Please read in PDF
ልንደርደር
መዝሙር
ከሰማየ ሰማያት ከመላእክት ዓለም ወደ እኛ ተንቆርቁሮ ፈስሶ፣ ያራሰን ሰማያዊ ጠልና የምንመገበው መና ነው፤ መላእክት የዘላለም
ደስታቸው ትዳርና ምድራዊ ብእል አይደለም፤ “እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ” እንደ ተባለው እንዲሁ፣
እኛም በፍጻሜአችን መንፈሳዊ አካል ስንለብስ፣ መንፈሳዊ ቅኔና መዝሙር ተቀኚና ዘማሪ ነን፤ “እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤” በተባለው በበጉ
ሰማይ ላይ ፣ የማያቋርጥና የማያባራ አስደማሚና አስደናቂ ምስጋናና
ዝማሬ አለ!!!
መሲሑ ኢየሱስ
በልደቱና በመስቀል ሞቱ ሰማያትን ከፍቶ፣ የሰማዩን የዝማሬ ቃናና ጣዕም አቅምሶናል፤ ጌታ ኢየሱስ እንደ ተናገረውና ቅዱስ ሄሬኔዎስ
እንደ መሰከረው፣ የእግዚአብሔር መላእክት የተመላለሱበት የሰማይና የምድር አገናኝ መሰላል ጌታ ኢየሱስ ነው፤ ርእሰ አበው ያዕቆብ
በፍኖተ ሎዛ እንደ ተመለከተው ሕልም፣ “እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር።” እንዲል፣ ራሱ ወደ
ሰማይ የደረሰው መሰላል ኢየሱስ፣ መላእክት ተመላልሰውበት ዘምረውበታል፤ የተዘረጋው መሰላል ላይታጠፍ ተዘርግቶአል፤ እኛም ከምስጋናና
ዝማሬው ቀምሰን፤ እንዘምራለን፤ ሲመጣ ግን በምልአት ክብሩን እያየን የዝማሬ ዶፍ እናወርዳለን! አሜን!
ሳይታጠፍ መዘርጋቱን እነሆ! በፍኖተ አበው ወንድሞችና እህቶች ዘማርያን
“ተሰንቆ” የተዘጋጀውን፣ “በክርስቶስ” የሚለውን የመዝሙር ሰንዱቅ (አልበም) አየኹት፤ በመከር ወቅት የፈሰሰው ዝማሬ፣ ባልታጠፈውና
ለዘላለም በተዘረጋው መሰላል ጸጋ የተዋበና የደመቀ ነው፤ በመላእክት፣ ለፍጡራን “ቅዱሳን” ሰዎች፣ ላልታወቁና መኖራቸው በብዙ ለሚያጠራጥር
“ሰዎች”፣ ለቊሳት፣ ለሥዕላት፣ ከመርጡላዊነት[ከኦሪታዊነት] ጭምር ሳንወጣ … የዘመርንበት ያንን ዘመን በትክክል እንድናፍርበት
የሚያደርግ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን እጅግ በሚልቅና አቻ በሌለው ፍቅር እንድንወደው የሚያደርግ ተወዳጅ ዝማሬ!!! ከሌላው መንነን ክርስቶስን
እንድናፈቅር ያደረጋችኹን ተባረኩ!
ድነናል በጸጋ
ወጥቶብናል ዋጋ
ስለዚህ በመንፈስ በእውነት
ኾነን
ለሞተልን ጌታ እንዘምራለን።
… በዳነ ማንነት
እንድንዘምርለት
በደሙ
ቀድሶን አነጻን ከኀጢአት
ቀድሞ ባዘጋጀው
በሥራው ለመትጋት
በኢየሱስ
ተፈጠርን መልካሙን ለመሥራት።
ባንዱ መንፈስ ገብተን ወደ አብ አባቱ
አንዳች ሳንደክም ሳንሠራ በከንቱ
እንግዶች ላንኾን
ልክ እንደ ቤተኛ
ባላገሮች ኾንን ቅዱሳኖች
እኛ!
