Friday 30 March 2018

በሕማሙና በትንሣኤው ዙርያ የነበሩ ምስክሮች (ክፍል አንድ)

Please read in PDF
    
    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኃጢአተኛው ዓለም ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፤ ራሱን አሳልፎ  የሰጠበትና ተሰቅሎ ዓለምን የሚያድንበት፣ ሁሉን ወደራሱ የሚያቀርብበት ኹኔታም፣ “እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ፤” (ዮሐ.12፥32) ተብሎ ተገልጧል፡፡ እርሱ የወደቁትን በማንሣት ወደር የለሽና የማይዝል የአብ ክንዱ ነው። ቢዋረድም፣ ዝቅ ዝቅ ቢል፣ በሰው ምስል ኾኖ እንደባርያ ቢያገለግልም ... እርሱ ለአብ አንድያ ልጁ፣ ከአምላክ የተገኘ አምላክ፣ ከብርሃን የተገኘ እውነተኛ ብርሃን ነው።
    “መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን የተነሣ” ነው፤ (1ቆሮ.15፥3-4)፡፡ ታላቁ መጽሐፍ ይህን እውነት የሚያስረዳን አጉልቶና አድምቆ ነው፤ የቤተ ክርስቲያንም ታላቅና ውድ ምስክር ነው፤ ምስክርነቷም የቃል ብቻ ሳይኾን በሚያስፈልግም ጊዜ በሕይወት ጭምር ዋጋ በመክፈል የምትመሰክረው የሕይወት ዘመን ምስክርነቷ ነው። ደግሞም ይህ የከበረ እውነት በብዙ ምስክሮች ያጌጠና ያሸበረቀ ነው።

     ምንም እንኳ አይሁድ ይህ ነገር የአደባባይ እውነት እንዳይሆን ለማፈንና እውነታውን “በእብለት ቃል” እንዲሻርና እንዲካድ ለማድረግ ቢጥሩም ግን ፈጽመው ማስቆም አልተቻላቸውም። ሞቱንና ትንሣኤውን ለማስተባበል ከተነሣው ከጠላት ክንድ ይልቅ፣ ሞቱንና ትንሣኤውን ለመመስከር ጸንተው የቆሙት ደቀ መዛሙርት በሰው ፊት ደም ግባትና ሞገስ ባይኖራቸውም፣ ድምጻቸው በዓለም ዳርቻ በጩኸት የተሰማ፣ በሰማያት ደግሞ ቅቡልና የተወደደ ነበር። ይህ በዘመናት የታየና ታሪክ እንኳ ገሃድነቱን ፈጽሞ መሸሸግ የተሣነው ነው።
   የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ የመሰከሩት ወዳጆቹ ደቀ መዛሙርት ብቻ አይደሉም፤ የማይወዱት፣ ጠላቶቹ፣ አሳልፈው የሰጡት፣ አሕዛብም እንኳ ሳይቀሩ ንጹሕ፣ ቅዱስ፣ በደል የሌለበት፣ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅና ጻድቅ እንደነበር፣ ለሚከሱት ኹሉ መልስን ባለመስጠት ዝምታው አስደናቂና እጅን በአፍ የሚያስጭን እንዲሁም፣ ከሙታን መካከል የተነሣና ሞት ይይዘው ዘንድ ያልቻለ መኾኑን አምነዋል፤ ተቀብለዋል፤ መስክረዋል። ምንም እንኳ አይሁድና የእነርሱ መሪዎች “አይደለም” በማለት  በኋላ ለማስተባበል በብዙ ጥረት ቢያደርጉም።
      እንግዲህ በብዙ ምስክሮች የተከበበውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ፣ ምስክሮቹ ምን ብለው እንደመሰከሩ በማንሳት ከቃለ እግዚአብሔር በማውጣጣት እንማማራለን፤ ይህን እንደዳሰሳ ስናነሣ የምታነብቡ ወዳጆቼ በብዙ እንደምታሰፉትና ለሌሎችም እንዲደርስ በማድረስ እንደምተጉ አምናለሁ። ጸጋ መንፈስ ለኹላችን ይብዛልን፤ አሜን።
1.     ቆዲሞስ፦ ከምስክሮች ቀዳሚ በማድረግ የምናነሳው የአይሁድ አለቃ የኾነውን ኒቆዲሞስን ነው፡፡ የከበረ፣ ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የነበረ ሰው ነው፤ በተለይም በዚያን ዘመን በአይሁድ ዘንድ እጅግ ተደማጭ የኾነውንና “ሲንሃንድሪየም” ተብሎ ከሚጠራው፣ እንዲሁም  የአይሁድ የመጨረሻ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ከሚመለከቱት “ሊቃውንት” ጉባኤ መካከል አንዱና ዋነኛው ሰው ነበረ። እጅግ ከመማሩም የተነሣ “የእስራኤል መምህር” ተብሎ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንደበት የተጠራ ሰው ነው፤ (ዮሐ.3፥1፤ 10)።

