Tuesday 3 December 2019

ንቀት (ክፍል ፬)

Please read in PDF
የአይሁድና የሳምራውያን መናናቅ
    ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር በመጣበት ጊዜ የአይሁድና የሳምራውያንን ኹኔታ ወንጌላዊው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል፤ “አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና።” (ዮሐ. 4፥9)። በጥንት ታሪክ ሳምራውያን ከአይሁድ ጋር አንድ ነበሩ፤ ነገር ግን ከአሦር ምርኮ በኋላ፣
   “የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ ከአዋና ከሐማት ከሴፈርዋይም ሰዎችን አመጣ፥ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ። በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶች ሰደደባቸው፥ ይገድሉአቸውም ነበር። ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ። ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁም፤ የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፥ እነሆም፥ ገደሉአቸው ብለው ተናገሩት። የአሦርም ንጉሥ። ከዚያ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፥ የአገሩንም አምላክ ወግ ያስተምራቸው ብሎ አዘዘ። ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱ መጥቶ በቤቴል ተቀመጠ፥ እግዚአብሔርንም እንዴት እንዲፈሩት ያስተምራቸው ነበር። በየሕዝባቸውም አምላካቸውን አደረጉ፥ ሰምራውያንም በሠሩት በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩበት ከተሞቻቸው አኖሩአቸው። … ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናት አደረጉ፥ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር።  እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር። እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ቀደመው ልማድ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም፥ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዓትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም አያደርጉም።  ” (2ነገ. 17፥22-29፤ 33-34)

እንዲል፣ በሰማርያ ከሰፈሩት ባዕድ አምልኮ ተከታዮች የተነሣ፣ እነርሱም በእንግዳ አማልክት አምልኮ ተጠመዱ፤ ከእነርሱም ጋር በጋብቻ አንድ ኾኑ፤ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ እናም ሳምራውያን ከአይሁድ የተለዩ ኾኑ፤ ከሌሎች ጋር በአማልክት አምልኮ በመዋሰባቸው ምክንያት፣ በአይሁድ ቤተ መቅደስ እንኳ ለማምለክ እስከማይፈልጉበት ድረስ ራሳቸውን አገለሉ።
  በጌታ ዘመን መሲሑን በመጠበቅና የያዕቆብን ተስፋ ጠባቂዎች ቢኾኑም፣ በአይሁድ ዘንድ እጅግ ዝቅተኛ ግምት የተሰጣቸው ነበሩ። አይሁድም ሳምራውያንን በአምልኮና ከአሕዛብ ጋር በዘር እንደ ተቀላቀሉ አድርገው ይቈጥሩአቸው ነበር፤ ስለዚህም በማናቸውም መልኩ ሊረዷቸው ፈቃደኞች አይደሉም። የታሪክ ሊቁ አይሁዳዊው ጆሴፈስ እንደሚነግረን፣ የገሊላ አይሁድ እንጂ የይሁዳ አይሁድ ሳምራውያንን ብቻ ሳይኾን ከተማዋን ሰማርያን ራሷን አይወዷትም ነበር። ንቀታቸው ጫፍ የነካ ነበርና ምድሩን እንኳ እስከ መጠየፍ አደረሳቸው።
   በእርግጥ በታሪክ ውስጥ እንደምናስተውለው፣ ሳምራውያን በአምልኮ ታማኝ አልነበሩም፤ ራሳቸውን ከአይሁድ በመልክዐ ምድር ብቻ ሳይኾን፣ በአምልኮ በመለየትም ጭምር፣ ለአያሌ ዓመታት በልዩነት ኖረዋል። አይሁድም የሳምራውያንን በመልክዐ ምድርና በአምልኮ መለየትን እንደ ዋና ነገር በመውሰድ አብሮ ለማምለክ ይቅርና በማናቸውም ችግር ውስጥ ቢኾኑ እንኳ ለመርዳት እስከማይፈቅዱበት ድረስ ወስነው ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ግን ከዚህ በተቃራኒ ለሳምራውያን ኹሉ ሲራራና በሽታቸውንም ጭምር ሲፈውስ እንመለከታለን።
   እስራኤል በልዩትነት ከመላው ዓለም ተለይታ በያህዌህ ኤሎሂም በታላቅ ክብር የተጠራችው፣ “ለአሕዛብ በረከት እንድትኾን” ነበር፤ ነገር ግን እስራኤል እንኳን ለመላው ዓለም “የመባረክ ምክንያት” ልትኾን፣ ለራስዋም በኀጢአት ስለ ተዘፈቀችና ባለመታዘዝ ስለ ተወረሰች ለሌላው ዓለም መድረስና ሌላውን ዓለም “ማዳን” አልቻለችም። እናም አይሁዳውያን ራሳቸውን ብቻ እንደ ንጹሕና ቅዱስ በመመልከታቸው ምክንያት፣ ሌላውን ዝቅ በማድረግና በመናቅ ኃጢአት ፈጽመው ተጠመዱ።
   እነርሱ ሌላውን ሲንቁ በእግዚአብሔር ፊት ራሳቸውን እንደ ቀናተኛ በመቍጠራቸው ምክንያት፣ ኀጢአት መሥራታቸው እንኳ አልታወቃቸውም። ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ ያለ ተግባር ሲያደርጉ ዝም ብሎ አልተመለከታቸውም፤ ይልቅ በተደጋጋሚ በወዮታ በመናገር እጅግ አስጠነቀቃቸው፤ (ማቴ. 23)፤ ጌታ ኢየሱስ የንቀት ድርጊታቸውን በድፍረት ቢናገርም በንቀት ግን አልተናገራቸውም! (ማቴ. 23፥13)
   አይሁድ ግን ለሳምራውያን ብቻ ሳይኾን፣ ከአይሁድ ውጭ ላሉና ለድኾች፣ ደግሞም ለኃጢአተኞች የነበራቸው ንቀት እጅግ አስቀያሚ ነበር። በታሪክ እንደምናጠናው አይሁድ ሳምራውያን የሠሩትን መቅደስ እስከማቃጠል በሚያደርስ ጥላቻ ተወርሰው ነበር። እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሳምራውያን ጋር ግንኙነትን ሲመሠርት እኒህን የጥላቻና ሥር የሰደደውን ንቀት ኹሉ በማለፍና በመተው ነበር። ዛሬ ላይ የማናየው እውነታ ከዚህ የተለየ ነውን?
   ንቀት ከፍጹም ጥላቻ የሚቀዳ አስነዋሪ ተግባር ነው፤ በተለይም እንዲህ ያለ ንቀት፣ እንደ አይሁድ “የእግዚአብሔር ቅንአት ነው!” ብለን ልንጠራው ኹሉ እንችላለን፤ ድርጊቱ ትክክል እንዳልኾነ እያወቅን እንኳ፣ መንፈሳዊ ከለላ ስለ ሰጠነው ከዚህ መራር ጥላቻ ለመውጣት በፍጹም እንቸገራለን፤ አይሁድ ሳምራውያንን ሲጠሉ፣ ጥላቻቸው በራሱ ኀጢአት እንደ ኾነ አላስተዋሉም፤ ይልቅ ለእግዚአብሔር እንደሚቀኑ ያስባሉ እንጂ። ስለዚህም ከዚህ ነውርና ዕድፈት ነጻ ለመውጣት ራሳችንን በንስሐ መንፈስ አንሰብርም! በስንፍና አምላክን ለማክበር ለሚጥሩ ሰዎች ማዘንና መራራት እንደሚገባንም አናስተውልም!
   በአገራችን ዛሬ ያለው እውነታ እንዲህ ነው፤ ሰዎች በብሔራቸውና በሃይማኖታቸው ጭምር ይናቃሉ፤ ይጠላሉ፣ ይገደላሉ፣ የሚያመልኩባቸው አብያተ ክርስቲያት ይቃጠላል፤ ይህ ኹሉ ሲኾንና ሲደረግ bxderagiwocu የሚሰጠው ምክንያት ለአምላካቸው እንደሚቀኑና ለብሔራቸው እንደሚቈረቈሩ ነው፤ ነገር ግን ሰይጣዊ ተግባር እንደ ኾነ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ንቀት አዕምሮን ያዝጋል፤ ለከረረ ጥላቻና ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ይሸጣል፤ በተለይም ክርስቲያኖች ለመላለሙ መዳን የወንጌል አዋጅ እንድናውጅ የተጠራን ነን፤ የትኛውንም ሰውም ኾነ ብሔር፤ ሃይማኖትም እንኳ ማበላለጥና ማቀዳደም አልተባለልንም፤ እጅግ ነውርና ጥዩፍም ነው።
   በንቀትና ሌላውን በማግለል የሚኖር ክርስቲያን ያልበሰለ ክርስቲያን ብቻ አይደለም፤ ይልቁን የጌታ ኢየሱስ ርኅራኄና ፍቅር የሌለው፣ በጭንጫ ላይ እንደ ተዘራው ዘር በፍጹም መቀጨጭ ውስጥ የሚመላለስና ፈጽሞ ለመንግሥቱ ያልተገባ ሰው ነው። ለወንጌል ሥራ በኢየሱስ ደም ተጠርተን ነገር ግን እንዲህ ባለ ነውር መያዝ፣ ከኹሉ ይልቅ ማነስና አለመታደል ነው። ኢየሱስን የሚያስከብር ሕይወት እንዲኖረን ጸጋው ይደግፈን፤ አሜን።
ይቀጥላል …

1 comment: