Wednesday, 20 November 2019

ንቀት (ክፍል ፫)

Please read in PDF
ጌታ ኢየሱስ ማንንም አልናቀም!
  “… በተስፋ የተጠበቀው መሲሕ ሌላ ዐይነት ክብር፣ ማለትም የትሕትናን ክብር ለብሶ ነበር በመካከላቸው የተገኘው። አባ ኔቪል ፈጊስ የተባሉ ካህን እንደ ተናገሩት፣ ‘እግዚአብሔር ታላቅ ነው የሚለው የሙስሊሞች እወጃ እውነትነቱ ጉልህ በመሆኑ ያለልዕለ ተፈጥሮአዊ ህልው እገዛ ሰው ሊረዳው ይችላል። እግዚአብሔር ትንሽ ነው የሚለውን ግን ኢየሱስ ለሰው ልጆች ያስተማራቸው እውነት ነው’ …”[1]
   ጌታ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት መንገድ እጅግ አስደናቂና ልብን በመደነቅ የሚመላ ነው። የመጣበት መንገዱና ዓላማው ለብዙዎች የሚጥምና የሚጣፍጥ አይደለም፤ በአዲስ ኪዳንም አገላለጥ ጠባብ መንገድ፣ የግመል መርፌ ቀዳዳ ታህል፣ እስከ መስቀል ሞት መታዘዝ፣ የራስ ክብርንና መብትን መተው፣ ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ … በሚል ውብ ሕይወትና ዝንባሌዎች የተመላ ነው።

   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበት ዋና ዓላማው፣ “የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን እንደ ኾነ በአንደበቱ ተናግሮአል። ምክንያቱም መላለሙ ከፊቱ ጠፍቶ፣ በበሽታ ተከብቦ፤ “ሞቶ”ም ነበርና። ኹላችንም በእርሱ ዘንድ “በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን”ና “የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን፣ እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።” በአጭር ቃል ከኃጢአታችን የተነሣ እኛ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ የተናቅን ነበርን!
   በኃጢአታችን የተናቅነውን እኛን ግን ጌታ ኢየሱስ ሊያድነን መጣ፤ “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤” እንዲል።እኛ በኃጢአታችን ምክንያት የተናቅን አልነበርንም፤ ይህን ምክንያት በማድረግ ደግሞ የሃይማኖት መምህራንና አንዳንዶች በመካከላችን ደግሞ ልዩነትን በማድረግ እጅግ ንቀው እንደ ነበር ታሪክንና ቅዱሳት መጻሕፍትን ስናጠና እናስተውላለን፤ ቅዱሳት ወንጌላት ይህን እውነት ፍንትው አድርገው ያሳዩናል፡፡
    የገሊላ ምድር ነዋሪዎች፣ ሴቶች፣ ሳምራውያን፣ ቀራጮች፣ ዝቅተኛ ኑሮ ነዋሪዎችና ሌሎችም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ተገልጦ ይመላለስ በነበረበት ወራት በእውነት ታይቶአል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኒህን ኹሉ እንዳልናቀ ብቻ ሳይኾን አብሮአቸው በመዋሉ ጭምር የደረሰበትንና ያገኘነውን ነቀፋ ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ያትታሉ።በእርግጥም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ለተናቁትና እጅግ ለተዋረዱት የመጣና ከእነርሱ ጋር በመኖሩም ክብርን ያለበሳቸው ነው።በተለይም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፦
1.      ሴቶችን አልናቀም፦ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣበት ወራት ለሴቶች እጅግ ዝቅ ያለ ክብር ይሰጥ እንደ ነበር ማስተዋል እንችላለን፤ ነገር ግን “ … ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፥ የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐናም ሶስናም ብዙዎች ሌሎችም ሆነው በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር።” እንዲል፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ውስጥ ሴቶች ራሱን የቻለ የአገልግሎት ድርሻ ነበራቸው፡፡
   በስቅለቱና በትንሣኤው፣ ደግሞም መንፈስ ቅዱስ በወረደበት ዕለት፣ ቅዱሳት አንስት የማያሳፍሩ ሴቶች ኾነው የተገኙት፣ ጌታችን ኢየሱስ በማያልቅና በተትረፈረፈ ምሕረቱ አክብሮ ስላቀረባቸውና እነርሱም ፍጹም ፍቅሩን ስለ ተመለከቱ ነው። ያልናቃቸው ሴቶች እርሱን በሞታቸውና በመናቃቸው፤ በመዋረዳቸውም ጭምር አምልከው አክብረውታል፡፡
2.     የታወቁ ኀጢአተኞችና በሽተኞች፦ “ቀራጮችና ኃጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር።  ፈሪሳውያንና ጻፎችም። ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል ብለው እርስ በርሳቸው አንጐራጐሩ።” እንዲል፣ ፈሪሳውያን ጌታችን ኢየሱስ የታወቁ ኃጢአተኞችን አብሮ በመብላቱና በመጠጣቱ ከንቀት ባለፈ ሲያንጎራጉሩበት እንመለከታለን፤ እርሱ እነርሱን ተቀበለ እንጂ ፈጽሞ አልናቃቸውም
    ላልተገባቸው የሚገባና ከሚገባው በላይ የተትረፈረፈ ጸጋ አበዛላቸው፤ ከኀጢአታቸው የሚበልጥ ፍቅርና ርኅራኄ አሳያቸው፤ ከመንግሥቱ በአፍአ መቅረት ለሚገባቸውና ሰዎችና የሃይማኖት መምህራን ላገለሉአቸው ኹሉ ኢየሱስ ቀርቦ አነጋገራቸው፤ ጨክነው በዮሐንስ መጥምቅ ስብከትና በእርሱም ትምህርት ቀርበዋልና መናቃቸውን እስኪረሱ ድረስ ራሳቸውን አክብረው በሕይወት መሰከሩለት፡፡
3.     ባሮች፦ ሮሜ 16ን ስናጠና ብዙ የሮማ ባሮችና ሴቶች ክርስትና መቀበላቸውን ስናስብና በስም መጠቀሳቸውን ስናይ፣ ክርስትና መላውን የሰውን ዘር እንዴት እንደሚያከብርና የኢየሱስ ደም ኹሉን እንደሚያነጻ እናስተውላለን። ክርስቶስ ማንንም ካልናቀና ከተቀበለ እኛም እንዲሁ እናደርግ ዘንድ ይገባናል። ክርስትና ይህን በማድረጉ፣ ለሰው ልጆች ኹሉ እኩል ፍቅርና ርኅራኄን ገንዘብ በማድረጉ እጅግ ታላቅ እምነት እንደ ኾነ እንመሰክራለን፡፡
   የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከኢየሱስ የተማሩት እንዲህ ያለውን ድንቅ ትምህርት ነውና ይህን በማድረግ ክርስቶስ ኢየሱስን ልንመስለው ይገባናል። እርሱ መናቅን ባለመጠየፍ ወደ እኛ እንደ መጣ እንዲሁ፣ እኛም ወደ ተናቁ ማኅበረ ሰቦችና ወገኖች ቀርበን ፍቅርን በመስጠት፣ ሕይወትና ትምህርቱን ልንከተል ይገባናል። መንፈስ ቅዱስ በኃይሉ ኹላችንን ይርዳን፤ አሜን
ይቀጥላል …



[1] ፊልፕ ያንሲ፤ ያላወቅኹት ኢየሱስ፤ 2008 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ራእይ አሳተሚ፤ ገጽ 38

No comments:

Post a Comment