Please read in PDF
እግዚአብሔር አይንቅም!
እግዚአብሔር
አምላክ በክብር የተከበበና በፍቅር የተትረፈረፈ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር ፍጥረትንም ሲፈጥረው በድንቅና በግሩም ክብር ነው፤ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።” (መዝ. 139፥14) እንዲል፣ ሰው በግሩም፤ በድንቅ አድናቆት ተመልቶ የተፈጠረ ነው። መዝሙረኛው እንዲህ
ሲል የፈጠርከውን ሰው የምታውቀው አንተ ነህ፤ እኔንም የፈጠርኸኝ አንተ ነህና በሚገባ ታውቀኛለህ፤ ምክንያቱም በእናቴ ማኅፀን ያበጃጀኸኝና
በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ ንቁ ኾነህ የተንከባከብኸኝ አንተ ነህ እያለ ነው፣ ያህዌ ኤሎሂምን!
አዎን! “ኑ የእግዚአብሔርንም ሥራ እዩ፤ ከሰው ልጆች ይልቅ በምክር ግሩም ነው።” (መዝ. 66፥5)።
በመቀጠልም ሌላኛው ዘማሪ ነቢይ፣ የእግዚአብሔርን እስከ ሽምግልና ድረስ
አለመለወጥንና ከጽንስ ልደት እስከ ሽበትም ድረስ ተሸካሚነቱን፤ ሠርቶ አክባሪነቱን “አንተ ነህና እስከ ሽበትና ሽምግልናዬ የምትሸከመኝ፤ የምትይዘኝ (ኢሳ. 46፥4) አንተ ነህና ፈጽሞ የማትንቀኝ
ይላል፤ በእርግጥም እግዚአብሔርን ማንንም አይንቅም፣ “እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም እርሱም በማስተዋል
ብርታት ኃያል ነው።” (ኢዮብ 36፥5)።
ደግሞም፣ የችግረኛን
ችግር አልናቀምና፥ ቸልም አላለምና፤ ፊቱንም ከእኔ አልሰወረምና፥ ነገር ግን ወደ እርሱ በጮኽሁ ጊዜ ሰማኝ” (መዝ.
22፥24)።
በተለይም በዚህ ዘመን፣ ስፍራ ከማይሰጣቸውና ከሚናቁት አያሌዎች
መካከል ድኾች፣ በታወቀ ወንጀል የታሠሩ እስረኞች፣ በሽተኞችና ፍጹም ኃጢአተኞች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። በተቃራኒው ደግሞ ዓለም
የ“አንደኞች”ና የጥቂቶች መኾኗን በብዙ መልኩ እያየን ነው፤ ድኾችና በሽተኞች በመንግሥትና በባለ ጠጎች ዘንድ ብቻ ሳይኾን፣
በገዛ ዘመዶቻቸው እንኳ እየተዘነጉ መኾናቸውን አከባቢያችንን ዘወር ብሎ ማየቱ በቂ ማስረጃ ነው። ነገር ግን “እግዚአብሔር ችግረኞችን ሰምቶአልና፥
እስረኞቹንም አልናቀምና።” (መዝ. 69፥33)።
ለድኻና ለእስረኛ፣ ለበሽተኞችና
ምድር ላገለለቻቸው ሰዎች ያለን ቦታና ከበሬታ የመንፈሳዊ ግለታችንንና በረዶነታችንን የሚለካበት አቅም ነው።
ጤናማ መንፈሳዊ ሕይወትና ውቅረ ሥነ ልቦናው ያልተዛባ ማኅበረ ሰብ ካለን ልቡ ፍትህ ላጡና ለድኾች፣ ለበሽተኞችና ለተገለሉ ኹሉ
ስስ ልብ ነው ያለው። ንቀት የእግዚአብሔርን ፍጥረት በማበላለጥ የመመልከት የትእቢት ዐይን ነውና።
እግዚአብሔር አይንቀንም፤
ምክንያቱም፦
1. ፍጥረቱ ነንና፦
ፍጥረት የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ነው፤ ክብሩንም መግለጫ ይኾን ዘንድ፣ በሰው ላይ መልክና አምሳሉን አስቀምጦአል፤ የትኛውም
ጌታና ገዢ የራሱን ክብርና ጌጥ ለባሪያው ወይም ከእርሱ በታች ላለ ሠራተኛ እንዲያው በፈቃዱ አይሰጥም፤ እግዚአብሔር ግን ሰውን
በመልኩና በአምሳሉ ሲፈጥር፣ የገነነ ክብሩን በእርሱ ላይ በማላቅ ነው።
እግዚአብሔር አይንቅም ስንልም፣ በእኛ ላይ ያኖረውን ክብሩን
አይቃወምም፤ አይክደውምም እያልን ነው። የትኛውንም ችጋረኛ ድኻ፣ ዘመድና ወገን ወደ ረሳው፣ መንግሥት በማረሚያ ቤት(በእስር
ቤት) የዘነጋውን፣ በበሽታ ምክንያት ዘመድና አዝማድ አፍሮበት የናቀውን … ጌታ ግን ፈጽሞ ሳይንቀው ይቀበለዋል። “ወደ ችግረኞች ጸሎት ተመለከተ፥
ልመናቸውንም አልናቀም።” (መዝ. 102፥17) እንዲል። ጌታ እግዚአብሔር በተናቀችው በናዝሬት
ከተማ የምትኖረዋን ድንግል ማርያምን አልናቀም፤ እርሷም “የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና” ስትል፣
በእርግጥም መናቋንና መዋረዷን ፈጽሞ ሳይጠየፍ፣ እርሷ ወደምትኖርበት ናዝሬት ድረስ መጥቶአል፣ ተቀብሎኛልም ብላ መናገሯ ነበር።
እግዚአብሔር ክብሩን ገልጦብናልና ፈጽሞ አይንቀንም፤ እርሱ እንኳን ለሰው ለግዕዛን እንኳ ፍጹም አሳቢና አስቦም ተንከባካቢም
ነው፤ ሰውን የሚንቅ እግዚአብሔርን የሚንቅ ነው፤ ምክንያቱም በእያንዳንዱ ሰው ላይ እግዚአብሔር መልኩንና አምሳሉን አስቀምጦአልና።
እያንዳንዱ ሰው የእግዚአብሔር ንድፍና የእጁ ሥራ ነው፤ መልካም በማድረግም ክብርን ያመጣ ዘንድ ተፈጥሮአል።
2.
ልጁን ሰጥቶናልና፦ እግዚአብሔር የገዛ አንድያ ልጁን መድኃኒትና ቤዛ አድርጎ ለዓለሙ
ሰጠው። ልጁን የሰጠን እጅግ አለልክ ስለሚወደንና መጥፋታችንን ስለማይፈቅድ ነው። እግዚአብሔርን የሟቹን ሞት አይፈቅድም፤ ሞት
የሚገባውን እንኳ እግዚአብሔር አይንቅም፤ እንዲያውም ሟቹ በልጁ መስቀል በኩል ከመጣ፣ የትኛውንም ኃጢአተኛ ሊቀበል ኪዳን
ገብቶአል። ጌታ ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወራት ውሎው ኹሉ ከኃጢአተኞችና ማኅበረ ሰቡ ካገለላቸው ሰዎች ጋር እንደ ኾነ
መዘንጋት የለብንም!
ልጁ
ለኹሉም የተሰጠው እኩልና ለኹሉም ሊበቃ በሚችል መልኩ ነው፤ በአገልግሎትና በመዳናችን ነጻነት አስባብ እንኳ፣ ማንንም መናቅ
እንደሌለብን ማስጠንቀቂያ ጭምር አለ፤ “አንተ እውቀት ያለህ በጣዖት ቤት በማዕድ ስትቀመጥ አንድ ሰው ቢያይህ፥ ደካማ ሰው ቢሆን ለጣዖት የተሠዋውን ለመብላት ሕሊናው አይታነጽበትምን? በአንተ እውቀትም ይህ ደካማ ይጠፋል፥ እርሱም ክርስቶስ የሞተለት ወንድም ነው።” እንዲል፣ ፍቅርና ርኅራኄን ገንዘብ ያላደረገ ዕውቀት ከመናቅና ሌላውን ካለመቀበል
የዘለለ ምንም ፋይዳ የለውም።
እግዚአብሔር ግን መዳን ያለበትን ዕውቀትና አንድያ ውድ ልጁን የሰጠን፣
እንድንዋደድና ለሌላው ታላቅና የተቀደሰ አክብሮት እንዲኖረን በማድረግ ጭምር ነው። በእግዚአብሔር ዘንድ እኩል ለመወደዳችን ማስረጃው
ክርስቶስ ለኹሉም እኩል መሰጠቱ ነው። ከምንም በላይ እጅግ በሚልቅ ደግሞ፣ እግዚአብሔር ልጁን ፍጹም በመታመን ወደ እርሱ የሚመጡትን
ፈጽሞ አይንቃቸውም፤ ይቀበላቸዋል፤ “በልጄ የምታምኑ ቡሩካን” ብሎ በባርኮት ቃልም ይጠራቸዋል።
3.
ሥራችንን፦
እግዚአብሔር ለክብሩ መገለጫ የኾንነውንና በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ የምናምን ልጆቹን ፈጽሞ አይንቀንም፤ ክብሩን ለማምጣት በፊቱ
የምንቆመውን ማናችንንም ቢኾን አክብሮ ይቀበለናል፣ በብሉይ ኪዳን
ናታኒሞች በቤተ መቅደሱ የተሰጣቸው የሥራ ድርሻ በሰው ዕይታ እጅግ ዝቅተኛው ነበር፤ ግን ጌታ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን
እንደ የትኛውም አገልግሎት ይቀበለዋል። ትንሽ የሚባል ሰው የሌለውን ያህል፣ የእግዚአብሔርን ክብር የሚያመጣ ከኾነ፣ ትንሽ
የሚባል ሥራ ወይም አገልግሎት በእግዚአብሔር ፊት ፈጽሞ የለም። ምክንያቱም ዋናው የአገልግሎት ማዕከል የእግዚአብሔር ክብር
ነውና!
እግዚአብሔር
ማንንም አይንቅም!
ይቀጥላል …
men Amen Amen EGZIABIHR abzto brk yadrgih.
ReplyDeleteአሜን አሜን አሜን
ReplyDelete