Thursday 8 March 2018

ስድስት ዓመታት በጡመራ መድረክ አገልግሎት

      “አስቀድሜ ስለ ሁሉም ነገር አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ።” (ሮሜ.1፥8) ላለፉት ስድስት ዓመታት በጡመራ መድረክ አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉ ትምህርቶች፣ ስብከቶች፣ ዕቀብተ እምነታዊ ምልከታዎች፣ ካነበብኳቸው፣ ግጥሞችና ሌሎችንም ጽሑፎችን ለአማኝ አንባብያንና ለሌሎችም ወገኖች አቅርበናል። በተለይም ዕቅብተ እምነታዊ ሥራዎችና ትምህርቶች በዚህ ዓመት በስፋት ከቀረቡት ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።
   ምክንያቱ ደግሞ፣ ከፊት ዓመታት ይልቅ የስህተት አስተምኅሮ በግልጥ ታይቷል፤ እጅግ ቅርባችን የነበሩትንም ሰዎች መርዘዋል፤ ከተሰቀለውና ከተነሣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማንያንን ለይተዋል፤ አደላድለዋል፤  ምንም እንኳ የሐሰት መምህራኑንና ደቀ መዛሙርቶቻቸውን የማውራት ሥራ ቢሠራም፣ ከዚያ በኋላ ግን ይህንን በግልጥ ለመቃወም አንዳች በራሳችን አልተማከርንም፤ የእግዚአብሔር ቃል የሚጠየፈውን ኹሉ ሳንራራ ተጠይፈናል። ስለዚህም በዚህ ረገድ ሰፋ ያለ ዕቀብተ እምነታዊ ሥራ በሥፋት ለመሥራት ጥረት ተደርጓል።

