Monday, 16 December 2019

ጌታን አትስቀሉ!

Please read in PDF
ሞት ክፋት ጭንገፋ
ርስቱ እንዳይሰፋ
ኃጢአት እድፈት ርኩሰት
ነግሠው እንዳይገዟት

የጨለማው ዓለም
ሲዖል ገሃነምም
ሰልጥኖ እንዳይኖር ግዛቱ እንዳይጸና
አንዱ የእግዚአብሔር በግ ጥንት ታርዷልና …

በቋንቋ በነገድ
እንዳንወጋገድ
በንቀት ጥላቻ
እንዳንበላላ
ዘር ብሔር በመቊጠር
ተዋርደን እንዳንቀር
ወለደን በሞቱ በመስቀሉ ችንካር።

ከሞተ አዳኙ እኛን ስለ ማዳን
ከደከመ ጌታ እኛኑ ሊረዳን
ታድያ ስለምን ነው በኃጢአት መጽናታችን?
ያረገውን ጌታ ዳግም መስቀላችን?
ኃጢአትን እንደ ጡት ምነው መጥባታችን?
የዋጀንን ጌታ ደግመን መስቀላችን?

ወገኔ!
ይሁዳን አንውቀስ፣
ጴጥሮስን አንክሰስ፣
እኛ ከይሁዳ በምን ተሽለናል
አልተስማማን ይኾን በሠላሣ ዲናር?
ፍረዱ እስኪ እናንተው በራችሁ ሚዛን
ከጽድቅና ኃጢአት፣
ከእውነትና ሐሰት፣
ከፍቅርና ከጠብ፣
ከዝማሬና ስድብ፣
የቱ በሕይወታችን ገዝፎ ይነበባል?
እግዚአብሔር ቢያየን የቱ እኛን ገዝቷል?

ስካር አንገዳግዶ፣
ዝሙት ከእሳት ማግዶ፣
ርኩሰት አጠልሽቶን፣
መዳራት በክሎን፣
ከዚህም በሚብስ አልተያዝን ይኾን?
ታድያ ያን ይሁዳ ያንን ምስኪን ጴጥሮስ
ለምን ነው ʻምንወቅስ ለምን ነው የምንከስ?

ኃጢአት እንዳይገዛን ነበር የጌታ ሞት
ወደʻርሱ እንድንገባ ወደ ሕይወት በረት
እኛ ግን አመጽን ጸናን በኃጢአታችን
አብዝቶ ሲጠራን አጥብቀነው ሸሸን።

ሕዝቤ ሆይ አትሙት ይቅርብህ አትጨንግፍ
በሞተልህ ጌታ እመንና እረፍ
በደሙ ተቀደስ ታጥበህ ጥራ ንጻ
ወደቤቱ ግባ ተመለስ አትጥፋ

ሞት ኩነኔህ ጠፍቷል
ሲኦልም ተረግጧል
የገሃነም ጉልበት በሞቱ ተሰብሯል
ልብስህን ልብህን በደሙ እጠብና
ሕያው ወደሆነው ወደአዲሱ መንገድ በእምነት ልብ አቅና።

እመን እንጂ አትፍራ ተንጓደድ በፊቱ
ከሞት ስላዳነህ ክርስቶስ በሞቱ
አትደፍ አትርከስ ዳግም አትበድል
ለዲያብሎስ ፈንታ አትስጥ አዲስ ዕድል
ወደ ጸጋው ዙፋን ሸክምህን አምጣና
አራግፈህ ተመለስ ኹን ዘወትር ደኽና።

እናንተ ሁላችሁም …
ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት ቅረቡ
ይምራል ይራራል ክርስቶስ ካህኑ
ጸንታችሁ በበድል ኃጢአትን አትሥሩ
ቤዛ ነው መሃሪ የዋጀን በደሙ
ዳግመኛ በአመጽ ጌታን አትስቀሉ …።
(በቀን 16/2/2006 ተጻፈ)

No comments:

Post a Comment