Monday 18 January 2016

መንፈስ ቅዱስ በጥምቀቱ በኢየሱስ ላይ ለምን ወረደ?


እንኳን ለጌታችን ጥምቀት መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡
    ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከመንፈስ ቅዱስ የተነሳ ያለወንድ ዘር ፤ ከሴት ዘር  ተወለደ፡፡ (ሉቃ.1፥31 ፤ 2፥6-7) እርሱ በኃጢአት ከወደቀውና በበደሉ ምክንያት ዘሩ ካደፈው አዳም ሳይሆን እኛን ከወንድ ዘር ያይደለ ፤ ከማይጠፋ ዘር ሊወልደን (ዮሐ.1፥13 ፤ 1ጴጥ.1፥23) በልዩና ፍጹም ቅዱስ በሆነ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ተወለደልን፡፡
    ጌታችን ከተወለደ በኋላ በአሥራ ሁለት አመቱ ወደኢየሩሳሌም ለበዓል ወጥቶ ከኢየሩሳሌም ሲመለስ፥ “ … ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር።” (ሉቃ.2፥51) ከሚለው በቀር እስከሠላሳ አመቱ ምን ይሠራ እንደነበርና የት እንደቆየ መጽሐፍ ቅዱስ ዝም ብሏል፡፡ ሠላሳ አመት በሆነው ጊዜ ግን ሊጠመቅና ይፋዊ አገልግሎት ሊጀምር ወደዮርዳኖስ መጣ፡፡ ኦሪት “አንድ ሰው ሙሉ ሰው ነው ፤ ይፋዊ አገልግሎት ሊያገለግል ይገባል” ብላ “ፈቃድ የምትሰጠው” በሠላሳ አመቱ ነውና፡፡ (ዘኍል.4፥47)

   እርሱ ሕግን ሊፈጽም የመጣ ጻድቅ ጌታ ነውና፥ (ማቴ.5፥17 ፤ ሉቃ.2፥39 ፤ ሮሜ.10፥4) እንደሕጉ በሠላሳ አመቱ ወደአደባባይ ወጣ፡፡ በዚያ ወራት መንገድ ጠራጊው ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ የንስሐን ጥምቀት እያጠመቀ ሳለ፥ ኢየሱስ ከገሊላ በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ ከተጠማቂዎች እንደአንዱ ቆሞም ነበር፡፡ ትሑቱ ጌታ በአገልጋዩ መጥምቁ ዮሐንስ እጅ በተጠመቀ ጊዜ ጌታ ኢየሱስ፦“ … የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ ፤ …” (ማቴ.3፥16)“ … መንፈስም እንደርግብ ሲወርድበት አየና ፦…” (ማር.1፥10)“ …መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ … ” (ሉቃ.3፥22)“ … መንፈስ ከሰማይ እንደርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ።” (ዮሐ.1፥32)
     የአራቱንም ወንጌላውያን ምስክርነት ያስቀመጥኩት ለአንድ ብርቱ ቁም ነገር ነው፡፡ ከየት እንዳነበብነው ባይታወቅም መንፈስ ቅዱስ “በርግብ አምሳል ወረደበት” የሚል ትምህርትና መዝሙር እጅግ የተለመደና የታወቀ ነው፡፡ ቃሉ ግን እንደርግብ እንጂ በርግብ አምሳል አይልም፡፡ የምንናገረውና የምናስተምረው በቃሉ ሚዛንነት ካልተመዘነ፥ እኛ የምንናገረው “እውነት ይሆንና” ፍጹም የሆነው የቃሉ እውነት ይዘነጋል፡፡
     እንደርግብ የሚለው መርበቡን ፤ መስፈፉንና መጸለሉን (ዘፍጥ.1፥2) ለማሳየት እንጂ ርግባዊ አምሳልነቱን ለመግለጥ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሕዝቡን ከግብጽ አውጥቶ በምድረ በዳ በመራ ጊዜ ንስር በጫጩቶቿ ላይ እንደምትረብብ (እንደምትሰፍፍ) ፤ ሰፍፋም እንዴት እንደምትጠብቃቸውና እንደምታሳድጋቸው ባለ ምሳሌ ራሱን ገልጧል፡፡ (ዘዳግ.32፥11-12) በእውነትም ሕዝቡን በምድረ በዳ እንደክንፍ ተዘርግቶ የመራቸው እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
    መንፈስ ቅዱስ ለአብም ለወልድም የባሕርይ ሕይወታቸው እንደመሆኑ፥ ከአብ ጋር ባለው ግንኙነቱ የእግዚአብሔር መንፈስ (ዘፍጥ.1፥2 ፤ ማቴ.3፥16) ፤ የጌታ እግዚአብሔር መንፈስ (ኢሳ.61፥1) ፤ የሕያው እግዚአብሔር መንፈስ (2ቆሮ.3፥3) ... በሚለውና በሌሎችም መጠርያዎች የተጠራውን ያህል ከእግዚአብሔር ወልድም ጋር ባለው ግንኙነቱም ልጁ መንፈስ (ገላ.4፥6) ፤ የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ (ፊልጵ.1፥19) ፤ የኢየሱስ መንፈስ (ሐዋ.16፥7) በሚለውና በሌሎችም ቅዱስ ስሞች ተጠርቷል፡፡
     ይህ ቅዱስ መንፈስ በጌታ ጥምቀት ቀን እንደርግብ በጌታ ላይ ሲወርድ ለአለሙ ሁሉ ታይቷል፡፡ ከጌታ ጽንሰት ጀምሮ አብሮት የነበረው መንፈስ ቅዱስ አሁን ለምን ይሆን በጌታ ላይ እንደርግብ ሲወርድ የታየው? ለዚህ ጥያቄ መልሱ አንዱና ዋናው ነገር፥ ጌታ ኢየሱስ ላይ መንፈስ ቅዱስ የወረደው ለአገልግሎት ሊሾመውና ሊለየው ፤ ሊያዘጋጀውም መውረዱን ያሳያል፡፡ አስተውሉ! ጌታ  ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ሰው ፤ ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ይሁንና ሥጋ የለበሰውን መለኮት ለመሲሕነት አገልግሎት ሊያዘጋጅ መንፈስ ቅዱስ መጣ፡፡
   “ … የባሕርይ ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስ በኔ ሕልው ነው ፤ ወዘ በእንትአሁ ቀብዐኒ ስለማስተማርም ያዋሐደኝ መንፈስ ቅዱስ ነዳያንን አስተምራቸው ዘንድ ላከኝ … ሦስት ዓመት ከሦስት ወር መዋዕለ ንስሐን አስተምር ዘንድ ሾመኝ ...” (አንድምታ ወንጌል ቅዱስ ፤ 1997 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት፡፡ ገጽ.282-283)
