Tuesday 12 January 2016

ወንድሜ ማን ነው? (ክፍል ሦስት)




                                     ዮሴፍና የአባቱ ልጆች ተገናኙ፤

     ምድር ሁሉ በረሃብ በተያዘችበት ዘመን እግዚአብሔር ዮሴፍን በግብጽ ምድር ሀገረ ገዢ አድርጐ፥ ጥበብን ሰጥቶ እህልን አከማቸ፡፡ ያዕቆብ በግብጽ እህል እንዳለ ሲሰማ፥ (ዘፍጥ.42፥1) ልጆቹን ወደዚያ ላከ፡፡ ብንያም ከቤት ቀርቶ አሥሩ “ወንድሞች” ተነስተው ወደግብጽ ወረዱ፡፡ እግዚአብሔር በጊዜው ሊሠራ፥ እነርሱ ከእግዚአብሔር ሃሳብ “ገፋንህ” ብለው ዮሴፍን ወደክብር ሰገነቱ እያስቸኮሉ አቀረቡት፡፡
     ግብጽ ሲደርሱ ሰገዱለት ፤ የዮሴፍ ሕልም ተፈጸመ፡፡ እርሱ አወቃቸው እነርሱ አላወቁትም፡፡ አውቆም ተለወጠባቸው ፤ እነርሱ ግን ለጠየቃቸው ጥያቄ በብዙ መሃላ ሊያስረዱት ፈለጉ፡፡ ሐሰተኞች ሆነው እውነተኞች ነን አሉ ፤ ከፊታቸው ያለውንና ቆሞ የሚያወራቸውን ወንድማቸውን ጠፍቷል ብለው ተናገሩ፡፡ (ዘፍጥ.42፥13)