የተዘረጋኸው የጽድቅ መሰላል ኢየሱስ ክርስቶስ በአንተ ይህ ኾኖልናልና
እናመሰግንሃለን፤ አሜን።
ቅዱሳት መጻሕፍት በዝማሬ ሲፈከሩ
የዝማሬው ማዕከላዊ ዐሳብ የተወሰደው፣ ቅዱስ ጳውሎስ ከጻፈውና ከቅዱሳት
መጻሕፍት አንዱ ከኾነው ከኤፌሶን መልእክት ነው፤ ዝማሬዎቹ በዚሁ መልእክት ውስጥ ተቀንብበው የተዘጋጁ ናቸው፤ ይኸንኑ መልእክትም
በዝማሬ ተፈክሮ(ተብራርቶ)፣ ታትቶ (በሐተታ ተባዝቶ)፣ “ተፍታቶ” አይተናል። መዳን በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ስለ መኾኑ፣ እኛ ኹላችን ያለ ክርስቶስ ኢየሱስ
ቤዝወትና ጽድቅ ባዶዎች መኾናችንን፣ በኹሉም መዝሙሮች ላይ እንደ አዋጅ ታውጀዋል፤ በታላቅ ጩኸት ቃል ተመስክረዋል። በአንድ መጽሐፍ
ላይ እንዲህ በትኵረት መሥራት ትጋትና ማጉተምተምን ይጠይቃል፤ ከዚህ በላቀ መልኩ ደግሞ በዚኹ መጽሐፍ ላይ ጠንካራ ሥራ እንጠብቃለን።
እግዚአብሔር ሩቅ አይደለም!
ባደግንበት ቤተ እምነት የእግዚአብሔር “መገኛው” ከስድስቱ ሰማየ ሰማያት
በላይ፣ ጫፍ በኾነው በሰባተኛው ሰማይ ነው፤ ከተነገረን ሰማይ አንጻር፣ ሩቅ የሚለው ቃል ራሱ ቅርብ ነው። ሰማዩ ከሩቅም እጅግ
ሩቅ ነው! እግዚአብሔር ሩቅ ስለ ኾነም፣ ለበቁና ለነቁ ወይም በሦስተኛው ፍጹማዊ ማዕረግ ወይም በተሰጥሞ ብርሐንና ከዊነ እሳትነት[ንጻሬ
ሥሉስ ቅዱስ] ለደረሱቱ ቅዱሳን እንጂ፣ ከደካማውና እንደ እኔ ካለው ኀጢአተኛ ጋር ሽርክናም፤ ዝምድናም ያለው አይመስልም። ኢየሱስ ለደካሞችና ለበሽተኞች መምጣቱ ባደግንበት
ቤተ እምነት ከፍ ባለ ድምጽ ሲሰበክና ሲነገር አንሰማም።
ስለዚህም ሰዎች
ለየትኛውም ችግራቸው መፍትሔና መላ የሚሉት ነገር፣ አልፋውም ኦሜጋውም ኢየሱስ አይደለም፤ እግዚአብሔር ሩቅ ስለ ኾነ “የእግዚአብሔር
ወደ ተባሉ ነገሮች” ይቀርባሉ፤ ጸበል፣ ቃል ተገብቶላቸዋል ወደ ተባሉ ገዳማት፣ ወደ ስዕላት፣ ወደሚዳሰሱና ወደሚቀቡ እመትና ቊሳት፣
ዘመናውያን የወንጌላውያን እንደሚያደርጉት ከኾነ ደግሞ፣ ዘይትና ውኃ ወደሚሸጡ “ነቢያት”፣ አትክልትና መሐረብ፣ ሶፍትና ሳሙና ወደሚያድሉት
“ሐዋርያትና ቢሾፕ፣ ሬቨረንድና ሜጀሪስቶች” … መሄድ መላ ማፈላለግ፣
ከችግር ለመውጣት መቃተት መፍትሔ እንደ ኾነ ሲሰብኩና ሲተገብሩ እናስተውላለን።
የ“በክርስቶስ”
ሰንዱቅ(Album) ግን እግዚአብሔር ሩቅ አይደለም ይለናል፤ እግዚአብሔር ቅርብ ነው፣ ከቅርብም ከወዳጅ ይልቅ እጅግ የሚጠጋጋ፣
ለጆሮ እንደሚያሾከሹክ፤ በወንጌል አነጋገር ደግሞ፣ ለቅዱስ ዮሐንስ እንደ ተነገረ “ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤ … እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ፣ …” እንደ ተባለው፣ እጅግ
ጥብቅ አንድነትና ወዳጅነት እንደ ነበረው እንደሚነግረን እንዲኹ፣ በዝማሬው እንዲህ ተዘምሮአል፤
“ከወዳጅ አብልጠህ የምትጠጋጋ
ለጆሮ ሹክ
እያልክ አንዱን ምታወጋ
ደግሞም ስለ
ኀጢአት ዓለምን የምትወቅስ
አንተ ነህ
አጽናኙ የእግዚአብሔር መንፈስ።
ራስህን ጣለው፤ ፈጥፍጠው![እኔነትህን
ካደው!]
