Friday 23 February 2018

“ቤተ ክርስቲያንን ያመለጠ ዕድል

      Please raed in PDF
   ቤተ ክርስቲያኑን በማገልግል ረገድ አፄ ዘርአ ያዕቆብን የሚወዳደረው ንጉሥ በተጻፈው በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የለም፡፡ ለቤተ ክርስቲያኑ ከልቡ አሳቢ ከሆነ፥ ሲሆን ከደቂቀ ኤዎስጣቴዎስ ጋራ ያደረገውን ዕርቅ[1] ዓይነት ከደቂቀ እስጢፋኖስም ጋራ አድርጎ አብሮ ቢሠራ፥ አለዚያም እንዳላየ ቢያያቸው ኖሮ ምናልባት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ተአምር ይታይ ነበር፡፡ ንጉሡ ደቂቀ እስጢፋኖስን ሲቀጣቸው ክርስቲያኖችን የሚጠሉ ወገኖች አግኝተው እስጢፋኖስን ሲቀጣቸው ክርስቲያኖችን የሚጠሉ ወገኖች አግኝተው እንዲያሠቃዩዋቸው፥ በዚያውም ክርስትናቸው ረክሶ በሰማይም እንዲኰነኑ ቤተ ክርስቲያን ከሌለበት ክርስቲያን ካልሆኑ ሕዝቦች መካከል ወስደው እንዲጥሏቸው ያዝዛል፡፡ ብዙ ጊዜ የፈለገው ሆኖለታል፤ የሰማዩ ኵነኔ በነሱ ላይ መድረስ አለመድረሱን ባናውቅም፥ እስላሞቹ ደም በማስተፋት “ቁጣውን አስተንፍሰውለታል፡፡”

        አንዳንድ ጊዜ ግን እግዚአብሔር የተጋዙበትን ሀገር “እየከፈተላቸው” ብዙዎቹን በስብከታቸው እያሳመኑ ክርስቲያኖች እንዲያውም መነኮሳት አድርገዋቸዋል፡፡ ንጉሡ ያንን ሲሰማ የታየው የቤተ ክርስቲያኗ ማደግ ሳይሆን፥ ለሱ የማይሰግዱ ሰዎች ቍጥር እየበዛ መሄድ ነው፡፡ እዚህ ላይ ለምሳሌ የሚጠቀስ ጥሩ ማስረጃ በፈጸጋር የሆነው ነው፡፡ ሰገቢ የሚባለው የፈጸጋር አንዱ ክፍል የእስላም ሀገር ኖሯል፤ እዚያ የሚኖሩት ደቂቀ እስጢፋኖስ እንደንጉሡና እንደዋናው ገዢ እንደ ራስ ዓምዱ ክርስቲያኖች ስለሆኑ እስላሙ የሰገቢ ሹም በሚሠሩት እየተናደደ የንጉሡንና የሀገረ ገዢውን “ወገኖች” ሊያጠፋቸው አልደፈረም ነበር፡፡ ገድለ አበው ወአኀው እንደሚያስረዳው፥ አሁን እየያዘ እንዲያመጣቸው ታዘዘ፤ እንዲቀበላቸው ፈቃድ አገኘ፤
   (138)(ዘታኦስ) የሚባል መነኵሴ የሰርማት መምህር ስለቅዱሳኑ የውሸት ደብዳቤ ጽፎ ከንጉሡ ዘንድ አመጣ፡፡ ንጉሡ የደብዳቤውን ቃል ሰምቶ (139) ዓምዱ ለሚባለው ለፈጸጋር አገረ ገዢ በሀገሩ (በግዛቱ) ያሉትን ቅዱሳን (ደቂቀ እስጢፋኖስን) እንዲያመጣቸው ነገረው፡፡ እሱም እነሱ ዘንድ (በስራቸው) ያሉትን ቅዱሳን እንዲያመጧቸው ለሀገሩ ፫ ሹማምንት የንጉሡን ተላላኪዎች ላከባቸው፡፡ የንጉሡ ተላላኪዎች ከነዚያ ሹማምንት ጋራ በየሀገሩ ሄዱ፡፡ ዘታኦስ የሚባለው መነኵሴም አብሯቸው ነበረ፡፡ ሲዲ የሚሉት የሰገቢ ሹም የቅዱሳኑ ጠላት ስለሆነ (ተላላኪዎቹን ቅዱሳኑ ካሉበት) ወሰዳቸው፡፡ ቅዱሳኑ በስደት በሐገሩ ዱር ይኖሩ ነበር፤ እንኮይ፥ ናኬ፥ ኮሽም፥ ጣንጦ፥ ቀምጠሮ የሚባሉ የዛፍ ፍሬዎችና ከስራስርም ቀጠቤሉ፥ ኡስስ፥ ከዛፍ ቅጠልም ቀረሞ የሚባል፤ ከምድር አትክልትና ከእህልም ሲያገኙ ይበሉ ነበረ፡፡ ከሰው ዘንድ ሲደርሱም ወንዱንም ሴቱንም ያስተምሩ ነበረ፡፡ ሲያዳምጧቸው ሕሊናቸው ይመሰጥ ነበረ፡፡ ከዓለማቸው እየወጡም ከነሱ ጋራ ስለተደባለቁ (ቅዱሳኑ) ብዙዎች ሆኑ፡፡ (እስላሙ) ሲዲ የሚባለው የዚያ ሀገር ሹም ቁጣ በዚህ ምክንያት ነበረ፡፡ እነዚያን የንጉሥ ተላላኪዎች ምክንያት አግኝቶ በውሾችና (139) በሰዎች አደናቸው፤ ከዱር ሰበሰባቸውና በማነቆ እንደታሰሩ ከንጉሡ አደባባይ አመጧቸው፡፡”

(ጌታቸው ኀይሌ፤ ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ “በሕግ አምላክ”፤ ካልጅቪል (ሚኒሶታ) 1996ዓ.ም፤ ገጽ.35-36)




[1]  ደቂቀ ኤዎስጣቴዎስ ቅዳሜ እንደእሑድ ካልተከበረች ብለው ከኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን ተገንጥለው ነበረ፤ ንጉሡ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ዕርቅ አወረደ፤ Taddesse Tamrat, Church and State in Ethiopia, pp.229-231

1 comment: