Thursday, 12 December 2019

ንቀት (ክፍል ፭)

Please read in PDF

እግዚአብሔርን የሚንቁ ይናቃሉ!

   እግዚአብሔር ኹሉን በሉዓላዊ ሥልጣኑ ተቈጣጣሪና ገዢ አምላክ ነው፤ ደግሞም ራሱን ዝቅ አድርጐ የሰውን ልጅ ውድቀቱን፤ ውርደቱን ሳይጸየፍና ሳይንቅ በፍቅሩ የቀረበ ገናና ተወዳጅ አምላክ ነው፤ አስቀድሞ እኛን ሲፈጥረንና ከወደቅንም በኋላ ወደ እኛ የቀረበበት፤ ወደ እርሱም እኛን የሳበበት ዋነኛ ምክንያቱ ክብሩን እንድንገልጥ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ብንቆም ግን በግልጥ የተነገረ ቃል አለ፤ “ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና” (1ሳሙ. 2፥30)።





በእግዚአብሔር ዘንድ የተናቁት እነማነን ናቸው?

1.    ቃሉን የማያከብሩ ኹሉ ይናቃሉ፦ እግዚአብሔር የሰጠንን ነገር የሰጠን ከሙሉ ኃላፊነት ጋር ነው፤ ያለ ኃላፊነት የተሰጠን ምንም ነገር የለም። በስሙ ምሎ እንዲያው የወደንና ያከበረን እኛም እንድናከብረው “ግዴታ” በሚያስገባን ኃላፊነት ነው። እንዳከበረን ወደን ባናከብረው፣ እኛው በፊቱ የተናቅን እንኾናለን። እርሱ ካከበረን ወዲያ እኛ “አናከብርህም” የማለት የእንቢተኝነት የሥነ ምግባር ችሎታ እንጂ መብት የለንም፤ ምክንያቱም ያለ ማክበራችንን ውጤቱን እንቀበላለንና። በምድረ በዳ የተፈታተኑትና የናቁትን እስራኤላውያንን እግዚአብሔር ምን ነበር ያላቸው? “ … በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ አሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥ ነገሬንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእነርሱም የናቀኝ ሰው ሁሉ አያያትም፤” (ዘኊ. 14፥22-23)

  ከካህኑ ዔሊ ቤት ለአንድያው ክህነቱ የተሰረዘውና የተነሣው፣ ልጆቹ የእግዚአብሔርን ቤት በንቀት መመልከታቸውና በንቀትም ያገለግሉ ስለ ነበር ነው። አባታቸው የልጆቹን ንቀት ተመልክቶ ዝም አለ፣ እግዚአብሔር ግን ንቀታቸው ጫፍ ነክቶ ነበር፤ ከመሥዋዕት አቅራቢ ደናግላን ጋር በመገናኛው ስፍራ በምናምንቴነት ይዳሩ ነበር፤ ስለዚህም ያህዌ በንቀት የጠገቡትን ልጆቹን ብቻ የሰበረ አይደለም፤ እንዲያውም የዔሊን ቤት መስበሩንና መደምሰሱን እናስተውላለን፤ (1ሳሙ. 22፥18-19፤ 2ሳሙ. 22፥35፤ 1ነገ. 2፥26-27)።
  ሳኦልም የእግዚአብሔርን ቃል በመናቅ እጅግ የታወቀ ነው፤ እንዲያውም መንገዱን በቅንነት ልብ ለመፈለግ የወደደ አይመስልም፤ ብዙ ጊዜ በራሱ መንገድ መሄድን የወደደ ነው፤ በአንድ ወቅት እግዚአብሔር አምላክ ሳኦልንና ሕዝቡን አንድ ነገር አዘዛቸው፤ እንዲህ በማለት፦ “እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ አማሌቅ በመንገድ እየተቃወመ ያደረገበትን እበቀላለሁ። አሁንም ሄደህ አማሌቅን ምታ፥ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፥ አትማራቸውም፤  ነገር ግን ሳኦልና ሕዝቡ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ቃል ሳይኾን በራሳቸው መንገድ ሳኦልና ሕዝቡ ለአጋግ፥ ለተመረጡትም በጎችና በሬዎች ለሰቡትም ጥጆችና ጠቦቶች፥ ለመልካሞቹም ሁሉ ራሩላቸው፥ ፈጽሞ ሊያጠፉአቸውም አልወደዱም፤ እንዲል፣ የእግዚአብሔርን ቃል በፍጽምና አልጠበቁም።

 “ … በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ አለ።” (1ሳሙ. 15፥22-23)
   ሳኦል የእግዚአብሔርን ቃል ናቀ፤ የራሱን ዐሳብና ፈቃድ አስቀደመ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ዐሳብ ፈጽሞ በመናቁ ምክንያት፣ እግዚአብሔር በእርሱ ሊሠራና ሊያደርገው የነበረውን ዐሳቡን ኹሉ ተወ፤ እግዚአብሔር መልካም ሥራውን ከእኛ ጋር እስከ መጨረሻው ሊሠራ የሚፈቅደው በፍጹም መታዘዝ አብረነው ካለን ብቻ ነው። ሳኦል እግዚአብሔርን በመናቁ ምክንያት ውጤቱ መራራ ሲኾን እንመለከታለን፤ ወዲያው የእግዚአብሔር መንፈስ ሲነሣና ክፉ አጋንንት ሲቆራኘው፣ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ሲያጣ (16፥14፡ 31)፣ የገዛ ልጆቹ ዮናታንና ሜልኮል፤ የእርሱ ባለሟሎች ኹሉ ሲክዱት እንመለከታለን፤ (22፥17)።

