Monday 22 January 2018

የብልጽግና ወንጌል፣ ከጌታችን ኢየሱስ ያልኾነ ልዩና እንግዳ ወንጌል - ክፍል ፱

Plesae read in PDF
የቃሉ እውነት ቁጥር 2 -   እግዚአብሔር ልጅነታችን እስከመለኮት መኾን የሚደርስ ነውን? አይደለም፡፡
    ሰዎች ክርስቶስን ይመስላሉ ስንል፦ የአዲስ ኪዳን ምንባባት ይህን አባባል በግልጥ ወስነው አስቀምጠውታል፤ ይኸውም፦ (1ዮሐ.3፥2፤ ሮሜ.8፥29፤ ፊል.3፥21፤ 1ቆሮ.15፥49) በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ፣ ሰው ከእግዚአብሔር ስለተካፈላቸው የቅድስናና የግብረ ገብነትን ባሕርይ እንጂ ሰው ፍጹም አምላክ ስለመኾኑ የሚያመለክቱ አይደሉም፡፡ ከፍጥረታችንም ሰው መኾን እንጂ፣ መለኮት የመኾንም ኾነ ወደዚያ የማደግ አንዳች ምክንያት የለንም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም በዚህ ረገድ የሚያስተምረን አንዳች ትምህርት የለውም፡፡
    በዚህ ምድርም ኾነ ከሙታን ትንሣኤ በኋላ በሚኖረን ሕይወት ከእግዚአብሔር ጥገኝነት ፈጽመን መላቀቅ አንችልም፡፡ ደግሞም፣ “We are independent”[1] “እኛ ነጻ፤ ከምንም ነገር ኢ ጥገኛ ነን” ማለት አይቻለንም፡፡ መጠጊያ ጥጋችን እግዚአብሔር ብቻ ነውና፡፡ እኛ በራሳችን በዚህ ዓለም ብቻችንን ለመኖር የሚያበቃን ሐለዎታዊ ሕይወትን አላገኘንም፤ አልተሰጠንምም፡፡ የሕይወት እስትንፋስን የሰጠን የሰማይ አምላክ ነው እንጂ፡፡

     ደግሜ እላለኹ! እኛ መለኮት መኾን አለመቻላችን ብቻ ሳይኾን፣ ከመለኮት ጥገኝነት መውጣት አይቻለንም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ምንም በማያሻማ መልኩ፣ “እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና(ዮሐ.15፥5) ብሏል፡፡ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ከሌለን በቀር አንዳችና ምንም ነገር በራሳችን ማድረግ አንችልም፡፡ እርሱ መረጠን እንጂ እኛ አልመረጥነውም፣ እርሱ “ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም” (መዝ.145፥3)፣ “የከዋክብትንም ብዛት ይቈጥራል፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል። ጌታችን ታላቅ ነው፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ ለጥበቡም ቍጥር የለውም።” (መዝ.147፥4,5)፣ ከፍጡር ወገን ማንም የማይደርስበት ከፍ ያለ ነው (መዝ.139፥6)፡፡
