Tuesday 3 April 2018

“ዓለም ያለድንግል ማርያም አማላጅነት አይድንም” ማለት፥ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ማክፋፋት ነው! (ክፍል ፩)

Please read in PDf

የስህተት ትምህርቶች በየዘመናቱ የየራሳቸው መልክና ጠባይ አላቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ ለሚነሱ ኑፋቄያትና የተዛነፉ አስተምኅሮዎች እንደቀደሙት ቅዱሳን አባቶች መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ መክራ ዘክራ፣ አስተምራ ሞግታ፣ የሳተውን አቅንታ፣ በስህተቱ የጸናውንና ሊመለስ ያልወደደውን ለይታ በቅዱስ ቃሉ ማዕከልነት ማስተካከል ይገባታል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጣት መለኮታዊ ሥልጣን አለ፤ ይህን ባታደርግ ደግሞ ከአምላካዊ ወቀሳ ፈጽሞ ላታመልጥ ትችላለች፤ (1ዮሐ.4፥1፤ ራእ.2፥2)፡፡
    ከላይ በርእስነት በተናገርነው ሃሳብ ዙርያ፣ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ማኅበር እየፈራና እየተባ፣ በግልጥ ከመቃወምና ካለመቃወም መካከል ቆሞ እንዲህ መናገሩ “ይደንቃል”፦
    “አንዳንድ ባሕታውያን ነን የሚሉ ሰዎች መናፍቃን ጸረ ማርያም በሆነ ትምህርታቸው ስለሚታወቁ ከዚያ በተቃራኒው በመቆም የበለጠ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ሲሉ እመቤታችንን ያከበሩ በሚመስሉ ስሕተትና ኑፋቄ አዘል ትምህርቶችን ያስተምራሉ፡፡ በዚህ ዓይነት መልኩ በአንድ ግለሰብ የተጀመረ መፈክር መሰል ትምህርት ባጭር ጊዜ ውስጥ ተሰራጭቶ ብዙዎች የሚደጋግሙት በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ሳይቀር የሚደመጥ፣ በታላላቅ ጉባኤዎች ላይ በጉልህ ተጽፎ ብዙ ሰዎች ሊመለከቱት በሚችሉት መልኩ ሲሰቀል ማየት ተለምዷል፡፡ አባባሉ የአምላክን ሁሉን ቻይነት የሚፃረር መሆኑን፣ አምላክ እርሱ በፈቀደው መንገድ ዓለምን ማዳን የሚችል መሆኑን ገልጠው የተናገሩ ሰዎች ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡
    አምላካችን ዓለምን ሲያድን እመቤታችንን ለተሰግዎት ቃል መረጣት እንጂ እርሷ አልመረጠችውም፡፡” [1]

