Tuesday 13 March 2018

“መጻጉዕ” ኢትዮጲያ ሆይ! እግዚአብሔር በምሕረት ይማርሽ!


Please read in PDF
   ኢትዮጲያ ታምማለች፤ ሕመሟም ጸንቶባታል፤ ክሳትዋ፣ ግርጣትዋ፣ መሞገጓ፣ መጥቆርዋ፣ መጠልሸቷ፣ ኩምሽሽ ኩምትር ማለቷ፣ አንዱ ሌላውን ሊበላላና ሊጠፋፋ ማሰፍሰፉ፣ ደም ማፍሰስ ወዳድነታችን ያመረቀዘበት፣ ሰው በሰውነቱ አልከበር ብሎ ብሔርና ቋንቋ መስፈርት አድራጊያን የበዙባት … ምድር ኾናለችና ምድሪቱ ታምማለች፤ አጐንብሳ ታቃስታለች፤ መሪዎቿ ሊያስታምሟት የወደዱ አይመስሉም፤ ከእጅግ በጣም ጥቂቶቹ በቀር ልባቸው ደንድኗል፤ ኅሊናቸው ታውሯል፤ ሽማግሌዎች ከመደመጥና ከመከበር ይልቅ መታፈሪያቸውና መከበሪያቸው “ያበቃለት” ይመስላል፤ ሁሉም ነገር “የራሳቸውን ሕይወት አውጥተው በማያስገቡና በማይደማመጡ” ወጣቶች እጅ ለመውደቅ እያዘመመ ይመስላል፤  … የኢትዮጲያ መጻጉዕነት መልኩና ፈርጁ እየበዛ እየሰፋ መምጣቱን ለመናገር ነቢይነት አያሻውም። እጅግ አሳዛኙ ነገር ግን ይህች “ቅድስትና ብዙ አማኞች እንዳላት የሚነገርላት አገር” በዚህ ሁሉ ነገሯ ለመንፈሳዊ ነገር መታወሯና ቅድሚያ ለመስጠት አለመወሰኗ እጅግ አስጨናቂና መራራ ኹኔታ ነው። እግዚአብሔር ስሙ እየተጠራባት እግዚአብሔር ባዕድ የኾነባት አገር!!!

    ለየትኛውም አማኝ ሚዛኑ፣ ማዕከሉ፣ የአንድ ነገር መለኪያ ቱንቢው ቃለ እግዚአብሔር ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ነገሮችን ከቃለ እግዚአብሔር አንጻር ሳይሆን፣ ከጊዜው ትኩሳት አንጻር ብቻ የምንዳኝ ከሆነ ፍጹም እንስታለን። ነገሮችና ኹኔታዎች የዘመኑን መልክ ሊይዙ ይችሉ ይኾናል፤ የእግዚአብሔር ቃልና ባሕርይ ግን የጸናና ለዘለዓለምም የማይናወጥ ነው። ስለዚህም ከጸናው ጋር እንጸናና እንቆም ዘንድ የቃሉ ስንቅ መመገብ የዘወትር ልማዳችን ሊኾን ይገባዋል ማለት ነው።

   ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አለ፦
  “ደመና ከምዕራብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ፥ ወዲያው፦ ዝናብ ይመጣል ትላላችሁ፥ እንዲሁም ይሆናል፤ በአዜብም ነፋስ ሲነፍስ፦ ትኩሳት ይሆናል ትላላችሁ፥ ይሆንማል። እናንት ግብዞች፥ የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፥ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው? ራሳችሁ ደግሞ ጽድቅን የማትፈርዱ ስለ ምን ነው?” (ሉቃ.12፥54-57)።
      የምናየውን ተፈጥሮአዊ ኹኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ዘመን መልኩ ምን እንደሚመስል ከቃለ እግዚአብሔር አንጻር መመርመር ይገባናል። ዕይታችን ተራና ከቃለ እግዚአብሔር አንጻር ያይደለ መኾን የለበትም፤ (ኢዮ.12፥2)፡፡ ዘመኑን በትክክል መመልከትና ንጹሕ ከሚመስሉ ምንጣፎች ላይ ያሉትን ርጋፊና አቧራዎች፣ እድፍና ቈሻሻን መመልከትና ማስተዋል ልበ ሰፊነት የበዛበት ዕይታን ይጠይቃል። ዘመንን መመርመር ዘመንን ለመዋጀት መሠረት ነው፤ አይሁድ የተወቀሱበት አንዱ ምክንያት፣ የመሲሑን ዘመን ጠባቂ ነን ብለው፣ መሲሑ ሲመጣ አለማወቃቸውና አለመቀበላቸው ነው። ከቅዱሳት መጻሕፍት መርምረው፣ ዘመኑ የቅዱሱ መሲሕ መኾኑን ማወቅ ሲገባቸው፣ እነርሱ ግን የማያርፉበትንና የማይረኩበትን ሌላ ምልክትና ተአምርን ፍለጋ ተንከራተቱ። ከቅዱሳት መጻሕፍት ግን ስለመሲሑ ቢመረምሩ እርሱን ባገኙት ዘመናቸውንም ሁሉ ባረፉበትና በረኩበት ነበር።
    ዘመንን በትክክል አለማወቅ በዘመን ውስጥ እግዚአብሔር አምላክ እንድንመሰክረው የሚሻውን እውነተኛውን ምስክር ወይም የሚያደርገውን መልካም ነገር ከማስተዋል ቸል እንድንል ያደርገናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክ በዘመን ውስጥ የራሱ እውነተኛ ምስክሮች አሉት፤ “… መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” (ሐዋ.14፥17) እንዲል፣ እግዚአብሔር አምላክ ክፉዎች ለነበሩትና ሊያመልኩት ላልወደዱት አረማውያን እንኳ መጋቢ፣ ሠራዒ፣ ጠባቂ፣ ታዳጊ … መኾኑን የሚመሰክርን መልካም ሥራን ከመሥራት ፈጽሞ አላቋረጠም። በየዘመኑም እግዚአብሔር አምላክ በታሪክ ውስጥ፣ እጅግ አስጨናቂ ገዢዎች በኾኑ ነገሥታት በኩል [ለምሳሌ፦ በባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነጾርና በፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ (ዕዝ.1፥1፤ 5፥13፤ ኤር.27፥6)]፣ በአረማውያን በኩል ብዙ መልካም ነገሮችን አድርጐ ነበር፤ (ሐዋ.14፥17፤ 17፥28፤ ቲቶ.1፥12)።
     ከኹሉ በላይ ደግሞ በምናምነውና ፈቃዱን በአንድያ ልጁ ለገለጠልን ለእኛ፣ እግዚአብሔር አምላክ ሊያደርግ የወደደውን ነገር ፈጽሞ አልሸሸገውም፤ ደግሞም አይሸሽገውም፡፡ ላላመኑት አሕዛብ መልካም ነገርን በማድረግ ከተገለጠ ለእኛ ከአንድያ ልጁ ጋር ሁሉን ነገር ለሰጠን ልጆቹማ (ሮሜ.8፥32) እንዴት አብልጦ ፈቃዱንና በጐነቱን አይገልጥልን ደግሞስ አያደርግልን ይኾን? አዎን! እግዚአብሔር አምላክ በዘመን ውስጥ ያኖረልንን ምስክርነት ልናስተውለው ይገባናል።
        አንድ ነገር መዘንጋት የለብንም፤ መንፈሳዊነት ወጥነት ነው፤ “ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም” (2ጢሞ.4፥2) እንዲል፣ እውነተኛ ክርስቲያን በማናቸውም ዘመን፣ በማናቸውም ሰዓት፣ በማናቸውም ኹኔታ ውስጥ ቢኾን የሚለዋወጥ ዓይነተኛ ባሕርይ የለውም። ምንም እንኳ ቃሉ የተነገረው አገልጋይ ለኾነው ጢሞቴዎስ የተነገረ ቢኾንም፣ የተገለጠ መልካምነትንና በመታገስ መስበክን ማድረግ ያለብን ምቹ ሰዓት በመጠበቅ ሳይኾን በማናቸውም ዓይነት ኹኔታ ውስጥ ሊኾን ይገባዋል። ብዙዎቻችን ምቹ ዘመንና ሰዓት በመጠበቅ ለማገልገል የምንሻ ነን፤ ነገር ግን ያ ጊዜ በሕይወታችን የማይመጣበት ጊዜ ብዙ ነው።
    ወቅታዊውን የአገራችን ኹኔታን ስንመለከተው ለመንፈሳዊ ነገር ፈጽሞ ምቹ ጊዜ አይመስልም። የሚነሡት ግጭቶችና አለመግባባቶች “አማኞችንና ክርስቲያን የተባሉትንም” ጭምር ማሳተፉ ደግሞ ጆሮን እጅግ ጭው የሚያደርግ ነው። አሉታዊም “አዎንታዊ”ም በኾነ መንገድ እየተንጸባረቀ ባለው በዚህ ተሳታፊነት ደግሞ፣  መንፈሳዊነትን ያላንጸባረቀና ቃለ እግዚአብሔርን ድጋፍ ያላደረገ ለመኾኑ ድርጊቱንና ውጤቱን ማየት ብቻ በቂ ነው። በማናቸውም ረገድ የሚፈጸመውንም ኾነ የሚነገረውን ነገር ከቃለ እግዚአብሔር አንጻር መዳኘት አለመቻል እጅግ ምስኪንነትና ከእግዚአብሔር መለየታችንን እርግጠኞች ኾነን በደስታ የተቀበልን ያስመስልብናል።
    አስተውሉ! ምድራችን ወደለየለት ባቢሎናዊነት “እያመራች” ነው፤ ልዩነታችንን መቀባበል አለመቻላችን የትላንት “የጸና” ሕብረታችንን ሲንድ እያየነው ነው፤ በዘር፣ በቋንቋ፣ በብሔር፣ በነገድ፣ በሕዝብ፣ በድንበር፣ በወንዝ፣ በመልክ … ልዩነታችን እጅግ መከባበርና መደናነቅ ሲገባን፤ ለመገዳደላችን፣ ለመከፋፋታችን፣ ለመጠላላታችን፣ “ዓይንህን ላፈር” ለመባባል ምክንያት ሲሆነን ማየት ልብን ያደማል፤ አንጀትን በቃጠሎ ያበግናል። የአንድ እናት ልጆች ሲለያዩ፣ ጐረቤት ለጐረቤት ሲራራቅና የጐሪጥ ሲተያይ፣ ባልንጀርነት ሲናድ፣ ትዳር ሲፈራርስ፣ ሕዝቦች ሲገፋፉ፣ ግላዊ ጠቦች አገራዊ መልክ ሲሰጣቸው … እንደሚያውክ ሌላ ነገር ምንም አያውክም።
    እጅግ ረጅም ጊዜ አብረን ያሳለፍነው አንድ ወዳጄ፣ በወቅቱ ጉዳይ ላይ እጅግ “በጠባቡ” እያወራን ሳለ፣ ድንገት ቱግ ብሎ፣ “ማንም ቢሆን የሚቃወምህና የማይቀበልህ ከሆነ፣ አንተም ልትቀበለውና አብረኸው ልትሆን አይገባም” ሲል፣ ጮኾ በማላውቀው ድምጸት፤ በበቀል ስሜት ሲናገር ስሰማው የወዳጅነታችንን መሠረት ደግሜ እንድመረምረው አስገድዶኛል፤ በእርግጥ ይህንን ሃሳብ ብዙዎች እንደሚጋሩት አውቃለሁ፤ ነገር ግን መንፈሳዊነት ወይም የእግዚአብሔር ሰው መኾን ወቅታዊ ኹኔታ የሚለዋውጠው፤ በክፋት ዘመን የሚከፋ፣ በደግ ዘመን ደግሞ ደግ የሚኾን ተለዋወጭ ጠባይ ያለው ሰው ዓይነት አይደለም። እንዲህ ከኾነማ ከግብዝነት መች ተላቀቅንና!?
   በሌላ መልኩ ደግሞ፣ እንደአገራችን ክርስቲያኖች ብዛትና ግን ደግሞ ተጽዕኖ አላምጪነት፣ የክፉዎችና የደመኞች፣ የአስጨናቂዎችና የዘራፊዎች ድምጽ ጮኾ መሰማቱንና ማሸነፉን ስናይ፣ “ይህ ስለምን ኾነ?” ማለታችንና ክርስቲያኖች ስለምን በዚህ ረገድ ተጽዕኖ መፍጠር ተሳናቸው? ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ እውነትም ግን፦
ጽዕኖውን ለምን ማምጣት ተሳነን?
     ዛሬ በዓለም ላይ ያለውን የዓለምን ሕዝብ ቁጥርን በተመለከተ፣ “2.18 ቢሊየን ክርስቲያኖች ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ1 ቢሊዮን በላይ ካቶሊክ፣ 800 ሚሊየን ፕሮቴስታንት፣ ኦርቶዶክስ ደግሞ 260 ሚሊየን እንደሆነና ቀሪው ሌሎች ቤተ እምነቶች እንደሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ። በዓለማችን የኦሬየንታል ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ኢትዮጲያን ጨምሮ በዋናነት በስምንት አገሮች ይገኛሉ፤ ቁጥራቸውም 82 ሚሊየን አከባቢ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ (40 ሚሊየን በላይ) አባላትን በመያዝ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቀዳሚ ናት።”[1]
    በኢትዮጲያ ውስጥ የክርስቲያኖች ቁጥር ከግማሽ ሕዝብ በላይ እንደኾነ እሙን ነው። እንደሕዝቡ ቁጥር ግን ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ ድኩምና ልምሾ ነው፡፡ የማኅበረሰብ ኃጢአት ኾኖ አገሩን ከጫፍ ጫፍ ያነካካውን የዘረኝነትን ነውር “እኛም” ጭምር በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ ተሳታፊዎች ስለኾንን፣ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ መፍጠርና ማስቆም አልቻልንም። ቤተ መንግሥት “ያራባውንና ያባዛውን” ብሔር ተኮር ፖለቲካና ምልከታ፣ በአንድም በሌላም የምንጋራ ነን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህንን “ኹሉ አማኝ ይዛ” ከዚህ ነውር አለመላቀቋ ጆሮ ጭው የሚያደርግ አስከፊ ፍርድን በራሷ ጮኻ እየተጣራች ይመስላል። በዚህ ኹሉ ደግሞ መጻጉዕነታችንን አለማመናችን እጅግ “ያስደንቃል”፡፡
   ለመያያዝ አለመፍቀዳችን፣ ሰውን ለመውደድ ሚዛኑን ሰውነት ብቻ አለማድረጋችን፣ በትንሹም በትልቁም መከፋፈልን እንደአማራጭ መያዛችን፣ ምድርን፣ ብሔርን … ልክ እኛ ተመርጠንበት ወይም ሌሎችም መርጠው እንደተወለዱበት አስበን መከፋፋታችን … በሰውም በእግዚአብሔር አምላክም ፊት አስነቅፎናል። እንኳን በሌላው ላይ መንፈሳዊ ተጽዕኖ ፈጣሪ ልንኾን፣ ከገባንበት ምድራዊ ማጥ ለመውጣት ሽንቁር የመፍትሔ ቀዳዳ ማየት ተስኖናል።
 ን እናድርግ?
