Sunday 1 April 2018

“ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው” (ማቴ.21፥11)



    አይሁድ መምህራንና የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል ካስቸኮላቸውና ቶሎ እንዲገድሉት ውስጣቸውን “እጅግ ካነሣሣው” ነገሮች አንዱ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሕነቱን መግለጥ ነው፤ ወደኢየሩሳሌም ሲገባ እርሱ የገባው እንደ አንድ ምድራዊ ንጉሥ ወይም የጦር መሪን በሚመስል መልክ በፈረስ አልነበረም፤ ነቢዩ ዘካርያስ እንደተናገረ፦ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ” ነበር፤ (ዘካ.9፥9)።

   ነቢዩ ዘካርያስ የጽዮንን ልጅ ደስታ ወይም የምትደሰትበትን ምክንያት በግልጥ ይነግራታል፡፡ የደስታዋ ምንጭ መሲሐዊው ንጉሥ፣ የዳዊትን ዙፋን ወራሹ ልዑል፣ ከገሊላ ናዝሬት የመጣው ኢየሱስ እንደኾነ ይናገራል፡፡ እርሱ ለጽዮን ልጅ ደስታዋም፤ ንጉሥዋም ነው፤ “ንጉሥሽ” ተብሎ የተነገረላት እርሱ ብቻ ነው። ከእርሱ በቀር ሌላ ንጉሥ የላትም፤ ብትፈልግ እንኳ ፈጽሞ ማግኘት አይኾንላትም፤ ከእርሱ በቀር ሌላውን ንጉሥ አድርጋ ለመሾም ብትፈልግ እንኳ፣ ትባርክናለች እንጂ ፈጽሞ በሠላምና በፍቅር አታርፍም፡፡ ከክርስቶስ ውጭ በሌላ አካል ለመገዛት የሚሹ፣ ደስታንም ከእርሱ ውጭ ለማግኘት የሚራኰቱ፣ ሌላ ንጉሥን በራሳቸው ላይ ሊሾሙ የሚወድዱ … በጭንቅ ከመገዛት፣ ከመቅበዝበዝና ፈጽሞ ባለመርካትና ባለመደሰት ለመኖራቸው ምንም ጥርጥር የለውም። የምድርና የሰማይ ኹሉ ደስታ ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን ብቻ ነው! ደስታን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተለይተን በትዳር፣ በልጅ፣ በሃብት፣ በሥልጣን፣ በቤተ ዘመድ መከበብ፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት እንኳ ቢኾን … ለማግኘት ማሰብ ከሁሉ ይልቅ ምስኪን መኾንን ያሳያል!
   የጽዮን ልጅ እርሱን በራስዋ የምትሾመው ለራስዋ ጥቅም ነው፤ “ለአንቺ ወይም ወደ አንቺ ይመጣል” የሚለው ቃል፣ መሲሑ እርስዋን ለመጥቀም የሚመጣ መኾኑን የሚያሳይ ነው፡፡ እርሱ ንግሥናው ከዘላለም እስከ ዘላለም ነው፤ መንግሥቱም ጊዜያዊና ምድራዊ ሳይሆን፣ ወደፊት የሚገለጥና ለዘለዓለምም ጸንቶ የሚኖር ነው፤ (ዮሐ.18፥36፤ 1ቆሮ.15፥24፤ 2ጴጥ.1፥11)፡፡ የእርሱ ንግሥና የባሕርይ ገንዘቡ ከኾነ፣ የምንጠቀመው እኛ እንጂ እርሱ አይደለም፡፡ እርሱ ንጉሣችን በመኾኑ በግዛቱና በመንግሥቱ ሥር ያለን ሁላችን የዘላለም መዳንና ዕረፍት አለን፡፡ እርሱ ንጉሣችን ቢኾን ከቶ ምን የምናጣው ነገር አለ?
    በእርግጥም የጽዮን ልጅ ደስታዋ እንዲኾንላት፦ ፍጹም ጻድቅ ሆኖ መጣ፤ እንከን ሳይኖርበት፤ በሕጉ አንዳች የሚነቀፍበት ነገር ሳይገኝበት መጣላት፤ ደግሞም ካለባትም ማናቸውም ሥጋዊም ኾነ ነፍሳዊ ደዌዋ ሊፈውሳት አዳኝዋም ኾኖ መጣላት፤ አዎን እንደጦረኞቹ ነገሥታት ጦር አዝምቶ፣ ነጋሪት መቶ፣ ሠራዊት አስከትቶ የመጣ አይደለም፤ ፍጹም ትሁትና ደግ ኾኖ ደቀ መዛሙርቱ ባመጡለትና ማንም ባልተቀመጠባት፣ በአህያይቱ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ መጣ (ማር.11፥2፤ ሉቃ.19፥20)፤  የመጣው በፍጹም ሰላምና ደግነት ነው።
    በፍጹም እንደጦረኛ አልመጣም፤ በፍቅርና በደግነት መጣ፤ በሠላምና በትህትና መጣ፤ ጻድቅና ሕዝቡን ኹሉ ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው አዳኝ ኾኖ መጣ፤ ማንንም ሳይንቅ ለመቀበል መጣ፤ ሊያከብርና ሊወድ መጣ፤ ኹሉንም ያድንና ይቤዥ ዘንድ መጣ፤ ከእግዚአብሔር አምላክ፣ ከቅዱሱ ኪዳን የተለዩትን ሁሉ ወደክብራቸው ሊመልስ፣ ዳግመኛ በብዙ ክብር ሊያከብራቸው መጣ፤ በሚያርዱት ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ ደግሞም ሲጎትቱት ዝም ብሎ እንደሚከተል በግ ሊፈልጋቸው፣ ሊታደጋቸው፣ ሸክማቸውን ኹሉ ሊሸከም መጣ፤ ነገር ግን ፈጽመው ሊቀበሉት አልወደዱም። ይልቁን እርሱ የተቀበሉትን በመገሰጽ ተቃውሞአቸውን ፊት ለፊት አሳዩ እንጂ፤ (ሉቃ.19፥39)፡፡ ዛሬም ለአገራችን፣ ለከተማችን፣ ለመንደራችን፣ ለቤተሰባችን፣ ለእኛ፣ ለእኔም … ጭምር እንዲህ መጥቶ ስንት ጊዜ ባለመቀበል ልባችንን አደንድነን ይኾን? መምጣቱንስ ተቃውመን ይኾን?
    ሞቱ እጅግ በተቃረበበት ማግስት ማን እንደኾነ፣ በዚህ በሆሳዕና ዕለት መሰወር ወይም አለመግለጥ አልፈለገም፤ በሥራዎቹና በትምህርቶቹ ሁሉ ጻድቅ፣ አዳኝ፣ ደግ፣ ሰላማዊና ትሁት መኾኑን አሳይቷል፤ ደግሞም አሁን መሲሕ መኾኑን በግልጥ ማሳየትና የመሲሕነቱን ክብር ለመቀበል ተገለጠ። በታላቅ ክብር፣ በብዙ ሆታ ወደኢየሩሳሌም ገባ፤ “ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር።” (ማቴ.21፥8፤ ማር.11፥1-11፤ ዮሐ.12፥12-15) እንዲል። አክብሮትን፣ እልልታውን፣ ሆታውን፣ ሽብሸባውን፣ ለእርሱ መገዛት መውደዳቸውን ተቀበለው፤ ተቃዋሚዎቹን ይልቅ ገሰጻቸው እንጂ።
     ልብሳቸውን፣ ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ ሲያነጥፉ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ መሬት ላይ ሲዘረጉለት (ዮሐ.12፥13)፣ አንዳንዶች ከገሊላ ጀምሮ ሌሎች ደግሞ ከኢየሩሳሌም አቅራቢያ በብዙ እልልታና ሆታ ሲከተሉት፣ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ሰላማዊና ደገኛ መኾኑን ሲያውቁ፣ … የሚቀድሙትም የሚከተሉትም “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም” (መዝ.118፥25-26) እያሉ በመጮኽ ሊገዙለት ወደዱ፡፡ ይህን ቅዱሳን መላእክት በሰማይ ሰዎችም በምድር ኾነው የሚያመሰግኑት ነው፡፡ መሲሑ በምድርም በሰማይም አምልኮና ምስጋናን ተቀባይ ነውና።
     እርሱ በእንዲህ ዓይነት ኹኔታ ወደኢየሩሳሌም ገባ፡፡ እርሱ እንዲህ ባለ መልኩ በመግባቱ ማንም በዝምታ ይቀመጥ ዘንድ አይችልም። ኢየሩሳሌምና መላው ሕዝቧ “ይህ ማን ነው?” እያለች ታወከች፤ እርሱ ለሠላሟ ሲመጣ እርሷ ግን ለሠላሙ ምላሽ ባለመስጠቷ ታወከች። መሲሑ ነቢይ ብዙ ምስክርነትን በምድሪቱ ፊት ቢያደርግም ከተከታዮቹ ይልቅ የበዙለትና ፋና በፋና እየተከተሉ ሰኰናውን በመንከስ ያላራመዱት ተቃዋሚዎቹ ናቸው፤ በአገልግሎታችን እንዲህ ቢኾን ምንም የሚደነቅ ነገር የለውም፤ ከሙሽራው ጋር ያለችው ሙሽሪት የሙሽራው ክብር ክብሯ፤ ውርደቱም ውርደቷ ነውና!
     ጌታችን ኢየሱስ መሲሕነቱን በግልጥ አሳይቷል፤ ለሚያምኑበት የተመረጠና የከበረ የማዕዘን ድንጋይ፣ ለማያምኑበት ደግሞ የማሰናከያ ድንጋይ ይኾን ዘንድ በግልጥ ተገለጠ፤ (1ጴጥ.2፥6-7)፤ “በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት” (ሉቃ.2፥34-35) ኾኖ መሾሙን ያሳይ ዘንድ፣ በግልጥ መሲሕነቱን ለሁሉም ገለጠ። እርሱ ለሚያምኑበት ሕይወት ነው፤ ለሚቀበሉትና እርሱን ብቻ ለሚደገፉት የዘላለም ክብርና ባለጠግነት ነው። መሲሕነቱን መግለጡ ግን ለአይሁድ ደስታ ሳይኾን ሞቱን ለማፍጠን ምክንያት ኾነላቸው፤ እርሱ እነርሱን ሊያድን ራሱን ሲገልጥ እነርሱ ግን ሊገድሉት ቀን ቆረጡ።
    ደቀ መዛሙርቱ ጌታ ኢየሱስ ራሱን እንዲህ ለምን እንደገለጠ በጊዜው በፍጹም አላስተዋሉም፤ “ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤” (ዮሐ.12፥16)፡፡ እያመሰገኑትና በብዙ ሆታ እልል እያሉለት፣ እርሱም በታላቅ ክብር ወደኢየሩሳሌም መግባቱን በደስታ ቢቀበሉትም፣ ነገር ግን በጊዜው ይኾን የነበረውን ነገር በትክክል አላስተዋሉም፤ ነገር ግን “ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያን ጊዜ ይህ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይህንም እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው።” የዘካርያስም ኾነ የዳዊት ትንቢቶች መፈጸማቸውን ያስተዋሉት ስቁሉ ኢየሱስ በታላቅ ክብርና በኃይል ከሙታን መካከል ከተነሣና መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ ነው፤ (ሉቃ.24፥25፤ ዮሐ.16፥13)፡፡
   የመሲሑ ወገኖች የኾኑት አይሁድ ለዘመናት መሲሑን በመናፈቅ ጠብቀውት ነበር፤ ነገር ግን በመጣ ጊዜ እንደንጉሥና ተዋግቶ ነጻ አውጪ አድርገው ጠብቀውት ነበርና፣ ትሁትና ደግ፣ የዋሕም ኾኖ በመምጣቱ ሊቀበሉት አልወደዱምና ላይገናኙ በመንገድ ተላለፉ፡፡ እርሱ በመሲሕነቱ በመካከላቸው እንደነቢይ አገልግሎ ነበር (ማር.6፥4፤ 11፥32፤ ሉቃ.4፥24፤ ዮሐ.4፥44)፤ የአምላካቸውና የአባቱን ፈቃድ እንደአገልጋይ ለእነርሱ ቢናገርም ፈጽመው ናቁት፤ ገፉትም፤ ከምኩራብና ከመቅደሳቸው እንዲወጣላቸው ወደዱ፡፡ እርሱ ግን በመሲሐዊ ነቢይነቱ “ለአሕዛብም እንኳ ሰላምን የሚናገር ነው፤” (ዘካ.9፥10)፡፡
   መሲሑ መሲሕነቱን ሲገልጥ እንኳን ሰው፣ ድንጋዮች እንኳ ዝም ማለት አይቻላቸውም፤ መሲሕነቱን ላለመናገርና ላለማየት የሚፈልጉ ማናቸውም ሰዎች በምድር ካሉት ኹሉ ድሆችና ጐስቋሎች ናቸው፤ መሲሕነቱን ላለመናገር ማሰብ ከዲዳነት የከፋ ዲዳነት፣ ከመታወር የባሰ መታወር ነው፡፡ መሲሐዊው ነቢይ የዳዊትን ዙፋን ብቻ ሳይኾን ኹለንተናችንን እንደሚወርስ፣ እንደወረሰም አለመመስከር ባለጠግነቱን መናቅ፣ ሳይሰስት ሕይወቱን በመስጠት እኛን ያዳነበት ፍቅሩን መንቀፍ ነው፡፡ ለዚህ ፍቅሩ ዘመናችንን ኹሉ አይደለም ዘለዓለምን በቀንና በማታ፣ ወራትና አዝማናትን፣ ዛሬም ነገም፣ በዚህ ምድር ኖረንም በዚያ በሰማይ ከእርሱ ጋርም ሆነን ብንዘምርለት የመሲሕነት ብድራቱን ፈጽመን መክፈል አይቻለንም! ይህን እውነት ማስተዋል መታደል፤ በታላቅ ሰማያዊ በረከት መባረክም ነው!!! በስሙ ለዳንንና በእርሱ ለምናምን መሲሕነቱ የሚያስደስተንና በፍቅር የሚያስጮኸን እንጂ የሚያስደነግጠን ወይም “ለምን ስሙ ተደጋግሞ ተመሰገነ? ተጠራ?” የሚያስብለን ሰነፎች አይደለንም!
   ጌታ መንፈስ ቅዱስ መሲሑን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በልባችን ያክብር፤ ያግንነውም፤ ማስተዋልንም ያብዛልን፤ አሜን፡፡ 

3 comments:

  1. የእግዚአብሄር ስም የተባረከ ይሁን፤የሚያቅተው ነገር የለለ አባቴ ተባረክ፤ ወደ እውነተኛው ወንጌል የመለሰን ጌታ ይባረክ

    ReplyDelete
  2. " ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤"
    አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።"
    (ወደ ሮሜ ሰዎች 8:29-30) የጌታ ስም ይመስገን

    ReplyDelete
  3. best menfesawi article

    ReplyDelete