   
    ስለመዳን ገና ማሰብ ስንጀምር ወደሕሊናችን ሊመጣ የሚችለው ያልዳነው አካልና ያልዳነበት ምክንያቱ ነው፡፡ ምክንያቱም “እገሌ ዳነ” ስንል፥ ከምን? በማን? ለምን? እንዴት? ማለታችን ግድ ይሆናልና፡፡ የሰው ልጅን (የዓለምን) መዳን መናገር ከመጀመራችን በፊት ደግሞ፣ የሰውን ጥንተ ፍጥረት በጥቂቱም ቢሆን መቃኘት ግድ ይለናል፡፡ ሰዎች ነገረ ድኅነትን በትክክል ለመረዳት ከሚቸገሩበት ምክንያቶች አንዱ የሰውን ኹለንተናዊ ውድቀትና ያስከተለበትን ጉስቁልና በአገባቡ ካለመረዳት የተነሣ ነውና፡፡
ሰው ጥንተ ልደት
    ሰው እንደእግዚአብሔር ሃሳብና እቅድ “በእግዚአብሔር መልክና አምሳል” ተፈጠረ (ዘፍ.1፥26)፡፡ ይኸውም ሰው እግዚአብሔር አምላክን በሚመስልበት ባሕርይና ጠባይ ተገኘ ማለታችን ነው፡፡ በተለይ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ስለተፈጠረም እንደእግዚአብሔር አምላኩ የራሱ ፈቃድ፣ ስሜትና ዕውቀት ያለው ሆነ፡፡ አዳምና ሔዋን ቅዱሳንና ጻድቃን ነበሩ፤ ልባቸውም እግዚአብሔር አምላክን የሚፈልግ ነበረ፤ በዔደን ገነት በነበራቸውም ኑሮአቸው ደስተኞችና “እንከን አልባዎች” ነበሩ፡፡
     ሰው በተሰጠው ዕውቀት የመረጠውንና የፈቀደውን የማድረግ አቅም ከጥንት ተሰጥቶታል፡፡ በዕውቀቱም የፈቀደውን ሲያደርግ የሚመጣውንም ኃላፊነት እንዲቀበለውም ተብሎለታል፡፡ ይህንንም በስሜቱ ያንጸባርቀዋል፡፡ በተሰጠው ዕውቀታዊ ፈቃዱ መልካሙን መርጦ ካደረገ ደስታንና ተድላን ሲያጭድ፤ ነውርና ዕድፈትን ከመረጠ ደግሞ ሃዘንና መጥፋትን ያጭድ ዘንድ፡፡ ስለዚህም ሰው በእግዚአብሔር አምላክ አምሳልና መልክ በተፈጠረ ጊዜ፥ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከፈጠረው በኋላ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ”(ዘፍ.1፥31) የሚል ቃል በመነገሩ ከሌሎች ፍጡራን ይልቅ የሰውን ታላቅነት ያሳያል፡፡
     እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በሙሉ ክብሩ የእርሱን ክብር “ወርሶ” እንዲኖር ፈጠረው፡፡ ከጥንትም የእግዚአብሔር ሃሳብ ሰውን የፈጠረና ያስገኘ እንደሆነ ሁሉ፣ በገነት መካከልም ለአዳም ድምጹን የሚያሰማው ራሱ እግዚአብሔር አምላክ ነበር፡፡ በእርግጥም የትኛውም የቅድስና ጫፍ ላይ ብንሆን ራሱ እግዚአብሔር አምላክ ካልተገለጠንና ካላገኘን በቀር እኛ በራሳችን ሁሉን ቻዩን ጌታ ልናገኘው አይቻለንም፡፡ “እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን የአምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ” (ዘፍ.3፥8) የሚለው ቃል፣ ዘወትር የሚያገኘውና የሚገለጥለት አባትና ወዳጅ እግዚአብሔር መሆኑን እናስተውላለን፡፡
   እውነት ነው! እግዚአብሔር አምላክ ለሚፈልጉትና እንደፈቃዱ ለሚታዘዙ ልጆች ቅርብና የሚገኝ አምላክ ነው፤ (ፊልጵ.4፥6)፡፡ ይህም ቢሆን እንኳ የእኛ ፈቃድ ያገኘው ሳይሆን የእርሱ መገለጥና መገኘት እኛን ያገኘን እንጂ፡፡ ይህንን ከሰው ውድቀትም በኋላ እንኳ ያላቋረጠ ፍለጋውን[ዴሬክ ያሕዌ] ያደረገ መሆኑን እናስተውላለን፡፡
   ሰው በዚህ ትልቅ ልዕልናና ቅድስና የተፈጠረ ቢሆንም፥ በተሰጠው ዕውቀታዊ ፈቃዱ ክፉውን ነገር በመምረጥ ከአምላኩ ተለየ፡፡ ሰይጣን ያቀረበው ክርክር ወይም ለማሳት ያቀረበው ሃሳብ ድኩምና ኢ አመክንዮታዊ ነበር፤ ሰው ማሸነፍ የሚቻለውን ፈተና በነጻ ፈቃዱ መርጦ ሲወድቅ፣ በክፉው ሰይጣን መታለል ምክንያት ወደቀ፡፡ ሰው ይህን በትክክል ማስተዋል አይችልም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ራሱ ካልረዳው በቀር፡፡
ሰው ውድቀት
     በአጭር ቃል ሰው አለመታዘዝን በዕውቀታዊ ፈቃዱ በመምረጡ ምክንያት ወደቀ፡፡ ስለዚህም ባለመታዘዙ ያደረገውን ነገር ውጤቱንም ሊቀበል የተገባው ሆነ፡፡ ይኸውም፥ “ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” (ዘፍ.2፥17) የሚለው አምላካዊ ፍርድና ቅጣት አገኘው፡፡ “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤” (ሮሜ.5፥12) እንዲል፡፡
