Sunday, 19 March 2017

“እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ” (ማቴ.24፥25)

                                          Please read in PDF

   ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ሳለ ከተናገራቸው የመጨረሻ ቃሎች መካከል፣ በደብረ ዘይት ለደቀ መዛሙርቱ ስለዳግመኛ መምጣቱ ምልክቶች የተናገረው አንዱና ሠፊውን ክፍል የያዘ ነው፡፡ በውስጡ ብዙ ነገር መናገሩን ወንጌላዊው ጽፎልናል፡፡ በመካከሉም ቅዱስ ማቴዎስ፣ ጌታችን “እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ” ብሎ መናገሩን ከጻፈልን የወንጌል ቃል ውስጥ ሁለት መሠረታዊ ጭብጦችን ማውጣት እንችላለን፤ ይኸውም፦
1.      ጌታችን ሁሉንም ነገር የነገረን  በግልጥ ነው፦ ጌታ ለእኛ ከሚያስፈልገን  ቀድሞ ያልተናገረን ምንም ነገር የለም፡፡ በሰማይም ሆነ በምድር ሊሆንና ሊመጣ ያለው ነገር ሁሉ ተነግሮናል፡፡ በዚህ ምድር ሕይወት ስላለው ብርቱ ሰልፍነት፣ ታ ኢየሱስንም አምነን በመከተላችንም ሆነ ሳናምን በመከተላችን ስለሚገጥመን ሕይወትና ሞት፣ ስሙን አምነን በመከተላችንና በመመስከራችን ስለሚያገኘን ነቀፋ፣ ስድብ፣ ግርፋት፣ ስደት፣ ስም ማጥፋት፣ ርስትና ጉልት ማጣት፣ በቤተሰብ ሁሉ ዘንድ ከበሬታና ቦታ መነፈግ፣ መጠላትና መገለል፣ መገደል፣  ... እኒህ ሁሉ አስቀድመው የተነገሩ ናቸው፤ (ማቴ.10፥16 ፤ 24፥9 ፤ ዮሐ.15፥19)፡፡

