Saturday 13 July 2019

ከክርስቶስ ይልቅ “ቄሣርን” አወዳሽ “ነቢያት”! (ክፍል - 1)

Please read in PDF
መግቢያ
   በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መካከለኛ ዘመን ታሪክ፣ የቤተ መንግሥትን አስነዋሪ ድርጊት ፊት ለፊት ከተጋፈጡት መካከል በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን የተነሡት ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን፣ በአጼ ፋሲል ዘመን የተነሡት መነኮሳት፣ አባ ፊልጶስና አኖሬዎስ ዘጸጋጅን ተጠቃሽ ናቸው፤ እኒህ አባቶች የነገሥታቱን አመንዝራነት፣ ፍትህ አልባነት፣ ድኃ ገፊነት፣ እጆቻቸውን በደም መታጠብ ፊት ለፊት የተጋፈጡና በሕይወታቸው ተወራርደው ዋጋ የከፈሉ ናቸው።
   እስጢፋኖሳውያን ዘርዐ ያዕቆብ እጁን ከቤተ ክህነትና ከቤተ ክርስቲያን እንዲያነሣ ደጋግመው ሞግተዋል፤ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት ጋብቻ ሊፈጽሙ አይገባም በማለት ይናገሩ የነበሩት የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን አማኞችና አባቶች ሳይሳሱ ፊት ለፊት ተጋፋጭና ተሟጋችም ነበሩ፤ በቤተ ክርስቲያን በትር ዙፋናቸውን ያጸኑ አያሌ ነገሥታት ኢትዮጵያ የነበራትን ያህል፣ ነገሥታት በቤተ ክርስቲያን በትር ዙፋናቸውን ማጽናታቸውን እንዲያቆሙ የተጋደሉ አያሌ አባቶችንም[መጨረሻቸው መሥዋዕትነት ቢኾንም] ነበሩ።