እምነትህን፣ ብቃትህን፣ በራስ መተማመንህን፣ ጸጋህን፣ መዳንህን፤ አንቆለጳጵሰው፣ ውደደው፣ እመነው፣ ተደገፈው፣ እዘዝበት፣
ናዝዝበት፣ ጠርምስበት፣ ጣስበት … ለሚለው አንክሮ ሰብ ወይም “ሰውና
ስጦታ አስመላኪ” ምልከታ ለበዛበት፣ እንደ ቁንጅና ጥላሸት ለተቀባባው፣ የአጋንንት ትምህርት ላገረጀፈውና ፊቱን ለጨመደደው … “ሰዋዊና
ትምክህተኛ” ፉርሽ ትምህርት በተመለከተም፣ የዝማሬው አንድ አንጓ እንዲህ ይላል፤
“የታበይኩበትን ትምክህቴን ጥያለሁ
አበርታኝ አጽናኙ ኃይልህን እሻለሁ
አቅሜ ጉልበቴ አጽናኝ እንደገና
ታስፈልገኛለህ ብቃቴ ነህና!”
መታዘዝና ምሪት በሰንደቁ ሲፈከርና ሲብራራ!
የማመናችን ጥራት መለኪያው፣ የሕይወታችን ልኬትና መስፈሪያው ያለንበት ተቋም
ወይም ማኅበር ወይም ቡድን አይደለም፤ በማናቸውም የሕይወት መንገድ ውስጥ ብናልፍ፣ የትም ብንኖር፣ የየትኛውም አገር ዜጋና ነዋሪ፣
የማናቸውም ብሔርና ጐሳ ተከታይ ብንኾን፣ የምንለካበት ቱንቢው፣ የምንመዘንበት ሚዛኑ፣ ለቃሉ ባለን መታዘዝና በዚያም ውስጥ ባለን
እጅግ ብርቱ ራብና ጥም፤ ፍለጋና መሻት ነው። በዚህ ባለንበት ዘመን በክርስትናው ስም ብቻ መኖር ብርቅ አይደለም፤ ብርቁ ለቃሉ
የሚታዘዝና በትክክል የቃሉንና የመንፈሱን ምሪት የሚከተል አማኝና አገልጋይ ማግኘት እጅግ ብርቅና ደስ የሚያሰኝ መልካም ነው። ስንቶች
ንግግራቸውንና ስብከታቸውን ሰምተን፣ ስንቀርባቸው ከሳማ ይልቅ ያቃጠሉንና ከአባጨጓሬ በላይ የኮሰኮሱን አሉና!
በዝማሬው፣
“ተለይተን ስንኖር ከእግዚአብሔር ውጪ
ሳለን በፍርድ ስር በቁጣው ተቀጪ
ጸጋው ሲበዛልን ስንኾን በክርስቶስ
በደሙ ቀርበናል መንግሥቱን ለመውረስ”
እንደ ተባለው፣ ይህ የኾነልን የሚታዘዙ እውነተኛ ልጆች እንኾንለት ዘንድ ነው።
ያቀረባችኹልን መዝሙር ከማርገድና ከማስረገድ አልፎአል፤ ሶፍቱና መሐረቡ ከስሜታዊ ርግደት ሲረገብ የፈሰሰውን ላብ መጥረጊያ ሳይኾን፣
ለኢየሱስ ፍቅር በደስታ ያነባኹትን እንባ እንድጠርግ አደርጎኛልና በብዙ ተባረኩልኝ፤ ከመዝሙሮቹ በብዙዎቹም ተገሽሬ በአምልኮ የቆምኩበት
ወይም የተቀመጥኹበት ሰዓት ብዙ ነው! የዳነ ማንነት የያዝነው እንዲያው ድነናል በማለት እንድንመካ አይደለም፤ ይልቁንም በዚህ ጠማማ
ትውልድ ፊት፣ በግል በተፈተነ እውነተኛ ሕይወትና ቅድስና ምስክሮች እንኾን ዘንድ ነው። ለዚህም ደግሞ የሚናገረንን መንፈስ ቅዱስን
በትክክል መስማት እጅግ ታላቅ ብጽዕና ነው!
“አንተ ስትናገር
ስትመሰክርልኝ
በምሪትህ ስኾን
እውነት ሲበራልኝ
በፊቴ ይሳላል የጌታ መስቀሉ
አያለሁ አጥርቼ
ኖራለሁ በቃሉ! …
ልስማህ
ደጋግሜ አትሰለችምና
አንተን
አንተን ልበል ከራሴ ልውጣና
ግራው ቀኝ ይኾናል ስኾን ካንተ ጋራ
ዘላለም ወርሰኸኝ
እንዳልከኝ ልመራ! አሜን!
ነገረ መዳናችን
በብሒል እንደሚባለው፣
ረጅም መንገድ ተጓዥ፣ በቅሎ ከነመለቃው እንደሚያዘጋጅ፣ ፈረስን ደግሞ ከነኮርቻው እንደሚያደላድለው እንዲሁ፣ መዳናችን በክርስቶስ
ጥንቅቅ ብሎ መፈጸሙንና እኛ በዚህ ትልቅ በር በመግባት እንደምንድን፣ በታላቁ የበጉ እራት ለመጋበዝ፣ የጽዮን ተጉዋዦች
መኾናችንን በዝማሬ ተፈክሮ፤ ታትቶ መቅረቡ እንዴት ልብ ያረካል! በግልጥ ኀጢአተኞች መኾናችን፣ አዳኝና ቤዛ ክርስቶስ ብቻ እንደ ኾነ መናገር ዕፍረት እየመሰለ በመጣበት በዚህ አጣብቂኝ ወቅት፣ ኹሉም
ከክርስቶስ በላይ ልጅነቱን፣ መዳኑን፣ መወደዱን፣ አገልጋይነቱን በሚያሞጋግስና በሚያሽሞነሙንበት፣ ሲከፋና ሲመር ደግሞ ዘሩንና ብሔሩን፣
መንደሩን በሚያሞካሽበት ጊዜ፣ እኛ ኹላችን የኾንነውንና የተደረገውን ኹሉ የኾንነውና የተደረግነው በክርስቶስ ብቻ ነው ብሎ በግልጥ
መናገር ታላቅ መንፈሳዊ ድፍረት ይሻል፣ [ይህን መናገር የሚያስፈልገው በሩቅ ላሉት ላላመኑት ብቻ ሳይኾን ለእኛም ጭምር ነው!]
ይህን ያደረግህ አብ አባት ሆይ! በኢየሱስ ስም ክብር፣ ውዳሴ፣ ስባሔ፣ ባርኮት፣ ቅዳሴ፣ መባረክ ይገባሃል ማለት እንዴት ልብን
ያረሰርስ ይኾን!? አዎን! ለክብሩ እስኪኾን ክብራችን በፊቱ መንጓደድን አንተውም!
ሌላው መዳንና ማምለጣችንን፣ መጠራታችንንና መባረካችንን በዓወደ ምስባክ
“እኛ” በሚል ዘዬ መቅረቡ እጅግ የወደድኹት ክፍል ነው፤ ብዙ ሰው ክርስትናን ታሪካዊ፣ በዚያ ዘመን ብቻ እንደ ተከናወነ ብቻ አድርጎ፣
ቀኖናና ዶግማ በተከለበት በዚህ ዘመን፣ “እኛም” ድነናል፣ ተጠርተናል፣ ተባርከናል፣ ደግሞም ከእርሱ ጋር የምንሠራ ሠራተኞች ነን
ማለት፣ የዳነና በክርስቶስ የኾነ መሲሐዊ ማኅበረ ሰብ መንፈሳዊ ድፍረት ነው! ይስሐቅ ያሻተተውን የምድረ በዳ አበባ እኛም አሻተትነው፤
መሲሑን አሻተትነው፤ ሊቁ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መሲሑን ሲተረጉሙ፣ “በቅባት ማሸት ማጣፈጥ” እንዳሉት፣ የጣፈጠውን መሲሕ በላነው፣
ጠጣነው፣ ረካንበትም!
በዚህ በኩል ልውጣ!
ለፍጡራንና
ለእግዚአብሔር፣ ቅዱስ ቃሉንና ከቃሉ ውጭ ያሉትን ድርሳናት፣ ገድላት፣ “ተአምራት” እና ሌሎችንም እኩል አድርገን ወይም ቀላቅለን
እንዘምርና እናመሰግን እንዳልነበር፣ ዛሬ ግን ያ ኹሉ ተሽሮና ተወግዶ የመንፈሳዊ ቅኔና ዝማሬዎችን ኹሉ፣ በአንድ ልጁ ለወደደን
ለአብ፣ ተሰቅሎ ላዳነን ውድና ስሙር መሥዋዕት ለኾነው ለአብ አንድያ ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ይህን አብራርቶ ላስረዳንና ላበራልን
አጽናኝ መስተፈስሒ[አስደሳች] መንፈስ ቅዱስ ብቻ፣ መዝሙርንና መንፈሳዊ ቅኔን ማቅረብና መስማት ከጀመርን እነሆ ዓመታት ተደጋገሙልን፤
ይህን ያደረገ አባትና አምላክ ክብር ይብዛለት!
በዚሁ
መንገድ ብትቀጥሉ፣ በሜሎሳዊ [ግራና ቀኝ በመቀባበል - እንደ በክርስቶስ] ቅኔ ከሰማይ ተቀብላችኹ እንድትመጡም ናፍቃለሁ! በተረፈ
ወደሌላ መንደር “ጩልቡቅ” ብለው ገብተው እንደ ቀሩትና ምርቅና ፍትፍት በተደገሰበት ኹሉ “አንቀርም!” ከሚሉቱ ወገን እንዳትኾኑ፣
የራስ ነጸነትና የገንዘብ ጥም እንደሚያልከፈክፋቸው እየታወቀ፣ “አገልግሎትና ጌታን መውደድ” የሚል እጅል ምክንያት እያቀረቡ ከሚክለበለቡት
ጋር እንዳትክለበለቡ፣ በተፈተነ የሕይወት ቅድስና ታጥራችሁ መኖር ይብዛላችሁ፤ ምሕረቱን አግንኖ ያትረፍርፍላችኹ፤ አሜን!!! በብዙ
ጉድለት ውስጥ ብትኾኑም ባትኾኑም፣ የነበራችሁበትን ቤት አትዘንጉ፤ የወጣንበት ቤት ጨለማና በጨለማው የሚመላሰሱትን ወገኖቻችንን
በማየት፣ እንዲድኑም በመጠማትና በመናፈቅ በምልጃና በብርቱ በመሻት እንዲኹ፣ መቀጠል፣ መስፋት፣ መብዛት እንዲኾንላችሁ ወንድማዊ
ጽኑ መሻቴ ነው!
(ይህ አጭር ጽሑፍ መዝሙሩ በተዘጋጀበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድርሰቱ[ግጥም] ላይ ብቻ የተሰጠ ግላዊ አስተያየት ነው!)
ተጻፈ ታኅሳስ 6 2012
ዓ.ም!
አቤንኤዘር ተክሉ(ዲያቆን)!
No comments:
Post a Comment