  ሁሉን ቻይና አዋቂው ጌታ፥ ሰው መውደቁን በትክክል ቢያውቅም አሁንም ግን “እንደመልካሙ ዘመን” ፈላጊውም እርሱ ነውና፥ ለፈጠረው የሰው ልጅ “ወዴት ነህ?” (ዘፍ.3፥10) የሚል ድምጽን አሰማው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር የጠፋውን ፍለጋ መጀመሩን ያሳያል፤ ይህንን የፍለጋ መንገድ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “ዴሬክ ያሕዌ” ብለው ገልጸውታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የጠፋውን ሰው፣ “የሰውን አላዋቂነት ገንዘብ ያደረገ” በሚመስል መልስ አዘል ጥያቄ በማቅረብ ፍለጋ መጣ፤ “ወዴት ነህ?” እያለ፡፡
   አዎን! እንኳን በውድቀቱ ጊዜ ሰው በገነት መካከል ከውድቀት ጊዜ በፊትም እግዚአብሔርን የሚያውቀው በተገለጠለት ልክ ብቻ ነው፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር አምላክን የምናውቀው በገለጠልንና እወቁ ብሎ ባሳወቀን መጠን ልክ ነው!
     ሰው በኃጢአት ወደቀ፡፡ አለመታዘዝን ገንዝብ ስላደረገ ከእግዚአብሔር አምላክ ጋር የሚገናኝበት መልካሙ ሕሊናው አደፈበት፤ ቆሸሸበት፤ ጐሰቆለበት፡፡ ስለዚህም በራሱ ችሎታና ብቃት በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ የማይቻለውም መሆኑን በራሱ አንደበት፥ “በገነት ድምፅህን ሰማሁ፤ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፥ ተሸሸግሁም” (ዘፍ.3፥10)፤ “ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል” (ኢሳ.64፥6) በማለት ተናገረ፡፡ ከዚህ የተነሳ ሰው ወደእግዚአብሔር አምላክ መቅረቢያ ልዩና ቅዱስ፤ አንድ ልዩና አዲስ መንገድ ያስፈልገው ዘንድ ግድ ሆነ፡፡ በዚህም በእግዚአብሔር አምላክ አንደበት “የመጀመርያው ወንጌል” እየተባለ የሚጠራው ኪዳናዊ ቃል፥ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” (ዘፍ.3፥15) ተብሎ ለመጀመርያ ጊዜ ተበሠረ፡፡
    የዚህም ኪዳናዊ ቃል እውን ሆኖ እስኪፈጸም፣ የሴቲቱ ዘር የቀዩን እባብ ራስ እስኪቀጠቅጥና ድል እስኪነሣው ድረስ አባቶችም፣. ነቢያትም፣ የእግዚአብሔር ባርያዎች የሆኑቱ ሁሉም ይህን ድንቅ የመምጣቱን ምስጢር ምሳሌውንና ጥላውን አገለገሉ፡፡ “እነርሱም ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ።” (ዕብ.8፥5፤ 10፥1፤ ቈላ.2፥17)፡፡
     በዚህ አገልግሎት ውስጥ ሰው “ልኩን በሚገባ እንዲያውቅ” ብዙ አዳኞች ተሰጥተውት ነበር፡፡ እኒህም፦
1.      ፦ ለእስራኤል ልጆች እግዚአብሔር አምላክ ሕግን የሰጣቸው እንዲድኑበትና ወደእርሱ እንዲቀርቡበት ነበር፡፡ ምክንያቱም ሕጉ ነውርና ዕድፈት የሌለበት ንጹሕና ቅዱስ ነበርና፤ (ዘሌ.18፥4፤ ምሳ.29፥18፤ ሮሜ.7፥10፤ 12)፡፡ ነገር ግን ሕጉን የሚፈጽም ባለመገኘቱ ምክንያት ሕጉ ገዳይና ይልቁን ኃጢአትን የሚጨምር፤ ከሳሽም ሆኖ ኰነነው፡፡
      ስለዚህም ሕጉ እነርሱን ወደእግዚአብሔር ከማቅረብ ይልቅ ባለመፈጸማቸው የሚያርቅ፣ አለመቻላቸውን የሚያጋልጥ፣ ብቃተ ቢስ መሆናቸውን የሚያስረግጥ ምስክር ሆነባቸው፤ (ሮሜ.5፥20-21)፡፡
V  ሕጉ የእግዚአብሔር ፈቃድ አመልካች ቢኾንም፣ (መዝ.1፥2፤ 19፥7፤ 119፥5፤ ሮሜ.3፥20፤ 4፥15፤ 1ቆሮ.15፥56፤ ገላ.3፥13፤ ያዕ.1፥25) ነገር ግን ብዙዎችን ከራሱ በታች የሚገዛ ኾነ፤ ፡፡ ምክንያቱም ሊፈጽመው የተቻለ አንድም አልነበረምና፡፡ እናም ሕጉ ይከሳል፣ ይወቅሳል፣ ኀጢአተኝነትን ያጋልጣል እንጂ፣ እንድንፈጽመው አይረዳንም፣ አያግዘንም፡፡ ሕግ በዋናነት፣ ኀጢአት ምን እንደኾነና ሰው ኀጢአተኛ በመሆኑ በሞትና በፍርድ ሥር መኖሩን ያሳያል፤ “ሕጉ መቅሠፍትን ያደርጋልና፤” (ሮሜ.4፥15) “በደልም እንዲበዛ ሕግ ጭምር ገባ፤” (ሮሜ.5፥20)፣ “ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤” (ገላ.3፥10) እንዲል፡፡
V  ከሕግ በታች መኾንም ለኃጢአት አሳልፎ ይሰጣል፤  (ሮሜ.6፥14)፡፡ ስለዚህም ሕጉ በእግዚአብሔር አምላክ ፊት አለመቻላችንን ብቁአን አለመኾናችንን እንጂ ፈጽሞ ሊረዳን፣ ሊያድነንም አልተቻለውም፡፡ ዛሬም ሕግን በመፈጸም እንድናለን የሚሉ ቢኖሩ ተሳስተዋል፤ (ሮሜ.3፥28፤ ገላ.2፥16፤ ኤፌ.2፥8)፡፡

