Monday 2 September 2019

ሐዋ. 2 ላይ የብሔርተኞቹ ሸቃጭነት!



በቃሉ ውስጥ ባዕድ ዐሳብ ቀላቅሎ ማቅረብና መሸቀጥ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የማይታዘዙ ሰዎች ኹነኛ መገለጫ ነው (2ቆሮ. 2፥17፤ 4፥2)፤ ከሰሞኑ የተነሡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም፣ ዝቅ ብለውና ወርደው “በክልል ደረጃ፣ በአንድ ብሔር ስም” ክርስትናን “እንመስርት” ባዮቹ አካላት፣ እጅግ ድፍረት በተሞላበት ንግግር መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሰው፣ ይህን እኩይና እቡይ ድርጊታቸውን እንደሚደግፋቸው ሲጠቅሱ ሰምተናቸዋል፤ በቋንቋና በብሔር ክርስትናን ለመደራጀት እንደሚፈቅድላቸው ከጠቀሱት ጥቅስ አንዱ ደግሞ  የሐዋርያት ሥራ ኹለትን ነው።


እውን የሐዋ. 2 እነርሱ እንደሚሉት “በዘርና በቋንቋ፣ በአንድ ቡድንና ጐሳ ለመቋቋምና ለመደራጀት” ፍቅድ ሃሳብ አለውን? ነገድና ቋንቋን ማዕከል ያደረገ ክርስትና አቋቋመ የሚል ሃሳብን በውስጡ ይዞአልን? … የሚል ጥያቄዎችን በማንሳት መጻፍ ግድ ቢለኝ ብእሬን አነሣሁ።
 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሰጠው ተስፋ ቃል፣ መንፈስ ቅዱስ ጌታ ባረገ በአሥረኛው ቀን ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርት ወርዶላቸዋል፤ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸውም ወቅት፣ “በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖችይናገሩ ጀመር” (ሐዋ. 2፥4)።  እንኪያስ ይህን ቅዱስ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ለምን ማርመጥመጥ ተፈለገ? እነርሱ እየሄዱበት ካለው ዐሳብ ጋር ፍጹም ተቃራኒ አይደለምን? አዎን ነው።
ሙግት አንድ
  ሐዋርያት የተናገሩት ቋንቋ እጅግ ብዙ ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ እንኳ ተጽፎ እንደምናገኘው “የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፥ በሁለት ወንዝም መካከል በይሁዳምበቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም፥ በፍርግያም በጵንፍልያም በግብፅም በቀሬናም በኩልባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትምየገባን፥ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች” (ሐዋ. 2፥9-11) ቋንቋን ሲናገሩ ተደምጠዋል፤ ቋንቋውን መናገራቸው ብዙዎችን እጅግ አስደንቆአል፤ አስገርሞአልም።
  ብዙዎች የተደነቁትና የተገረሙበት ምክንያት ቅዱሳን ደቀ መዛሙርት የገሊላ ሰዎች ስለ ነበሩ ነው፣ የገሊላ ሰዎች ነበሩ ማለት እጅግ የተናቁ፣ የትምህርት ደረጃ የሌላቸው፣ ያልተማሩና ዝቅተኛ ኑሮ ነዋሪዎች ነበሩ (ማቴ. 21፥11፤ 26፥69፤ ማር. 1፥9፤ ዮሐ. 7፥41፤ ሐዋ. 1፥11፤ 2፥7) ማለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ለወንጌል አገልግሎት የጠራቸው ሰዎች የገሊላ ሰዎች ማለትም በሰው ዘንድ ምንም ዕውቅና ሊሰጣቸው የማይቻላቸው ሰዎችን ነው፣ ቀለም አልጨበጡም ነገር ግን ሰማያዊውን ሥራ ሊሠሩ ተመርጠዋል፣ ፊደል አልቆጠሩም በዚያን ዘመን የሚነገሩትን ቋንቋዎች ግን በሚገባ ይናገራሉ፤ ቋንቋዎቹ ለእነርሱ የተሰጠበት ዋናው ምክንያትም የወንጌልን እሳት በመላው ዓለም ይለኩሱ ዘንድ ነው።
 ሐዋርያት ባላቸው ማንነት የተመረጡ አይደሉም፤ ወይም እኛ ብሔራችን ይህ ነውና “ልንቋቋም ይገባናል! መብታችን ነው! ከእኛ በቀር ለሕዝባችን ወንጌልን ሊሰብክልን የሚገባው አካል ሊኖር አይገባም!” በሚል እብሪተኛና ዓመጸኛ ሃሳብ ተነሣስተው አልነበረም። ወይም እኛ የሌላው ወገን ቋንቋ ለምን ይገለጥልናል? ከሕዝባችን በቀር የምናገለግለው ሊኖር አይገባም” ብለው በመሲሑ ላይ አላመጹም። እንዲያውም የራሳቸው ባልኾኑት ሌሎች ቋንቋዎች በዓለም ኹሉ ወንጌልን ለመስበክ ተቻኮሉ። የዛሬዎቹ የአንድን ብሔር “ክርስትና” አስፋፊዎች የገሊላ ሰዎች ናቸውን? ኢየሱስ እንዲሠራባቸው ራሳቸውን የሰጡ ናቸው ወይስ በራሳቸው ለመሥራት የተነሡ? እውነታውን፣ በራሳቸው ተመክተው የቆሙ መኾናቸውን ማንም በዳበሳ ይመልሰዋል!