     “ወንድሞቹ” ከብዙ ዓመት በኋላም ያው ያልተለወጡ ፤ ውሸታሞች ነበሩ፡፡ ዮሴፍ በብዙ መንገድ የአባቱን ልጆች ሲፈትናቸው፥ ከትላንቱ ዛሬም የተሻለ ማንነት የላቸውም፡፡ ይህ ዮሴፍ የታመመበት ሕመም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከአባቱ ልጆች መካከል ወንድም ፍለጋ ይንከራተታል ፤ ግን ደግሞ ፈልጎ ፤ ፈልጎ ያጣል፡፡ ፈላስፋው ዲዮጋንስ በእኩለ ቀን መብራት ይዞ ምን ትፈልጋለህ? ሲሉት “ሰው”  ቢል፥ “ይሄ ሁሉ ሰውስ?!” ቢሉት፥ “ሰው ነው የምፈልገው!” እንዳለው ፤ ዮሴፍ ከነዚህ መካከል “ወንድሜ ማን ነው?” ብሎ ባዘነ፡፡
    ዮሴፍ የተሸጠው በአሥራ ሰባት አመቱ ነው (ዘፍጥ.37፥2) ፤ በግብጽ የነገሰው ደግሞ በሠላሳ ዓመቱ ነው፡፡ የጥጋቡ ዘመን ሰባት ዓመት ሲሆን፥ የአባቱ ልጆች ወደግብጽ የመጡት የረሃቡ ዘመን ሲጀመር ነው፡፡ ይህን ስናሰላ ሐያ አመት ሙሉ ማለትም ሁሉም ከአርባ ዓመት በላይ እንኳ ሆኗቸው ሰው ፤ ሰው፥ ወንድም ፤ ወንድም አይሸቱም ነበር፡፡ በእርግጥም ያለመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እውነተኛ ወንድም መሆን አይቻልም፡፡
      ዮሴፍ፥ ከመካከላቸው ስምዖንን ይዞ፥ “ትንሹን ካላመጣችሁ” አላቸው፡፡ በኃጢአታቸው ሊናዘዙ አልወደዱምና ዘወትር ከጉድለት መንገድ ፈቀቅ አይሉም፡፡ ስምዖንን ከግብጽ ምድር ትተው እህላቸውን ይዘው ሄዱ፡፡ ያዕቆብ አሁንም ስምዖንን ጥለው ሲመጡ እኒህ ልጆቹ ለትልቅ ኃላፊነት ፤ ለበረከት እንደማይበቁ ሳያስብ አልቀረም ፤ ነገር ግን መለወጣቸውን ናፍቆ እየጠበቀ ነው፡፡ ያዕቆብ የሚባረክ ልጅ ሲፈልግ ፤ ዮሴፍ እውነተኛውና የተለወጠ ወንድሜ ማን ነው? እያለ በብዙ ይፈልጋል፡፡
     በዓመቱ ምግቡ አለቀና አሁንም ቀለብ እንዲሰፍሩ ያዕቆብ በነገራቸው ጊዜ፥ ያ ሰው ያላቸውን አስታወሱ፡፡ የስምዖንን መታሰር አስበው፥ ያ ሰው ብንያምን ካላመጣችሁ ማለቱን በነገሩት ጊዜ ያዕቆብ፥ “…ልጅ አልባ አስቀራችሁኝ ዮሴፍ የለም፥ ስምዖንም የለም፥ ብንያምንም ትወስዱብኛላችሁ ይህ ሁሉ በእኔ ላይ ደረሰ።” (ዘፍጥ.42፥36) በማለት ልብ የሚነካ ንግግር ተናገረ፡፡
      እኒህ የአባቶች አለቃ (ሐዋ.7፥9) ለምን ይሆን የአባታቸውን ሰቆቃ እያዩ ያልራሩለት? ልጅ በተነሳ ቁጥር፥ ያዕቆብ ሲንገበገብና ውስጡ ሲቃጠል ምነው አንዳቸው እንኳ አልደነገጡም? በእውኑ የልጅን ጣዕም ከገዛ ልጆቻቸው አያውቁትምን? አዎ! የሮቤል ንግግር ይህን ገላጭ ይመስላል፡፡ “ወደአንተ መልሼ ያላመጣሁት እንደሆነ ሁለቱን ልጆቼን ግደል እርሱን በእጄ ስጠኝ፥ እኔም ወደአንተ እመልሰዋለሁ።” የሮቤል ንግግር ስንፍና ነበር፡፡ አንድ ስምዖንን ለማዳንና ለማምጣት ሁለት ልጆቹ እንዲገደሉ ወደደ፡፡ ምናልባት የገዛ ልጆቻቸውን የሚያበላልጡቱ የዚህ ዘመን ወላጆች ዘመናቸውን ዘወር ብለው ቢያዩ መልካም ነው፡፡
     ያዕቆብ ግን የልጅን ፍቅር በሚገባ ያውቀዋልና በቁጣ የመለሰለት ይመስላል፦ “ልጄ ከእናንተ ጋር አይወርድም ወንድሙ ሞቶ እርሱ ብቻ ቀርቶአልና በምትሄዱበት መንገድ ምናልባት ክፉ ነገር ቢያገኘው ሽምግልናዬን በኅዘን ወደመቃብር ታወርዱታላችሁ።” በዚህ ሁሉ ንግግር ውስጥ ያዕቆብ የልጆቹን መብሰልና አለመብሰል በሚገባ እያሰላሰለ ነበር፡፡
