Sunday, 28 June 2015

ስለግብረ ሰዶማዊነት ከአየርላንድ ስህተት ምን እንማራለን?

     
                            Please raed in PDF                        

   ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል ልጆች ከግብጽ በወጡ ጊዜ እርሱን በማክበርና በመፍራት እንዲያመልኩት በዓላትን ሰጥቷቸዋል፡፡ ከተሰጡት በዓላት መካከል ደግሞ የፋሲካ ፣ የመከርና የዳስ በዓላት የትኛውም እስራኤላዊ ከሚኖርበት ከስደት ምድሩ በመምጣት በእስራኤል ምድር ተገኝተው እንዲያከብሩ አዟቸዋል፡፡ (ዘጸ.23፥14፥17) በእነዚህ የበዓል ወራት የእስራኤል ጎዳናዎች ሁሉ የሚሸቱት እጅግ የተወደደውን የመንፈሳዊነትን ለዛና ዝማሬ ነው፡፡
      ከጥቂት ዓመታት በፊት በካቶሊክና በፕሮቴስታንት ጎራ ክርስትናዋን ከፍላ ጎዳናዎቿን በደም ያጨየቀችው አየርላንድ ፤ አሁን በጎዳናዎቿ የተሰማው ነውር ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነው፡፡ ግብረ ሰዶምን በወንጀል ህጓ ጠቅሳ በመከላከልና ለጋብቻ ባላት እሴቷ በአገራችን ካለው ሕግና እሴት ጋር እጅግ የተቀራረበ ነበር፡፡ አየርላንድ በወንጀል ህጓ በግልጥ ግብረ ሰዶምን መከልከል ብቻ ሳይሆን ፈጽመው የተገኙትንም ትቀጣ ነበር፡፡

     ነገር ግን ይህን እውነት ለመገልበጥ ከውጪ ያሉት ዜጎቿ ሁሉ፥ አገር ቤት ካሉት ጋር በአንድነት ተሰባስበው ስለግብረ ሰዶም “መልካምነትና ቅዱስነት” አወጉ ፤ አውግተውም ዝም አላሉም ፤ ጋብቻን  “No”፥ ግብረሰዶምን ደግሞ  “Yes” በማለት ድምጽ ለመስጠትና አብላጫ ድምጽ ያገኘው ሕግ ሆኖ ሊጸድቅና ሊደነግጉት፡፡ መልካም ባህልና ሕግ እያላቸው ይህንን በመናቅ ለአለም ክፉና የስህተት መንገድ መገለጫ ሆነው ታዩና ፥ ግብረ ሰዶምን “Yes” ብለው አጸደቁት፡፡
     መልካሙ የጋብቻ እሴቷና ግብረ ሰዶምን የከለከለው የወንጀል ሕጓ እንደመርገም ጨርቅ ማንም ላይነካው ረከሰ፡፡ የቀደመው ትውልድ “የጠበቀውንና ያስተላለፈውን የጋብቻና ሃይማኖታዊ እሴት” አዲሱና እንግዳው ትውልድ በሚበዛ ቁጥር መረዘው፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጋብቻ የኋላቀርነትና የአላዋቂነት ድርጊት ተደርጎ ግብረ ሰዶም “ትክክለኛና ለሁሉ እንደተገባ ድርጊት” ተቆጥሮ “ይሁንልን ፤ ወደነዋል” በማለት ጸደቀ፡፡ ይህንን ዜና እንደምሥራች ይሁን ሌላ ምንነቱ ባልታወቀ መንፈስ ቢቢሲና አልጀዚራና ሌሎችም አራግበውታል፡፡
       ይህንን ወደአገራችን እውነት ስናመጣ ፤ እንደአክራሪነት መንፈስ የግብረ ሰዶማውያንም መንፈስ የታመቀ መንፈስ ብቻ አለመሆኑን ድርጊታዊ ምልክቶቹን  በየዋና ከተሞች እያየን ነው፡፡ በአዳማ ናዝሬት ከተማ አንድ ግለሰብ የግብረሰዶምን ጥቃት በተለያዩ ዘጠኝ ሕጻናት ላይ (ይህ በምስክር የተረጋገጠ እንጂ ሌሎችም እንደሚኖሩ ይገመታል) መፈጸሙን ፤ በሐረር በአንድ የታወቀ ሆቴል ውስጥ ከዘበኛ ጋር ተስማምቶ ተከራይን የደፈረ ግብረ ሰዶማዊ … እና ሌሎችም ድርጊቶች አደገኛ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
      አየርላንድ ምናልባት ያን የሚያህለው መልካም እሴቷ በአንድ ጊዜ ከአመድ የተደባለቀው ፤ “ተጽዕኖ ፈጣሪ” እንደሆኑ የሚያስቡቱ “ ዲያስፖራዎቿ” የሠሩት ሥራ ቀላል እንዳልሆነ በስፋት ይነገራል፡፡ ይህንን ቀጥታ አንዳንድ ከማለት ወደሚያልፉ የአገራችን ዲያስፖራዎች ብናወርድ አስፈሪ ነገር እንዳለው ለማሰብ ብዙ አያታክትም፡፡ የጎዳና ወንዶች ህጻናት በብዙ ብር ሲሸጡና ለዚህ ነውር ሲማገዱ እየሰማን ነውና፡፡ በተለይም አሁን እኛ አገር በአንዳንድ ገዳማት ነዋሪ በሆኑ መነኮሳት አከባቢ ፣ “እንደታወቁ” በሚያስቡ አገልጋዮች ዘንድ ፣ በማረሚያ ቤቶች ፣ ማሳጅ ቤቶች ፣ ሆቴሎችና ሞቴሎች ፣ አዳሪ ትምህርት ቤቶች … ካለው ነገር ሲደመር ቁጥሩ ላለማሻቀቡ መተማመኛ የለም፡፡  ብዙ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ስለመሆኑም ማቅማማት አያሻም፡፡
     የግሎባሌይዜሽን አንዱና ዋና አሉታዊ ተጽዕኖው፥ ተመሳሳይ ኃጢአቶችን በአንድ ጊዜ ማዛመት ፣ “በመጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአት ለመሆናቸው የተረጋገጡ ተግባራትን እንደመብት ሊሰብክ እንደሚችል ፣ በተለይ የባህል ተጽዕኖው በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ፈተና ስለመሆኑ ፤ ይህም የሆነው የባህል አንጻራዊነት (Cultural relativism) ሁልጊዜ ያለ ቢሆንም የድሃ አገራት ባህል በሀብታም አገራት ተጽዕኖ ሥር ሊወድቁ መቻላቸውንና በዚህም የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ከባድ መሆኑን የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር በአንድ ጽሁፉ አስፍሮ ነበር፡፡ (“የአብያተ ክርስቲያናት ትብብር ለሰላምና ለልማት” ሰኔ 16 2004 ዓ.ም.፡፡(መጽሔት))
      ከድህነት ማዕቀፍ ያልተላቀቁ አህጉራት እንደዋና አስፈላጊ ምግብ በብዛት ከምዕራቡ አለምና ከእኛም “ምግባረ ቢስ ወገኖች” እየቀረበላቸው ያለው ሕልውናቸውን የሚሽር ባዕድ ነገር ነው፡፡ ከሚቀርቡት ገፍ አስነዋሪ ድርጊቶች መካከል ግብረ ሰዶም በአሁን ሰዓት የቀዳሚነቱን ሥፍራ እየያዘ ነው፡፡ በአገራችን በአንድ ቤተ ክርስቲያን ከውጪ የሚገኝ ዕርዳታን ለመቀበል እንደአስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ “የግብረ ሰዶምን ጥቃት በዝምታ” ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትቀበል የሚል ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱም የግብረ ሰዶምን ሃሳብ ከመርገም ጋር ባለመቀበሏ ምክንያት የመጣው ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ መመለሱን ሰምተናል፡፡
     እንግዲህ “መስማትን ጆሮ ያለው ይስማ!” እንዲል መጽሐፍ ለጎረቤት የመጣ የኃጢአት ግብዣ “ለእኛም አይመጣም” ብሎ መዘናጋትና መቀመጥ አገባብ አይመስለኝም፡፡  ይልቁን እኛው ቤት (በመካከላችን) የሚንቀለቀል የግብረ ሰዶም እሳት እንዳለ ደጋግመን ብዙ ብለናል፡፡ እንኪያስ አጥርተን መስማትና መሥራት ያለብን ጊዜ ላይ አይደለንንምን?
     የምዕራቡን አለም ማህበረሰብ  መልካም የትዳር እሴት ከአፈር የደባለቁትና ያረከሱት፥ የነሲግመን ፍሮይድ ደቀ መዛሙርት የነበሩት “የእኛዎቹ” እነስብሐት ገብረ እግዚአብሔርና ሌሎች በትውልዱ ላይ በጽሁፎቻቸው በግልጽነትና በመብት ተገንነት የለቀቁት “ስድነትና መረን የለሽነት” ከሴሰኝነት ፣ ከአመንዝራትና ከልