Tuesday 5 January 2016

“ …ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” (ማቴ.1፥21)


Please raed in PDF

እንኳን ለበዓለ ልደቱ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡ አሜን፡፡
      ለሁለት ሺህ ዓመታት ያልተዘነጋ ፤ ለአንድም ቀን ሳይነሳ የተዋለበት ቀን የሌለ ድንቅ ስም፤ ክርክር ፣ ሙግት ፣ ክህደት ፣ ፍልስፍና ፣ ነቀፋ ፣ ስድብ ፣ ትችት ፣ መሸቃቀጥን ድል ነስቶ ያሸነፈ ፤ ነቢያት ሊሰሙትና ሊያዩት የወደዱት፣ መላዕክት በምስጋና ያደነቁት ግሩም ስም ፤ ባለፈው ፣ ባለውና ገና በሚመጣው ትውልድ ተወዶ ያልተጠገበ ስም ቢኖር ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡
    ኢየሱስ የሚለው ቃል “የሹዋ” ለሚለው የዕብራይስጥ ቃል አቻ የግሪክ መጠሪያ ስም ሲሆን፥ ትርጉሙም “እግዚአብሔር ያድናል ፤ እግዚአብሔር ድኅነት ነው” ማለት ነው፡፡ በሌላ ንግግር ኢየሱስ በግሪኩ ሲሆን በዕብራይስጡ ኢያሱ ነው፡፡ ትርጉሙም አንድ ነው፡




    “ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” በማለት ለአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ የተናገረው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ይህን የሚባልበት ምክንያቱን ሲነግረው፥ “እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና” በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ የነቢያት ፤ የአበው ቅዱሳን ሁሉ ተስፋ ሕዝቡን ሁሉ ከኃጢአታቸው የሚያድናቸውን በዘመናቸው ሁሉ በመቃተት ፤ እጅግ በመጠማትም ፈልገዋል፡፡ ዳሩ ግን ከምድር ሊገኝም ፤ ሊሆንም ስላልቻለ እግዚአብሔር ብስራታዊውን ከሰማያት መላክ በፈቃዱ ወደደ፡፡
      እስራኤል በብዙ መሥዋዕት የእንሰሳቱን ደም ፤ ቁርባኑንና ብዙ ጸሎትን ማድረጓ መሲሑን የመፈለግ ብዙ ጥማት ጨምሮባታል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ በብዙ ኃጢአትና ነውር መጠላለፏ ፣ በብዙ ምርኮ ሥር መውደቋና ተስፋዬ ያለችውን ነገር ሁሉ ሞክራ ምንም አለማግኘቷ ትልቁን ተስፋና ቤዛ እንድትጠብቅ አድርጓታል፡፡ ብዙ የተራበ ብዙ መብላት እንደሚመኝ ፣ ብዙ የተጠማ እጅግ መጠጣት እንደሚሻ ፣ እስራኤል በብዙ የፈጣሪን አይኖች ፤ የማዳኑንም ክንዶች በምጥ ተጨንቃ ፈልጋለች፡፡
     እግዚአብሔር እስራኤል ተስፋ ቆርጣ ፤ ነገር ሁሉ ተጠናቆ ሊፈጸም ሲል መልአኩ ገብርኤል ዜና ብስራት ይዞ መጣ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ አጥኚዎች ከነቢየ እግዚአብሔር ሚልክያስ ዘመን ጀምሮ ለአራት መቶ አመታት ያህል እግዚአብሔር ሕዝቡን ሳይናገር ዝም ያለበት ዘመን ነው ይላሉ፡፡ እንዲህ ባሉት ወራት ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ ከእግዚአብሔር ዘንድ ራዕይ ፣ ሕልምና ትንቢት የሚጠብቁ ሕዝቦች ላሏት እስራኤል ቃሉ እንዲህ ይላል፦
      “ …በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ ራእይም አይገለጥም ነበር።” (1ሳሙ.3፥1)
     በእነዚህ ወራት የነበረው ጨለማ ከወትሮው የደመቀና የሚታይም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለአራት መቶ አመታት ዝም አለ ማለት ለመንፈሳዊ ሰው እንጂ እውቀት አለኝ ለሚለው የሚገባ ቋንቋ አይደለም፡፡ አዎ! ተቆጥቶ እንኳ ቢናገረን ይሻላል፡፡ ለጥቅማችን እንጂ ሊያጠፋን አይቆጣምና፡፡ (ዕብ.12፥10)ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ (ዮሐ.20፥26) እንዲል፥ ነገርና ፍጥረት ወደጨለማ በተከተተበት ወራት ጌታ ወደሕዝቡ መልአኩን ልኮ ብስራትን አሰማ፡፡ መድኃኒት ላጣ በሽተኛ መድኃኒትን ማግኘት ምን ያህል እንደሚናፍቅና እንሚያስጠማ ማወቅ ምናልባት ያየው እጅግ ይረዳዋል፡፡ ከዚህም በላይ በነፍስ ነውርና ኃጢአት ለተያዘ ፤ በነፍስ ለምጽ ተመትቶ እጅግ ለረከሰ ሰው ደግሞ ይህ ሕመም መግለጫ ቋንቋ ፈጽሞ አይኖረውም፡፡
     እስራኤል ከግብጽ ባርነት ሲወጡ “ኢያሱ” በሚለው ስም እጅግ ተጽናንተዋል፡፡ በእርግጥም ኢያሱ ከሙሴ በተቀበለው የመሪነት ሥልጣን ሕዝቡን ወደእረፍቱ መርቷቸዋል፡፡ ከርስታቸውም አድርሶ ተስፋይቱውን ምድር አውርሷቸዋል፡፡ “ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ፥  … ” (ዕብ.4፥8) እንዲል ግን ያም ቢሆን የእስራኤልን ልጆች ለመዳን ያላቸውን ጥማት የመለሰላቸውና የከተተላቸው አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ ጌታ በሥጋ ተገልጦ በመጣበት ዘመን እጅግ አስፈሪና ድቅድቅ ጨለማ የነበረ መሆኑን መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡ አይሁድ ጌታ በመጣበት ዘመን በሃይማኖት ረገድ ፈሪሳውያን ፣ ሰዱቃውያን ፣ ሳምራውያን ፣ እሴናውያን ወይም የቁምራን ማህበረሰብና በሚባሉ ሌሎችም ክፍፍሎች ተከፋፍለው ፤ በፖለቲካው ዘንድ ደግሞ በሮማውያን የባርነት ቀንበር ሥር ወድቀው “ገባሮች” የነበሩበት ፣ ሴቶች በቤታቸው መጻተኞች የነበሩበት ፣ ሰው እንደሸቀጥ በባርነት ይሸጥና ይለወጥ የነበረበት ዘመን … ነበር፡፡
     ጌታችን በመጣበት ዘመን ሁሉ ነገር ፈውስ የራቀው ድቅድቅ ነበር፡፡ አንዳንድ ከተሞች እንዲያውም “መልካም ነገር አይወጣባቸውም” የተባሉና ተስፋ የተቆረጠባቸው ከተሞች ናቸው፡፡ (ዮሐ.1፥47)በዚህ ሁሉ ውስጥ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀ የተቈረጠ ነገርን በምድር ሁሉ መካከል ይፈጽማል።” (ኢሳ.10፥23) እንደተባለው ነገር ሊያልቅ ፤ ዘንግ ሊወድቅ በመሰለበት ጊዜ ለምድር ሁሉ የሚሆን ምስራች ኢየሱስ መጣ፡፡
     ኢየሱስ ከምድር ለተቆረጠውና መልስ ለታጣበት ነገር ሁሉ መልስ ሊሆን ከሰማየ ሰማያት መጣ፡፡ እግዚአብሔር ያድናል የሚለው የስሙ ትርጓሜ ኢየሱስ፥ ወደፊት ገና ሊያደርግ የወደደውን ድንቅ ተስፋ በስሙ ተሸክሞት ፤ ገልጦትም መጣ፡፡ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ብዙዎች ኢያሱ በሚለው ስም ቢጠሩም መድኃኒት መሆንን ግን አልቻሉም፡፡ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ አመታት ያህል እልፍ ቅዱሳን ፤ አዕላፍ አገልጋይ ካህናት ፣ የት የለሌ እንሰሳት በምሳሌነት እንጂ በእውነት መሆን ያልቻሉትን መድኃኒት፥ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ አለሙን ሊያድን መጣ፡፡
    ኢየሱስ መድኃኒት ብቻ አይደለም ፤ ክርስቶስ የተባለም ብቻውን ብቃት ያለው አዳኝ ነው ፤ ለዚህም ነው ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ሁሉ ያድናቸዋል የተባለለት፡፡ ከእርሱ በቀር የሕዝቡን ኃጢአት ማስተስረይና ይቅር ማለት የሚቻለው ማንም የለም ፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡ ተስፋ የቆረጠው አለም ተስፋው የተቀጠለለት በሕጻኑ መድኃኒት በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡
    ሕጉ፥ “አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤” (ሮሜ.3፥9) እንዲል ማንም ከማንም ላይበልጥ በኃጢአተኝነት ቀንበር ሥር ወድቋል፡፡ ከቶ ፤ አንድስ እንኳ የተገባ ስላይደለ ኢየሱስ የተገባ ሆኖ ለፍጥረት መድኃኒት ሊሆን መጣ፡፡ መድኃኒት የሚሆን ለራሱ መድኃኒት የማያስፈልገው ንጹሕ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ንጹሕ ያልሆነ ግን ለራሱ መድኃኒት ያስፈልገዋልና መድኃኒት መሆን ፈጽሞ አይቻለውም፡፡ እንዲህ ያለመድኃኒት ከምድር ስለጠፋ ኢየሱስ እርሱ መድኃኒት የማያስፈልገው ጌታ መድኃኒት ሊሆነን መጣ፡፡ ክብር ይግባው፡፡አሜን፡፡
አዎን! እርሱ ብቻ ኢየሱስ ፤ መድኃኒት መባል ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ንጹሕና መድኃኒት የማያስፈልገው መድኃኒታችን ነውና፡፡ የቤዛነትን ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ቤዛ ለመሆን ዕዳ የሌለበት ንጹሕ መሆን ይገባል ይላሉ፡፡ ከሰው ወገን አንድስ እንኳ ማንም ንጹሕ የሆነ ስለሌለ (ሮሜ.3፥10) ንጹሑና ጻድቁ ኢየሱስ ብቻውን ቤዛ ሊሆነን መጣልን፡፡
የሁላችን ጠላት የሆነውን ፤ ነፍሳችንንና ሕይወታችንን የሚያጠፋውን ኃጢአት ሊቀጣና በመቤዠቱም የሰውን ሁሉ ልጅ ሊያድን ስሙ ኢየሱስ የተባለው መጣ፡፡ ስሙ የኃጢአታችን ማስተስረያና መድኃኒት ፤ የደኅንነታችንም ቀንድ ነው፡፡  አረጋዊው ዮሴፍ የሕጻኑን ስም መልአኩ እንደነገረው ኢየሱስ ብሎ ጠራው፡፡ እንዲያ ብሎ ሲጠራው ፈጽሞ አላፈረበትም ፤ ከዚያኔ ጀምሮ ይህ ስም በትውልድ ሁሉ ደምቋል ፤ ገኗል ፤ ተወዷል ፤ ተፈርቷል ፤ ኃጥአንንም ሁሉ በፍቅር ማርኳል፡፡ አዎን! በዚህ ስም የማታፍሩ ደስ ይበላችሁ፡፡ ስሙን ለመጥራት አፋችሁ የሚያያዝ ፤ የምትንተባተቡ ግን ንስሐ ግቡና ተመለሱ ፤ ስሙ አለሙ ሁሉ እንዲድንበት የተሰጠ አቻ የሌለው ስም ነውና፡፡
ኢየሱስ ሆይ! ስምህን እወደዋለሁ ፤ አመልከዋለሁም ፤ ከኃጢአቴ ሁሉ ፈውሶኛል አድኖኛልና፡፡ አሜን፡፡

1 comment:

  1. I have been surfing online more than three hours
    as of late, yet I never found any attention-grabbing article like yours.

    It's pretty value enough for me. In my view, if all webmasters and bloggers made just right content as you
    probably did, the net might be much more helpful than ever before.



    My weblog - throne of spirits hack

    ReplyDelete