   ዳሩ ግን የነገሥታት ሎሌዎችን አሽከሮች፤ አጋፋሪዎችና የዕድፋቸው መራገፊያዎች እጅግ ለቊጥር እስኪታክቱ ድረስ፣ እስከ ዘመናችን ድረስ ታይተዋል፤ ለነገሥታት የሐሰት ትንቢት በመናገርና ሐሰተኛ ተስፋ በመስጠት የታወቁ ሐሳዌ ነቢያት በቅዱሳት መጻሕፍት አሉ፤ እንዲህ ያሉ ነቢያት ለብዙዎች መሞትና በሰቆቃ መኖር ዋና ተጠያቂዎች ናቸው። የነገሥታትን የፈገገ ፊት ለማየት ሲሉ እውነትን የሚሰዉ፣ የሰውን ደስታና ከሰውም ክብርን ለማግኘት ሲሉ በቆሙበት አደባባይ ያልተጠሩበትን ሕይወት የሚለፍፉ እጅግ አሳፋሪ ነቢያት ከትላንት እስከ ዛሬ በሽበሽ ናቸው። ስንቶቻችን በቅዱሳት መጻሕፍት ሚዛንነት መዝነን ለይተን፤ አበጥረን፤ አንጠርጥረን እናውቃቸው ይኾን?!
የተጠሩበትን አሳንሰው …
   የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር በየትም ይሁን በየት፣ ከጠራው ጌታና ከተጠራበት አዋጅ ውጪ ሌላ መልእክት፣ ሌላ የአደራ ቃል የለውም። ለኢየሱስ ወንጌል ተጠርተን ሌላ ነገር ከቀባጠርን፣ የመስቀሉን ሥራ ትተን በፖለቲከኞች ምጣድ ተጥደን ከተንጣጣን፣ በእርግጥም የጠራን አንሶብናል፤ የተጠራንለትም የወንጌል መልእክት አንሶብናል። ምናልባትም ደግሞ ለመዳን ወንጌል አገልጋይነትም አልተጠራን፤ ከመጀመሪያውኑ ምሪት አልነበረንም ማለት ነው።
    ቅዱስ ጳውሎስ እንኳን አትሮንስ ተዘርግቶ፣ መድረክ አጊኝቶ፣ እንኳን ወንበር ተለቆ፣ እንኳን “ና!” ተናገር የሚል ጋባዥ አጊኝቶ … እንዲያውም እጅና እግሩ በሰንሰሰለት ታስሮ፣ ስብከቱ ወንጌል፣ ሃሳቡ የተሰቀለው ክርስቶስ፣ ርእሱ መሲሑ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። በየትም ይኹን በየት፣ በማናቸውም መድረክ ቆሞ ከክርስቶስ ውጪ አንዳችም አጀንዳና ጉዳይ የለውም። ከታላቁ ጥሪና ከታላቁ ሕይወት ወደ ውራጅና እራፊ ክብር፣ ከእግዚአብሔር ክብር አንጻር፣ እላቂ ልቅላቂ ከኾነው “የፖለቲካ መንደር” የክብር ፍርፋሪ ፍለጋ መች ተንከላወሰና! ሮማውያኑ የፖለቲካ ባለሥልጣናት ፊት ፊልክስ ይኹን አግሪጳ ፊት በሰንሰለት ታስሮ ሲቆም ከኢየሱስ በቀር ምን ርእስ፤ ምን ስብከት ነበረውና?!
   በትክክል ተጠርቷልና ከተጠራለት ውጪ ሕይወትና ኑሮ የለውም። መልእክቱ ግልጥ፤ ሃሳቡ የማያወላዳ ነበር፤ እርሱ የመንግሥት ሚዲያና መድረክ ቢያገኝ ዲስኩረኛ አይደለም። ልኩ ወንጌል፤ ሕይወቱ ክርስቶስ ነው። አንድም ቀን የሰውን ፊት ደስ ለማሰኘት አልቀባዠረም፤ አላለሳለሰም፤ አልቀላመደም፤ አላመቻመቸም፤ የማይለወጥ የዘለዓለም ርእሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነበር፤ ነውም!!!
    ከሰሞኑ ከወደ ወንጌላውያኑ “ነቢያት” የሰማነው ነገር፣ “ባለተረኛ አወዳሽ መሪጌቶችና አጋፋሪዎች” አስመስሎአቸዋል፤ ስቁሉን ኢየሱስ ወዲያ አሽቀንጥረው ቤተ መንግሥቱን ለጉድ ይክቡታል፤ ያገኑታል፤ ያቆነጁታል፤ ይኩሉታል፤ ያሞካሹታል፤ ያንቆለጳጵሱታል፤ በተቃራኒው ደግሞ የጽድቅ “አገልጋይነታቸውን” ከምንጣፍ ሥር እንዳለ ቈሻሻ ረግጠውት ሲያበቁ፣ ያልነበሩበትና ያልኖሩበት ይመስል፣ “ጠላት፣ የጨለማ ዘመን፣ የሰቆቃ ዘመን” እያሉ፣ “የቀደመውን” ዘመነ መንግሥት ሲራገሙ እንሰማቸዋለን፤ ምነው አኹን የታያቸው ያኔ ተሰወረባቸው?! የጽድቅ አገልጋይ በጊዜው እንጂ አለጊዜው ተናጋሪ ፖለቲከኛ ወይም ግብዝ አይደለምና።
   ይህ ኹሉ ግፍ፣ ያ ኹሉ ሰቆቃ፣ ያ ኹሉ ትርምስ፣ በምድራችን ላይ የሚታየው መቋጫ አልባ የደም መፍሰስ … መነሻ ምክንያቱ የቤተ ክርስቲያን ቅጥ ያጣ ዝምታ ነው፤ ለዘመናት ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት አጋፋሪ እንጂ የጽድቅ ምስክርና ተሟጋች አልነበረችም፤ ቤተ ክርስቲያን ለመልካም ነገር ዝም ባለች ቁጥር ዐመጽ ገደቡን ጥሶ አይተናል፤ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ብቻ ከብዙ አሰቃቂ ዕልቂትና ጦርነት መትረፋችንን እኛው ምስክሮች ነን፤ ዛሬ እንደሚታየው የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከኢየሱስ የፍቅር አገልጋይ ይልቅ፣ የቄሳርና የሰው ብልሃታዊ መልቲ አገልጋይ መኾንን በመምረጣቸው ወንጌሉ በማያምኑ ዘንድ እስከ መሰደብ ደርሶአል።
ጌታንና ቄሳርን ለማስደሰት የሚጣር ጥረትና ግረት ከንቱ ብቻ አይደለም፤ ስለትን በአንገታችን ትይዩ የመሰንቀር ያህል ሰቅጣጭና እረፍት አልባ ስቃይ ነው። ለዘመናት ከበጎች ጋር የኖረ ውሻ አንድ ቀን ድንገት፣ እረኛው በሥጋ ቤት በር በኩል በጎቹን ሲነዳ፣ መታገስ ተስኖት ራሱን በውሻነት እንደ ገለጠው ውሻ፣ ዕድልና ገላጭ ነገር እስኪመጣ ድረስ አማኝ መስሎና አገልጋይ ነኝ ብሎ ራስን መካብ፣ እንዲህ ባለ ቁርጥ ሰዓት ማንነት መገለጡ አይቀርም። የኢየሱስ እውነተኛ ማንነት ያለው እውነተኛ አገልጋይ ዓይኑ መስቀሉ ላይ፣ ልቡም የተሰቀለው ክርስቶስ ላይ ብቻ ነው፤ ከዚህ መውረድ ምስኪንነትና እጅግ መታለል ነው፤ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን ብቻ በሚያከብረው በመስቀሉ ሥራ ልባችንን ይሰረው፤ ይያዘውም፤ አሜን።
ይቀጥላል …

2 comments:

  1. fetari yibark wendme ene erasus yeyaziw beg wsha new bayi sibeza tedenegagre neber eyesus kene gar new adis geta yelem

    ReplyDelete
  2. ጌታንና ቄሳርን ለማስደሰት የሚጣር ጥረትና ግረት ከንቱ ብቻ አይደለም፤ ስለትን በአንገታችን ትይዩ የመሰንቀር ያህል ሰቅጣጭና እረፍት አልባ ስቃይ ነው። ewnet new

    ReplyDelete