2.     እንሰሳ መሥዋዕት፦ የእንሰሳቱ የደም መሥዋዕት “ለጊዜው የሚሆን የማሥተስረያ ሥርዓት” ነበረው እንጂ፣ ፍጹም ኃጢአትን የሚያስተሰርይ ብቃት አልነበረውም፡፡ ምክንያቱም፦
2.1.  እንሰሳት በፍጥረት ደረጃ ከሰው የሚያንሱና “የሰው መገልገያዎች” ነበሩ፡፡ ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ሲፈጠር እንሰሳት በ“ይሁን” የተገኙ ደመ ነፍሳውያን ብቻ ናቸው፡፡
2.2.  እንሰሳት ከሰው የሚያንሱ ከሆኑ ቤዛነታቸው ፍጹም መሆን አይቻለውም፡፡ የሚፈሰው የእንሰሳቱ ደም ክቡር የሆነውን የሰውን ሕይወት በሚያፈሱት ደም ሊያድኑትና ከዕድፈቱ ሊያጠሩት አይቻላቸውም፡፡
    እንኳን እንሰሳትና መሥዋዕታቸው ሰው ዓለሙ ኹሉ የእርሱ ቢሆን፣ ዓለሙ ሁሉ ለአንዲት ነፍሱ ቤዛ ሊሆነው አይቻለውም፡፡ “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” እንዲል፤ (ማቴ.26፥16)፡፡
3.     ቢያት (አባቶች)፦ ምንም እንኳ ነቢያትና ቅዱሳን አባቶች “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ብለው መልእክትን “በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና” (ዕብ.1፥1) እየተቀበሉ ሰዎችንና እግዚአብሔርን ያገለገሉ ቢሆኑም፥ መዳንን በተመለከተ ግን አንዳች ማድረግ አልተቻላቸውም፡፡ ምክንያቱም፦
3.1. ሁሉም ከአዳም አብራክ ተካፍለዋልና በእርሱ በደለኞችና ኃጢአተኞች ነበሩ፡፡ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ይሠሩት የነበረው መልካም ነገር እንኳ እጅግ በእግዚአብሔር ፊት አጸያፊና እርባና ቢስ መሆኑን ቅዱስ መጽሐፍ፣ “ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል።” (ኢሳ.64፥6)፣ “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥... ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ ” (ሮሜ.3፥11፤ 23) በማለት አሰምቶ ተናግሯልና፡፡
3.2.         በአዳም ላይ የተላለፈውን የአምላክን ቅጣታዊ ፍርድ ራሱ እግዚአብሔር እንጂ ማንም ማስወገድ ወይም ማንጻት ፈጽሞ አይቻለውም፡፡ በሌላ ንግግር ፍርድ በእግዚአብሔር ከነበረ ቤዛነት ከፍጡር ቢሆን ተካካይ ምላሽ መሆን አይችልም፡፡ ስለዚህም የፈረደብን ጻድቅ አምላክ ካልሆነ በቀር ከፍጡር ወገን እኛን በማዳን የእግዚአብሔር ልጆች ሊያደርገን የሚቻለው ማንም አይኖርም፡፡
3.3.         ሰዉ ለራሱም ሆነ ለሌላው ነፍስ ቤዛ መሆን ፈጽሞ አይቻለዉም (ማቴ.16፥26)፡፡
    እኒህና ሌሎችም ሁሉ ነገሮች ሰዉን ወደእግዚአብሔር አምላክ ማቅረብ ስላልቻሉ፣ ሰዉ ዋና አዳኝና ቤዛ ቅዱሱን መሲሕ አብዝቶ በመጠማት እንዲናፍቅ አደረገዉ፡፡
V  አሁን አድን (መዝ.118፥25)
V  ፍጠን እርዳን (መዝ.22፥19 ፤ 38፥22 ፤ 44፥26 ፤ 70፥1፤ 79፥9)
V  መቼ ትመጣለህ? (መዝ.101፥2)
V  “አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር ይነሣል፥” (ዘኊል.24፥17 ፤ ኢዮ.19፥26-27) በማለትም አሻግረው በመመልከት የፍፁም አድነንና የእርዳን የጣዕር ድምፅ ወደእግዚአብሔር አሰሙ፡፡
    ሕይወትን መመለስ የሚቻለው የሕይወት ባለቤት ልዑል ፈጣሪ እግዚአብሔር ብቻ መኾኑን ስለተረዱም አጥብቀው ለመኑ፤ ሻቱ፤ ፈለጉ፤ ቃተቱ፤ ደጅ ጠኑ፤ እግዚአብሔርም የሥጦታዎችን ሁሉ ዳርቻ አንድ ልጁን ሊሰጥ ኪዳን ገባ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ባለፍቅር ስለወደደን ክብር ይኹንለት፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …



     [1] (ሐመረ ተዋሕዶ ፤ ጥር 2008 ፤ አዲስ አበባ ፤ ኤች ዋይ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ.191-192) ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ ጽሑፉ ለምን በግልጥ መናገር እንዳልፈለገና ሃሳቡንም ለምን ማወሳሰብ እንደፈለገ ግልጥ አይደለም፡፡ በተውሸለሸለ ሃሳብ፦ “አንዳንድ ባሕታውያን … በአንድ ግለሰብ የተጀመረ መፈክር መሰል ትምህርት … አባባሉ…” በማለት አደብዝዞ ያለፋቸው ቃላት በራሳቸው ብዙ የሚያወያዩ ናቸው፡፡ እውን ይህን ትምህርት የሚያነሱትና የሚያስተምሩት ባሕታውያን ብቻ ናቸው? በመጽሐፍ ደረጃ ወጥቶ መታተሙን ሳያውቅ ቀርቶ ነውን? ነው ወይስ መጻሕፍቱንና ይህን ትምህርት የሚያራምዱትን ቢቃወም የሚደርስበትን “ምዕመናናዊና ደጋፍያኑ የሚያደርሱበትን ውግዘት” ፈርቶ ይኾን? ወይስ ከጊዜው ጋር በመመሳሰል አባዜው ተውጦ ይኾን?
      ከዚያ ባለፈ ማኅበሩ እንደዓይኑ ብሌን የሚሳሳለት “ሰባኪ” ዘበነ ለማ፣ የግል ላይክ ፔጁን ያጌጠበትን ቃል አላስተዋለ ይኾን?  ለምን ይኾን በቸልታ ያለፈው? “ያለ ድንግል ማርያም አማላጅነት አለም አይድንም” የሚለው ዓይን ያፈጠጠው ክህደት መሆኑ ጠፍቶት ነውን? ወይስ መምህሩን ላለማስከፋት ፈልጐ? እውነት እንናገር ከተባለ “ያለ ድንግል ማርያም አማላጅነት አለም አይድንም” የሚለውን ፈጣጣ ክህደት የተቃወሙት እነማን ናቸው? ትክክለኛ ኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮች ናቸው ወይስ ራሱ ማኅበረ ቅዱሳን? እስኪ ማኅበረ ቅዱሳን ይህን ሐሰት፤ ሐሰት ነው ብሎ ቃል በቃል ገልጦ ሲቃወም ድምጹን ያሰማን፡፡ (መቼም አንድ ቀን አይቀርም ብለን እናምናለን) ያም ሆነ ይህ ግን ማኅበረ ቅዱሳን እየፈራ እየተባም ቢሆን እንዲህ ማለቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

3 comments:

  1. ante lj difreth yigermal. Geta kekifu sewoch yitebkh

    ReplyDelete
  2. mn= krkr yelebetm

    ReplyDelete