Tuesday 31 December 2019

ንቀት (ክፍል ፮)

Please read in PDF

ሌሎችን በመናቃቸው ምክንያት የወደቁ ሰዎች

  መጽሐፍ ቅዱስ አያሌዎች ሌላውን በመናቃቸው ምክንያት መውደቃቸውንና መንኮታኮታቸውን በግልጥ ያስተምረናል፤ በዓለም ላይ ከተከናወኑ ጥቂት ያይደሉ ታሪኮች ውስጥ እንኳ፣ ገናና የተባሉትንና ያልተጠበቁትን ሲያዋርድ ተመልክተናል፤ አንብበናል። በተለይም “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” የተጻፈልን ሕያው የእግዚአብሔር እስትንፋስ የኾነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ በንቀታቸው ምክንያት ስለወደቁት ሰዎች እንዲህ ያስተምረናል፦
1.    የጎልያድ ንቀት
  መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጎልያድ የጦር ትጥቅ እንዲህ በማለት ይናገራል፤ “… የጌት ሰው ጎልያድ፥ ቁመቱም ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ፥ ዋነኛ ጀግና መጣ። በራሱም የናስ ቍር ደፍቶ ነበር፥ ጥሩርም ለብሶ ነበር፤ የጥሩሩም ሚዛን አምስት ሺህ ሰቅል ናስ ነበረ። በእግሮቹም ላይ የናስ ገምባሌ ነበረ፥ የናስም ጭሬ በትከሻው ላይ ነበረ። የጦሩም የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅልያ ነበረ፤ የጦሩም ሚዛን ስድስት መቶ ሰቅል ብረት ነበረ።” ጎልያድ እንዲህ ያለ አለባበስ በመልበሱና የውጊያ ትጥቅን በመታጠቁ፣ ከፍልስጥኤማውያን ኹሉ አንደኛ አድርጎታል፤ በዚህ ሳይበቃ እስራኤልንና ንጉሡ ሳኦልንም ጭምር በማንቀጥቀጡ የሚደርስበት ፈጽሞ አልተገኘም።