    ከቀደሙት ዓመታት ይልቅ በስውር ይነገሩ የነበሩ የኑፋቄ ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መቃወማችን፣ ብዙዎችን በአዎንታዊም፤ በአሉታዊም መንገድ መድረስ እንደተቻለ ብዙ ማሳያዎች አሉ። አንዳንዶች “የአባቶችን ትምህርት እንድምንቃወም” ጭምር አጽንተው ሲናገሩ ሰምተናል፤ የቱ ጋ ምን ብለን እንደተቃወምን ባይገለጽልንም፣ መጽሐፍ ቅዱስን በመቃወም አንድም ጽሑፍ አለመጻፋችንንና አለማስተናገዳችንን እርግጠኛ ኾነን መናገር እንችላለን። ብዙዎች ከሳሾቻችን የእምነት እንቅስቃሴ (Faith Movement or Word Faith Movement) እና የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ (New age Movement) አማኞችና መምህራንን በመቃወማችን እጅግ ሳይደነቁ አይቀሩም፤ ምክንያቱም ብዙዎች ከእነርሱ ጋር አንድ እንደኾንን ያስቡ ነበርና። አንዳንዶች እኛን ሳይሰሙን እንኳ “ማን እንደኾንን ሲናገሩ አያፍሩም”። በእርግጥ ከሳሽ ለክሱ መች የተሻለና መልካም ቃላትና ሃሳቦችን ይመርጥና?!
    እጅግ ያልታሰቡ ወንድሞችና እህቶች፣ አባቶችና እናቶች የትምህርታችንን እውነተኛነት መረዳት በመቻላቸው እጅጉን ደስተኞች የኾንነውን ያህል፣ ሰዎች ለምን ሳይሰሙን በክፋት ልብ “የጥላቻ የመደምደሚያ ሃሳብ” እንደሚይዙም ስናስብ በጥቂቱ “አዝነናል”። በዚህም ኾነ በዚያ ግን ሰዎች ወደክርስቶስ ፊታቸውን ዘወር በማድረጋቸው፣ ከኑፋቄ ትምህርት በመጠበቃቸው፣ ለእውነት ቃል በመሸነፋቸው ብቻ እጅግ ደስተኞች ነን።
  ምንም እንኳ በዚህ ዓመት ስፋት ያላቸው ተቃውሞዎች ያስተናገድን ቢኾንም፣ የሥራው መሠራት ዋነኛ ማሣያ ምክንያት ነው። ተቃውሞዎች ሥራ ያሠራሉ፤ ትችቶች የት መቆማችንን ያሳያሉ፤ ዘለፋዎች ሥራችንን እንድንመለከት፣ እንድንገመግም ይረዱናል፤ ነቀፋዎች “ዕንቁዎቻችንን በእሪያ ፊት እንዳናስቀምጥ” ጠቋሚዎች ናቸው፤ ስድቦች የክብር አክሊላችንን የሚያበዙ ሽልማቶች ናቸው[መቼም ስደቡን ብለን አንለምን ነገር፤ የመንግሥት ልዩነት ካለን ተቃዋሚዎች የሚቃወሙት መንግሥታችንን እንጂ እኛን አይደለም]… እናም እንዴት ለአሳዳጆቻችን ምሕረትና ይቅርታን ከመማለድ በቀር ምን እናደርግ ዘንድ ይቻለናል?
  አገልግሎት ሸክም ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሸክሞ ተሸከሙት ያለን ቀሊል ሸክምና ልዝብ ቀንበር። አገልግሎት ራእይ ነው፤ ራእዩም ክርስቶስ ያየውንና የኖረለትን ዓይቶ መኖርና ለዚያ ኹለንተናን አሰልፎ መስጠት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ያየውን አለማየት፤ ያሳየንንም እርሱን ትኩር ብሎ አለመመልከት የተላክንበትን ሳንረዳ መልእክቱን ለማድረስ የምንቸኩል ይመስላል። ለስድስት ዓመታት ያደረግነው ነገር ቢኖር ከኢየሱስ ጌታችን አምላካችን ሊቀ ካህናታችን ውጪ ማንንም ለማስደስት አልጣርንም፤ የአገልግሎታችን ግብ እርሱን ማስደሰትና የእርሱ የኾነውን ነገር ብቻ መናገር ነው። “እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን[ማንንም] እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ (ሐዋ.4፥19) እንዲል።
በዚህ አገልግሎት ውስጥ በብዙ ነገር የተራዳችሁኝ ወንድሞችና እህቶቼን ሳላመሰግን አላልፍም፤ ኹለቱን ሙሌዎችና ደሬ፣ አግዝ[የበርታ ድምጻችሁ አኹንም ይሰማኛል]፣ ሰብሊ[ሎጐዎችን በማሳመር አሁንም አብረሽኝ አለሽ]፣ ቢኒ [ጽሑፎችን ቡስት በማድረግ]፣ ሚሻ[የእህትነት አጋርሽ ልብን ይደግፋል]፣ መጻሕፍትን በመለገስና በመጠቆም፣ በጸሎትና በምክር፣ ለጽሑፉ ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦችን በመስጠት አብራችሁኝ ለነበራችሁ ከልብ አመሰግናለሁ፤ ጌታ ዘመናችሁን በሚያስፈልጋችሁ ነገር ኹሉ እንዲባርካችሁ የዘወትር ጸሎቴና መሻቴ ነው። እግዚአብሔር አምላክ በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊቱን ያብራላችሁ፤ ይራራላችሁም፤ መንገዳችሁንም ያቅናላችሁ፤ አሜን።
    ጌታችንና መንጽሒያችን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አገልግሎታችንን ይባርክ፤ አሜን።

3 comments:

  1. Geta tsegawn yabzalh gena bzu tiseraleh

    ReplyDelete
  2. ለአሳዳጆቻችን ምሕረትና ይቅርታን ከመማለድ በቀር ምን እናደርግ ዘንድ ይቻለናል? ewnte new

    ReplyDelete
  3. የተባረክ ነክ።በዚህ ዘመን እርግማን ውግዘት በአንተ ላይ አይሰራም።በአዲስ ኪዳን አንድ አርግማን አውቃለው " ጌታ እየሱስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን " የሚለውን።ይህ እርግማን ደግሞ አንተን አይመለከትም።ተባረክ።አሜን

    ReplyDelete