Monday 15 January 2018

የብልጽግና ወንጌል፣ ከጌታችን ኢየሱስ ያልኾነ ልዩና እንግዳ ወንጌል - ክፍል ፰


·        1ቆሮ.316፦ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?” በሚለው ቅዱስ ቃል ውስጥ፣ የእምነት እንቅስቃሴ መምህራን “ቤተ መቅደስ” የሚለውን በመውሰድ፣ የሥጋን አገልግሎት የማደርያነት ብቻ እንጂ ዘላለማዊ ወይም ከሰውነት ኹለንተና አንዱ አለመኾኑን ለመሞገት ያቀርቡታል፡፡
    ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ክፍል እየተናገረ ያለው፣ ስለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ማለትም በጥቅሉ ስለጉባኤው የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ስለመኾናቸው ነው፡፡ ከክፍሉ ዓውድ እንደምንረዳው እየተናገረ ያለው አንድን ሰው ሳይኾን በጠቅላላ ተደራስያን የኾኑትን የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን አማኞች ነውና፡፡ ክፍሉን እንደምናስተውለው፣ ከሰው የሥጋ ሰውነት ጋር በመያያዝ የተነገረ አይደለም፡፡

    ቁ.17 ላይ፣ “ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ” በሚለው ንባብ ውስጥ፣ “ያውም እናንተ ናችሁ” ሲል፣ አማኞችን ኹሉ ከማካተቱ ባሻገር፣ ቤተ መቅደሱን የሚያፈርሱት ከንቱና ታካች ሠራተኞች ከእውነተኛ አገልጋዮች አንጻር እጅግ ከባድ ማስጠንቀቂያን እየሰጣቸው መኾኑን ያሳያል፡፡ ቃሉ በምዕ.1፥11 ላይ ቤተ ክርስቲያን በግልጥ በቅናትና በክርክር ተከፋፍላ ነበርና፤ ከዚያ ጋር በማያያዝ የእነርሱን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስነት “በጩኸት ቃል” ያስታውሳቸዋል፡፡ ለመከፋፈልም ኾነ አንዱ ሌላውን ሊያፈርሰው አለመጠራታቸውን አጽንዖት በመስጠት፡፡
     ቅዱስ ጳውሎስ በተመሳሳይ መልኩ፣ “እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል፦ በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።” (2ቆሮ.6፥16) ሲል፣ “እኛ” በማለቱ ሐዋርያው ራሱንም በማካተት ቆሮንቶሳውያንን ኹሉ መናገሩን እናስተውላለን፡፡ ምናልባት ቤተ መቅደስ የሚለውን በግልም ቢናገርም እንኳ (1ቆሮ.6፥19)፣ ለእግዚአብሔር እንደሚገባና እንደክቡር ሰውነት እንጂ ሥጋን ምንም እንደማይጠቅም በማሰብ ያነሣበት አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ቅዱስ ጴጥሮስም የሥጋን ማደርያነት[ድንኳንነት] በመልእክቱ ጽፏል፤ (2ጴጥ.113-15)፡፡ ያለርኩሰት፣ በፍጹም ቅድስናም ለእግዚአብሔር መቅረብ እንዳለበትም ጭምር፡፡
·        ሐ.10፥34፦ ሌላው የእምነት እንቅስቃሴ መምህራን ለዚህ ትምህርታቸው በተመሳሳይ መንገድ የሚጠቅሱት ጥቅሳቸው ነው፡፡ ቃሉ ግን እነርሱ እንደሚሉት የማይል መኾኑን እንዲኽ እንመለከተዋለን፡፡
     የእግዚአብሔር ቃል በቀጥታ ሰዎች አማልክት መኾናቸውን አይናገረንም፡፡ በምንም ዓይነት መንገድም ክርስቲያኖች ራሳቸውን አማልክት አድርገው እንዲቆጥሩ የሚያስተምር ክፍል የለም፡፡ በግልጥ የእግዚአብሔር ቃል፣ “ ... ነገር ግን ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ ብታደርግም አንተ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም፤” (ሕዝ.28፥2)፣ በሌላ ሥፍራ ስለግብጻውያን ሲናገርም፣ “ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፥ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤” (ኢሳ.31፥3) ተብሎ ተነግሯል፡፡ ራሳቸውን እንደአማልክት የሚቆጥሩ ኹሉ ከእውነተኛው እግዚአብሔር ፍርድ በታች ናቸው፤ (ኤር.10፥11)፡፡