 ጎልያድ የለበሳቸው ልብሶችና የታጠቃቸው ትጥቆች፣ ለአንድ ጦረኛ ሰው ያስፈልጉት ይኾናል፤ ነገር ግን ሌላውን ለመናቅና ከኹሉ በላይ ራስን የተሻለ ሰው እንደ ኾነ ለማሰብ ፈጽሞ አመክንዮአዊ አይደለም። ይህን አለማስተዋል ከንቀት ባሻገር ለመታበይ በር ይከፍታል። ይልቁን እስራኤልና ሳኦል በጎልያድ ፊት በፍርሃት መርበድበዳቸው እጅግ የሚደንቅ ነው። ሥጋዊ ግዝፈትን ብቻ ተመልክተው በተዋጊውና በድል ነሺው እግዚአብሔር መታመንን መዘንጋታቸው እጅግ ይደንቃል!
  ጎልያድ ከፍ ባለ በንቀት መንፈስ፣ የእስራኤልን ቅዱስ ያህዌህ ኤሎሂምን እየተሳደበና እየተራገመ፣ ዳዊት ብላቴናውን በንቀት ዓይኖች እየተመለከተ ሲዘብት፣ አለመቅናታቸውና “ለምን እንዲህ ኾነብን?” ብለው ራሳቸውን አለመመልከታቸው ከጎልያድ ንቀት ይልቅ የእነርሱ ድንዛዜ ይደንቃል! ጎልያድ ተሳዳቢ መኾኑ፣ ምናልባትም ተሸናፊነትና ፍርሃት ውስጡን ቀፍድዶት መያዙን ማስተዋል ይችሉበት ነበር፤ ነገር ግን እስራኤል አላስተዋሉም፤ በያህዌህ አልተማመኑም እንጂ ጎልያድ በዚህ ንግግሩ የመጨረሻ ዕድል ፈንታውን ድንገት አስቀድሞ የገለጠበትን ኹኔታ ሊያመለክት እንደሚችልም በተረዱ ነበር።
  ንቀት ግን ጎልያድን አዋረደችው፤ ከታላቅ ትጥቁና ከግዝፈቱ ይልቅ ከትንንሽ ኳሶች ከፍ በምትልና በእረኛው ብላቴና በዳዊት በተወነጨፈች አንዲት ድንጋይ፣ በምድር ላይ በግንባሩ ተደፍቶ ወደቀ፤ አበቃለት! ማንንም አትናቁ ንቀታችሁ በግንባራችሁ እንዳይደፋችሁ!
2.   የሜልኮል ንቀት
   እግዚአብሔር ዳዊትን ባከበረበት ወራት፣ ዳዊት ላከበረው እግዚአብሔር ክብሩን ጥሎ ዘመረ፤ በኪዳኑ ታቦት ፊት ሲዘልና ሲያሸበሽብ ሚስቱ ሜልኮል ስትመለከተው፣ በልቧ ባልዋንና ንጉሥዋን ናቀችው። ዳዊትን በመዘመሩ ምክንያት ስትንቀው ማንም አልተመለከታትም፤ ምክንያቱም የንቀት ተግባሯን የፈጸመችው በልቧ ነውና፤ የሳሙኤልን መጽሐፍን የጻፈልን እንደሚነግረንና በመንፈስ ቅዱስ መነዳት እንደ ጻፈው ግን ድርጊቱ በሜልኮል ልብ የተከናወነ ነበር፤ ማንም ባያይ ግን እግዚአብሔር ተመልክቶአል።
 ሜልኮል ራሱን እንዲህ ዝቅ በማድረጉ ነቀፈችው፤ ዳዊት ግን እንዲያውም ከዚህም በላይ ዝቅ ማለት እንደሚገባው ተናገረ፤ ከዚህም በላይ ልናቅና የተናቁ በተባሉ ገረዶችና ሰዎች ፊት እግዚአብሔርን ማክበር ይገባኛል በማለት ጮኾ፤ አሰምቶ፣ ሳያፍር ተማምኖ ተናገረ፤ በዚህ ኹሉ ግን ሜልኮል ንስሐ ገብታ አልተመለሰችም፤ እናም በንቀቷ ምክንያት እስክትሞት ድረስ መካን ኾና ቀረች፤ መውለድ እየቻሉ ባለመውለድ የማኅፀን መዘጋት መባረክ አይደለም። አመስጋኝን ትውልድ መናቅ መውለድን ከሚያህል ጸጋ አጉድሎአል!
   በሰው እይታ ላለመናቅ በሚል የስንፍና ዐሳብ አለማመስገንን አትምረጡ፤ እግዚአብሔር እጅጉን ያክብረን እንጂ የሰዎች እኛን መናቅ ራሳቸውን ከመጉዳት ባለፈ አንዳች አይጎዳንም!!
3.     የሐማ ንቀት
  የአስቴርን መጽሐፍ ስናጠና፣ አያሌ አስደናቂ ነገሮችን እናስተውላለን፤ ሐማ ምንም ደግነት ሳይነገርለት የንጉሡ ዋና ሰው ኾኖ ተመርጦአል፤ መርዶክዮስ ደግሞ ለንጉሡ ታላቅ ነገርን አድርጎ አንዳች ሽልማት ወይም ብድራትን አላገኘም፤ የኹለቱ ሰዎች ንጽጽር በራሱ ምጸታዊ ይመስላል፤ ከዚህ የሚብሰውና የሚከፋው ደግሞ ምንም መልካምነት ያልተነገረለት ሰው በንቀትና በጥላቻ የተሞላና መላ ልቡም በዚህ የተወረሰ ነው። አጋጋዊው ሐማ መርዶክዮስንና አይሁድን ከመናቁም ባሻገር እነርሱን በመጥላት ነፍሱ ተጠምዳ ነበር።