     ረሃቡ እጅግ ጸና ፤ ተነስተው እንዲሄዱ ያዕቆብ ቢናገራቸውም እነርሱ ግን በግብጽ ያለው ሰው የተናገራቸውን አሰቡ ፤ ወንድማችንን ይዘነው ካልሄድን “ፊቴን አታዩትም” ብሎን ተናግሮናል ብለው ለአባታቸው ነገሩት፡፡ ያዕቆብ እጅግ ልብ በሚሰብር ስሜት ተናገረ፥ የዚህን ጊዜ ይሁዳ እንዲህ አለ፦ “እኛና አንተ ልጆቻችንም ደግሞ እንድንድን እንዳንሞትም ብላቴናውን ከእኔ ጋር ስደደው፥ እኛም ተነሥተን እንሄዳለን። እኔስ ለእርሱ እዋሳለሁ ከእጄ ትሻዋለህ ወደአንተ ባላመጣው፥ በፊትህም ባላቆመው፥ በዘመናት ሁሉ አንተን የበደልሁ ልሁን።” (ዘፍጥ.43፥8-9) ያዕቆብ የዚህን ጊዜ ወዲያውኑ ወንድማቸውን ይዘው እንዲሄዱ ተናገረ ፤ ለምን?
1.     እስከአሁን የነበረው የያዕቆብ ልጆች ንግግር የስንፍና ንግግር ነው፡፡ የይሁዳ ንግግር ግን የተለወጠና ኃላፊነትን ለመውሰድ የተዘጋጀ ጽኑ ንግግር ነው፡፡
2.    ይሁዳ የትላንቱ ይሁዳ አይደለም ፤ ትላንት ወንድሙ እንዲሸጥና ርቆ እንዲሄድ ገንዘብን አብልጦ ወንድሙን አሳንሶ ሃሳብ ያቀረበውና ወንድሞቹን ያስማማው ይሁዳ ነበር፡፡ ትላንት ይሁዳ ለወንድሙ ራሱን አሳልፎ ያልሰጠ ፍቅረ ነዋይ አፍቃሪ ነበር፡፡
     ዛሬ ግን ይሁዳ ራሱን አሳልፎ ለወንድሙ ሰጠ፡፡ ወንድሙ እንዲሸጥ ወንድሞቹን ያስማማው ይሁዳ ፣ በትዕማር በግብዝነቱና በአመንዝራነት ኃጢአቱ የተሰናከለው ይሁዳ በትልቅ ንስሐ ራሱን ቀደሰ፡፡ ለወንድሙ ስሜት አልባው ይሁዳ ለወንድሙ ሕይወት ተያዥና ባለዋስ ሆነ፡፡
3.    ይሁዳና ወንድሞቹ ትላንት፥ ዮሴፍ ሞቷል ፤ አውሬም በላው ብለው ቀሚሱን በፍየል ደም ነክረው ወደአባቱ ሲልኩ አንዳች ርኅራኄ ያልተሰማው ሰው ነበር፡፡ አባቱን ሲያጽናኑትም እንቢ እንዳለ ያስተዋለ ሰው ነበር ፤ ይሁዳ፡፡ (ዘፍጥ.37፥35) አሁን ግን ለአባቱ በፍጹም ርኅራኄ ራራ ፤ ጥልቅ በሆነ ስሜትም እንደንስሐ ተጸጽቶ ተናገረ፡፡ (ዘፍጥ.44፥18-34)
    ኦ! ይሁዳ እጅግ ውድ ታላቅ ወንድም!!!
     ዮሴፍ የይሁዳን ቃሎች ከሠማ በኋላ “ዮሴፍም በእርሱ ዘንድ ቆመው ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊት ሊታገሥ አልተቻለውም፡፡ … ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ …” (ዘፍጥ.45፥1-2) በእርግጥም ትላንት የሸጠው ወንድሙ ስለወንድምነት ፍቅር ተዋሽ ሆኖ ፤ ፍጹም ተለውጦ ቢያየው አላስችል ብሎ አለቀሰ፡፡ ትላንት ደንታ ቢስ የነበረው ይሁዳ ዛሬ በጽኑ መሃላ ስለወንድሙ ራሱን በማሰር (በማማል) ኃላፊነትን የሚወስድ ሆነ፡፡
    ይሁዳ ራሱን በመሃላ አስሮ ለወንድሙ ኃላፊነትን ወሰደ፡፡ ዛሬ በመካከላችን ያለው ትልቁ ችግር ኃላፊነትን የሚወስድ ብርቱ ወንድም ማጣት ነው፡፡ እርግጥ ነው ትላንት ሁላችንም ደካሞችና በብዙ ውድቀት ውስጥ የነበርን ነን ፤ (ኤፌ.2፥1) ጌታ እግዚአብሔር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በገባልን ጽኑ መሃላ (ዕብ.6፥17-18) ለወንድሞቻችን ኃላፊነት የሚሰማን ወንድም እንድንሆን ይወዳል፡፡
     አዎ! ወንድም ኃላፊነትን የሚወስድ ጠንካራ ነው!!!  እኛ የገዛ ወንድሞቻችንን ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ ነን? አስበነውስ እናውቃለን?
ጌታ እግዚአብሔር በቅዱስ መንፈሱ ማስተዋለን ያድለን፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል...

No comments:

Post a Comment