5. እግዚአብሔርፍርድያደላድላል፤
“ … ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል ፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው
አዋርዶአል ፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል” (ሉቃ.1፥51-52)
|
ብዙዎቻችን የክፉዎችን
ክፋት አይተን፥ ለእግዚአብሔር ከማሳሰብና በፊቱ ጥቂት ከመታገስ ካለመቻልም በላይ፥ በብዙ ማጉረምረም የተጠመድን ነን ፤ በውጪው
አለም የሚኖሩ እልፍ አዕላፍ ዲያስፖራዎቻችንና አገር ቤትም ያሉ ጥቂት የማይባሉ ወገኖች መንግሥት በመክሰስ የተጠመዱ ናቸው፡፡ አንድ
ነገር እንደአማኝ እጅግ አምናለሁ ፥ መንግሥት ያጥፋም ፤ አያጥፋም ከሁሉ በፊት ጸሎት እንደሚገባው (1ጢሞ.2፥1-2) ፤ የሚያጠፋ
ከሆነም ደግሞ በአገባቡ ሊመከር ፣ ሊወቀስ ፣ ሊገሰጽ እንዲገባው
አምናለሁ፡፡ ይህን ሳያደርጉ ከመሬት ተነስቶ ቱግ ማለት ከድንግል ማርያም የምስጋና ቃል አለመማር ነው፡፡
ባለፈረሱና ፈረሰኛው ፈርዖን ከነትዕቢታቸውና አለማመናቸው በባህር የሰጠሙት
(ዘጸ.15፥19) ፣ በጦሩ ብዛት የተመካው ሰናክሬም የተዋረደው (2ነገ.18፥19-29) ፣ በልቡ የትዕቢት እጅለት ስብዕናውን ያጣው
ናቡከደነጾር (ዳን.4፥30) ፣ በትዕቢቱ በትል ተበልቶ የሞተው ሄሮድስ (ሐዋ.12፥23) ፤ የተናቀውና የተረሳው ዳዊት የታወሰውና
ከፍ ከፍ ያለው (1ሳሙ.16፥11-13) ፣ የተገፋው ሕዝቅያስ በክብር ያደገደገውና ተስፋው የለመለመው (2ነገ.19፥1-6) ፣ የተናቁት
የገሊላ ሰዎች የአዲሱ ኪዳን ባላደራዎች የሆኑት (ሐዋ.2፥7) ፣ ጭንጋፉ ሳውል የተወደደ ሐዋርያ የሆነው (1ቆሮ.15፥8) በትህትና
ጉልበት ነው፡፡ ድንግል ማርያምም ራስዋን እንደባርያ ቆጥራ ዝቅ በማድረግ በትህትና ስትቀርብ እናያታለን፡፡
ትህትና የትዕቢት
ተቃራኒ ነው፡፡ ዲያብሎስ አገልጋይ ሆኖ ሳለ፥ “ከእኔ በላይ ሌላ የለም” በሚል ትዕቢት ስለተያዘ ከታላቅ ክብሩ ወደቀ፡፡ ብዙ ጊዜ
በትዕቢት መንፈስ የምን ያዘው የአገልጋይነትን መንፈስ ስለምን ዘነጋና በአገልጋይነት መንፈስ መኖርን እንደታናሽነት ወይም እንደመዋረድ
ስለምንቆጥረው ነው፡፡ ክብርን ወይም ከበሬታን በዝቅታ ከማግኘት ይልቅ አለልክ ከፍ ከፍ ከማለት ማግኘት እንፈልጋለን ፤ ነገር ግን
ክብር እንዲህ ባለ ሥፍራ የለችም፡፡
እግዚአብሔር በልጁ
በኢየሱስ ክርስቶስና (ማቴ.11፥29) በቅዱሳኑ ያየውን ትህትና በእኛም ሕይወት ማየት ይፈልጋል፡፡ በእርሱ ፊት ራሳችንን ብናዋርድ
ለራሳችን ጥቅም ነው፡፡ ትሑት ብንሆን ጸጋ የሚበዛልን ለእኛው ነውና፡፡ ትዕቢተኞች ብንሆን ግን እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ፈጽሞ
ይቃወማል፡፡ (1ጴጥ.5፥5)
እግዚአብሔር
“የትዕቢተኞችን ሃሳብ ይበትናል”፡፡ ዲያብሎስ አንድን ሰው ለመጣል ሲያስብ ቀጥታ ወደሃጢአት ድርጊት አይመራውም ፤ ቅድሚያ “
…. ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ፥ … ” (ዮሐ.13፥2) እንዲል ቅድሚያ
ሃሳቡን ያበላሸዋል ፤ ማለትም በሃሳቡ ለኃጢአት ተላልፎ እንዲሰጥ ሰፊ በር ይከፍታል፡፡ የትዕቢተኞች የክፋት ሃሳብ ጥልቅ ነው ፤
ሰናዖራውያን ከምድር ዝፍጥ ጭቃ ሕንጻን መገንባት ሲጀምሩ እግዚአብሔር ሃሳባቸውን አየ ፤ በሃሳባቸውም “ትልቅ ለመሆን ፤ ለመብለጥ
፤ ከእኛ በቀር” በሚል መንፈስ “ … ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ ፤ በምድር ላይ ሳንበተን ምስማችንን
እናስጠራው” (ዘፍጥ.11፥4) የዚህ ሕዝብ ትልቁ አላማ በትዕቢት ራሳቸውን ከፍ ከፍ ለማድረግ ማሰባቸው ነው፡፡ ስለዚህም “እግዚአብሔርም
ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው” (ቁ.8)
ድንግል ማርያም
“ሃሳባቸውን በትኖአል” ስትል፥ ነገረ ሥራቸውን ከመነሾው ገለበጠ ማለቷ ነው፡፡ አጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ መርዶክዮስ ላይ በትዕቢት
ተነሳስቶ በማን አለብኝነት ደግሞ በወገኖቹ አይሁድ ሁሉ ላይ ሞትን ሲያሳውጅ ሃሳቡ ከመነሾው እንደተገለበጠ አላስተዋለም ነበር፡፡
ትዕቢት የማንችለውን እችላለሁ ሲያስብል ፤ ትህትና ግን የምንችለውንና የምናውቀውን እንኳ ራስን በሚገዛና በድኻ መንፈስ ዝግ ማለትን
ታስተምራለች፡፡ ድንግል ማርያም ይህን የጸሎት ክፍል ስትናገር እጅግ በጣም በትሁት ልብ አጎንብሳና ተዋርዳ ነበር፡፡
በመንፈሳዊው አለም
አብዝተን ልንጠነቀቅ የሚገባን ሃሳባችንን ነው፡፡ የሃሳብ በር መዝጊያው ደግሞ ከእግዚአብሔር ፊት የሚደረግ ትጉ ጸሎት ነው፡፡ ብዙ
ጊዜ የማንጠብቃቸውና እንዲህ አይሆኑም የምንላቸው ሰዎች ወድቀውና የቀደመ ሃሳባቸው ተበትኖ ተለውጦ የምናያቸው “እባብ በተንኮሉ
ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና በመለወጡ” ምክንያት ነው፡፡ (2ቆሮ.11፥3) እግዚአብሔር
ይህን ሃሳብ በእርግጥ ይበትነዋል፡፡
ትዕቢት “ትልቅ
ነኝ ፤ ሁሉን እችላለሁ” የሚል ክፉ ሃሳብ ስላለበት ለትንሹም ኃጢአት ተላልፎ የመሰጠት ሂደቱ ሰፊ ነው ፤ ትህትና ግን ራስን ለሚበልጠው
ማንነት አሳልፎ መስጠት ነውና ኃጢአት ለመሥራት የሚያስደፍር ማንነት የለውም፡፡ በሌላ ንግግር እውነተኛ ትህትና ለኃጢአት አቅም
ማጣት ነው፡፡ ዲያብሎስ በአምልኮ መንፈስ በመገዛት ራሱን ዝቅ በማድረግ ቢገዛ ፤ ለትልቁ ኃጢአት ለትዕቢት ተላልፎ ባልተሰጠ ነበር፡፡
አዎን! እግዚአብሔር
ፍርድ አደላዳይ ነው ፤ ትዕቢተኞችን ያዋርዳል ፤ ለትሁታን ደግሞ ጸጋን ይሰጣል፡፡ አሜን ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡
No comments:
Post a Comment