    አዎን! መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ላይ የወረደው መሲሕ ክርስቶስን ሊቀባው ነው፡፡ እርሱ እንደቀደሙት ነቢያት (1ዜና.16፥22) ፤ ካህናትና (ዘጸ.28፥41 ፤30፥30) ነገሥታት (1ሳሙ.9፥16 ፤ 24፥5-6 ፤ 26፥9) በዘይት የሚቀባ ፤ ለአገልግሎት የሚሾም የሚመረጥም አይደለም ፤ ሊያገለግል ልዩ ሊቀ ካህናት ሊሆን ይገባዋልና በመንፈስ ቅዱስ ተቀባ፡፡
      ጌታ በጽድቅ ሕይወቱ ላደረገው ለየትኛው አገልግሎቱ መንፈስ ቅዱስ ትልቁን ሥፍራ ወስዷል፡፡ የላከውና የሾመው መንፈስ ቅዱስም እንደመሆኑ መጠን፥ ጌታ ኢየሱስ ለመንፈስ ቅዱስ ሃሳብ የታዘዘ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አገልግሎቱ ኀይልን የተቀበለው ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ስብከቱ የተወደደው ፣ ፈውሱ ነቅ ያልነበረው ፣ በመከራው ሁሉ ያልዛተው ፣ በአፉ አንዳች ተንኰል ያልተገኘው ፣ “ከእናንተ ስለኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው?” (ዮሐ.8፥46) በማለት ፍጹም ሰውነቱን የመሰከረው ከመንፈስ ቅዱስ የተነሳ ነው፡፡
    ጌታ ኢየሱስ ያለ መንፈስ ቅዱስ ኀይል አንዳች ነገር አላደረገም ፤ወልድ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት የሚኖር ብቻ አይደለም ፤ በተሠግዎቱ ዘመን ያለእርሱም ኀይል አንዳች የሠራው ሥራ የለም፡፡ ሲጸነስ ከመንፈስ ቅዱስ የተነሳ ተጸነሰ (ሉቃ.1፥35) ፤ እንደሕጉ ወደመቅደስ በወሰዱት ጊዜ ሊሞት እንዳለ መንፈስ ቅዱስ በስምዖን አማካይነት ትንቢትን ተናገረለት (ሉቃ.2፥22-32) ፣ በጥበብና በቁመት በእግዚአብሔር ፊት ያደገው ቃሉን ባሰላሰልን ጊዜ ጥበብና ማስተዋልን በሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ ነው (ሉቃ.2፥52 ፤ መዝ.119፥99 ፤ ኢሳ.11፥1-4 ፤ 42፥1) ፣ ሲጠመቅ ፤ ሲጾምና በምድረ በዳ በነበረ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ጋር ነበር(ሉቃ.4፥1) ፤ ለድሆች ወንጌልን ሲያስተምር ፣ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን ሲሰብክ፥ የተጠቁትንም ነጻ ሲያወጣ ፥የተወደደችውንም የጌታን ዓመት ሲሰብክ መንፈስ ቅዱስ ቀብቶት ፤ ለአገልግሎት ሾሞት ፤ ለይቶት ነው፡፡(ሉቃ.4፥14-19)
    ጌታ ኢየሱስ መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ የዞረው (ሐዋ.10፥38) ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተነሳነው ፤ በተሠግዎቱ ዘመን ሁሉ በምስጋናና በደስታ የተመላው (ሉቃ.10፥21)፤ ራሱን ለቤዛነት ቅዱስ መሥዋዕት በማድረግ ለሞት ያቀረበው (ዕብ.9፥14) ፤ ከሙታን መካከል ኃጢአትን ድል በመንሳት ሞትን የዋጠውና “ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን የተነሳው” ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል፥ “እንደቅድስና መንፈስ” ነው፡፡(ሮሜ.1፥3 ፤ 1ጴጥ.3፥18)፡፡
     እርሱ ጌታና አምላክ ሲሆን በለበሰው ሥጋ አባቱን ፍጹም ለማስደሰት ፍጹም የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል አስፈልጎታል፡፡ እንኪያስ እኛስ እጅግ የተሳሰረ ፤ የተሰናሰለ ፍጹም የሆነ ሕብረት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሊኖረን አይገባምን?! እጅጉን ይበልጥ እንጂ!!!
     አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሰውን ልጅ በማዳን በማይነጣጠል አንድነትም ፤ በየራሳቸውም ተሳትፈዋል፡፡ አብ ወልድን ለመሥዋዕትነት ሲመርጥ ፤ ወልድ ደግሞ መሥዋዕት ሊሆን ራሱን በታዛዥነት አቅርቧል ፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ወልድን ቀብቶታል ፤ ፍጹምም ሾሞታል ፤ እንዲሁም በምድር የሠራውን ሥራ በማጽናት ፤ ለፍጥረትም ሁሉ በመናኘት እስከአሁን ሕያው አድርጎታል፡፡ የክርስቶስ ደም ሕያውና ቅዱስ ሆኖ ዛሬም በአብ ፊት ስለእኛ ለመታየቱ ትልቁ ምስጢር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
      ጌታ ኢየሱስ በተሠግዎቱ የተገባ ሊቀ ካህናት ይሆን ዘንድ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያስፈልገው ዘንድ ይገባዋል፡፡ (ማቴ12፥28 ፤ ሉቃ.4፥1 ፤ ሮሜ.8፥11 ፤ ዕብ.9፥14) ለዚህም የተገባ ሆኖ ተገኘ፡፡ ከዚህም የተነሳ ለአባቱ መንግሥት ሕዝብን አበዛ ፤ ምርኮንም አፈለሰ፡፡
      ይህ የጌታ የጽድቅ ሕይወት ለክርስቲያን ተከታዮቹ ፍጹም የሕይወት ምሳሌ ነው፡፡ የጌታን የጽድቅ ሕይወቱን እንድንመላለስበት ተጠርተናል፡፡ የጌታ ኢየሱስን ሕይወት ልንኖረውና ልናደርገው የማይቻለን የሰውን ልጅ ለማዳን የተቀበለውን የቤዛነት መከራውን ብቻ ነው፡፡ በምድር ኖሮ ያሳየንን የጽድቅ ሕይወት ግን እንመላለስበት ዘንድ ተጠርተናል፡፡ (1ጴጥ.2፥21) ለዚህም ኃይልና ብቃታችን መንፈስ ቅዱስ ነውና እያንዳንዱ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ የተመላ ሕይወት ሊኖረው ይገባል፡፡
በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማኅተም ከታተምንና ልጅነትን ካገኘን በኋላ በእምነት በሚሆነው ማደግ፥ በመንፈስ ፍሬ ልናድግና ልናፈራ (ገላ.5፥22) ይገባል እንጂ፥ “ለቤዛም ቀን የታተምንበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ ልናሳዝነው” (ኤፌ.4፥30) ፣ ልንዋሸው ወይም ልናታልለው (ሐዋ.5፥1-11) ፣ ልንሰድበው (ማቴ.12፥32 ፤ ራእ.13፥6) ፣ ልንቃወመው (ሐዋ.7፥51) አይገባም ፤ ይልቁን እንደጌታ ኢየሱስ ልንታዘዘው ፤ እሺ በማለት ልንገዛለት ይገባናል፡፡
      መንፈስ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን ዋና ነገር ነው ፤ ሙሽራው ኢየሱስ በምድር በነበረበት ዘመኑ የሥራው ሁሉ ውበት መንፈስ ቅዱስ ነው ፤ ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያንም ዋናና ልትረሳው የማይገባት ጌጥና ሽልማቷ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ያለመንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን፥ ቤተ ክርስቲያን ልትባል አትችልም፡፡ አማኝም የመንፈሳዊ ቅድስና መጠበቂያው ትልቅ ኃይሉ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የአገልግሎትም ትልቅ ውበት መደመጥና ደጋፊ ማብዛት ፤ በየሚድያውና በማኅበራዊ ድኅረ ገጻት የሰዎችን ስም ማጥፋት አይደለም ፤ የአገልግሎት ትልቁ ሚስጢር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ እርሱ አገልግሎታችንን ከመራ ሰዎች ወደ እኛ ሳይሆን ወደጌታ ቀራንዮ ማንም ሳይጠራቸው ይሰበሰባሉ፡፡

      ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ልባችንን ለእውነት ስላስጨከንህ እናመሰግንሃለን፡፡ አሜን፡፡

4 comments:

  1. May God bless you our beloved brother. Thank You for the truth.

    ReplyDelete
  2. አረ ቅቤው የጻፍከውን ኑፋቄ ልብ ብለኸዋል? መንፈስ ቅዱስ ጌታን ሊያከብረው ሊሾመው ነው በርግብ አምሳል የታየው?
    ከጽንሰቱ ጀምሮ አብሮት የነበረው መንፈስ ቅዱስ አልክ ከጽንሰቱ በፊትስ አብሮት አልነበረም?
    መንፈስ ቅዱስስ ለምን በርግብ ተመሠለ?
    .

    ReplyDelete
  3. መጀመሪያ ተማር ከዚያ ትጽፋለህ እሽ?

    ReplyDelete
  4. ያላዋቂ ሳሚ________________ ፡፡
    ያሉት ይኸንን ነው፡፡ ለምን መጀመሪያ የማስተዋል ጥበብን በደንብ አትማርም አስቀድመኽ የኑፋቄ መርዝኽን ከምትዘራ?

    ReplyDelete