     ወደቃሉ ዓውድ ስንመጣ፣ ቃሉን ከመዝ.82፥6 ላይ በመጥቀስ የተናገረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ራሱን ከአብ ጋር አስተካክሎ፣ እግዚአብሔር ነኝ ማለቱን አይሁድ ተረድተዋል፤ ይህ ደግሞ ለየትኛውም አይሁድ ያህዌን እንደመሳደብ ይቆጠራል፤ (ማር.14፥64 ፤ ዮሐ.5፥18፤ 8፥59)፡፡ እናም አይሁድ ጌታችንን ሊወግሩት ድንጋይን አነሡ፡፡ ጌታችን ፈጽሞ ከፊታቸው አልሸሸም፡፡ ይልቁን፣ “ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ?” በማለት ሞገታቸው፣ እነርሱም፣ “ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ፤” አሉት፡፡ ጌታችን የዚህን ጊዜ ነው እንደልማዱ ከቅዱሳት መጻሕፍት በመጥቀስ፣ “እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፦ ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?” ብሎ ተናገራቸው፡፡
   አይሁድ ሁለት ነገር ስላላስተዋሉ ሳቱ፣ ጌታችን ኢየሱስ ስለራሱ የተናገረው ሁሉ ትክክልና እውነት መኾኑን አላስተዋሉም፤ ደግሞም ጠቅሶ እንደተናገረው፣ በብሉይ ኪዳን ሰው ኾነው ሳለ ሰዎች፣ “አማልክት”[1] ተብለው ከተጠሩ፤ እኔ ራሴን የእግዚአብሔር ልጅ እንደኾንሁ ብናገር ምን ይደንቃል? በማለት በጥያቄ መለሰላቸው እንጂ፣ ሰዎች ወይም ጌታችን ኢየሱስን የሚከተሉና የሚያምኑ ሁሉ አማልክት ናቸው የሚል ሃሳብን ፈጽሞ አልያዘም፡፡
    ሰዎችና እግዚአብሔር የተለያዩ መኾናቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ ይመሠክራሉ፡፡ “ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም” (ዘኊል.23፥19)፣ “እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፥” (ሆሴ.11፥9)፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል” (ማቴ.19፥26) ሲል፣ የእግዚአብሔርን ኹሉን ቻይነትና የሰውን እጅግ ውሱንነት በሚገባ ይገልጥልናል፤ (ሐዋ.12፥22፤ 1ቆሮ.14፥2) በእኒህና በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሰውና እግዚአብሔር አንድ አለመኾናቸውን በትክክል እንገነዘባለን፡፡
    በመዝ.82 ላይ “እኔ ግን፦ አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤” በማለት የተናገረው አሳፍ እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ ይህንንም “ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ፥ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ አልሁ።” በማለት የተናገረው ራሱ አሳፍ ነው፡፡ በሰው ዘንድ እንደአማልክት ወይም ገዢዎች ቢታዩም ነገር ግን እንደሰው ሟቾች ወይም ውዳቂዎች መኾናቸውን መናገሩ ነው፡፡ ቃሉ የተነገረውም በምሳሌ መልክ እንጂ እነርሱ አምላክ መኾናቸውን በሚያመለክት ኹኔታ አይደለም፡፡ ሰዎችን ሰዎች እንጂ እግዚአብሔር አማልክት አላላቸውምና፡፡ እንዲያውም ራስን ከአማልክት እንደአንዱ ማቅረብ ወይም አምላክ ነኝ ብሎ ማቅረብ የጥፋት ልጅ የተባለው ሐሰተኛው ክርስቶስ ከሚፈጽማቸው ኀጢአቶች ዋናውና ትልቁ ነው፤ (2ተሰ.2፥4፤ 11)፡፡
    የእምነት እንቅስቃሴ መምህራን እኒህንና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለራሳቸው ሃሳብ እንዲመች አድርገው በማቅረብ “ሰው መንፈስ ነው” የሚለውን የሐሰት ትምህርታቸውን ያስተምራሉ፤ ነገር ግን ከላይ እንደተመለከትነው ጥቅሶቹ ኹሉ ትምህርቶቻቸውን አይደግፉም፡፡ ሌሎች የሚጠቅሷቸውም ጥቅሶች አሏቸው፤ ነገር ግን ዘወትር መዘናጋት የሌለብን ነገር የሚጠቅሷቸውን ጥቅሶች ኹሉ በዓውዳቸው ልናጠናቸውና ሃሳባቸውን ልናፈርሰው ይገባናል፡፡ 
ስለሰው ነገር ማጠቃለያ
    አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላቸው “ሰው” የሚለውን ቃል ሲተረጕሙ፦ “ሰብእ(ዕብ.ሽባእ)፦ ባሕርያዊ ስም፤ በቁሙ ሰው አዳም የአዳም ዘር ኹሉ ነፍስና ሥጋ ያለው ከነፍስ ከሥጋ አንድ የኾነ በነፍስ አካልነት የቆመ የተፈጸመ ሥጋ ብቻ ወይም ነፍስ ብቻ ያይደለ፡፡”[2] በማለት በግልጥ ያብራራሉ፡፡ ስለዚህም ሰውን ከዚህ በተለየ ለማየት ወይም ለመተርጐም የሚያስችለን አንዳች መንገድ አናገኝም፡፡ ሰውንም ነፍስና ሥጋ ብሎ ኹለንተናውን ከፍሎ ማየት በራሱ አደጋ አለው፤ እንዲኽ ላለ ኑፋቄያዊ ትምህርት ይዳርጋል፡፡
   ደግሞም ሰው በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረው በኹለንተናው እንጂ ሥጋ ወይም ነፍስ ብቻ ሆኖ አይደለም፡፡[3] በዘፍጥ.1 ላይ የተጻፈው ጠቅላላው የሰው አፈጣጠር ሲኾን፣ በዘፍጥ.2 ላይ ግን ከሌሎች ፍጥረታት በሚለይና ልዩ በሆነ ክብር የሰው አፈጣጠር “እንዴት ተፈጠረ?” የሚለውን “ሙሉ መልስ” ለመመለስ በዝርዝር የቀረበ ነው፡፡ የእምነት እንቅስቃሴ መምህራን በትምህርታቸው እኒህን ሁለቱን ድንበሮች መለየት ተስኗቸው ፍጹም ሲሳሳቱ አይተናል፡፡ ቃሉንም እንደምናጠናው የሰው ሥጋ የተካደበትን የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍል ፈጽሞ አናገኝም፡፡
   ለሰው ልጅ ኹልጊዜ፣ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” (ዘፍ.1፥31) ብሎ የተናገረውን አምላካዊ ቃል ችላ በማለት፣ የሰው-ነት[ቊሳዊ የመኾን] ሕልውናን በማናናቅና በማንኳሰስ፣ ነፍሳዊነትን በጣም የተሻለና የሚበልጥ አድርጐ ከሚያቀርብ የተሳሳተ አካሄድ እጅግ በጣም መጠንቀቅ መንፈሳዊ ማስተዋል ነው፡፡ ሰው ልዩና ክቡር ፍጥረት ቢኾንም አምላክ ወይም ትንሽ አምላክ አይደለም፤ እንዲያውም ስለእግዚአብሔር ብዙ እየተረዳን በሄድን ቁጥር ታናሽነታችንን ይበልጥ እየተረዳን አምልኮ እናቀርባለን እንጂ በምንም ዓይነት መንገድ አንታበይም፤ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን አናስብም፡፡
     የበዛው የቅዱሳት መጻሕፍትም ማብራሪያ፣ ሰው “የእግዚአብሔር መልክና አምሳል ነው” የሚለውን ትርጉም ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ተመሳሳይነት[አምሳያነት] እንጂ ፍጹም አንድነት[አንድ ዓይነትነት] የሚያጸባርቅ አለመኾኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ እናም ሰው የእግዚአብሔር ፍጡር ነው፤ የመልኩና የአምሳሉ ነጸብራቅ ነው፤ ይህ ሰው የፊተኛውን “እግዚአብሔራዊ” መልክና አምሳሉን በኃጢአት ሲያበላሽ፣ እግዚአብሔር ዳግመኛ ሰውን በክርስቶስ ኢየሱስ በሥጋ ሞቱና ትንሣኤው በመልኩ ፈጥሮ አዲስ ፍጥረት አድርጎታል፤ (ኤፌ.2፥10፤ 4፥24፤ ቈላ.3፥10)፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ባለማስተዋል እንድንጸና ጸጋውን ያብዛልን፤ ደግሞም ለቅዱስ ቃሉ ክብር እንድንተጋ ስለረዳን ክብር ይኹንለት፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …




     [1] ቄስ ኮሊን፦ “አማልክትን፣ “የእግዚአብሔር ስሞችና የባሕርዩ መገለጫዎች” በሚለው ርእስ ሥር ስለእግዚአብሔር ስሞች በተናገሩበት አንቀጽ ሲናገሩ፣ “ … በመጽሐፍ ቅዱስ ኤሎሂም ጣዖታትን (ዘጸ.18፥11 ፤ መዝ.95፥3፤ 96፥5)፣ መላእክትን (መዝ.8፥5) እና ሰዎችን ሊያመለክት ይችላል፤ (ዘጸ.7፥1፤ 21፥6፤ 22፥8፤ መዝ.82፥1-6፤ ዮሐ.10፥34-35)፡፡ ኤልና ኤሎሂም እንደዐውዱ በአምላክ ወይም በአማልክት ሊተረጎሙ ይችላሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ትክክለኛ ትርጉም የሚሆነው እግዚአብሔርን የሚያመለክት ነው፡፡” (ቄስ ኮሊን ማንሰል፤ ትምህርተ እግዚአብሔር፤ 1995 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡ ገጽ.174)
    [2] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፤ 1948 ዓ.ም፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ.843
    [3] ከዚህ ቀደም የሰው ከእግዚአብሔር መመሳሰያ መንገዱን የአበውን ትምህርት አንስተን በጥቂቱ መናገራችንን ይታወሳል፡፡ አኹንም በድጋሚ ማንሳት ግድ ሳይኾንብን አልቀረም፡፡ መልክና አምሳል ሰዎች ከእግዚአብሔር ስለወረሷቸው ጠባያት እንጂ ራሱን እግዚአብሔርን ስለመኾናቸው ያወሱት እንድም ታሪካዊ ሰነድ በማስረጃነት ማቅረብ አይቻልም፡፡ ቄስ ኮሊን በተደጋጋሚ፣ “ሰው በእግዚአብሔር መልክ ተፈጠረ፣ የሰውም ሥጋ (አካል) የነፍሱን ሁኔታ ይገልጣል፤ ሰው ሕያው ነፍስ ነውና፡፡ የሰው ሥጋና ነፍስ በአንድነት መታየት አለባቸው፤ ስለዚህ ለሥጋው ዝቅተኛ ደረጃ ሊሰጠው አይገባም፤ ክብሩ ከፍ ያለ ነውና፡፡ …” (ቄስ ኮሊን ማንሰል፤ ትምህርተ ክርስቶስ 2 እትም፤ 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ.33)፤ በማለት ይናገራሉ፡፡ ይህንን የቄስ ኮሊንን ሃሳብ ቅዱስ አውግስጢኖስና አምብሮስ ይግባቡበታል፡፡
     ከዚህ ባሻገር “ነፍስ ወይም መንፈስ አስቀድማ ከሥጋ በፊት ተገኝታለች” የሚለው የእምነት እንቅስቃሴ አማኞች ትምህርት፣ የፍልስፍና ተጽዕኖ ውጤት መኾኑንም፣ “ከፕሌቶ ጀምሮ ያለውን የግሪክ ፍልስፍና ተጽዕኖ ውጤት መኾኑን ‘ፊደል የቆጠረ’ አይስተውም፡፡” ፕሌቶ ሰው ሳይጸነስ ነፍስ አስቀድሞ እንደነበረች አመነ፡፡” (ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ.41) ስለዚህ እውነታውን ካስተዋልን ከዚህ ፈጽሞ ፈቀቅ የሚል አይደለም፡፡ እውነትን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ላይ ቆሞ ለሚያስተውል ግን እውነታውን አንዳች የሚያዛንፍ ነገር የለውም፡፡ 
    ከበጋሻው ደሳለኝ ጋር በአንድነት የሚሠራውና የእርሱን ሽፋን በመጠቀም በብዙ ይህን የስህተት ትምህርት ተግቶ የሚያስተምረው ያሬድ ዮሐንስ በአንድ ስብከቱ እንዲህ ይላል፦ “ … እግዚአብሔር ሕይወቱን በሰው ሕይወት ውስጥ ጨመረው፡፡ …ነፍስ የምንለው ነገር ሥጋችንና መንፈሳችን በመደባለቁ ምክንያት የተገኘች የሥጋ ሕይወት ናት፡፡ … የተፈጠረ መንፈስ እንጂ የተፈጠረ ነፍስ የለንም፡፡” ይላል፡፡ አንግዲህ በግልጥ “እኛ ያልተፈጠረ ነፍስ ያለን እግዚአብሔር ነን” ላለማለት በቃላቶቻቸው ለምን እንደሚያወሳስቡ እናውቃለን፡፡ ምክንያቱም ትምህርቶቻቸውን ሰዎች ቶሎ እንዲረዱት አይፈልጉም፡፡ ስለዚህም ነገር በማወሳሰብ ራሳቸውን እንደተሻሉ አደርገው ለማቅረብ ይፈልጋሉና፡፡ 

1 comment:

  1. የሰማይ አምላክ ይርዳህ berta

    ReplyDelete