Tuesday 16 July 2019

ከክርስቶስ ይልቅ “ቄሣርን” አወዳሽ “ነቢያት”! (ክፍል - 2)

Please read in PDF
ጸያፍ ድፍረት
   ራሱን ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እንደ አንዱ እንደ ኾነ የሚቈጥረው፣ የ“Christ Army” ቴሌቪዥን ባለቤት ኢዩ ጩፋ፣ ስሙንና ክብሩን በሚናኝበት በገዛ ቲቪው ላይ “ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጻፍኩት” ባለውና በገዛ ቲቪው ላይ “ሲደሰኩር”፣ ለኢየሱስ የሚነገሩትን ምሳሌዎች በመላ ወስዶ ለጠቅላዩ ሲናገር እንሰማዋለን፤ እንዲህ ይላል …
“ … ዕውቀትህ አስገራሚ ነው፣ ንግግርህም ይፈውሳል፤ እንደ ነቢይ ትተነብያለህ፣ እንደ መምህር አስተማሪ፣ እንደ አባት መካሪ ነህና ዕድሜ ይጨምርልህ፤ አባት ነህና እንደ አብርሃም፣ ንጉሥ ነህና እንደ ዳዊት፣ ነቢይ ነህና እንደ ሙሴ፣ ካህን ነህ እንደ ኢያሱ፣ ጠቢብ ነህ እንደ ሰሎሞን፣ ደፋር ነህ እንደ ጳውሎስ፣ ታጋሽ ነህ እንደ ኢዮብ፣ ቆራጥ ነህ እንደ ሩት፣ ባለ ራእይ ነህ እንደ ዮሴፍ … እነዚህን ኹሉ ነህና …”
  ከሰማኹት በኋላ ጆሮዬ ጭው ብሎአል፤ ደንግጬ ከመናገርም ከመስማትም ተቆጥቤ፣ ነገሩን ነፍሴ ተጸይፋውም በተደጋጋሚ “በኢየሱስ ስም እንዲህ ያለ ክፉ ነገር ከእኔ ይራቅ!” ብዬአለሁ። የመሸታ ቤት አዝማሪ እንኳ ይህን ያህል ገንዘብ ለከፈለው ወርዶ አያወድስም!!!


    የአብርሃምን አባትነት ያስረሳ ከኢየሱስ በቀር ማን አለ? የዳዊትን ዙፋን የወረሰ ከመሲሁ በቀር ከወዴት አለ? እንደ ሙሴ ያለና ሙሴ ራሱ የተነበየለት ዋና ነቢይ ከኢየሱስ በቀር በውኑ አለን? ኢያሱንና ታላላቅ ካህናትና ሊቃነ ካህናትን ያስረሳና የሻረ … በሙሉ መሥዋዕታዊ ሞቱም ወርሶ የጠቀለለ በውኑ ከኢየሱስ በቀር ሊነገርለት የሚገባው አለን? እንዲህ ያሉ ብርቱ ቃላትስ ከኢየሱስ በቀር ለማን ሊነገር ይቻለዋል? የእኒህን ኹሉ ቅዱሳንን ክብር የጠቀለለና ለአባቱ መንግሥት በመታዘዙ፣ አባቱን ደስ ያሰኘ በሰማይም ይኹን በምድር፣ ከሰውም ኾነ ከመላእክት ወገን … ቢፈለግ፣ ቢታሰስ … ከኢየሱስ በቀር ከየት ሊገኝ ይችላል?
  በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ፣ የሃይማኖት አባቶችን ሰብስበው ባናገሩበት ወቅት፣ ከኹለት የሚበልጡ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች “እንቶ ፈንቶ” ሲያወሩ፣ የካቶሊኩ አባት፣ “ቄስ ዕጣን፤ ዕጣን እንጂ ፖለቲካ፤ ፖለቲካ መሽተት አይገባውም” ማለታቸው የማይረሳ የብዙዎች ትዝታ ነው። ወርዶ ምድር ለምድር ከሚርመጠመጥ አገልጋይ ጌታ ኢየሱስ ይጠብቀን! አሜን።
   ከኢአማኒ ድፍረት የአማኝ ድፍረት እንዴት ያለ ጸያፍና አስነዋሪ ነው። በቤተ ክህነት መሪጌቶችና አጋፋሪዎች በየሰንበቱ መወድስና ቅኔ የሚያቀርቡላቸው የደብር፣ የአድባራት፣ የገዳማት አስተዳዳሪዎችና ጳጳሳት ቊጥራቸው የዋዛ አይደለም፤ በነገሥታት ዘመን ደግሞ ለነገሥታትም ይሰጥ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ተረኛ ነን ባዮቹ “ለጠቅላዩ የጸጋ ክብር” ሲያቀርቡ እንመለከታለን።
 የኢዩ ጩፋ ዕውርነት፤ ከንቱ አወዳሽነት እንዴት ልብ ይሰብራል? እንኳን ፍጻሜው ምን እንደ ኾነ ያልታወቀ አንድ ምድራዊ መሪ አይደለም፣ የሰሎሞንን ፍጻሜ ያየ የቱም አማኝ፣ ከምልጃ፣ ከጸሎትና ከመቃተት ባለፈ…  “ሰው ከንቱ፣ ጌታ ብቻ ብርቱ” ብሎ እጁን በአፉ ከመጫን የዘለለ ሥራ አይሠራም፤ ምድራዊ መወደድን ለማግኘት ሰማያዊውን ነገር ለማልኮስኮስ ማሰብ ከአለማመን እኩል ነው፤ እንዲህ ያለ ሰው ቀድሞ ወንጌል ባይሰማ ይሻለው ነበር!!!
የመጽሐፍ ቅዱስን ዐውድ ሰጋጊ “ነቢያት”
  ሌላው የማርሲል ቴሌቪዥን ባለቤት ደግሞ “ኢትዮጵያ ብዙ ጠላቶች እንዳሏትና እርሷ ግን ኹሌም አሸናፊ እንደ ኾነች አበክሮ ሲናገር ሰምተነዋል፤ ጠላቶቿ እነማን እንደ ኾኑ ባይነግረንም”። በተመሳሳይ መንገድ ደግሞ ኢዩ ጩፋ፣ “ኢትዮጵያ ከዓለም ተለይታ የቃል ኪዳን ምድር መኾንዋን” እጅግ በተደጋጋሚ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐውድ ውጭ የኾኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባትን አጥምሞ በመተርጐም ሲያቀርብ ተመልክተነዋል፤ “ኹለቱ ነቢያት” የኢትዮጵያን ገናናነት፣ የኪዳን አገርነት ሊነግሩን ሲቃጣቸው ተመልክተናል። [ይህን ግን ከየትኛው ድርሳነ ባልቴት አገኙት ይኾን?]