1.      ስሐ እንግባ፦ ዘረኝነት እግዚአብሔር በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረውን ፍጥረት መናቅ፣ ትክክል አይደለም ብሎ ሠሪውን መቃወም፣ በሠሪው ጌታ ላይ ማመጽ ነው። ይህ ደግሞ እጅግ አጸያፊ ርኩሰት ነው። ስለዚህ እንመለስ፤ በፊቱ እንበርከክ፤ እናልቅስ። ዳግም ላንበድል የልዩነቶቻችንን ምልክቶች ኹሉ እናስወግድ።
2.     መቀባበል እንያያዝ፦ ልዩነቶቻችንን በፍቅር ከመቀባበል ይልቅ በየመገናኛ ብዙሃኑ መሰዳደባችን፣ መገፋፋታችን፣ መናናቃችን፣ መጠላላታችን፣ መገዳደላችን ... ከመጠፋፋት፣ በዓለሙ ኹሉ ፊት መሳለቂያ፣ መሣለቂያ፣ መዘበቻ፣ መሰደቢያ፣ መዝፈኛ ... ከመኾን በቀር ምንም አልረባንም። ብንቀባበል፣ ብንያያዝ ግን በሰማይም በምድርም የእውነት ምስክሮች መኾናችን በታወቀልን ነበር!
3.     ሳ እንካስ፦ ዘረኝነታችን አደባባይ ላይ ናኝቶ የብዙዎችን ቤት አፍርሰናል፣ ንብረት አቃጥለናል፣ ዘርፈናል፣ ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር ለግል ጥቅማችን ገድለናል፣ ፍትሕ አዛብተናል፣ ትዳር አፍርሰናል፣ ቤተሰብ አፍርሰናል ... ስለዚህ ስለበደልነው በደል ካሳ እንካስ፣ ያዋረድነውን እናክብረው፣ ያፈረስነውን ትዳር ዳግም እንገንባ፣ የበተነውን ቤተሰብ እንሰብስብ።
ማጠቃለያ
    የኹላችንም መገኛ ምንጭ አንድ ነው፤ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ከኾነው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። በእያንዳንዱ ሰው ላይ የእግዚአብሔር ልዩ ዓላማና እቅድ አለ። ማንም በማንም ላይ ሥልጣን የለውም። ሰውን ከፈጠረው በቀር ነፍስና ሥጋውን የሚለይ ሠሪው በእርሱ ላይ ያለውን ዓላማና እቅድ ይቃወማል፤ ማናቸውንም ሰው የሚንቅ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ሊሠራ ያለውን ነገር ኹሉ ይንቃል። ዘረኛ[መጻጉዕ] ሆይ! “ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮለት! በምድር ሸክላዎች መካከል ያለ ሸክላ ነው። ጭቃ ሠሪውን፦ ምን ትሠራለህ? ወይስ ሥራህ፦ እጅ የለውም ይላልን?” (ኢሳ.45፥9)። አዎን! ሰውን ኹሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን ልብ በመቀበል፣ እግዚአብሔር በሰው ኹሉ ላይ ያለውን ዓላማ እናክብር፤ ኢትዮጲያን ከተያዘችበት የዘረኝነት ድውይ ወይም መጻጉዕነት እግዚአብሔር አምላክ ይማራት፤  ጌታ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን።



[1] http://List_of_christian_denominations_by_number_of_members

1 comment: