Thursday 29 March 2018

የብልጽግና ወንጌል፣ ከጌታችን ኢየሱስ ያልኾነ ልዩና እንግዳ ወንጌል - ክፍል ፲

Please read in PDF

  እግዚአብሔር ልጅነታችን እስከመለኮት መኾን የሚደርስ ነውን? በሚለው ርእስ ሥር፣ “አይደለም” በማለት ጥቂት ነገር መጨመርን ፈልጌያለሁ፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ስንል፣ ራሱ እግዚአብሔር ነው ማለታችን ነው፡፡ እግዚአብሔር ከኾነ ደግሞ መጀመርያና መነሻ የሌለው፣ ያለ፣ የነበረና የሚመጣው ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፣ ሕያውና ዘላለማዊ ነው ማለታችንም ጭምር ነው፤ (ራእ.1፥8)፡፡
     ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር፣ “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።” (ዮሐ.1፥3) ይለናል፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን እግዚአብሔርነትን ከጊዜ ብዛት ወይም በኾነ ጊዜ ያገኘው አይደለም ወይም እግዚአብሔርነትን ያገኘው በኾነ በታወቀ ጊዜ[ለምሳሌ፦ ከቅድስት ድንግል ሲወለድ ወይም በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ] አይደለም፤ ከዘላለም ጀምሮ እግዚአብሔር ነበረ፤ በዘላለም ውስጥም እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ “ቃል እግዚአብሔር ነበረ” ሲል፣ ከመጀመርያውም የነበረበትን መለኮታዊ፣ ፍጹም አምላካዊ ሁኔታን የሚያስረግጥ ነው፡፡

    ይህ እግዚአብሔር አምላክ የነበረው ቃል፣ ሥጋ ሆነ፤ ሥጋ የኾነው ያው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ሥጋ በመኾኑ በመለኮታዊ ማንነቱ ላይ ያስከተለው አንዳች ነገር የለም፡፡ ሥጋ ሲለብስ፣ በመለኮታዊ ማንነቱ ላይ ሥጋ ብቻ መጨመሩን የሚያመለክት እንጂ፣ አምላክነቱ መጀመሩን ወይም ከመለኮታዊ ማንነቱ ማነሱን አንዳች አያመለክትም፡፡
   ሥጋ የኾነው አካላዊ ቃል፣ ቃልነቱ ዘላለማዊና የማይለወጥ ነው፤ እርሱ ከሥጋ መገኘት በፊት የነበረ እግዚአብሔር አምላክ ነውና፡፡ “ሆነ” የሚለው ቃል፣ ቃል ሥጋ በመሆን ገንዘቡ ያልነበረውን ሥጋ ገንዘብ አደረገ፣ ተዐቅቦ ባለበት ተዋሕዶ ሰው ሆነ ማለታችን ብቻ ነው፡፡ “ለምን ሥጋ ሆነ?” ብንልም፣ ከዘላለም አምላክ እንጂ ሰው ስላልነበረ ሰው ሆነ፡፡
     አካላዊ ቃል ሥጋ ሊለብስ ከቀድሞ አምላካዊ ማንነቱ ወደእኛ መጣ፡፡ “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥” (ዮሐ.1፥11) ሲል፣ ከአምላካዊ ማንነቱ ሥጋ ሊለብስ መምጣቱን፣ በቀደመው ኪዳን ወገኖቹ ከነበሩት እስራኤላያውንም ጋር የነበረ አምላክ ያህዌ መሆኑንም ያሳያል፡፡ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር፣ ያህዌም ነው፡፡ የቀደመውን ኪዳን መሥራች እርሱ ነው፤ ኋለኛውን አዲሱን ኪዳንም የመሠረተው እርሱ ነውና “መጣ” ተብሎ ተነገረለት፡፡ የመጣው አምላካዊ ክብሩንና መብቱን የሰው ልጆችን ሁሉ ለማዳን ሲል በመተው መምጣቱን አመልካች ነው፡፡
   ”ነበረ፣ መጣ“ የሚሉት ቃላት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ኑባሬ ያለው መሆኑን ወንጌላዊው ዮሐንስ ያለጥርጥር ይመሰክራል፡፡ ወንጌላዊው ይህን እውነት በሌሎችም ክፍሎቹ በሚገባ ይገልጣል፤ ለምሳሌም ሁለት ክፍሎችን ብናነሣ፦ ጌታችን ኢየሱስ በገሊላ ቃና ያደረገው ተአምር አምላካዊ ክብሩን ለመግለጥ እንደኾነ፣ “ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” (ዮሐ.2፥11) በማለት ገልጦታል፤ አምላክ ስለኾነ ልዩ ተአምርን አደረገ፤ ደቀ መዛሙርቱ በእርሱ አመኑ፡፡ የአዳምና ሔዋንን ቤተሰብ አስቀድሞ የመሠረተው እርሱ ነው፤ ደግሞም የምልክቶችን መጀመርያም በማድረግ ሲጀምር፣ በገሊላ ቃና በሠርግ ቤት በመገኘት አስቀድሞ ቤተሰብ በመመሥረት የነበረው ያው አምላክ፣ አሁንም ቤተሰብን ሲመሠርት አምላካዊ ማንነቱን ሊገልጥ ምልክትን አሳየ፡፡
    በኹለተኛው ምሳሌ ሐዋርያው ቶማስ ምክንያታዊ ጥያቄን በማቅረቡ፣ ጌታችን ኢየሱስ፣ “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን” ብሎ በተናገረው ጊዜ፣ “ጌታዬ አምላኬም” ብሎ መስክሯል፤ (ዮሐ.20፥27-28)፡፡ ሐዋርያው ቶማስ ነገሩን በተጨባጭ እይታ ለማመን ያሰበ ይመስላል፤ በማየቱም አመነ፤ ደግሞም አምላክና ጌታ መኾኑንም መሠከረ፡፡
   ወንጌላዊው ዮሐንስ በወንጌሉ መጀመርያና በወንጌሉ ፍጻሜ አካላዊው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናምንበት አበክሮ ይነግረናል፤ (ዮሐ.1፥12፤ 20፥31)፡፡ እርሱ አምላክና ጌታ ስለኾነ እንድናምንበት ተጠርተናል፡፡ ሰው ቢኾንም መለኮታዊነትን በፈቃዱ በመተዉ ከአብ የሚያንስ አይደለም፤ ከእውነተኛ አምላክ ጋር ተካካይ ነው፤ “ከብርሃን የተገኘ እውነተኛ ብርሃን” ነው፡፡ ሰው በመኾኑም በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን እንደመቀማት ያልቆጠረ ነው፤ (ፊል.2፥8)፡፡