    እኒህ የሃይማኖትን ጉዳይ የሚመለከቱ የሲንሃንድሪየሙ ሰዎች በአይሁድ ዘንድ የተከበሩና የተፈሩ፣ እንደዋና መምህራንም የሚታዩ ነበሩ፤ ምናልባትና የተናገሩትና ያዘዙት ከመሬት ጠብ የማይል የተፈሩና የተከበሩ ሰዎች እንደኾኑ መገመቱ የሚከብድ ነገር አይደለም። ብዙ ነገራቸው የተደላደለ ስለኾነ ምንም የሚቸገሩበት ነገር ያለ አይመስልም። “ወንጌል አንድምታ” የኒቆዲሞስን የአለቅነቱን ነገር “በትምህርት በሹመት በባለጸግነት”[1] እንደኾነ ይናገራል። ስለዚህም በኹለንተናዊው መልኩ ተሰሚነት ያለውና ጫና ፈጣሪ መኾኑን ማስተዋል ይቻላል።
    ምንም እንኳ በአይሁድ ዘንድ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መምህርነት ዕውቅና የተነፈገው ቢኾንም፣ ኒቆዲሞስ ግን የክርስቶስን መምህርነት በሙሉ ልቡ አምኖ ተቀብሏል። ኒቆዲሞስ ክርስቶስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር እንደተላከና እንደታላቅ መምህር ለመቀበል ሁለት ታላላቅ ነገሮችን በዋቢነት ጠቅሷል፤ ይኸውም ትምህርቱንና ያደረጋቸውን ምልክቶችን አንስቷል፤ “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር አምላክ ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን” እንዲል (ዮሐ.3፥2)።
    በእርግጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል እኒህ ሁለት ነገሮች በቂና የተሟሉ ናቸው። የጌታችን ኢየሱስ ትምህርቶቹ ፍጹማንና አንዳች እንከን የሌለባቸው ነበሩ፤ ማንም የእርሱን ትምህርቶች ሰምቷቸው ወደልቡ ከመመለስ የሚዘገይ ወይም ፊቱን ወደእግዚአብሔር ዘወር ከማድረግ የሚዘለል አንዳች አይኖርም። ብዙዎች በጌታ ኢየሱስ ትምህርት እጅግ ተገርመዋል፤ ተደንቀዋል፤ (ሉቃ.2፥47፤ ማቴ.7፥29፤ ማር.1፥22)። ከአንደበቱ የሚወጣው ቃል ፈዋሽና ሕይወትን የሚሰጥ ነው። እርሱ ራሱ ዘላለማዊ ሕይወት ነውና፤ (ዮሐ.14፥6)።
   ብዙዎች በእርሱ ትምህርት የተገረሙ ብቻ አይደሉም፤ ያመኑና ሕይወትንም የተቀበሉ ናቸው እንጂ፤ “ስለ ቃሉ ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ” (ዮሐ.4፥41፤ 8፥30፤ 10፥42) እንዲል። ትምህርቶቹን ሰምተው በእርሱ ያላመኑትን መጽሐፍ፣ “ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና” (ዮሐ.12፥43) በማለት በከባድ ወቀሳ ወቅሷቸዋል፡፡ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶች ሰምቶ በእምነት ለሚተገብራቸው ማናቸውም አማኝ ግልጥና የማያሻሙ ናቸው፤ ነገር ግን ሰዎች እግዚአብሔር አምላክን[ጌታችን ኢየሱስን] ከማስደሰት ይልቅ ሰዎችን ለማስደሰት የሚሠሩትና የሚሰሙት ከኾነ ግን ፈጽሞ ሊታነጹበት አይችሉም።
   ጌታችን ኢየሱስ በትምህርቶቹ ከኹሉም ይልቅ አባቱንና መንፈስ ቅዱስን አጉልቶ ያሳየ ሲሆን፣ ስለራሱም አምላክ፣ ጌታና መምህር መኾን በግልጥ ተናግሯል። ይህ ትምህርቶቹ በብዙዎች ዘንድ እንዲወደድ ያደረገውና የተመሰገኑ ትውልዶች በእርሱ እንዲደገፉ፣ እንዲያመልኩትም ያደረገ ነው፤ እኛም ብንኾን በክርስቶስ ኢየሱስ ትምህርቶች የተማረክንና እጅግ የተወደድን ነን! ላለፉት ኹለት ሺህ ዓመታትም ትምህርቶቹ ፈጽሞ ያልተሰለቹና ፍጹም ደስ እንደሚያሰኝ ምንጭ አወራረድ በፍቅርና በመወደድ የሚሰሙ ናቸው። አዎን! እንደእርሱ ተወዶ የተሰማ ማን አለ?! ማንም!