     ሰዎች ኹሉ ስለእርሱ የሚያውቁት እጅግ በጣም ጥቂቱን ነው፤ ኢዮብ፣ “እነሆ፥ ይህ የመንገዱ ዳርቻ ብቻ ነው፤ ይህም የሰማነው ነገር ምንኛ ጥቂት ነው! የኃይሉንስ ነጐድጓድ ያስተውል ዘንድ ማን ይችላል?” (ኢዮ.26፥14) እንዲል፣ “ …ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነው … እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና …በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን፤” (ሐዋ.17፥25፤ 28)፣ የፍጥረት ደጋፊ፣ ፍጥረትን ያጋጠመና የያዘ (ቈላ.1፥17፤ ዕብ.1፥3)፣ ሰማይና ምድር ብቻውን የፈጠረ፣ ከፍጥረቱ የተለየ ቅዱስና ጻድቅ የሚመስለው የሌለ ልዑል ነው፤ (መዝ.92፥8፤ ኢሳ.44፥24)፡፡
    እኛ ግን ያለእርሱ ዕርቃናችንን ያለን (ዘፍ.3፥7)፣ ፍጥረትን አንዳች ማዘዝ የማይቻለን (ዘፍ.3፥17)፣ ልባችን በክፋት የተመላ (ዘፍ.8፥21፤ ኤር.17፥9)፣ ወራዳና ትቢያ(ዘፍ.6፥3፤ ኢዮ.34፥14-15፤ መክ.12፥7)፣ … ከንቱ ፍጥረት ነን፡፡ ክብራችንና ግርማችን የእርሱ መልክና አምሳል ስላለብን(ራእ.21፥26) ብቻ ነው፡፡ ከእርሱ ስንለይ እንኳን መለኮት፣ ሰው-ነትን እንኳ “በወግ” አናሟላም፡፡ ከእግዚአብሔር ወይም ከሰይጣን መገዛት መቼም መች ነጻ መኾን አይቻለንም (ማቴ.6፥24፤ ዘዳግ.30፥19)፤ ወደን ለእርሱ ለአምላካችን እግዚአብሔር ብንገዛ ግን ሕይወትና ሠላም ይኾንልናል፡፡
     “እውነትን በዓመፃ ለሚከለክሉ ሰዎች… በአሳባቸው ከንቱ ሆነው ለማያስተውሉና ልባቸው ለጨለመ… የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ለለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ለሚያመልኩና ለሚያገለግሉ” (ሮሜ.1፥18፤ 21፤ 25) ግን ከላይ የተናገርነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት እጅጉን መራራ ነው፡፡ ምክንያቱም የተፈጠረውን እንዲመለክ የሚያደርግ ማናቸውም ትምህርት የምንቃወም ብቻ አይደለንም፤ ከዲያብሎስ ነውና አንቀበልምም፡፡
   በክርስቶስ ያገኘነው ልጅነት መለኮት ስለመኾን የተለየ የሚሰጠን መብት የለም፤ ወይም መለኮት እንድንኾን ፈጽሞ አያደርገንም፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳየነው ልጅነት የአባትን ፈቃድ በእውነትና በትክክል ስለመታዘዝ፤ ስለመፈጸምም የሚያመለክት ነው፡፡ ስለዚህም ልጅነትን የሰጠን ቅዱስ እግዚአብሔር እርሱን እንድንመስል በፈቀደልን ልክ እርሱን እንመስለዋለን፤ እናም በተሰጠን ልጅነት ሕይወትን ወርሰን በምድር እንደምናመልከው እንዲኹ፣ በበጉ ሰማይም በጉን፣ አብንና መንፈስ ቅዱስን አምላኪዎቸ እንጂ አምልኮን ተቀባይ አይደለንም፡፡ አዎን! እውነቱ ይህና አንድ ብቻ ነው፤ ሰው እንጂ ዛሬም ቢኾን ነገ ለዘላለምም እግዚአብሔርን አንኾንም!
    ይህንን የበዛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዓይኖቻቸውን ጨፍነው በመካድ፣ የዚህ እምነት መሥራች የኾኑት ኢሴክ ዊሊያም ኬንዮን እና ደቀ መዛሙርቱ ኬኔት ሐጌን እና ኬኔት ኮፕላንድ በግልጥ ቃል እንዲህ ይላሉ፦
    “እግዚአብሔር ለቃል ወይም ለክርስቶስ ዝቅተኛ ግምትን አይሰጥም፡፡ … ቃል እናንተ የሆናችሁትን እንድትሆኑ አድርጐ ፈጥሮአችኋልና ሌሎችንም እንደእናንተ እንዲሁ ያደርጋል፡፡ እናንተ በቃል ውስጥ ጠፍታችኋል ሆኖም ቃል በእናንተ ውስጥ ተገኝቷል፡፡ አንዴ ቃል ሥጋ ሆኗልና፡፡ በመንፈሳችሁ ውስጥ መንፈስ ሆኖአል፡፡ … ቃልና እናንተ አንድ ናችሁ፡፡”[2] ይልና፦
   አሁንም በድጋሚ፣ “… ኢየሱስ በዮሐ.14፥9 ላይ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” አለ፡፡ ይህ መቼም አንድን ሰው በሚገርም ሁኔታ የሚያስደንቅ አባባል ነው፡፡ … ታዲያ እኔም አንድ ቀን … የአዲስ ፍጥረትነትን መገለጥ በጨረፍታ አየሁ፡፡ እኛ በምድር የኢየሱስን ስፍራ መተካታችንን እኛ በእኛ ውስጥ ኢየሱስ ያለው ተመሳሳይ ሕይወት ያለንና ያንኑ ተመሳሳይ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ባሕርይ የተጎናጸፍን መሆናችንን መመልከቴ ነው፡፡”[3]
    ኬንየን በሌላ የስንፍና ንግግሩ ከክርስቶስ ጋር መተካከልን ያገኘነው በመወለድ እንደኾነ ሲናገር፦ “አንድ ሰው ልጁን እንደግል አዳኙ አድርጐ ሲቀበል ጌትነቱንም ሲያውጅ … መለወጥን የሚያመጣ አዲስ ፍጥረትነትን ይቀበላል፡፡ ይህ ታላቅ ተአምር ነው! እርሱም ከኢየሱስ ጋር በእኩል መደብ ይሆናል፡፡”[4]
    እስኪ ከዚህ ንግግር የማሰላሰያ ጥያቄ እናንሳ፦ እንደኬንየን ንግግር ስንፈጠር ነው እንደቃል [እንደክርስቶስ] ኾነን የተፈጠርነው ወይስ በክርስቶስ አምነን፣ ጌትነቱን አውጀን ነው በኢየሱስ መደብ የምንኾነው? ለመኾኑ በክርስቶስ የምናምንና ጌትነቱንም የምናውጅ ከኾነ እንዴት ኾነን ነው ከእርሱ ጋር በእኩልነት አንድ መደብ ውስጥ የምንገኘው?
    ኬኔት ሔገንም ይህንን ኑፋቄ ሲያጸኑ እንዲህ ይላሉ፦ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤  ሰውም በመንፈስነት ደረጃም ተፈጠረ፡፡ ስለዚህ ክላሱ[ደረጃው] እግዚአብሔር ነው፡፡ … ስለዚህ ያለምንም ታናሽነት በእግዚአብሔር ፊት ይቆማል …”
   “እንግዲህ ይህን እናውቃለን፤ እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነና ሰውም ከእግዚአብሔር ሕብረት ለማድረግ የተፈጠረ ስለሆነ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር በደረጃ እኩል መኾኑን እናውቃለን፡፡ … በ1ቆሮ.6፥18 ላይ ሰው የሚያደርገው ኀጢአት ሁሉ ከሥጋው ውጪ ነው፤ … ስለዚህ ከሥጋው ውጪ የሚደረግ ከሆነ ይህ በመንፈስ የሚደረግ መሆን አለበት፡፡ ዝሙት እንኳ ቢሆን የሚመነጨው ከመንፈሳችን ነው፡፡ መንፈሳችሁ ሲመራችሁ ኀጢአት ይሠራል፡፡ መንፈሳችሁ ኀጢአት እንዲሠራ ካልፈቀዳችሁለት ሥጋ ምንም ሊሠራ አይችልም፡፡”[5] ብለው በተቃራኒው ግን “መንፈሳችን የነበረው አሮጌው የሰው ተፈጥሮ ተወግዷል፡፡ በሥጋችሁ ያለው የኀጢአት ተፈጥሮ በሥጋችሁ ውስጥ አሁንም አለ፡፡” ይላሉ፡፡ ኮፕላንድም ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ አለው፡፡