   እግዚአብሔር ዓለሙን ኹሉ የወደደበትን የልጁን የመንግሥት ወንጌል ለምንሰብክ አማንያን፣ ኢትዮጵያ ለእግዚአብሔር የኪዳን አገር ከኾነች፣ ሶማሊያ፣ አፍጋኒስታን፣ ማሌዢያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሮም፣ ካዛኪስታን፣ ማልታ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ … የኪዳን አገራት የማይኾኑበት ምክንያት አይገባኝም። ቅልጥ ያለው ዘረኝነታችንን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሰፍተን ለመልበስ ካልዳዳንና ካልከጀልን በቀር፣ የኢየሱስ ኪዳን የመላለሙ ኪዳን ነው፤ ከዚህ ኪዳን ነጥሮ ለኢትዮጵያ የተሰጠ የተለየ ኪዳንም፣ ውልም፣ ስምምነትም እግዚአብሔር የገባውም የሰጠውም ነገር የለም።
  አለ የሚል ካለ፣ ሲያቃዣቸው ወይም ለማሳት በሰይጣን ተልከው ከጻፉት ከደባትራን ድርሳንና ገድል ለመጥቀስ ካልኾነ በቀር፣ ኢትዮጵያ ከአለም አገራት በተለየ ኪዳን መጠራቷን የሚነግረን አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም፤ ኹል ጊዜ የሚፎከርበት ነገር ቢኖር፣ “እኛ ከ40 ጊዜ በላይ ስማችን በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎአል” የሚል ነው፤ ከእኛ በብዙ ዕጥፍ የተጠሩት አገራት ምነው እንደ እኛ አልሸለሉ? አልፎከሩ? አልተመኩ? … ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ስሟ በተደጋጋሚ የተጠራችው እስራኤል፣ በመመካቷና በእግዚአብሔር ላይ በመቀማጠሏ ምክንያት የተከላት ያው ያህዌ እንዴት እንደ ነቀላትና በምድር ኹሉ ፊት በትኖ እንዴት እንዳዋረዳት ያነበብን አይመስለኝም!!! ለዚህ ነው እኛም በተደጋጋሚ በዘረኝነት ሱስ ተጠላልፈን ከዓለም የተለየን አድርገን ራሳችንን በመቊጠር የምንጃጃለው!!!
  ይህን እውን ለማድረግ ኢዩ ጩፋ ጥቅስ ያጣምማል፤ አሞጽ የተናገረውን ግልጹን ትንቢት ኢትዮጵያን ለማወደስ በማሰብ ብቻ ዐውዱን አጥምሞ ሲተረጉም እንመለከተዋለን፤ የተጠቀሰው ቃል እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር። እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?” (አሞ. 9፥7)። ቃሉ የተነገረው በመመረጧ ለኮራችውና ለደራችው እስራኤል ነው፤ እግዚአብሔር በአጭር ቃል ሊናገራቸው የፈለገው፣ “አንቺ እስራኤል ሆይ! እጅግ ስለኮራሽ፣ ስለተመካሽም በእኔ ዕይታ ከኢትዮጵያውያን፣ ከግብጽ፣ ከፍልስጥኤም፣ ከሶርያ ምንም አትለዪም፤ ምክንያቱም አንቺን ክግብጽ ምድር መርቼ እንዳወጣኹ እንዲሁ እነርሱንም በስደት መራኋቸው፤ ሉዓላዊ አምላክ እኔ ነኝና” ማለቱን እንደ ኾነ ዐውዱን ስናጠና እናገኘዋለን፤ እንጂ ለእንቁልልጭ ኢትዮጵያውያን ከእስራኤላውያን ይሻላሉ የሚል ሰጊጎታዊ ትርጉምን አይሰጥም።
   ደግሞስ አሞጽ የተናገረላት ኢትዮጵያ፣ የትኛዋ ኢትዮጵያ ትኾን? አኹን ያለችውን ኢትዮጵያን ወይስ መልክዐ ምድሯ ከዚህችዋ እጅግ የበዛውንና የሰፋውን? በዚህ ረገድ በዚሁ ብሎግ ላይ የተጻፈውን ሰፊ ጽሁፍ መመልከት ይቻላል።
በሚሊኒየም አዳራሽ ንግግሩ ዮናታን፣ “ዳዊት ቂም አወረሰ” ማለቱን ከወዴት አመጣው?
  መቼም የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነተኛ ትርጉም ሳያውቁ ደፍሮ እንደ መናገር ያለ ትዕቢት ፈጽሞ የለም፤ አድማጭ አገኘን ብለን ሆዳችን ያባውን ኹሉ የምንዘረግፍ ከኾንን፣ ጤናማነታችንን አስቀድመን መመርመር እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። በውኑ ዳዊት ቂም ነው ያወረሰውን? ዳዊትስ በግል ሕይወቱ እንዲያ ያለ ዝንባሌ ያለው ሰው ነውን? ዳዊት በግል ሕይወቱ፣ ለኢያቢስ ገለአድ ሰዎች “ … እናንተ ለጌታችሁ ለሳኦል ይህን ቸርነት አድርጋችኋልና፥ ቀብራችሁትማልና በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ሁኑ” ብሎ የተናገረ አይደለምን? (2ሳሙ. 2፥5)፣ ደግሞስ ለዮናታን ቤት እንዴት ያለ ቸርነት እንዳደረገ መዘንጋት ማበል አይኾንምን?