  የኪዳኑን መሥዋዕት መናቅ ታላቅ ኃጢአት ነው (1ሳሙ. 2፥17)፤ እግዚአብሔርንም እንደቃሉና እንደ ፈቃዱ አለመፈለግና አለመታዘዝ፤ በሥርዓቱ አለማምለክ ዐመጸኝነትና እልኸኝነት፣ ንቀትና ተገዳዳሪነት ነው፤ ቢመረንም ቢጣፍጠንም ለእግዚአብሔር ቃልና ትእዛዝ መታዘዝ እጅግ መልካም ነው! ቢገድለንም እንኳ እግዚአብሔርን መታመንና መደገፍ እርሱ ሕይወትና ዕረፍት ነው! ስንቶቻችን እንኾን እንደ ቃሉ በትክክል በመታዘዝና በመሸነፍ እግዚአብሔርን በማክበር ሥራ የበዛልን?!

   እግዚአብሔርን የሚንቅ ትውልድ እርሱን እንደ እንግጫ የሚረግጠውና የሚንቀው እንግዳና ጨካኝ ትውልድ እንደሚያገኘው ጥርጥር የለውም፤ የእግዚአብሔርን ቃል በንቀት ያላከበረና ትእዛዙን የሰበረ ፍጻሜው ሞት ነውና፤ (ዘኍል. 15፥31)፤ እግዚአብሔርን ማክበር ግን ከሰንፔር ይልቅ በሚያበራ ዐለት ላይ ያቆማል! አሜን።

2.   ባዕዳን አማልክትን ስናመልክ፦ ከእግዚአብሔር ውጭ ሌሎች አማልክትና ማናቸውንም ነገሮች ማምለክ ወይም በእነርሱ መታመን ጣዖትን ማምለክና በእግዚአብሔር ላይ ፍጹም ማመጽ ነው፤ የእግዚአብሔርን ክብር በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ ለመውሰድ በማሰብ የሚደረግ ማናቸውም ተግባር፣ እግዚአብሔርን መናቅና በእርሱ ላይ ደባል አማልክትን ደብሎ የማምለክ ተግባር ነው። 

   እስራኤል በምድረ በዳው ጉዞ አማልክትን በማምለክና ምስክሩን ባለመጠበቅ፣ እንግዶች አማልክትን በማምለክ ያስመረሩትንና ያስቆጡትን ተግባር መዝሙረኛው ሲናገር እንዲህ ገልጦታል፤

 “ልዑል እግዚአብሔርን ፈተኑት አስቈጡትም፥ ምስክሩንም አልጠበቁም፤ ተመለሱም እንደ አባቶቻቸውም ከዱ፤ እንደ ጠማማ ቀስትም ተገለበጡ፤ በኰረብታ መስገጃዎቻቸውም አስቈጡት፥ በተቀረጹ ምስሎቻቸውም አስቀኑት። እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፥ እስራኤልንም እጅግ ናቀ፤ የሴሎምን ማደሪያ ተዋት በሰዎች መካከል ያደረገባትን ድንኳኑን፤ ኃይላቸውን ለምርኮ፥ ሽልማቱንም በጠላት እጅ ሰጠ። (መዝ. 78፥57-61)
  እግዚአብሔር እርሱንና ምስክሩን፣ ቃሉንና ክብሩን የናቁትን ኹሉ ናቃቸው፤ ተዋቸው፤ እናም ሲተዋቸው፣ “ኃይላቸውን ለምርኮ፥ ሽልማቱንም በጠላት እጅ ሰጠ”። እንዴት ያለ ታላቅ ስብራትና ውርደት ነው?! ብልጣሶር ለእግዚአብሔር ክብር መገለጫ በኾኑት የቤተ መቅደሱ ንዋያተ ቅድሳት በንቀትና በስካር መንፈስ ሊጠጣ በጀመረ ጊዜ፣ እግዚአብሔር መንግሥቱን ለኹለት ቀደደው፤ ሄሮድስ ደግሞ እግዚአብሔርን በመናቅ፣ ራሱን በእግዚአብሔር ቦታ አድርጎ ሲናገር በትል ተበልቶ ሞተ።
   ብዙ “ክርስቲያኖች” ጣኦት እንደማያመልኩ እርግጠኞች ናቸው፤ ነገር ግን አገልግለው ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ከመስጠት ይልቅ፣ በአገልግሎቱ ቦታ ራሳቸውን ሲሾሙና ሲቀቡ፣ በዚያም ክብርን ሲቀበሉ ይህ ጣዖት አምልኮና የእግዚአብሔርን ክብር መሻት እንደ ኾነ አያስተውሉም፤ በእግዚአብሔር ጉባኤ የተለየ አለባበስና ወንበር አዘርግተው ሲቀመጡ፣ የተለየ ክብርና የስም አጠራር እንዲደረግላቸው ሲፈልጉ ይህ ጣዖትና እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ጉባኤ መናቅ እንደ ኾ አያስተውሉም። አዎን! ዛሬ እልፍ አብያተ ክርስቲያናት ሥጋ ለባሽነታቸውን ፈጽመው የዘነጉ ይመስላል! እግዚአብሔር እንዲህ ያሉትን እጅግ ይንቃቸዋል!  
       የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” (መዝ. 51፥17)
ይቀጥላል …


1 comment:

  1. ዋው እውነት! በሀይማኖት ስም ጠበቃና ተከራካሪ ለመሆን ለሚሞክሩ ግን የሚሳደቡ ወዘተ ክርስትና ውስጥ ንቀትና ስድብ የለም

    ReplyDelete