    እንግዲህ ግልጥ ክህደቶችን በመጽሐፎቻቸው በግልጥ አስፍረዋል፤ እንዲያውም ኬንየን በታላቅ ድፍረት፣ “የአብም አንዱ ሕልም በእኛ አማካይነት ራሱን ማባዛት ነው”[6] በማለት በአመጽ አንደበቱ ተናግሯል፡፡ በቀደመው ዘመን የነበሩት ምድራዊ ጠቢባን፣ “ሰው መገኛው ዝንጀሮ ወይም ጦጣ እንደነበር ይነግሩናል፡፡[7] አኹን ሊያስተምሩን የተነሡት መናፍቃን ደግሞ “ሰውን እግዚአብሔር ነው” ከሚል ከንቱ ቅዠት ጋር አስተሳስረውታል፡፡
   ኬንየን፣ “ቃል እናንተ የሆናችሁትን እንድትሆኑ አድርጐ ፈጥሮአችኋልና” ይለንና፣ መልሶ ግን “የአብ ሕልሙ በእኛ አማካይነት ራሱን ማብዛት ነው” ይላል፡፡ ኬኔት ሔጌንም፦ “ሰው እግዚአብሔር የኾነው እንደእግዚአብሔር በመንፈስነት ደረጃ ስለተፈጠረ ነው” ይላል፡፡ እጅግ እርስ በእርስ የሚቀዋወሙ ሃሳቦች፣ አንዱ የተፈጠራችኹት ቃል እንድትኾኑ ነው ሲል፣ በሌላ ድኩም ሃሳብ ደግሞ፣ አብ እኛን እንደራሱ ያባዛናል እያለ አኹንም በሌላ ተቃርኖ፣ “የተፈጠርነው በእግዚአብሔር የመንፈስነት ደረጃ፣ በእርሱ መደብ[እኩል ኾነን] ነው” ይለናል፡፡ እርስ በእርሱ የሚራገጥና የደፈረሰ ትምህርት፡፡ በጋሻው ደሳለኝ የኬኔት ሔገንን ሃሳብ በመጋራት፣ “ሰው በመንፈስነት ደረጃ ብቻ መፈጠሩን እንደሚያምን” በባለፉት ጽኹፎቻችን አሳይተናል፡፡
     መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የኑፋቄ ትምህርት በግልጥ ይቃረናል፤ እግዚአብሔር፦ “በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ?” (ኢሳ.46፥5) ይላል፣ እርሱ ወደር የለውም፤ እርሱንም የሚመስል የለም፤ (ዘዳግ.33፥26)፣ “ከጥንቱ ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማን ነው? ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፥ ከእኔም በቀር ማንም የለም” (ኢሳ.45፥21)፣ “ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፥ ከእኔም በቀር ሌላ መድኃኒት የለም” (ሆሴ.13፥4) ብሎ፣ ብቸኛ አምላክነቱን የተናገረ ጌታ አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር፣ “ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?” (ኢሳ.44፥24) ብሎ ተናግሯል፤ “እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና፤ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፤ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው” (ኤር.10፥16)፣ እንደተባለ ሕላዌን በራሱ ማምጣት የሚቻለውና መልክ ማስያዝ የሚቻለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ (መዝ.33፥6፤ ዕብ.11፥3፤ 2ጴጥ.3፥5)፡፡
   እኛና ፍጥረት ግን መነሻና መጀመርያ አለን፤ እግዚአብሔር ግን ከፍጥረት በፊትና ከሰው ልጅ መገኘት በፊት ያለ፣ የነበረና የሚኖር ነው፤ (ዘጸ.3፥14፤ ራእ.1፥8)፡፡ “ዓለም ሳይፈጠር፥” (ኤፌ.1፥4፤ 1ጴጥ.1፥19) “የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት” (ቲቶ.1፥2፤ 2ጢሞ.1፥9) በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ የመረጠን እግዚአብሔር ነው እንጂ፣ እኛ ራሱ እግዚአብሔርን አይደለንም፤ አንኾንምም፡፡
    ስለዚህ እኛ ለእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች እንጂ የባሕርይ ልጆቹ አይደለንም፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ መሲሐዊ ልጅነቱ በአምላካዊ ልጅነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ዓለማትን በእርሱ ፈጠረ (ዕብ.1፥1)፣ ዓለሙንም ሊያድን እርሱን አብ ላከው (ዮሐ.3፥16፤ ሮሜ.8፥3፤ ገላ.4፥4)፣ ደግሞም ከሙታን መካከል በኀይል በመነሣት (ሮሜ.1፥3-4) የአግዚአብሔር የዘላለም የባሕርይ ልጁ መኾኑን ገለጠ፤ (ዮሐ.20፥31)፡፡ ስለዚህም የአባቱን ክብር በትክክል የሚገልጥና ፈቃዱንም በመፈጸም ያረካው የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ እንጂ እኛ ወይም ሰዎች አይደለንም፤ (ማቴ.11፥27-30፤ ዮሐ.1፥18፤ 6፥37)፡፡
     እናስተውል! የአብ ልጁ አንድ[አንድያ] ብቻ ነው፡፡ ሌላ አምላክ የኾነ የባሕርይ ልጅ የለውም፡፡ አንድያ ልጅነቱ አንድያ እግዚአብሔርም መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ከዘላለም ከእርሱ ጋር ስለነበርም በሊቀ ካህናትነት ጸሎቱ፣ “አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” (ዮሐ.17፥5) በማለት፣ ተካካይ ወደኾነው አባቱ ጸለየ፡፡ ይህም ፍጹም ዘላለማዊ አምላክነቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ስለዚህም አንድያ ልጅነቱ ጅማሬ የለውም፤ ከአብ ጋርም እኩልና ከዘላለምም በአንድነት የነበረ ነው፡፡
    እኛ ግን፣ “እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን” (ኤፌ.2፥10) የተባለልን ነን፤ እኛ ለእግዚአብሔር ፍጥረቱ፣ የእጆቹ ሥራዎች (ኢሳ.29፥23፤ 60፥21)፣ የተፈጠርን (ኤፌ.4፥24)፣ ገንዘቦቹ (ቲቶ.2፥14) ነን፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር የምንጋራበትን ጥቂቱን ግብረ ገባዊ ባሕርያቱን እንጂ ኹለንተናውን አልሰጠንም፡፡ ያ ቢኾን፣ “የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፥ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?”(መዝ.8፥3-4) ባልተባለልንም ነበር፡፡
    “ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤ በሰማይም ያንጐደጕድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤ ለንጉሡም ኃይል ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል”(1ሳሙ.2፥10)
   የሰውን ሰውነት የሚክዱ የተለያዩ የአስተምኅሮ ዝንፈቶችን ሊያስከትሉ ይገደዳሉ፤ ከእኒህም ዝንፈቶች መካከል ጥቂቱን ብንጠቅስ፦
ü የክርስቶስን በሥጋ መገለጥ ይክዳሉ፤
ü ክርስቶስም በሥጋ ሞቱ አድኖናል ብለው ደፍረው መናገር አይችሉም፤
ü ክርስትና የቆመበትን አንዱን የአካላዊ ትንሣኤን ትምህርት ፈጽመው ይክዳሉ፤
