Wednesday 1 May 2019

“መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል” (ዮሐ. 10፥11)

Please read in PDF
   ወንጌላዊው ዮሐንስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እረኝነት እጅግ አድምቆ ከሚያሳዩ ትምህርቶች አንዱንና ሰፊውን ጠቅሶ ጽፎልናል፡፡ ምዕራፉ ስለ እረኝነት ብዙ ነገር የምንማርበት ቢኾንም፣ አንዱን ዘለላ ብቻ መዝዘን ለመማማር ወደድን፤ እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ የማኖሩን ወይም አሳልፎ የመስጠቱንና ስለ በጎቹ ማናቸውንም ዋጋ ከፍሎ የሚያድን ስለ መኾኑ የተነገረውን አንድ አንቀጽ፡፡
    በምድረ እስራኤል እረኝነት የተወደደ ተግባር ነው፤ በተለይም የበግ እረኝነት፡፡ በብሉይ ኪዳንም ኾነ በአዲስ ኪዳን ብዙ ጊዜ ከእረኝነት ጋር በተያያዘ በጎች ሲጠቀሱ፣ መልካም እረኞችም ለበጎቻቸው ባላቸው እንክብካቤና ጠባቂነት፣ ታዳጊነትም ሲመሰገኑ እናያለን፤ ልክ እንዲሁ ደግሞ ምንደኛና ሙያተኛ እረኞችም ለሚጠብቋቸው እረኞች ባላቸው ተላላነትና ዝንጉነት፣ እንዲሁም ጥቅመኛ ብቻ ስለ መኾናቸው እየተነሳ ሲወቀሱና ሲዘለፉ፣ ፍርድንም ሲቀበሉ እንመለከታለን፡፡

   እውነተኛ እረኞች ስለ መንጎቻቸው ራሳቸውን ለአደጋ ጭምር አሳልፈው ይሰጣሉ፤ ያዕቆብ የላባን በጎች በእረኝነት ያሠማራ በነበረ ጊዜ እጅግ ዋጋ ከፍሎአል፤ (ዘፍ. 31፥39)፣ ዳዊት እርሱ በጎችን እንዴት ይጠብቅ እንደ ነበር ለንጉሥ ሳኦል ሲያስረዳ እንዲህ አለ፤ “እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር።” (1ሳሙ. 17፥34-35)፡፡ ዳዊት እንዴት ካሉ አስፈሪ አራዊት ጋር ስለሚጠብቃቸው በጎች ሲል ይታገል፣ ይከላከል፣ ይሟገትላቸው፣ ሕይወታቸውና አካላቸው እንዳይጎዳ በመሰጠት ይጠብቃቸው እንደ ነበር እናስተውል!!! አማናዊው እረኛ ጌታችን ኢየሱስ ከዚህ በሚበልጥና በሚልቅ መንገድ ስለ እኛ ከነጣቂው ተኩላ እንደሚሟገትልን፣ ከጠላት እንደሚጠብቀን፣ እጅና አካላችንን እንዴት እንደሚጠብቅ ታስተውላለህን!?
   እረኛ ኹል ጊዜ ስለ በጎቹ ሕይወቱን ለአደጋ ጭምር  አሳልፎ በመስጠት፣ በማዳንም ከበጎቹ ጋር በአንድነት መኖር እንደሚችል ያምናል፡፡ ስለዚህም የትኛውም ተግዳሮት ቢመጣ በሕይወቱ ጭምር ከፍሎ በጎቹን ለማዳን ይተጋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይኾን ለበጎቹ የሚያስፈልጋቸውን ማናቸውንም ነገር ለማድረግ ከቶ አይሳሳም፡፡ መዝሙረኛው በመዝሙሩ “በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል።” (መዝ. 23፥2) በማለት የዘመረው፣ በሕይወቱ የተለማመደውን የእረኝነት እውነተኛ ጠባይ ነው፡፡ በልጅነቴ እረኛ ሳለሁ እሾኽ ሥር የበቀሉ ለምለም ሳሮችን ለመመገብ ስል፣ የሚወጋኝን እሾኽ ድንገት አስታወስሁ! እውነተኛ እረኛ ስለሚጠብቃቸው በጎቹ የትኛውንም አደጋና ጉዳት፤ መጠቃትና ስቅየት ፈጽሞ ይታገሳል፡፡
   እረኛው ይህን የሚያደርገው ማንም አስገድዶት አይደለም፤ በገዛ ፈቃዱ ለበጎች ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ ብቻ እንጂ፡፡ ሁል ጊዜ በጎቹን መጠበቅ እንደሚችልና ከአደጋውም ኹሉ ከልሎና ጋርዶ ደግሞ እንደገና አብሮአቸውም እንደሚኖር ጽኑ ተስፋ አለው፡፡ ጌታ ኢየሱስ መልካም እረኛ እኔ ነኝ አለ፤ በእርግጥም ነቢያት የተነበዩለትና የተናገሩለት፣ ምሳሌም የመሰሉለት እውነተኛ እረኛ እርሱ ነው፤ (መዝ. 23፥1፤ ኢሳ. 40፥11፤ ሕዝ. 34፥23፤ 37፥24)፡፡ በዚህ ኹሉ ምሳሌና ትንቢት ውስጥ የምንመለከተው የጌታ ኢየሱስን አዛኝነት፣ ሩኅሩኅነት፣ የማያቋርጥ መግቦቱንና ትድግናውን፣ በስስትና በፍቅር የሚያዩ ዐይኖቹን፣ ለበጎቹ እጅግ የሚጠነቀቅ ውድ እረኛ፣ እጅግ አፍቃሪ፣ ለበጎቹ ስስ ልብ ያለው፣ ኹሌም አብሮአቸው የሚኖርና የማይተዋቸው፣ እውነተኛና መልካም እረኛ መኾኑን ነቢያት፣ አባቶች፣ ራሱም ጭምር ተናግረዋል፡፡ ወዳጄ ሆይ! አንተን የማይተውህ እውነተኛ እረኛ፣ ከአደጋ ኹሉ የሚከልልህ፣ ስለ አንተ ራሱን ለአደጋ የሚያጋልጥ እውነተኛ እረኛ ኢየሱስ ብቻ ነው!!!
   ከኹሉም እረኞች ጌታ ኢየሱስ የሚለየውና እጅግ የሚልቀው፣ ነፍሱን ስለ በጎቹ ሊያኖር ወይም በገዛ ፈቃዱ ሊሞትላቸው መፍቀዱ ነው፡፡ ይህ የእረኝነቱን ወደር የለሽነት ፍጹም ያሳየናል፤ ጌታችን “ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና” (ኢሳ. 53፥12) እንደ ተባለ፣ ራሱን አሳልፎ ለበጎቹ በፈቃዱ ሰጥቶአል፡፡ “ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ” (ማቴ. 20፥28) የመጣ ብቸኛና እውነተኛ የበጎች መልካም እረኛ ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡
   እርሱ ራሱን ለእኛ አሳልፎ የሰጠበት ምክንያቱ ፍቅር ብቻ ነው፤ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” (ዮሐ. 15፥13) እንደ ተባለ፣ ኢየሱስ ብቻ እኛን ስለ መውደዱ ራሱን አሳልፎ በፈቃዱ ሰጥቶአል፡፡ አስተውሉ! አርብ እለት ከተሰቀለ በኋላ ኹለቱ ወንበዴዎች ቶሎ ስላልሞቱ ገዳይ አስፈልጎአቸዋልና ጭናቸውን ተሰብረው ሞቱ፤ (ዮሐ. 19፥32)፡፡ አማናዊው የፋሲካ በግ (ዘጸ. 12፥46፤ ዮሐ. 1፥29፤ 19፥33) ኢየሱስ ግን ነፍሱ በገዛ ፈቃዱ አኑሮአት ነበርና ወይም ስለ እኛ ኀጢአት አሳልፎ ሰጥቶ ነበርና ጭኑ ፈጽሞ አልተሰበረም፤ ምክንያቱም ጻድቁ ኢየሱስ እኛን ስለ ማዳን አስቀድሞ ነፍሱን ሰጥቶ ነበርና፡፡ ኢየሱስ በሰው እጅ በግድ ያይደለ ነፍሱን በፈቃዱ በመስጠት እኛን ከመከራ፣ ከሃዘን፣ ከአውሬው፣ ከነጣቂው፣ ከቦጫቂው … ሊያድነን ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት አድኖናል፤ ክብር ይኹንለት!!! እርሱ ባያድነን ማን ሊያድነን ይቻለው ነበር?!!! ራሱን ጠላቶቹ ለምንኾን ለእኛ የሰጠ አንድ ብርቱ ወዳጅ ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው!!!
   ስለ እኛ ኀጢአት ብቻውን በመስቀል ራሱን አሳልፎ የሰጠ፤ እርሱ ብቻ በእረኝነቱ በእኛ ላይ ሥልጣን አለው፤ ምክንያቱም ራሱን አሳልፎ ለእኛ ሰጥቶአልና፤ እጅግ የሚወድደን ሰው በእኛ ነገር ላይ ድፍረትና ሥልጣን አለው፣ ሊቆጣን፣ ሊገስጸን፣ አብሮን ሊሰነብት … ይወዳል፤ ኢየሱስ ግን ከሚወደን ከማንም ወገን በላይ በእኛ በልጆቹ ላይ ሥልጣን አለው፤ ምክንያቱም እኛን ስለ መውደድ በመስቀል ተሰቅሎ ነፍሱን ሰጥቶአልና፡፡ ንጉሤና እረኛዬ ሆይ! መቅደስህን እንደ ወደድህ እዘዝበት፣ ናዝዝበት፣ ተመላለስበት፤ ታርደህልኛልና፣ ሞተህልኛልና፣ እረኝነትህን በትክክል ገልጠሃልና፡፡
  አንተ እንደ ሌሎች እረኛ አይደለህም፤ የአንተ እረኝነት ልዩና ውድ ነው፤ የእረኝነት ዓይኖችህ የላይን መልክና ቁመና ሳይኾን፣ የውስጥን ጕስቊልናና ስብራት፣ ሕመምና ትካዜ ያያሉ፤ (ማቴ. 9፥36)፣ ያንተ እረኝነት ከዳዊትና ከአባቶቻችን ይበልጣል፤ በቀራንዮ መስቀል ላይ ተሰቅለህ የእሾኽ አክሊል ደፍተህ፤ ደግሞም ሞትን ትውጠውና እረኝነትህ የዘላለም መኾኑን ታሳየን ዘንድ ከሙታን መካከል ተነሥተሃል፡፡
   እናንተ የቤተ ክርስቲያን “እረኞች” ሆይ! ይህን መልካም እረኛ ብቻ ተመልከቱ፤ እርሱ ወደር የለሽ ታላቊ እረኛና የእረኞችም አለቃ ነውና፤ (ዕብ. 13፥20፤ 1ጴጥ. 5፥4)፡፡ እርሱን የሚያዩ ዐይኖች አይዝሉም፤ አይታክቱም፤ እናንተ በጎችም ሆይ! ከኢየሱስ በቀር ውድ እረኛ የላችሁምና ከእርሱ በቀር ሌላ ድምጽ አትልመዱ፤ ነፍሱን ለእናንተ የሰጠ እርሱ ብቻን ስሙት!!!
   ውድ ጌታዬ ኢየሱስ ካንተ በቀር ነፍሱን ለአደጋ ሰጥቶ ያፈቀረን፣ መቃብር ድረስ ወርዶ ያከበረን አላገኘንም፤ ደግሞም እውነተኛ እረኛ ኾነኸን፣ ለአባትህ የበኵራት ስጦታ አድርገህ ልታቀርበንና፣ ለዘላለም በጽዮን ትነግሥ ዘንድ ከሙታን መካከል በኃይል ተነሥተሃልና ክብር፣ አምልኮ፣ ውዳሴ፣ መግነን፣ መወደስ፣ መቀደስ፣ ቡሩክ መባል ይገባሃል፤ አሜን፡፡


2 comments:

  1. amen ለዘላለም በጽዮን ትነግሥ ዘንድ ከሙታን መካከል በኃይል ተነሥተሃልና ክብር፣ አምልኮ፣ ውዳሴ፣ መግነን፣ መወደስ፣ መቀደስ፣ ቡሩክ መባል ይገባሃል፤

    ReplyDelete