Friday 12 July 2019

የዓምዳዊ ስምዖን ጸሎት

በመስቀል ላይ ሳለህ ራስህን ዘንበል(ዘለስ) ያደረግህ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ወደ አንተ ምስጋና አሳርግ ዘንድ ለሞተውና ላዳነኝ ምስጋና ይሁን እያለች ነፍሴ በአምላካዊ በገና ታመሰግን ዘንድ የነፍሴን ራስ ከፍ ከፍ አድርግ፡፡
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በመስቀል ላይ የሞትክ፥ በሞትህም ሞት ድል የሆነ አንተ እንደ አባትህ ሕያው ስትሆን በሥጋ ሞትን የምትቀበል ሁነሃልና፡፡ ሞትንም የምታጠፋ አንተ ነህና፤ አንተስ መቼም መች አንተ ነህ፤ አንተም የሕይወት አካል ነህ፡፡


ለሞት ተሳብክ፥ በአንተም ሞት ሞት ጠፋ፤ ሕይወትነትህንም በአሳወቅኸኝ ጊዜ አይቶህ ሞት ጠፋ፤ ድምጽህንም ሰምቶ ሞት ጠፋ፡፡ ሙታንም ባወቁህ ጊዜ ዳኑ፤ ሕያው አንተ የሞትን ልብስ ለብሰህ ሙታን ወዳሉበት ወርደሃልና፡፡
ነፍስን የሕይወትን መዐዛ እፍ ባለችባቸው ጊዜ ዳኑ፡፡ ድምጽህን በሰሙ ጊዜ ኃይልህን ተዋሐዱ፤ የፊትህንም ፀዳል ባዩ ጊዜ በብርሃንህ ብሩሃን ሆኑ፤ አንተ የሕይወት ቃል የአብ ኃይሉ ነህና፡፡ አዳምም ድምጽህን በሰማ ጊዜ አወቀህ፤ ፈጣሪው በገነትም ሹመኸው የነበርክ አንተ ነህና፡፡
እርሱ አስቀድሞ ትእዛዝህን ባልሰማ ጊዜ፤ የሞት ገመዶች ተጠመጠሙበት፤ እርሱ ትእዛዝህን ተላልፎአልና፡፡ ዳግመኛም አንተ ሕይወት በሆነ ቃልህ ጠርተህ አዳንከው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ከእንቅልፍ ወደ መንቃት፥ ከመራራ ወደ ጣፋጭ አሳለፍከው፡፡
እንዲሁም ነቢያት በውስጣቸው እንደነበርክ አወቁህ፤ የትንቢት በገናዎቻቸው እንግዲህ ሞት ሆይ መውጊያህ ወዴት አለ?ጨለማ መቃብርስ ድል አድራጊነትህ ወዴት ነው? እያሉ ጮኹ፡፡ ዳዊትስ የነሐስ መዝጊያዎችን ሰበረ፤ የብረት መቈለፊያዎችን ቀጥቅጦ አጠፋ ብሎ ጮኸ፡፡
የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሆኖ ወደ እኛ መጥቶ በእርሱ ነጻ ወጥተን ድነንበታልና፡፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እኔን ኃጢአተኛ ባሪያህን ነጻ አውጥተህ አድነኝ፡፡ በታላቁ መምጫህ ቀን እቀበልህ ዘንድ የነፍሴን ሃይማኖቷንና ምግባርዋን አጽና፡፡ በስህተት መንፈስም በኀልዮ ከመውደቅ አድነኝ፡፡
ነጻ አድርገኝም፤ በሕይወት ምንጭ ዘንድ አኑረኝ፤ አንተ የሕይወት ምንጭ ነህና፡፡ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ አመጣቸው ዘንድ አለኝ፤ እነርሱ አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ ያልክ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ቡሩካን ፍጹማን ከሆኑ በጎችህ ጋር አንድ አድርገኝ፡፡
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የጠፋውን በግ አዳምን ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት የመለስከው አንተ ነህ፡፡ የሰው ልጆችንም ሕያው በሆነ ቃል በሚንበለበልና በሚያላልብ አንደበት እንዲያመሰግኑ ያደረግሃቸው፡፡ በአምላካዊት በገናም እንዲያመሰግኑ ቃላቸውንም ከመላእክት ቃል ጋር አንድ አደረግህ፤ መላእክትንና ሰውን አንድ ማኅበር አደረግህ፤ በመካከልም ሁነህ አስታረቅህ፤ ፍቅር እንድነትና ዕርቅ በአንተ ሁኖአልና፡፡
ያንን ሰላምህን ስጠኝ፤ ከአባትህና ከቅዱሳን መላእክቶችህም ጋር አስታርቀኝ፡፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ጎንህ በጦር ተወግቶ ከእርሱ ደምና ውኃ የወጣ ዓለምን በአነጻሕበት ከዚህ የውኃ ምንጭ አጠጥተህ አድነኝ፡፡
ከአዳም ጎን ተገኝታ ሔዋን የምድር ነገዶችን ወለደች፤ እንዲሁም ከማሕየዊት ጐንህ ለመንግሥተ ሰማይ ልጆች ልንሆን የምትወልደንን የሕይወት ውኃ አወጣህ፡፡ ፍታሜ የሌላትን ሕይወት ወርሼ በአንተ ሕያው ሁኜ እኖር ዘንድ በስምህም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ከዚህች እናት (ጥምቀት) ውለደኝ፤ ስምህም በልቤ ውስጥ ይጻፍ፡፡
ይህ ስምህም የሕይወት ምንጭን ለነፍሴ ያፍስላት፤ ስምህ የሕይወት ምንጭ ነውና፤ ስምህ የሚቀረጽባት ሰውነት ሁሉ ዕውቀት ሕይወትና ብርሃን በውስጧም ይምላ፡፡ ከአንተ ተራቊታ የምትኖር ሰውነት ጥልቅ በሆነ የድንቊርና ዳርቻ ትሞላለች፤ ስምህ በልቡናዬ ውስጥ ይገባ ዘንድ ስጠኝ፤ ልቡናዬንም በኀሳብ ከመውደቅ አድነው፡፡
የከበረ ስምህንም ለማመስገን አንቃው፤ ኀሳቤንና ልቤን ብሩህ ዕውቀትን አሳድባቸው፤ እግዚአብሔር ተነሣ እኛንም ከእርሱ ጋር አስነሣን እያሉ ይሰብኩ ዘንድ፤ አሜን፡፡[1]



[1] መጽሐፈ ግብረ ሕማማት፤ 2005 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት፤ ገጽ 903-905

No comments:

Post a Comment