    ኒቆዲሞስ የእስራኤል ዋና መምህር ነው፤ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “መምህር ሆይ” በማለት ሲጠራው እንመለከተዋለን፤ ኒቆዲሞስ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች የተመሰጠና የተማረከ ብቻ አይደለም፤ መምህርነቱንም ከልቡ አምኖ ተቀብሏል። ይህ ለአይሁድ ባሕል ፈጽሞ የማይመችና ፈጽሞ ተጻራሪ የኾነ አካሄድ ነው። አይሁድ ያላከበሩትን እርሱን ክርስቶስን፣ አይሁድ የሚፈሩትና እንደአለቃቸው የሚቆጥሩት ኒቆዲሞስ እጅግ በመፍራትና በማክበር በእርሱ ታምኖበታል። አይሁድ ክርስቶስን ላለመውደድ ምንም ምክንያት የላቸውም፤ እነርሱ የሚወዱትና የሚያከብሩት መምህራቸው ራሱን ከጌታችን ኢየሱስ ሥር አዋርዷልና፤ ዛሬም ቢሆን ክርስቶስን ላለመውደድ ምንም ምክንያት የለንም፤ እርሱ በትውልድ መካከል በብዙ ትውልዶች ዘንድ ክቡርና እጅግ የተወደደ ርእስና ዋና ነውና!
    ጌታችን ኢየሱስ በሥራዎቼ እመኑ ብሎ በግልጥ ተናግሯል፤ ስለምልክቶቹም ብዙዎች አምነዋል፤ (ዮሐ.2፥23፤ 7፥31፤ 11፥45፤ 12፥11)፤ ሥራዎቹ በቀጥታ አባቱን ወይም እርሱን ወይም ፍጹም አምላክነቱን የሚያመለክቱ ናቸው፤ (ማር.11፥22፤ ዮሐ.10፥38፤ 12፥36፤ 14፥1፡ 11)። ኒቆዲሞስ የጌታችን ኢየሱስ የእጁን ተአምራት ወይም ምልክቶችንም ተመልክቷል፤ ዓይቶም ፍጹም አምኗል፤ ምልክቶቹ በዛሬ ዘመን እጅግ በብዙ እንደምናየው ባለ መልኩ የማስመሰል ጉዳይ ያይደለ ትክክለኛና እውነተኛ ነበሩ፤ ለዚህም ነው ኒቆዲሞስ፦ “እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና” በማለት ፍጹም የመሰከረለት።
    ይህ ታማኝ የሌሊት ደቀ መዝሙር በክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን ሞትና ትንሣኤ ሰዓት ዋናና ታላቅ ምስክር ነበር፤ በቀብሩ ጊዜም፦ “ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ” (ዮሐ.19፥39)፤ ይህ ለክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን ግንዘት የወጣው እጅግ ውድ ዋጋ ነው፤ እጅግ ድፍረትና ራስን መግለጥ በሚያስፈልገው በዚህ ሰዓት ኒቆዲሞስ በትክክልና በታላቅ ጭካኔ ከጌታችን ኢየሱስ ጋር ለመታየት ወሰነ። ሰው ሁሉ ስቁሉን ጌታችን ኢየሱስ በራቀበትና ጀርባውን በፍርሃት ብዛትና በጥላቻ በለወጠበት ወቅት ኒቆዲሞስ በአስደናቂ ጉልበት ሲመጣ እንመለከተዋለን።  እኛስ በቁርጥ ቀን እንዲህ ለክርስቶስ የተገባን ምስክር ኾነን መቆም የሚቻለንን ነንን? ክብራችንና ሥልጣናችን አልበለጠብን ይኾን? አናስቀድምስ ይኾን?
     ክርስቶስ በሰውነቱ ለኃጢአታችን እንደሞተ ካሉን ምስክሮች አንዱና ዋናው ኒቆዲሞስ ነው። ያመንነውና የምመሰክረው እውነት የከበረና መንፈስ ቅዱስ በብዙ ምስክር ያጸናው ነው። ጌታ መንፈስ ቅዱስ ይህንን እውነት በማየት እንድንጸና ይርዳን፤ አሜን።
ይቀጥላል ...




[1] ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ.388

3 comments:

  1. የጌታችን ኢየሱስ ትምህርቶቹ ፍጹማንና አንዳች እንከን የሌለባቸው ነበሩ፤ ማንም የእርሱን ትምህርቶች ሰምቷቸው ወደልቡ ከመመለስ የሚዘገይ ወይም ፊቱን ወደእግዚአብሔር ዘወር ከማድረግ የሚዘለል አንዳች አይኖርም። amen

    ReplyDelete
  2. kalehiwot yasemaln

    ReplyDelete
  3. ጌታ ይባርክህ ቃለ ሕይወትም ያሰማህ

    ReplyDelete