Sunday 5 March 2017

ምኩራቡን ለምኩራቡ ጌታ አገልግሎት!

    
Please read in PDf
  የእስራኤል ልጆች በስደት ምድር በባቢሎን ሳሉ፣ በኢየሩሳሌም የነበረው ዋናው ቤተ መቅደስ  ስለፈረሰና በምርኮ ምድር ደግሞ ቤተ መቅደስ መሥራት ስላልተቻላቸው ለጸሎት፣ ቃሉን ለማንበብና ለማጥናት እንዲሁም መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ለማሳደግ ምኩራብን በየአቅራቢያቸው ሠሩ፡፡ በምኩራቡ ውስጥም በየቀኑ የሚነበቡ የተለያዩ የሕግና የነቢያት የብራና ጥቅልሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ቅጂዎችን አስቀመጡ፡፡
   የእግዚአብሔር እውነተኛ ሕዝብ በየትኛውም ሥፍራና ሁኔታ ሊያስቀድመውና ሊጠነቀቅለት የሚገባው ነገር ከአምላኩ ጋር ያለው ዝምድና፣ ትስስሩና ግንኙነቱ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ግንኙነት ሊያሳስበው፤ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው በምቹና የተደላደለ ትርፍ ሰዓት ባለው ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁን በስደት፤ ፈጽሞ ምንም ዓይነት ዕድል ላይገኝ በሚችልበት መንገዱ፣ የጌታ ነገር ቀዳሚና ትኩረቱን ሳቢ ሊሆን፤ በሕይወቱም ጭምር ሊሰጥለት ይገባል፡፡

   አይሁድ በስደትና በማይመቹ ሕዝቦች መካከል ያሉ ቢሆንም፣ ምኩራብን ለመሥራት ጸሎትን ለመጸለይ፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቅጂዎችን ለመሰብሰብ፣ ቃሉንም ለማንበብና ለማጥናት ያገዳቸው የስንፍና ተግባር አልነበረባቸውም፡፡ በዚያ ተገኝተውም ቃሉን በጋራ ያጠናሉ፤ እንግዳ መምህርም የመጣ እንደሆን በምኩራብ መሪው ጋባዥነት በዕለቱ የተነበበውን ቃል እንዲያብራራ ይጠይቃሉ፤ ደግሞም ይሰማሉ፡፡
    ጌታ ኢየሱስ በተደጋጋሚ ወደምኩራብ የመግባት ልማድ ነበረው፤ (ሉቃ.4፥16)፡፡ እርሱ የሕግ ሁሉ ፍጻሜ[ፈጻሚ] ነውና እንደታማኝ አይሁዳዊ ወደምኩራብ በመሄድ የሚገባውን ሥርዓት በማድረግ ሰንበትን አክብሯል፡፡ ማክበር ብቻም ያይደለ ከሌላ ሥፍራ እንግዳ ረቢዎች ከቅዱሳት መጻሕፍት እንዲያነቡና እንዲተረጉሙ ይጋበዙ እንደነበር እንዲሁ፣ ጌታ ኢየሱስ ይህ ዕድል በተሰጠው ጊዜ ተጠቅሟል፤ (ማቴ.13፥43 ፤ ማር.6፥1)፡፡ አገልግሎት በሚያገለግሉት ሕዝብ መሃል ተቀምጦ ማገልገል ነው፤ ችግሩን፣ አላዋቂነቱን፣ ሰቆቃውን፣ ሕመሙን እያደመጡ እንደማገልገል ያለ መታደልና መባረክ የለም፡፡ ጌታ ኢየሱስ የሕዝቡን ችግር በትክክል እንጂ በማስረጃ ይሰማ አልነበረም፡፡
   ደግሞም፣ “ተጋባዡ” መምህር ጌታ ኢየሱስ ሲያስተምር፣ እንደፈሪሳውያን፣ “እንደ ጻፎቻቸው [የባለሥልጣናትን ቃላት በማስተጋባት] ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር” (ማቴ.7፥28-29)፤ ከሚያስተምረውም የጸጋ ቃል የተነሳ የሚሰሙት ይደነቁም ነበር(ሉቃ.4፥22)፡፡ ቃሎቹም ልብን የሚያሳርፉና መጽናናትን የሚያድሉ ነበሩ፡፡
    ቅዱሳን ሐዋርያትም ልክ ይህንን የጌታን መንገድ በመከተል፣ በምኩራብ በመገኘት ተጋባዥ “መምህራን” በመሆን ቃሉን በማንበብና በማብራራት አገልግለዋል፤ (ሐዋ.13፥14 ፤ 14፥1 ፤ 17፥2-4 ፤ 18፥4)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከበርናባስ ጋር በመሆን በጲስዲያ አንጾኪያ በተጋባዥ አስተማሪነት በአንድነት ተገኝተው ያደረጉትን አገልግሎት(ሐዋ.13፥14-52) ስንመለከት እጅግ የሚያስደንቁ ፍሬ ነገሮችን እናስተውልበታለን፡፡ ይኸውም፦
1.      የምኩራብ አለቆቹ እነጳውሎስን፣ “  ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ ብለው ላኩባቸው” በማለት ጋበዙ፤ (ሐዋ.13፥15)፤
     ይደንቀኛል! እኒህ የይሁዲ እምነት ተከታዮች ክርስትናን ያልተቀበሉ ቢሆኑም፣ እነጳውሎስን አብረው የሚሠሩ ያህል “ወንድሞች” ብለው ተቀብለው ጋበዟቸው፡፡ ይህን ሳስብ ሁለት አካላት ወደኅሊናዬ ይመጣሉ፣ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በማዕረግ ወይም በመንቆለጳጰስ ካልተጠሩ እንጂ ወንድሞች ሲባሉ የሚያኮርፉ፤ የሚቆጡና የምዕመናንን ወንድምነት መቀበል የሚቸግራቸው “የቤተ መቅደስ አገልጋዮች”፡፡
   በምኩራብ ለመገኘት የጳውሎስና የበርናባስ ነፍስ ፈጽሞ አልጠየፈችም፤ የእግዚአብሔርን ክብር ባላዩ ሰዎች መካከል የእግዚአብሔርን ክብርና ፈቃድ ጠብቆ በትጋት መኖር፣ የትጉሃንና የታማኝ አገልጋዮችና አማኞች ዋና መገለጫ ነው፡፡ ምኩራቡን የከበቡት ለምኩራቡ ጌታ በሕይወታቸው የማይመቹ ቢሆኑም እንኳ፣ ቅዱሳን ሐዋርያት በዚያው ትውልድ መካከል ሆነው ጽድቅን በሚገልጥ ኑሯቸውና በፍቅር እውነትን በሚያውጅ ትምህርታቸው ለጌታ የማይመቹትን ኮንነዋል፡፡ እንደቃላቸው “ምግባራቸውም ገዢ ሥልጣን” ነበረው፤ ስለዚህም የእነርሱ ወንጌል ክፉውን ዓለም ጸጥ ያሰኛል እንጂ፣ በዚያው እንደጨው ሟሙተው የሚቀሩ አይደሉም፡፡
     አልተረዳንም እንጂ ቢገባን፣ አገልጋይ ከመባል የተሻለውና ስሜት የሚሰጠው ወንድም መባል ነበር፡፡ አገልጋይነት ዝቅ ብሎ ማገልገልን እንጂ እንደወንድም በቤቱ ውስጥ የወራሽነትና የመብትን ተካፋይነት ሥልጣን አያስገኝም፤ ዛሬ ግን ስንገፋፋ የምንታየው ስለተወለድንበት ልጅነትና እንድንኖርበት ስለታዘዝነው ወንድማማችነት ሳይሆን “ስለአገልጋይነት” ነው፡፡ ምኩራቡ ግን የጌታ የሆነ ሁሉ እንዲያገለግልበት እንጂ እኛ በባለቤትነት ይዘን እንድንኩራራበት ወይም የገቢ ምንጭ አድርገን ለምድራዊ ኑሯችን እንድንቀማጠልበት አልነበረም፡፡
    ሌላውና አሳዛኙ ነገራችን፣ የጲስዲያ አንጾኪያ የምኩራብ አለቆች እነጳውሎስን ወንድሞች ያሉበት መንፈስ፣ አንዱን ጌታ እናመልካለን፣ እርሱንም እንገለግላለን በምንለው በእኛ ዘንድ አለመኖሩ ነው፡፡ እኛ በቆምንበት ዓውደ ምሕረት ሌላው እንዳይቆም የማንፈነቅለው ድንጋይ፤ የማንፈጥረው የስም ማጥፋት ዘመቻ የለም፡፡ እናም ምን ያህል ከምኩራብ አለቆች ማንነት ያለን መሆኑን በግለጥ ያሳያል፡፡  እባካችሁ ምኩራቡን ለምኩራቡ ጌታ ባለቤት እናውለው!
2.   በምኩራብ ለቃሉ የተጋበዙትን ግብዣ ሁሉ፣ ለጌታ ክብር ብቻ አዋሉት፤
   ደቀ መዛሙርት በየትኛውም ምኩራብ ሄደው ሲያገለግሉ፣ በሄዱበት በዚያ ራሳቸውን ሳይሆን ክርስቶስን ብቻ ይገልጣሉ፤ ስለዚህም አገልግሎታቸው ተጽዕኖ ፈጣሪና “ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፥ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው” (ሐዋ.13፥43) እንዲል፣ ሰዎችን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለመኖር አስተማሩ እንጂ፣ ደቀ መዛሙርትን ወደራሳቸው አላከማቹም፡፡
    ጌታ ኢየሱስ ራሱ፣ ሕዝቡን በብዙ ሌላ ምክር እየመከራቸው ወንጌልን ይሰብክ የነበረውም (ሉቃ.3፥18)፣ የእግዚአብሔርን ክብር ለመግለጥ ብቻ በማሰብ ነበር፡፡ እንዲናገር በተጋበዘበትና በሚያስተምርበት ሥፍራ ሁሉ የተጋውና ያስቀደመው የአባቱን ፈቃድ በመፈጸምና ደስ በማሰኘት ብቻ ነበር፡፡ ትምህርቱም ተአምራቱም ብዙዎችን ሕዝብ እጅ በአፍ አስጭኖ ቢያስደንቅም (ማር.1፥27 ፤ 2፥12 ፤ 5፥20 ፤ 42 ፤ 6፥2 ፤ 51 ፤ 7፥37 ፤ 10፥26 ፤ 11፥18)፤ የአባቱን ክብር እጅግ ከመግለጥና ሰዎች በእርሱ እንዲያምኑ ከማድረግ አንጻር ብቻ ነበር፡፡ ደቀ መዛሙርትም ከእርሱ እንደተማሩት የአገልግሎቱን ክብር ሁሉ ሰዎች በጸጋው ወንጌል እንዲድኑ፤ ወደኢየሱስም ዘወር እንዲሉ እንጂ ምንም ሌላ ዒላማ አልነበራቸውም፡፡

     ዛሬ ጌታ ሊሰበክበትና የመዳኑ ወንጌል ሊታወጅበት የሚገባው ዓውደ ምህረትና የሰው ልብ ምን እየተከናወነበት ይሆን? አገልጋዩ ሁሉን ለጌታ ክብር እያዋለና ሰዎች ሁሉ ፊታቸውን ወደጌታ ዘወር እንዲሉ እያደረገ ይሆን? ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን፡፡

3 comments:

  1. Absolutely incredible & tangible article.
    l agree we need to check our stand point,& we got to know the difference between culture and faith.but most of
    the time as point of my view we got lost.I am not blaming religious leaders,
    what ever they say we believe them instead of proofing according to the bible,BC we weren't devoted to go farther and get reasonable sources,we
    need to dig deeper until we reached the point.
    be blessed.thanks.

    ReplyDelete
  2. የበሰለ ጽሁፍ ነው

    ReplyDelete