ü ሥጋን ፈጽመው ይክዳሉና በሥጋ ለሚሠራ የትኛም ኃጢአት ኀላፊነት ባለመውሰድ፣ ሰውን ኹሉ ለኃጢአት ልምምድ ይጋብዛሉ፡፡
     እኛ ግን ቅዱሳን ሐዋርያት፦ “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤” (2ጢሞ.3፥14) ብለው እንዳስተማሩን፣ ከቅዱሳን ሐዋርያትና ነቢያት በተማርነው ትምህርት ጸንተን እንኖራለን፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! በዚህ ታላቅ የወንጌል እውነት እንድንጸና ጸጋህ ስለገነነልን እናመሰግንሃለን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …






     [1] ኃይሉ ዮሐንስ ስለሰው ተፈጥሮ ሲያስተምር በቀጥታ የተወሰደ ነው፡፡
   [2] ኢሴክ ደብሊው ኬንዮን፤ New creation Realities (የአዲስ ፍጥረት እውነታዎች)፤ ዓ.ም እና አሳታሚው ያልተጠቀሰ፤ ገጽ.25-27
   [3] ዝኒ ከማኹ ገጽ.56
   [4] ዝኒ ከማኹ ገጽ.67፤ [ኹሉም የእምነት እንቅስቃሴ መምህራንና ደቀ መዛሙርቶቻቸው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዊ ማንነትና ፍጹም የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅነትን ሽምጥጥ አድርገው ይክዳሉ፡፡ ለዋቢነት ግን እኒህን ብቻ መጥቀሱ በቂ መስሎ ታይቶኛል፡፡]
  [5] በጋሻው ደሳለኝ[ኃይሉ ዮሐንስም] ይህንን ትምህርት በቀጥታ ያስተምራሉ፡፡ በጋሻው፦ “ነፍስ ላስገዛላት ትገዛለች” በማለትም ደፍሮ ይናገራል፡፡ ነፍስ በራስዋ ማንነት ወይም አካል የሌላትና ላስገዛላት የምትገዛ[ለሥጋ ወይም ለነፍስ] ናት በማለት፣ በአንድ ጐን ነፍስን ሥጋ[ሥጋን በግልጥ እየካዱ] ያስገዛታል ሲሉ፣ በሌላ ጎን ደግሞ መንፈስም ካሸነፋት ያስገዛታል በማለት እርሱ በእርሱ የሚጋጭን ትምህርት ያስተምራሉ፡፡
   [6] ዝኒ ከማኹ ገጽ.110
   [7] ቻርልስ ዳርዊን ይህን ትምህርቱን በዝግመተ ለውጥ ትምህርቱ በስፋት ማስተማሩንና በብዙዎች ዘንድም መታመኑን የምንዘነጋው አይደለም፡፡ 

4 comments:

  1. ስለዚህ እኛ ለእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች እንጂ የባሕርይ ልጆቹ አይደለንም፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ መሲሐዊ ልጅነቱ በአምላካዊ ልጅነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ዓለማትን በእርሱ ፈጠረ (ዕብ.1፥1)፣ ዓለሙንም ሊያድን እርሱን አብ ላከው (ዮሐ.3፥16፤ ሮሜ.8፥3፤ ገላ.4፥4)፣ ደግሞም ከሙታን መካከል በኀይል በመነሣት (ሮሜ.1፥3-4) የአግዚአብሔር የዘላለም የባሕርይ ልጁ መኾኑን ገለጠ፤ (ዮሐ.20፥31)፡፡ ስለዚህም የአባቱን ክብር በትክክል የሚገልጥና ፈቃዱንም በመፈጸም ያረካው የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ እንጂ እኛ ወይም ሰዎች አይደለንም፤ (ማቴ.11፥27-30፤ ዮሐ.1፥18፤ 6፥37)፡፡ melkam tenagerk

    ReplyDelete
  2. Geta tsegawn yabzalihi berta tru mankiya new

    ReplyDelete
  3. እኛስ በክርስቶስአምላክነት የምናምን ንፁህ የኦርቶዶክስ ልጆች ነን ሰው የፈለገውን ቢል ጌታ በህይወት መዝገብ ፅፎናል

    ReplyDelete