Thursday 1 February 2018

“ኢትየጲያ እጆቿን ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች”፤ መቼ?

    Please read in PDF
ይህ ቃል ለዘመናት በኹሉም አብያተ ክርስቲያናት ለማለት በሚያስደፍር መልኩ፣ በተደጋጋሚነት ሲጠቀስ የነበረ ነው፡፡ ቃሉ በአብዛኛው ሲጠቀስና አገልግሎት ላይ ሲውል ያየነው በአዎንታዊና በበጐ ገጽታው እንጂ በተጠቀሰበት ዓውድ ልክ እንደሚገባው ኾኖ አይደለም፡፡ “ኢትዮጲያ እጆቿን ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለውን ቃል ሰዎች ሲጠቀሙ ያየኹት፣ “ዘርግታለች ወይም ለእግዚአብሔር ተማርካለች” የሚለውን ቃል በማስገባት ነው፡፡
    ይህን ቅዱስ ቃል የተናገረው ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ነው፤ የሚገኝበትም ክፍል በመዝ.68፥31 ላይ ነው፡፡ ምዕራፉን ጠቅላላ ርእስ እንስጠው ብንል፣ “እግዚአብሔር የድኾች አባት ነው” ወይም “የድል መዝመር” ብለን ልንሰይመው እንችላለን፡፡ በዚህ የመዝሙር ክፍል ውስጥ ብዙ ነገሮች ተካትተዋል፡፡ እግዚአብሔር ተዋጊ ኾኖ ልክ እንደቀድሞ(ዘጸ.15፥3)እንዲመጣ (ከቁ.1-3)፣ ከ4-6 ደግሞ ማኅበሩ ለእግዚአብሔር በቀል የምሥጋና በዓልን እንዲያደርግ ሲጋበዝ፣ ተዋጊው እግዚአብሔር ባደረገው ነገር ላይ የተሰጠ ሰፊ ማብራሪያ (ከቁ.7-18)፣ ስለብድራቱ የቀረበ ውዳሴ (ቁ.19-20)፣ በውጊያው ውስጥ እግዚአብሔር ምን ዓይነት ፍርድ እንደሚያደርግ (ቁ.21-23)፣ ይህ ታላቅና ተዋጊው እግዚአብሔር ጦረኛ ኾኖ መገለጡን፣ “እግዚአብሔርን በጉባኤ፥ ጌታችንንም በእስራኤል ምንጭ” ማኅበሩ እንዲያመሰግኑት መጋበዙ (ቁ.24-31)፣ “አቤቱ፥ ኃይልህን እዘዝ፤ አቤቱ፥ ይህንም ለእኛ የሠራኸውን አጽናው” በማለት ማኅበሩ መጸለዩን፤ (ቁ.28-31) ያካትታል፡፡