ሙግት ኹለት
 ደቀ መዛሙርት ለራሳቸው ሕዝብና መብት ቅድሚያ መቆም አለብን አላሉም፤ እንዲያውም እንዲህ ያለውን ሃሳብ ጴጥሮስ ኹለት ጊዜ ሲያንጸባርቅ መንፈቅ ቅዱስ በግልጥና በቅዱስ ጳውሎስ አማካይነት ፊት ለፊት ተቃውሞታል፤ “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ፤ …”፣ “ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና።  አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ። (ሐዋ. 10፥28፤ ገላ. 2፥11-12)።
 የመንፈስ ቅዱስ ዓላማ በመላለሙ ቋንቋ ወንጌል እንዲደርስና እንዲሰፋ ነው። ከራሳቸውም አልፈው ለሌላው በመቆረስና በመሰጠት ጭምር ወንጌልን እንዲያዳርሱ ነው፣ አንዳንዶች “ደቀ መዛሙርት ወንጌልን ከኢየሩሳሌም ጀምሩ ተብለዋልና ከገዛ ወገናችን መጀመራችን ምን ችግር አለው?” ሲሉም ተደምጠዋል፣ በቀና ልብ ወንጌልን ከራስ ወገንና ማኅበረ ሰብ መጀመር አንዳች ችግር የለውም፤ እኛም ወንጌልን መስበክ የጀመርነው ከገዛ ቤተሰባችን ነውና፤ ነገር ግን በዐመጽና በልዩነት፣ ሌላውን ወገን በመናቅና በመግፋት የሚደረግን ሃሳብ በሐዋ. 2ም ኾነ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ላይ አናገኝም።
ሙግት ሦስት
  ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ወዲያው እንደ ተሞሉ፣ ሕይወታቸው ተለወጠ፣ የኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት በሕይወትና በንግግራቸው ተብራራ፣ በድፍረትም ተሞሉ፣ መጠራጠርና ፍርሃት ከሕይወታቸው ተወገደ፤ ስለዚህም ኢየሱስን በገደሉት ፊት ቆመው፣ “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” (ሐዋ. 2፥36) አሉ እንጂ ሌላ ሰዋዊ ጥበብን አልተጠቀሙም። ስለዚህም መንፈስ ቅዱስን እንደ ተሞሉ በቀጥታ የተናገሩት የተሰቀለውን ኢየሱስን ብቻ ነው።
 የቋንቋው በብዛት መገለጥና በመንፈስ ቅዱስ አብርሆት ጥርት አድርገው መናገር መቻላቸው ምክንያቱ ወንጌልን ለመስበክና በተሰቀለው ኢየሱስ ትምህርትና ሕይወት አማኞችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ነው። ሐዋርያትም ይኹኑ ኹሉም ደቀ መዛሙርት ከዚህ በዘለለ እንጀራቸውን ለማብሰል፣ ቂጣቸውን ለመጋገር፣ ትዳራቸውን ለማድራት፣ የፖለቲካቸውን ስውር አጀንዳ በሰው ልብ ለመርበብ ፈጽሞ አላደረጉም። እንዲያውም፣ “ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን።” በማለት ደፍረው ተናገሩ እንጂ።
ሙግት አራት
  መንፈስ ቅዱስን ከተሞሉ በኋላ የአገልግሎቱን ክብር ከሚያዋርዱ ጋር ፈጽሞ አልተባበሩም። “ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ …” (ሐዋ. 2፥14) እንዲል፣ በኢየሱስ አንድ የነበሩት ብቻ በአንድነት ተባበሩ እንጂ እነርሱን ከማይመስሉት ማናቸውም አካላት ጋር አልተባበሩም። መልእክታቸውም በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ብቻ አልነበረም፣ “አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ” የሚል ነበር እንጂ።
 የዛሬዎቹ ግን የሐዋ. 2ን እየጠቀሱ ከእነማን ጋር ተባብረው ይኾን የቆሙት? በእውኑ በወንጌል ከሚያምኑት ጋር ነውን? የእነማንንስ መገናኛ ብዙሃን ይጠቀማሉ? ከጀርባቸው ያሉትስ እነማን ናቸው? መንፈስ ቅዱስና የተሰቀለው ኢየሱስ በእርሱ ንግግርና በትምህርታቸው ውስጥ ዋና ናቸውን?
 በእውነተኛ የወንጌል ትምህርትና ሕይወት መገለጥና መመስከር ሲሳን፣ ከፖለቲከኞች ጋር እየተዳሩ ወንጌልን በሰው ብልሃትና ጥበብ ለመመስከር ማሰብ ከትዕቢተኛ ኅሊና አልያም የተዋረደውንና የከበረውን መለየት ከማይችል የወረደ ማንነት የሚመነጭ ነው።
ማጠቃለያ

   የሐዋ. 2 ዋና ጭምቀ ሃሳብ መንፈስ ቅዱስ ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርት መውረዱን፣ ቤተ ክርስቲያን መወለድዋን፣ ደግሞም የቤተ ክርስቲያንን ልደትና የተሰቀለውን ኢየሱስን ለመናኘት የመላለሙ ቋንቋ እንደ ተገለጠላቸው፣ እነርሱም ከእነርሱ ቋንቋ ውጭ መናገራቸው፣ የዚህም ዋነኛ ዓላማ ወንጌልን ለዓለሙ እንዲሰብኩና እንዲያዳርሱ ማድረግ ነው፣ እንጂ የራስን ብሔርና ቋንቋ በማግነን እንድንመካና እንድንታበይበት ሥረ ምክንያትና አመክንዮ የለውም። በራስ ወዳድነት ተጠምደን ራሳቸውን ለመላው ዓለም ቆርሰው በመስጠት ያገለገሉትን ሐዋርያትን ሳናፍር በአንደበታችን ሞልተን፣ ከእኛ ርካሽ ሥራ ጋር ለማዛመድ መጥራታችን ግብዝነታችንን አጥርቶ ከማሳየት በቀር ሌላ ትርጉም የለውም! ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ምድሪቱን ለክፉዎች አሳልፈህ አትስጥ! አሜን።

1 comment:

  1. ati garuu isaan maaliif hin dhistu. isaan bar hojji issanii hojjaacha jiran.

    ReplyDelete