  ሐማ፣ መርዶክዮስ ስላልሰገደለት ነፍሱ ዘወትር በጥላቻ ጥዝጣዜ ተያዘች፤ ባለፈ ባገደመ ቊጥርም መርዶክዮስን በንቀትና በጥላቻ እየተመለከተ፣ የመርዶክዮስን ዘር በሙሉ ሊፈጅ ተነሣ፤ ፍጻሜው ግን ተቃራኒ ነበር፤ የሐመዳቱ ልጅ ንቀቱን ወደ ጅምላ ጭፍጨፋ አሳድጎት፣ እስራኤልን ኹሉ በቀላሉ ለማጥፋት የወጠነው ውጥኑ፣ እርሱኑ እንደ ደራሽ ጎርፍ ጠርጎት ወሰደው፤ ሟቹን ሊሰቅል ባዘጋጀበት በዚያው መስቀል ሐማ ተሰቀለ፤ ሥልጣናችሁንና ያላችሁን መደመጥ አስባችሁ ሰዎችን አትናቁ፤ እግዚአብሔር የተረሳና የተዘነጋ የሚመስል በጎ ሥራን አስታውሶ የተናቁትን ያከብራልና!
   በብሉይ ኪዳን በንቀታቸው የተመሰከረላቸው አያሌዎችን ማንሳት እንችላለን፤ ሰናክሬምን፣ ሖሮናዊውም ሰንባላጥ፥ ባሪያውም አሞናዊው ጦብያ፥ ዓረባዊውም ጌሳም እና ሌሎችንም በምሳሌነት መጥቀስ እንችላለን፤ ነገር ኹሉም በፍጻሜአቸው እጅግ ተዋርደዋል ወይም ስም አጠራራቸው ፈጽሞ አልታወቀም።
4.      በበዓለ ሐምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ፣ “በጸሎት የተጉ” የተባሉቱ አይሁድ እንዴት ይኾን ሐዋርያትን የናቁት? ሃይማኖተኞች ግን ሌላውን በመናቅ የታወቁ፤ በጸሎት የተጉ የተባሉ ነገር ግን ሐዋርያትን ያልተማሩ በማለት የሚያቃልሉ፤ ለሥርዓታቸውና አምልኮ ላሉት ተግባራቸው ከዓለም ጥግ ተሰባስበው በኢየሩሳሌም ቢገኙም ግን በንቀትና በጥላቻ የተመሉ ነበር።
   በአያሌ አብያተ ክርስቲያናት ለሰዎች ወይም ለአማኞች ደረጃ ተመድቦአል፤ የተለየ ወንበር፣ አለባበስ፣ ስፍራ፣ ከበሬታ … ያላቸው አማኝና አገልጋዮች አሉ፤ እንዲህ ያለ ነገር በኢየሱስም ኾነ በጌታ ደቀ መዛሙርት ሕይወትና ትምህርት ውስጥ ፈጽሞ የለም፤ ግን ዛሬ ላይ በብዙ ቦታ ልክ የተፈቀደ ያህል ተስፋፍቶ አለ፤ “የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም፦ አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን?” እንዲል፣ ክፉና አድሎአዊ ዳኝነት በንቀት በተመሉ ዓይኖች መካከል ናቸው!!!
   “እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ፥ …” እንዲል፣ እግዚአብሔር በትእቢትና ቀና ቀና በማለት የሰባውን ዓይን ይንቃል፤ ሥጋ ለባሽ ሆይ! ሌላውን ሥጋ ለባሽ ለመናቅ ምንም አቅምና ብርታት የለህም! አትናቁ ትናቃላችሁና፤ ትዋረዳላችሁና፣ በዚያም መንገድ ፈጽሞ ትተዋላችሁና፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበት መንገድ እጅግ የተዋረደና የተናቀ ነው፤ ነገር ግን ወደንና ፈቅደን እናመልከዋለን፤ እርሱ የመጣበትን መንገድ ከወደድን እርሱን በመውደድ የመጡትን ኹሉ እንደ ወንድምና እህት ልንወድድ ይገባናል፤ የደቀ መዝሙርነት ሕይወትና ተግባሩ፣ የኑሮ ዘይቤው እንዲህ ነውና! ጸጋው ይብዛላችሁ፤ አሜን።
ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment