Thursday, 30 May 2019

በሕማሙና በትንሣኤው ዙርያ የነበሩ ምስክሮች (ክፍል አራት)

  2.  ክርስቶስ ኢየሱስን ሕይወት አይታለች፦ ጌታችን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የእርሱን ሕይወት ከእርሱ ጋር ውለው፤ አድረው እንዲያዩ ደግሞም አብረውት እንዲኖሩ ፈቅዶአል፤ (ዮሐ. 1፥40)። ከዚህም ባሻገር ጌታችን ኢየሱስ ራሱ ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ ካደረ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ሲመርጥ “ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥” ወዶ እንደ ኾነ ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ ይመሰክራሉ፤ (ማር. 3፥13-14)።
   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀጥአንን ተቀባይ መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ደጋግመው ገልጠዋል፤ ግብዞችንና አስመሳዮችን፣ የሕይወት ቲያትረኞችን እጅግ ይጠየፍ የነበረው ጌታ ኀጥአንን ግን በአደባባይ ሳይታዘባቸው ተቀብሏል፤ አብሮአቸው ተመግቦአል፤ ሳይጠየፋቸው በአንድነት ከእነርሱ ጋር አሳልፎአል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከኀጢአተኞች ጋር ማሳለፉ ለብዙዎች አይሁድ የማይዋጥላቸው ተግባር ነበር፤ ምክንያቱም በግልጥ እንደ ሕጉ መለየትና መወገዝ እንጂ ተቀባይነትን ማግኘት አለባቸው ብለው ያምኑ አልነበረምና።

   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደርገው የነበረውን ይህን አስደናቂ ሥራ የመግደሎሟ ሴት ማርያም ተመልክታለች፤ የተመለከተች ብቻ አይደለችም፤ እርሷ ራሷ ምስክር ናት እንጂ። ጌታችን ኢየሱስ እርሷን እንኳ ከነኃጢአተኛ ማንነቷ የተቀበለ ነው፤ ሌሎች ኃጢአተኞችን የተቀበለው ጌታ ኢየሱስ እርሷንም እንደሚቀበል እርግጠኛ ነበረችና፣ ወደ እርሱ በእምነት ቀርባ ነበር። ሌሎች ኃጢአተኞችን የተቀበለው የኢየሱስ የርኅራኄ ልብ በሕይወቱና በትምህርቱ በእርጋታ ይነበቡ ነበርና፣ ማርያም መግደላዊት ይህን በሚገባ አስተውላለች።
   የትኛውም ኀጢአተኛ ከኢየሱስ ፊት ቢቀርብ፣ ራሱን አለመመልከት አይችልም፤ የትኛውም ኀጢአተኛ ደግሞ ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘ በኋላ የመጀመርያውን ዐይነት የሕይወት ምልልስን ፈጽሞ አይመላለስም። ብዙ ኀጢአተኞች ከኢየሱስ ጋር ከተገናኙ በኋላ በሕይወቱ ፍጹም ተማርከው ለአንድያው ቀርተዋል፤ የነበሩበትንም ሕይወት ፈጽመው እጅግ ተጠይፈውታል፤ የቀድሞ የኀጢአት ሕይወታቸውንም ማየት እስኪጠሉት ድረስ አፍረውበታል። ኢየሱስ የነበርንበትን የኀጢአት ሕይወት የሚያሳየንና እንድናፍርበት የሚያደርገን ብቻ አይደለም፤ ደግሞም ከዚያ ሕይወት እንድንወጣ እጅግ ብርታትና አቅምን፤ ኃይልንም የሚሰጠን የተወደደ ውድ አምላክና አባት ነው።
   ማርያም መግደላዊት ያልታዘባትንና ያልናቃትን፣ ከነሙሉ ድካሟና ብርታትዋ የተቀበላትን የኢየሱስን ሕይወት ከተመለከተች በኋላ ራስዋን እንደ ውኃ በማፍሰስ ተከትላዋለች። ኢየሱስ እጅግ የተዋረደና ዝቅ ያለ ሕይወትን በመኖር፣ ከመላእክት እንኳ ጥቂት አንሶ፣ የባርያን መልክ ይዞ፣ ከኃጢአተኞች ጋር እንደ ኃጢአትና እንደ ኃጢአተኛ ተቈጥሮ መናቁና መተዉ ማርያም እስከ መጨረሻ እንድትሰበርና እንድትሸነፍ አድርጐአታል። ትልቁ ትንሹን፣ ክቡሩ ወራዳውን፣ ቅዱሱ ኀጢአተኛውን ... መቀበሉና ማክበሩ ክርስትናን ከሃይማኖቶችና ከኹሉም ሰዋዊ አመለካከቶች ልዩና ወደር የለሽ ያደርገዋል።
   ሕይወት የሚለወጠው በሕይወት ነው፤ የተሰጠ ሕይወት ሕይወትን ያሰጣል፤ ብዙ ኃጢአተኞች እስከ ሰማዕትነት ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡት ኢየሱስ ሕይወቱን ሳይሰስት እንደ ሰጣቸው በትክክል ስላስተዋሉ ነው። እሳት፣ ስለት፣ የአንበሳ መንጋጋ፣ ራብ፣ ጥም፣ የሞት ማስፈራት፣ ስደት፣ ዝቅታ፣ ማጣት፣ የመንግሥታት ግርማ፣ የወታደሮች ጭካኔ፣ የዓላውያን ነገሥታት ዛቻ ... የዝማሬ ርእስ የኾኑት ኢየሱስ እኒህን ኹሉ ታግሦ ሕይወትን ስለከፈለልንና ስለሰጠን ብቻ ነው።
   ዛሬ ብዙች ለጌታችን ኢየሱስ ሕይወትን መስጠት የሰሰትነው፣ ሕይወቱን በትክክል እንደ ሰጠልን ስላላመንን ወይም ስላላስተዋልን ነው። ለብዙዎች ስሙን ሲመሰክሩ ለሚመጣባቸው ስደት የሚያዝኑት፣ የቀብር ቦታ እናጣለን ብለው የሚሰጉት፣ ከዕድር እንፈናቀላለን ብለው የሚርበተበቱት፣ ከጓደኝነት እንጐድላለን ብለው የሚባክኑት፣ ግራ ቀኝ በማየት ዘመናቸውን ያነቀዙት ... ኢየሱስ ሕይወቱን እንደ ሰጣቸው በእውነት ማየት ስለተሳናቸው ብቻ ነው። የኢየሱስን ሕይወት አይቶ ያልጨከነ ሰማዕት፣ ከዓለም ከንቱነት ያልመነነና ዓለማዊነትን ለመካድ ያልበረታ መናኝ፣ በእውነት ለመኖር ያልቈረጠ ጻድቅ፣ በሕይወት ንጽሕና ሊያገለግለው ያልወሰነ ቅዱስ ... ፈጽሞ የለም። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ያዩት ኹሉ እስኪያዩት የድንጋይ መወገርን እንኳ እንደ ሙሉ ደስታ ቈጥረውታል።
   የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱ የጠራ ሕይወት ነው፤ እንከን አልባና ቅዱስ ሕይወት ነው። ሰዎች ኹሉ በሕጉ የደረሰባቸውን ነቀፋና ክስ ሁሉ የተሸከመና ወክሎ የቆመ ብቸኛና አንድ ቤዛ ነው። ሕይወቱ አንዳች የክስ ምክንያት ያልተገኘበትና ከሳሾቹ፣ ፈራጆቹ፣ ወቃሾቹ ... እንኳ የተደነቁበት ቅዱስና ነውር አልባ ሕይወት ነው።  “ታላላቅ” ዓመጸኞችና ኀጢአተኞች የኢየሱስ ሕይወት ከተመለከቱና ካነበቡ በኋላ እጅግ በተሰበረ ልብና ማንነት ሲመለሱና ሲለወጡ ተመልክተናል።
  ማርያም መግደላዊት ለኢየሱስ ሕይወቷን ሳትሰስት የሰጠች ናት፤ ምክንያቱም የተገለጠውንና ኀጢአተኛ ለመቀበል የማይጠየፈውን የኢየሱስን ሕይወት በትክክል ተመልክታዋለችና፤ የኢየሱስን ሕይወት ያዩ ኹሉ ልክ እንደ ማርያም መግደላዊት በፈቃዳቸው ሕይወታቸውን ሰጥተው፣ የፈቃድ በሪያዎች ኾነዋል!!! ሕይወቱ ሕይወትን የሚገዛ ጌታ፤ እርሱ ኢየሱስ ብቻ ነው! ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ኀጢአተኛን ሳይጠየፍና ሳይታዘብ በትክክል የሚቀበለውን የኢየሱስን ቅዱስ ሕይወት እንመለከት፣ እናስተውል፣ ተማርከንም እንቀርለት ዘንድ በጸጋህ ደግፈን፤ አሜን።

ይቀጥላል ...

1 comment: