቸው፤ ከዚያም የሰውን ውድቀት አመለከታቸው፤ ሚካኤልና ነገዱ አዘኑ፤ እናም በውድቀቱ አዝነው እግዚአብሔርን አትፍጠረው ይቅር አሉ። ከዚያም እግዚአብሔር ማርያምን ፈጠረ፤ ወደ መላእክቱም አመጣት፤ በእርሷ እጅግ ደስ ተሰኙ፤ እናም መላእክቱ እንዲህ አሉ፤ “ስለ እርሷ ብለህ እርሱን[ሰውን] ፍጠረው” አሉት፤ ፈጠረ። ጊዜው ደርሶ ማርያም እስክትገለጥም፣ እግዚአብሔር የማርያምን ምስል ወስዶ ከሚካኤል ክንፍ ላይ አተመው፤ ሚካኤልም ከዚያን ቀን ጀምሮ ለማርያም ምስል ክብርን ስለ መስጠት በአንድ ቀኙ አጋደለ፤ ሚካኤል ሲሳል ክንፉ እንዲያጋድል የተደረገውም ለዚህ ነው ይላል ተረቱ።



ቅዱስ ቃሉ ምን ይላል?

እግዚአብሔር ፍጥረትን ብቻውን ፈጠረ፤ ማንም ምን አላማከረውም፤ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።” (ዘፍ. 1፥1)፣ “ … እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም። … እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤” (ኢሳ. 40፥26-27) “… አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል።” (ኢሳ. 37፥16)፣ “በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚከለክላት ወይም፦ ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም።” (ዳን. 4፥35)፣ “ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” (ሮሜ 11፥36) እንዲል፣ ኹሉን ብቻውን የፈጠረና ለራሱ ክብር ወደ መኖር ያመጣው እግዚአብሔር ነው።

ፍጥረትን ሲፈጥር ከእርሱ ጋር ማንም አልነበረም፤ አልረዳውም፤ አላማከረውምም፤ ብቻውን ፈጥሮ ብቻውን ይመግባል፤ ይቈጣጠራልም። ደግሞም ፍጥረት ለእርሱ ብቻ ክብርን ይሰጣል።

የማርያም ሰባኪዎች

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማርያምም ኾነች ማናቸውም በሰማይና በምድር ያሉ ቅዱሳን የስብከት ርዕስ ወይም የስብከት ማዕከል ሊኾኑ እንደማይችሉ ይናገራል፤ በግልጥ ቃል፣ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤” (1ቆሮ. 1፥23) በማለት። ማርያምን ከኹሉ በላይ ለማድረግና “ወደ አራተኛ ሥላሴ” ለማስጠጋት ብሎም የተሰቀለውን ክርስቶስን ለመጋረድ የሚተረኩ አያሌ ተረቶችና ድርሳናት አሉ።  በዚህ መንገድ ግን ማርያምንም ኾነ ማናቸውንም የሰማይ ኀይላት አናከብርም።

እንደ ዘበነ ለማ፣ ምሕረተአብ አሰፋ ያሉ የማርያምን ቤዛነት ሰባክያን እንዲህ ካለ ጸያፍ ተግባራቸው መታቀብ፤ ማፈርም ይገባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማርያም የሚናገረውን “እናስተምራለን” እንጂ አንሰብክም፤ ስብከትና ምስክርነት ከክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛነትና ከመስቀሉ ሥራ ጋር ብቻ የተገናኘ ነው።  ሐዋርያት የሰበኩትና የመሰከሩት የሰው ልጆች መዳን የኾነውን የክርስቶስን ሞትና መስቀል ብቻ ነው። ከዚህ የወጣው ትምህርት እንጂ ስብከት ሊኾን ከቶ አይችልም፤ መዳን አይገኝበትምና። ለምን ስለ ማርያምና ሌሎች ፍጡራን አትሰብኩም ለሚሉን፣ ከዘላለም ሞት ስለማያድኑና ስለማይቤዡ ነው ብለን እንመልስላቸዋለን።

ማጠቃለያ

ጌታ ኢየሱስ ከማርያም መወለዱ ወደ ዓለም እኛን ለማዳን የገባበት አስደናቂ ተአምር ነው።  ተአምርነቱም የእርሱ ወደ እኛ ለመውረድ ከእርሷ ያለ ወንድ ዘር ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ መወለዱ ነው። ይህ ፍጥረት ከተፈጠረ ጀምሮ ያልተደረገ ወደፊትም የማይደረግ አስደናቂ የማዳን ተግባሩ ነው፤ በዚህ ጉዳይ እርሱን እናደንቃለን፤ እንወድሳለን እንጂ በዚህ ስፍራ የተገኙትን ማርያምን፣ በግርግም የነበሩ እንሰሳትን፣ እረኞችን፣ ሰብዓ ሰገልን፣ ዮሴፍንና ሌሎችን አናደንቅም። ማርያም ራሱ የዚህ ነገር ተደማሚና አድናቂ ነበረች እንጂ ከልጅዋ ይልቅ ትኵረትን ፈላጊና እንዲሰጣትም ጠባቂ እንደ ነበረች መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። እናም እባካችሁ የማርያም ሰባኪዎች ስታችሁ አታስቱ፤ ወደ ልባችሁ ተመለሱ፤ መንፈስ ቅዱስ በጨለማ ልባችሁ ላይ ብርሃንን ያብራ፤ አሜን።

4 comments:

  1. Indeed our LORD & savior JESUS CHRIST is the only one to shine!!!!!

    ReplyDelete
  2. May The Holy Spirit’s anointment increase upon you. May God keep you from the enemy.

    ReplyDelete
  3. ማንም የመሠለውን ይስበክ አንተም እንደዛው የሠው ስም እየጠቀሱ የምታመልከው አምላክ ልክ አይደለም የኔ ነው ልክ ማለት አግባብ አይደለም ሠው የፈለገውን እምነት መከተል መብቱ ነው ነገር ግን የኔ ብቻ ነው ትክክል ብሎ የሌላን ሰው ማጥላላት አንደ ትልቅነትህ እና እንደ አዋቂነትህ ተገቢ አይደለም እኔ በበኩሌ ፅሑፍክን አንብቤዋለው ሀሳብክን ብቻ ጠቅሰክ ብታቆም ደስ ይለኝ ነበር የሰው ስም ባትጠራ ጥሩ ነው ይህ አስተያየቴ ላንተ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሠው ነው

    ReplyDelete
  4. ሆዳም መናፍቅ!!!ኢየሱስ ከማን ነው ሥጋን ለብሶ የተገለጠው ወዳጄ??

    ReplyDelete