    እንደርእስ ያነሣነው ቃል የሚገኘው የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ኃይሉን እንዲያዝና ብርታቱን እንዲገልጥ በተናገረበት ክፍል ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት እግዚአብሔር ሕዝቡን ሊያድን ታላቅ ግርማውንና ተዋጊነቱን ገልጧል፡፡ እስራኤልን ከፈርዖን የባርነት ቀንበር ሊታደገው ሙሴን ባስነሣ ጊዜ፣ “ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ” አለው፤ (ዘጸ.9፥16)፣ ደግሞም “አቤቱ፥ ሥራችንን ሁሉ ሠርተህልናልና ሰላምን ትሰጠናለህ” የተባለለት እግዚአብሔር ብቻ ነው፣ (ኢሳ.26፥12)፣ ለዚህም ነው እስራኤል እንዲህ የተባለችው፤ “ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ፡፡ እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤” (ኢሳ.60፥1-2) … ተዋጊያቸው እግዚአብሔር የክብራቸው ነጸብራቅ ነው፡፡ ይህ ተዋጊ ብርቱ ክንድ የሕዝቡ መዳን እስኪፈጸም ድረስ የሚቀጥል መኾኑንም፣ “አምላካችንስ የደኅንነት አምላክ ነው፤ ከሞት መውጣትም ከእግዚአብሔር ነው።” በማለት በደስታ ይናገራል፡፡
     ስለዚህም እግዚአብሔር ዘወትር የሚያስጨንቁ ጠላቶችን ድል ማድረጉን፣ በመናገር ጸሎትን በትጋት ያቀርባል፡፡ “ብርቱ ክንድህን አንሣ” በማለት፡፡ ተዋጊው እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደሱ ታላቅና አስፈሪውን ግርማውን አስፍኗል፡፡ ስለዚህም “በኢየሩሳሌም ስላለው መቅደስህ ነገሥታት እጅ መንሻን ለአንተ ያመጣሉ” እንደተባለ፣ ድል የተነሡት “ሰልፍን የሚወድዱ አሕዛብ” በንጉሣቸው እየተመሩ የእጅ መንሻን ያመጣሉ፤ (መዝ.76፥11)፡፡
     አሕዛብ ለእግዚአብሔር ባለመገዛታቸው ምክንያት እግዚአብሔር እንዲመታቸው መዝሙረኛው ጸሎትን ይጸልያል፡፡ እኒህ አሕዛብና መሪዎቻቸው የተመሰሉበት፣ “በሸምበቆ ውስጥ እንዳሉ አራዊት” እና “በበሬዎችና በወይፈኖች ጉባኤ ወይም መንጋ” ነው፤ ይህም እኒህ ሕዝቦች እጅግ ጨቋኞችና ኹከተኞች መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ እንዲኹም እንደኮርማ ኹከትን፣ ሌላውን መጨቆንና ማፈን፤ ደግሞም መውጋትን የሚወድዱ[ጦር አውርድ ባዮች ወይም ደምን ተጠሚዎች] መኾናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
     እኒህ ሕዝቦች በእግዚአብሔር ፊት ያልተወደዱ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ኹለንተናቸውን ለዓመጽና ላለመታዘዝ በማስገዛት ተገኝተዋልና፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ጦርነትንና መማለጃን ወይም እጅ መንሻን የሚወድዱትን ሕዝቦች እንደመታ፤ እንደበታተነ እንዲኹ በዚህ ብልሹ ምግባር ውስጥ ያሉ ሕዝቦችም በተመሳሳይ መንገድ ሊቀጡ እንዳላቸው ይናገራል፡፡
    በተለይ በዚህ አስከፊ ምግባር ተባብረውና እንደሌሎቹ ሊቀጡ እንዳላቸው ስማቸው ተጠቅሶ የምናገኛቸው በጊዜው ኃያላን የነበሩት ግብጽና ኢትዮጲያ[ኢትዮጲያዊ መልክ ጥቁር፣ በበረሃ ዋዕይ የበለዘ መልክን የሚያመለክት ነው፡፡[1]] ናቸው፡፡ እኒህ ሕዝቦች የጦር ቃል ኪዳንን በማድረግ ጦር ወዳድነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ስለዚህም በተዋጊውና ለሕዝቡ በሚቀናው በእስራኤል ቅዱስ ድል ተነሥተው ይሸነፋሉ፤ እጃቸውንም በመዘርጋት ለእግዚአብሔር ይገዛሉ፡፡
     ሊቀ ጳጳስ ጎርጎርዮስ ይህን ክፍል ጠቅሰው በተናገሩበት መጽሐፋቸው እንዲህ ብለው ጠቅሰውታል፣ “በዜና መዋዕል ካልዕ[፪ዜና መዋ.፲፬-፱፤፲፭፤ ፲፮-፰] እንደተተረከው ኢትዮጲያውያን ዜራህ(ዝሪ) በሚባለው ንጉሣቸው እየተመሩ ዘምተው ምድረ ይሁዳን ከያዙ በኋላ በንጉሥ አሳ ድል ሁነዋል፡፡ ኢትዮጲያውያን፤ በኃይላቸው ተመክተው በሚሠሩት ሥራ ነቢያት ይገስጿቸው ነበር፤ [ሶፎ. ፪-፲፪] በእግዚአብሔርና በኢትዮጲያ መካከል ያለውን የማያቋርጥ ፍቅርና ግንኙነት ሲገልጡ ደግሞ፦ “ኢትዮጲያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ታደርሳለች” እያሉ በግልጽ ተናግረዋል፡፡”[2] በማለት ሦስት የሚጎረብጡ ሃሳቦችን ያቀርባሉ፤ አንደኛው ኢትዮጲያውያን በሃይላቸው የሚመኩ መኾናቸውን፣ ኹለተኛ ደግሞ በዚህም የነቢያት ተግሳጽ ያገኛቸው መኾናቸውን ይጠቅሱና፣ መልሰው ደግሞ እግዚአብሔርና ኢትዮጲያ የማያቋርጥ ፍቅርና ግንኙነት ያላቸው መኾኑን አመልክተው ለግንኙነታቸው ማስረጃን ለርእስ የተጠቀምነውን ጥቅስ ተጠቅመዋል፡፡
     እንግዲህ ቃሉ ላልተጠቀሰለት ነገር ማዋል ማለት ይህ ነው፡፡ “ኢትዮጲያ እጆቿን ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለው ቃል እግዚአብሔርና ኢትዮጲያ የማያቋርጥ ፍቅርና ግንኙነት ያላቸው መኾኑን ፈጽሞ አያመለክትም፡፡ ይልቁን ከዓውዱ እንደምንረዳው የግብጽ መኳንንት መምጣትና የኢትዮጲያ እጅ በመዘርጋት[በመሸነፍ] ለእግዚአብሔር መገዛትና በእግዚአብሔር ተዋጊነትና ድል ነሺነት ገና ወደፊት ልትገዛ ያለች መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡
    ኢትዮጲያ አኹን ያለችበት ኹኔታ ከምንም በላይ መሪዎቿና ሕዝቦቿ በአንድነት ኾነው እጃቸውን ለእግዚአብሔር መዘርጋት ያለባቸው ጊዜ ነው፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰውነት ተክዶ ብሔርተኝነት በመካከላችን ገንኗል፤ “የትላንቱ አንድነታችን” መቀነቱ ላልቷል፣ በኹሉም ልብ ጥላቻና ዘረኝነት እንደሙጫ ተጣብቋል፤ ድሃውና ባለጠጋው መካከል ያለው ልዩነት ላይነካካ ምዕራብና ምሥራቅ ኾኗል፤ የመሪዎቹ ሴሰኝነት የአደባባይ ገመናና እፍረታችን ኾኗል፤ ያለጉቦና መማለጃ የሚሠራ ማግኘት አጥማቅያን፣ ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ መጋብያን በበዙባት ምድር … በቤተ ክህነትም በቤተ መንግሥትም መናኛ ኾኖብናል፣ ፍትሕ ድል ነሥቶ አልወጣ ብሏል፤ ድኻው ያለቅሳል፣ የከተሞች ጐዳና በሕጻናትና በአረጋውያን ተመልቷል …
    ኢትዮጲያችንን መውደዳችንን የምንገልጠው ያልተነገረላትን ቃል እንደተነገረላት አድርጐ በማቅረብ አይደለም፡፡ ባልታዘዝንለትና ባልተገዛንለት እውነት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሲዘልፈን፣ ሲገስጸን ፈጥነን ንስሐ በመግባት መመለስ ሲገባን ለመልካም እንደተነገረልን ቆጥረን መመካት ፈሪሳዊነት ብቻ ነው የሚኾንብን፡፡ ምክንያቱም ካይደለን አይደለንምና፡፡ ያውም አይደላችኹም፤ አልተገዛችኹም፤ አልታዘዛችኹም፤ እጃህኹን አልዘረጋችኹም ያለን ቅዱስ ቃሉ ነው፤ ስለዚህም ቃሉ እኛን ያለን ነን እንጂ፣ እኛ ራሳችንን ያልነውን አይደለንም፡፡ ይህን ለመቀበል ከተቸገርን ከቅዱስ ቃሉ ይልቅ ራሳችንን ቅዱሳን ለማድረግ እየጣርን ነውና እጅግ ታላቅ ዓመጽና ድፍረት ነው፡፡ 
   ከእጅ ወደአፍ በኾነው በዚህ ኑሮ ነጋድያን ለሕዝባቸው[ለገዛ ወንድሞቻቸው] የማይራሩ ኾነዋል፣ ለምእመናንና ምእመናት የማይራሩ ጨካኝ ተኩላ አገልጋዮች ከፊት ይልቅ ገንነዋል፣ ክፋት ሥር ሰድዷል፣ ዓመጽ ናኝቷል፣ በደል አብቧል፣ ኀጢአት ጐምርቷል፣ አለመከባበራችን ደምቆ ታይቷል፣ አለመቀባበላችን ጮኾ ይሰማል … ለዚኽ ኹሉ ግን በልባችን ተመክተን ተቀመጥን እንጂ ለንስሐ ራሳችንን አላዘጋጀንም፣ አንገታችንን አልሰበርንም፣ ልባችንን አላዋረድንም፡፡ አዎን! የልብ ትምክህት ከእኛ ይራቅ፤ እጃችን የሚዘረጋበት ቀን ዛሬና አኹን ይኹን! ፊታችንን ለኀጢአታችን ወደሞተልንና ሊያጸድቀንም ወደተነሣው ጌታችን ኢየሱስ በእምነት ዘወር እናድርግ፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ይርዳን፤ አሜን፡፡




   [1] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ [ገጽ.163] እንዲሁም ስለኢትዮጲያ መልክዐ ምድር 1990 ዓ.ም ለ2ኛ ጊዜ በታተመ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና “የዛሬዋ ኢትዮጲያ የቅዱሳት መጻሕፍት፤ የታሪክና የሥነ ጥንት ኢትዮጲያ ናት” ተብሎ በተሰየመው “መጽሐፍ”፣ የብዙ ታሪክ ጸሐፊዎችን ማስረጃነት በመጥቀስ የደረሱበት መደምደሚያ፣ “እንግዲህ ከነዚህ ምንጮችና መረጃዎች ላይ በመነሣት ከታሪክና ከመልክዐ ምድር አንጻር ኢትዮጲያ የሚለውን ስም የያዘው አካባቢ ከግብጽ ደቡብ ጀምሮ ያለው የጠይም ሕዝቦች አካባቢ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡” (ገጽ.18) ይላል፡፡
     ነገር ግን ኹሉም የጠቀሷቸው ማስረጃዎችን ብንመለከት ከደረሱበት መደምደሚያ ጋር ይቃረናል ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ለምሳሌነትም ከጠቀሷቸው ማስረጃዎች ሦስት ማስረጃዎችን ብንጠቅስ ይህን እውነታ ለመረዳት ያስችለናል፤ (1) “ … ሄሮዶቶስ … በግብጽ ብዙ ጊዜ የቆየና ከአከባቢው ዐዋቂዎች ጋር በመወያየት ስለኢትዮጲያ ብዙ ነገሮችን ለመረዳት ችሎ የነበረ በመሆኑ በዚህም በአገኘው ማስረጃ መሠረት የኢትዮጲያ ወሰን ከግብጽ ደቡብ ጀምሮ እስከ ሲናሞሞፎሩስ(ሕንድ ውቅያኖስ መዳረሻ) ድረስ እንደነበረ፥ ከዚህም ጋር ኢትዮጲያ ሁለት ክፍሎችን የያዘች አካባቢ መሆኗን ሲያመለክት …” (ገጽ.14)፣ (2)ሮማዊው የመልክዐ ምድር ሊቅ ፕሊኒ ኢትዮጲያ በሰሜን ከሴዩን(አስዋን) በምሥራቅ ከውቅያኖስና በምዕራብ ከሊብያ ጋር እንደምትዋሰን ሲገልጽ በደቡብ በኩል ግን ያላትን ወሰን ለማወቅ እንደአልቻለ ሲያመለክት … ወደደቡብ በሚያመለክተው አቅጣጫ … ከመርዌ ጀምሮ እስከውቅያኖስ ድረስ በባሕርና በየብስ ያለውን ርቀት ጉዞ አመልክቷል፡፡” (ገጽ.15-16) ሲል፣ (3)የኢትዮጲያን ወሰኖች በሁሉም አቅጣጫ በደንብ ለማመልከት የቻለው የመልክዐ ምድር ሊቅ የነበረው ፕቶሎሚዎስ ክላውዲዮስ ነበር፤ በዚህም መሠረት ከግብጽ ቀጥሎ(ከታች) የምትገኘው ኢትዮጲያ በሰሜን ከግብጽና ሊቢያ፥ በምዕራብ ከሊቢያ ውስጣዊ ማዕዘን እንደምትዋሰን አመልክቷል፤” (ገጽ.16) በማለት ይጠቅሳል፡፡
    እንግዲህ የሦስቱንም መረጃዎች ብንጠቅስ ኹሉም ለየቅል መኾናቸውን እናስተውላለን፤ ሄሮዶቶስ ሰሜኑን የሕንድ ውቅያኖስ፣ ፕሊኒ ደግሞ አስዋን እንደኾነና ፕቶሎሚዎስ ከላውዲዎስም ሰሜኑ ግብጽና ሊቢያ ነው ይለናል፡፡ ሄሮዶቶስ ደቡቡን ግብጽ ያዋስናል ሲል፣ ፕሊኒን ደግሞ አያውቀውም ከተባለ በኋላ፣ “… ወደደቡብ በሚያመለክተው አቅጣጫ … ከመርዌ ጀምሮ እስከውቅያኖስ ድረስ በባሕርና በየብስ ያለውን ርቀት ጉዞ አመለክቷል” በማለት ይገልጣል፤ ምዕራቡን በተመለከተም ፕሊኒ ሊብያ እንደኾነ ሲናገር ፕቶሎሚዎስ ደግሞ የሊብያ ውስጣዊ ማዕዘን ያዋስናል በማለት ተናግረዋል፡፡ እንግዲህ እንዲህ እርስ በእርሱ እንዲህ የተሳከረውን ነገር ጠቅሶ፣ መልሶ ደግሞ ኢትዮጲያ የምትባለው ይህችው አገር ናት ማለት ፈጽሞ ሚዛን ሊደፋ የሚችል አይደለም፡፡
     “ኢትዮጲያም ማለት ከኵሽሞት በኋላ በ፪ ሺህ ካ፬፻፶ ዓመት በበጥሊሞስ ዘመን የወጣ ሐዲስ እንግዳ ጽርአዊና ደኃራዊ ስም ነው፡፡ ፸ ሊቃናት ብሉያትን ከዕብራኒ ወደ ዮናኒ ሲመልሱ ዕብራይስጡ ኵሽ የሚለውን የኵሽን ስም ኹሉ ኢትዮፕስ ስላሉት በዚህ ምክንያት ከግብጽ ወዲህ ያለው የኵሽ አገር ኹሉ ኢትዮጲያ ተብሏል፡፡ የግእዝም ብሉይ ከጽርእ ስለ ተቀዳ እንደጽርኡ ኢትዮጲያ ይላል እንጂ እንደዕብራይስጡ ኵሽ አይልም፤ ትርጓሜውም ጥቁር ጠቋራ ማለት ነው፡፡ (ዘፍ.፪፥፲፫፡፡ ኤር. ፲፫፥፳፫)” (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፤ 1948 ዓ.ም፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ.13)፡፡ ስለዚህ ኢትዮጲያ ይህችው ምድር ብቻ ናት ብለን መመካትም አይገባንም፡፡ ነገ አንዱ መጥቶ ኤርትራችን የኢትዮጲያ አካል አይደለችም ላለማለቱ ምን ዋስትና አለን? እናም የዛሬው መከፋፋታችን ከመለያየት፣ ከመበላላት፣ ከመጠፋፋት፣ ከመወጋጋት … ፈጽሞ ሊታደገን አይችልም፡፡ እባካችኹ በመንፈስ አንድ ለመኾን በንስሐ እንመለስ!!!
    [2] አቡነ ጎርጎርዮስ(ሊቀ ጳጳስ)፤ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ 1986 ዓ.ም 2ኛ እትም፤ አዲስ አበባ፤ አሣታሚ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ.14

5 comments:

  1. Geta yasben betaam ychenkal.tsega yibzalh wendmachn

    ReplyDelete
  2. Geta yasben betaam ychenkal.tsega yibzalh wendmachn

    ReplyDelete
  3. kalhyiete Yasemane

    ReplyDelete
  4. እንግዲህ ቃሉ ላልተጠቀሰለት ነገር ማዋል ማለት ይህ ነው፡፡ “ኢትዮጲያ እጆቿን ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለው ቃል እግዚአብሔርና ኢትዮጲያ የማያቋርጥ ፍቅርና ግንኙነት ያላቸው መኾኑን ፈጽሞ አያመለክትም፡፡ ይልቁን ከዓውዱ እንደምንረዳው የግብጽ መኳንንት መምጣትና የኢትዮጲያ እጅ በመዘርጋት[በመሸነፍ] ለእግዚአብሔር መገዛትና በእግዚአብሔር ተዋጊነትና ድል ነሺነት ገና ወደፊት ልትገዛ ያለች መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ mn malet new algebanyim? gena wedefit new malet new?

    ReplyDelete