    ይህ ብቻ አይደለም፤ “ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት” (1ቆሮ.2፥9) ልጆቹ በሰማያት ትልቅ “የዘላለም ሠርግ”ና ደስታን፣ ሕይወትና መንፈሳዊ ተድላን፣ ውብና ልብ የሚመላ ሐሴትን እንዳዘጋጀ፣ ጌታ ኢየሱስ ዋና ሊቀ ካህናትና ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በስሙ ያመኑና ከእርሱ የተነሳ ድል የነሱ ሁሉ አብረው ካህናት ሊሆኑና ሊነግሡም እንዳላቸው ድል የነሣው በግ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡
     ደግሞም፣ በእርሱ የሚያምኑ፤ አምነውም በሥራቸው ፈጽመው ኃይሉንና እርሱን የሚክዱ ደግሞ (2ጢሞ.3፥5 ፤ ቲቶ.1፥16)፤ ማስጠንቀቂያ ብቻ ያይደለ ድቅድቅ ጨለማ፣ ጥርስ ማፋጨትና ልቅሶ፣ ትሉ የሚያስፈራ እሳቱ የሚበላ … አስፈሪና አስጨናቂ እጅግ ታላቅ መከራና ስቃይ እንደሚጠብቃቸውም ጭምር ጌታ አስቀድሞ ነግሮናል፤ (ማቴ.13፥42 ፤ 50 ፤ 22፥13 ፤ 24፥51 ፤ 25፥30 ፤ ሉቃ.13፥28 ፤ 2ጴጥ.2፥17 ፤ ይሁ.13)፡፡
    አዎን ጌታችን ሁሉን ነገር አስቀድሞ የነገረን ስለሁለት ነገር ነው፤ ብንል፦
1.1.  እርሱን ያመንን ተስፋችንን በእርሱ ላይ ብቻ እንጥል ዘንድ፤ ጌታችን ቢፈጽመውም ባይፈጽመውም፤ ቢጎዳንም ቢጠቅመንም፤ ብንኖርም ብንሞትም ስለተናገረው ተስፋ ቃሉ አምነን እንከተለዋለን፡፡ እናምናለን፤ እርሱ የተናገረውን ይዋሽም ዘንድ ሰው አይደለም፡፡ አዎን! የተናገረውን እንደሚደርገው እንታመናለን፡፡
1.2. ለምክንያተኞች ምክንያታቸውን ይሽር ዘንድ፤ ጌታችን እንዲህ አለ፣ “እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም” (ዮሐ.15፥22)፡፡ ጌታን እያዩ ግን ምክንያታቸው በልጦባቸው እርሱን ማየት[በእርሱም ማመን] የማይፈልጉ አሉ፤ (ዮሐ.9፥41)፡፡ ጌታችን ሁሉን ነገር ሳይደብቅ መናገሩ በተለይ ለኃጢአተኞች ልዩ ዕድል ነው፡፡ ይህ ዕድል ደግሞ ከሰሙት ቃል የተነሣ ትልቅ ኃላፊነትን ማስከተሉ ግድ ነው፡፡ ሰምተው ቢመለሱ ሕይወት ባይመለሱ ግን ጥፋት እንደሚያገኛቸው ግልጥ ነውና፡፡ ከሰማነው ከጌታ ቃል የተነሳ በማመናችን ብፁአን የመሆናችን ያህል ባለማመናችንና ባለመመለሳችን ደግሞ ርጉማንና ኃጢአተኞች እንሆናለን፡፡
   በአይሁድ የሆነው ይህ ነው፤ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ብዙ ነገር ከገለጠላቸው ባሻገር፣ አንድና ውድ ልጁ በመካከላቸው እንዲገኝ ፈቀደ፤ ይህ ትልቅ በረከትና እጅግ የበዛ ዕድል ነበር፤ አይሁድ ግን ጌታ ኢየሱስን ፈጽሞ ባለመቀበል ከፊት ይልቅ የበዛ ኃጢአትና ዓመጽ በመፈጸም ራሳቸውን ለይቅርታ ያልተገቡ አደረጉ፡፡ ስለዚህም በሚብስ ፍዳ ተያዙ፡፡
    ኮራዚዮንና ቤተ ሳይዳም ብዙ ዕድል ተሰጣቸው፤ ግና እድላቸውን ሊጠቀሙ ባለመውደዳቸው ጌታችን፣ “ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና፡፡ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል” (ማቴ.11፥21-22) በማለት በብርቱ ቃል ወቀሳቸው፤ ጽኑ ፍርድም እንደሚጠብቃቸው ተናገረ፡፡
     ዛሬም የጌታ ቃል በደጃችን አለ፤ የነገረንም በግልጥና አስቀድሞ ነው፤ ምንም ሳይደብቅ የሚጠቅመንንና የሚረባንን ሁሉ ለነገረን ጌታ ታማኞች ሆነን ያልተደበቀ ሕይወት ያለን ነንን? ወይስ ከሰው እንደምንሸሸግ እንዲሁ ከእርሱም የምንሸሸግበት ነገር አለን?
2.     ቅዱስ ጴጥሮስ፣ “እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም” (1ጴጥ.2፥22) ብሎ ስለጌታ ኢየሱስ ኃጢአት አልባነት ተናገረ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ፍጹም ጻድቅና ቅዱስ ስለሆነ ሲነግረን በግልጥና በእውነት እንጂ አልሸነገለንም፤ አላባበለንንምም፡፡ እንዲያውም እርሱ ስለሁላችን መከራና ሕማምን ተቀብሎ የዘላለም ሕይወትና ተድላን ሰጥቶናል፤ ስለዚህም የገዛ ሕይወቱን ሳይራራ የሰጠን ጌታ ዋናና እውነተኛ ምሳሌ ስለሆነን ስለምን በሽንገላ ቃል ይጠራናል?!
    ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎችን ሲጠራ ከአፉ የተሰማው ቃል “ተከተለኝ” (ማቴ.9፥9 ፤ 19፥21 ፤ ዮሐ.1፥44 ፤ 21፥19-22) የሚል ነበር፣ እንጂ ፈጽሞ ሽንገላ አልነበረበትም፤ እርሱ በብዙ መከራ ውስጥ እንዳለፈ፣ ስለጽድቅ ቃል እነርሱም ሊሰደዱ እንዳላቸው ሳይሸፋፍን፣ ሳይሸነግል ነገራቸው፤ በሌላ ሥፍራም ሰው ሁሉ ከኋላው ሲሸሽ እነርሱም ሊሸሹ እንደሚቻላቸውና ሸንግሎ እንዳልጠራቸው፣ “ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ፦ እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?” (ዮሐ.6፥66) በማለት ተናገረ፡፡ አዎን! እርሱ ዓለሙ ሁሉ ቢክደው ብቻውን የታመነ እውነተኛ ነው፡፡
    ጌታ ኢየሱስ ራሱ እውነት ነው፤ ስለዚህም ፈጽሞም አይዋሽም፤ አይሸነግልምም፤ (ዮሐ.14፥6 ፤ ቲቶ.1፥1 ፤ ዕብ.6፥17)፡፡ እንደሐሰት መምህራን ሰዎችን ታገኛላችሁ፣ ያልፍላችኋል፣ ትጥሳላችሁ፣ ትወርሳላችሁ፣ … ” እያለ ሳይሆን ስለሚበልጠውና ስለሚሻለው፤ እጅግ ስለከበረው ሰማያዊ መንግሥት እርሱ በከፈለው የጽድቅ ዋጋ አምነው ታማኝነታቸውን በመግለጥ እንዲድኑና እንዲጸኑ፣ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” (ማቴ.6፥33) በማለት አጽንቶ ተናገረ፡፡ የምድሩ ነገር ቢሆንም ባይሆንም፣ ቢሳካም ባይሳካም፣ ቢሞላም ባይሞላም፣ … ሰማያዊው እውነት ግን ለሚያምኑትና ድል ለነሡ ቀድሞ በጌታ አንደበት እንደተነገረ የተጨበጠ፣ የሚወረስ፣ የሚሳካ እውነተኛ ሕይወት ነው፡፡
     እናንተ በስሙ ከማመን ቸል ያላችሁ ሆይ! ይህ የምትሰሙትና የምታነብቡት ቃል አስቀድሞ በሕይወት ባለቤትና ራስ በጌታ ኢየሱስ የተነገረ ቃል ነው፤ በሽተኞችና ኃጢአተኞች ናችሁ፤ መድኃኒቱን ተቀበሉ፤ ባትቀበሉት ግን ዕድላችሁንና ይቅርታችሁን በገዛ እጃችሁ ስላልፈለጋችሁ እጅግ አስፈሪ መከራና ስቃይ ይጠብቃችኋል፤ ይህንን ጌታ አስቀድሞ በቃሉ መናገሩንም ቸል አትበሉ! በምጽአቱ ዋዜማ የሚያገኛችሁ መከራ እንኳ ቀድሞ የተነገረና የታወቀ ነውና ፊታችን በንስሐ ወደተናገራችሁ ጌታ አቅኑ፡፡
    እናንተ በስሙ የምታምኑ ሆይ! ጌታ ኢየሱስ በእውነት ቃሉ አስቦ ያለሽንገላ አስቀድሞ እንደተናገራችሁ አስቡ፤ በእርሱም ታመኑ ተስፋችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ብቻ ጣሉ፤ ሎሌ ከጌታውም ስለማይበልጥ አስቀድሞ የተነገረንን ማስተዋል ይገባናል፡፡ ደግሞም ዓለሙ ሁሉ ቢጠላችሁና ሐሰተኞች እንደሆናችሁ ቆጥሮ ዓለሙ ሁሉ ቢነሳባችሁ በእርሱ ፊት የተወደዳችሁና እውነተኞች መሆናችሁን አስቀድሞ የተናገረውን አምላካዊና ንጉሣዊ ቃል ማስታወስ ያበረታችኋል፤ ያጽናናችኋልም፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ስለዚህ እውነት ሰግደን እናመልክሃለን፤ አሜን፡፡

1 comment:

  1. ዓለሙ ሁሉ ቢጠላችሁና ሐሰተኞች እንደሆናችሁ ቆጥሮ ዓለሙ ሁሉ ቢነሳባችሁ በእርሱ ፊት የተወደዳችሁና እውነተኞች መሆናችሁን አስቀድሞ የተናገረውን አምላካዊና ንጉሣዊ ቃል ማስታወስ ያበረታችኋል፤ ያጽናናችኋልም፡፡ smart article

    ReplyDelete