“ …የሳኦልም ልጅ የዮናታን ልጅ ሜምፊቦስቴ ወደ ዳዊት መጣ፥ በግምባሩም ወድቆ እጅ ነሣ፤ ዳዊትም፦ ሜምፊቦስቴ ሆይ፥ አለ፤ እርሱም፦ እነሆኝ ባሪያህ አለ። ዳዊትም፦ ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ቸርነት ፈጽሜ አደርግልሃለሁና አትፍራ፤ የአባትህንም የሳኦልን ምድር ሁሉ እመልስልሃለሁ፥ አንተም ሁልጊዜ ከገበታዬ እንጀራ ትበላለህ አለው። እርሱም፦ የሞተ ውሻ ወደምመስል ወደ እኔ የተመለከትህ እኔ ባሪያህ ምንድር ነኝ? ብሎ እጅ ነሣ። ንጉሡም የሳኦልን ባሪያ ሲባን ጠርቶ፦ ለሳኦልና ለቤቱ ሁሉ የነበረውን ሁሉ ለጌታህ ልጅ ሰጥቻለሁ። አንተና ልጆችህ ሎሌዎችህም ምድሩን እረሱለት፤ ለጌታህም ልጅ እንጀራ ይሆነው ዘንድ ፍሬውን አግባ፤ የጌታህ ልጅ ሜምፊቦስቴ ግን ሁልጊዜ ከገበታዬ ይበላል አለው። ለሲባም አሥራ አምስት ልጆችና ሀያ ባሪያዎች ነበሩት።” (2ሳሙ. 9፥6-10)
   ዳዊት ይህ ብቻ ሳይኾን ለሌሎችም ብዙ ቸርነትን በማድረግ ይታወቃል፤ ነገር ግን በሚሊኒየሙ አዳራሽ ንግግር፣ ይህን የዳዊትን እውነታ ሽምጥጥ አድርጐ ሲክድ የማርሲል ቲቪን ባለቤት እንመለከተዋለን፤ ዳዊት ሽበቱን በቂምና በበቀል ውርስ አላወረደም፤ ዳዊት ሚዛናዊ ነበር፤ መቃብሩ ተቃርቦ እንኳ ቸርነትን ከማድረግ አልተከለከለም፤ ለሰሎሞን ሲናዘዝ፣ ለቤርዜሊ ልጆች የተናገረውን መዘንጋትም ፈጽሞ አይገባም፤ “ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ ቀርበውኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች መልካም ቸርነት አድርግላቸው፥ በማዕድህም ከሚበሉት መካከል ይሁኑ” (2ነገ. 2፥7)።
  ዮናታን ቂም ብሎ የሚናገረው፣ “… አንተም ደግሞ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ፥ ሁለቱን የእስራኤልን ጭፍራ አለቆች የኔር ልጅ አበኔርን የዬቴሩንም ልጅ አሜሳይን ገድሎ፥ በእኔ ላይ ያደረገውን ታውቃለህ፤ የሰልፉንም ደም በሰላም አፈሰሰ፥ በወገቡም ባለው ድግና በእግሩ ባለው ጫማ ንጹሕ ደም አኖረ። አንተም እንደ ጥበብህ አድርግ፥ ሽበቱንም በሰላም ወደ መቃብር አታውርደው” (2ነገ. 2፥5-6) በማለት የተናገረውን አስቦ እንደ ኾነ እሙን ነው። ነገር ግን ይህ ክፍል የዳዊትን ቂመኝነት ፈጽሞ አያመለክትም፤ ይህን እንደ ቂም ከቈጠርን የቀደመውን ኪዳን መሠረትና እውነታ ፈጽመን አናውቅም ማለት ነው።
   ምክንያቱም የቀደመው ኪዳን የቆመውና የተመሠረተው በሕጉ ላይ ነውና፤ በሕጉ ደግሞ አንድ ሰው አንድን ሰው መግደል አይችልም፤ ኢዮአብ ግን እንዴት ባለ ጥላቻና ቂም ታስሮ፣ አሸምቆ አበኔርን እንደ ገደለ ማስታወስና አሜሳይንም እንደ ገደለው መናገር ይበቃል፤ (2ሳሙ. 3፥23-27፤ 20፥10)፤ እንዲህ ያለ ታስቦ ለሚፈጸም ግድያ ሕጉ ምን ይላል? ብሎ መጠየቅ ፍጹም ከመሳሳት ይጠብቃል፤ “ሰው ግን ባልንጀራውን ቢጠላ፥ ቢሸምቅበትም፥ ተነሥቶም እስኪሞት ድረስ ቢመታው፥ ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ፥ የከተማው ሽማግሌዎች ይልካሉ፥ ከተማጠነበትም ከተማ ይነጥቁታል፥ እንዲሞትም በደም ተበቃዩ እጅ አሳልፈው ይሰጡታል። ዓይንህ አትራራለት፤ ነገር ግን መልካም ይሆንልህ ዘንድ ንጹሑን ደም ከእስራኤል ታስወግዳለህ” (ዘዳግ. 19፥11-13)።
   ሕጉ በግልጥ ይህን ይላል፤ ኢዮአብ ያለምንም ርኅራኄ ኹለት የእስራኤል ኃያላንን፣ በኋላ ሰሎሞን እንደ መሰከረላቸው ደግሞ “ከእርሱ የሚሻሉትን ሁለቱን ጻድቃን ሰዎችን” (1ነገ. 2፥32) ኢዮአብ አሸምቆ፣ አስቦበት ገድሎአል፤ በዚህ ሳያበቃ ከአዶንያስ ጋር “ሰሎሞንን ለመግደል” ሴራ ሲሸርብ ሲደረስበት፣ ያልተፈቀደለትን ተግባር ማለትም፣ ወደ መማጸኛ ከተማ ገብቶ የነሐሱን መሠዊያ ጨብጦአል፤ ነገር ግን ወደ መማጸኛ ከተማ መግባትና መማጸን የሚቻለው አስቦ ለሚገድል ወይም ለመግደል ላሰበ ሰው ሳይኾን ሳያስብ ወይም በቸለተኝነት ለገደለ ሰው ነው፤ ኢዮአብ ግን አኹንም በሌላ በደል ተያዘ፤ እናም ሰሎሞን በሕጉ በደል የተገኘበትን ሰው ገደለው። ጉዳዩ የቂም ጉዳይ ሳይኾን ለሕጉ የመታዘዝና ያለ መታዘዝ ጉዳይ ነው፤ ይህ ደግሞ በቀደመው ኪዳን ለሕጉ በመታዘዝ በረከትን ባለ መታዘዝ ደግሞ መርገምን የማጨድ ጉዳይ ነው። ይህን አቅልሎ፤ የኪዳኑን እውነታ ሽሮ “ቂምና በቀል” ብሎ መናገር ፍጹም አለማስተዋል ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ለእውነትና ለፍቅር መታዘዝን ይስጠን፤ ለቅዱስ ቃሉም ሥልጣን እንድንገዛ ጸጋውን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያብዛልን፤ አሜን።
ይቀጥላል …

2 comments:

  1. yemisema kale tru mikr new.

    ReplyDelete
  2. እነዚህ መች ይሰማሉ ገና ሳይመለኩ ይቀራሉስ

    ReplyDelete