    ፈጣሪ በነበረው በእርሱ በክርስቶስ ጌታችን ሁሉ ሆነ፤ ከፍጥረት መገኘት በፊት ነበረ፤ በፍጥረትም መገኘትም ጊዜ ከመጀመርያውም የነበረና ያስገኘ ነው፡፡ ስለዚህም መለኮታዊ ክብር ስላለውና መለኮትም ስለኾነ የሰው ልጆች ሁሉ ሊያምኑት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ደግሞም አምላክ ስለኾነም ያለአንዳች ረዳት ሰዎችን ሁሉ ያውቅ፣ ሃሳባቸውም ምን እንደኾነ ያስተውል ነበር፤ “ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።” እንዲል (ዮሐ.2፥24-25)፡፡
     እርሱ ለሚያምኑትና እምነታቸውን በእርሱ ላይ ለሚያደርጉ ሁሉ አዳኝ (ሐዋ.4፥12)፣ ሕይወት (ሐዋ.14፥6)፣ አምላክ (ዮሐ.10፥30፤ ሐዋ.20፥28፤ 1ቆሮ.6፥11፤ ኤፌ.5፥20፤ 1ተሰ.3፥11፤ 2ተሰ.1፥11፤ ቲቶ.2፥11) እና ጌታም ነው (ሮሜ.10፥9፤ 13)፡፡ አምላክ ስለኾነም የእግዚአብሔር ባሕርያት ሁሉ አሉት፤ ዘላለማዊነት (ዮሐ.8፥58)፣ በሁሉ ቦታ በአንዴ መገኘት (ማቴ.18፥20)፣ ሁሉን አዋቂነት (ዮሐ.16፥30)፣ ሁሉን ቻይነት (ራእ.1፥8)፣ አይለወጥምም[አለመለወጥም የእርሱ ገንዘቡ ነው] (ዕብ.1፥12)፡፡ በሥራዎቹም ኹሉ የአምላክ ያሕዌን ሥራ ይሠራል፤ ኃጢአትን ይቅር ይላል (ማር.2፥1-12)፣ ሕይወትን ይሰጣል (ዮሐ.5፥21)፣ ሙታንን ያስነሣል (ዮሐ.6፥39፤ 54፤ 11፥38-44)፣ ፍርድንም ይፈጽማል፤ (ዮሐ.5፥22)።
    መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስን እግዚአብሔር እንደኾነ መናገሩ፣ እኛ መረዳት ከምንችለው በላይና ድንቅ ነው፤ ደግሞም አንድም ቦታ የክርስቶስን አምላክነት ሳይጠራጠር ፍጹም ይመሰክራል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ሲለብስ በሥጋ የተገለጠ እግዚአብሔር አምላክ (1ጢሞ.3፥16) ተባለ እንጂ፣ በሥጋ የተገለጠ ሥጋ ወይም ሰው ወይም ከጊዜ በኋላ አምላክ የኾነ አይደለም፤ እርሱ ለዘላለም የማይለወጥ የዘላለም አምላክ ነው፤ አምላክነትም የባሕርይን ገንዘቡ ነው፡፡ እኛ ግን የእርሱ የራሱ ገንዘቦች ወይም የእጁ ፍጥረቶች ነን!
    የክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት ራሱ እግዚአብሔር መኾን ነው፡፡ እኛ ግን ልጆች ብንባል ከእርሱ ክብር ከመወደዳችን የተነሣ ብቻ ነው፡፡ በእርሱ ባንወደድ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን (ኤፌ.2፥3)፣ እርሱ ባይኖረን እንኳንስ ልጆቹ ወገኖቹ የመኾን መብት የለንም፤ ይልቁን ከቁጣው በታች ወድቀን ነበር፤ (ዮሐ.3፥36)፣ በክርስቶስ መንፈስ ግን የእርሱ ወገኖች ኾንን፤ (ሮሜ.8፥8)፡፡ እርሱ አምላክ ነው፤ እኛን ሰዎች ሊያደርገን ብቻ ሰው ኾነ፤ እኛም ሰው መኾን ብቻ ይበቃናል፤ አሜን፡፡
     ይቀጥላል …

3 comments:

  1. ወንድሜ ዲ/አቤነዘር እንደምን ከርመሀል?እንካን ለሆሳህና አደረሰህ!! በእውነት ከድንግል የተወለደው እሱ እየሱስ ክርስቶስ ደግሞም እግዚአብሔር ውስጥህ ያለውንና ያ ከልጅነትህ ጀምሮ የነበረውን እውነት በደንብ እንድትረዳ መንፈስ ቅዱስ ስላገዘህ, ስለሁሉም እግዚአብሔር ይመስገን!!ለሳቱትም ወደእውነቱ አይምሮአቸውን እንዲያደርጉ አምላክ ይርዳቸው።

    ReplyDelete
  2. ወንድማችን እጅግ የሚያስመሰግን ሥራ ነው፡፡ በርታ እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልህ ይህ ትልቅ ትጋት የሚፈልግ መንፈሳዊ ሥራ ነው፡፡ አንተን በአካል፡ በአድራሻ፡ ማግኘት የምንችልበት መንገድ ብታመቻች ጥሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር የተዋህዶ አምላክ ይጠብቅህ፡፡

    ReplyDelete
  3. ተባረክ ወንድም

    ReplyDelete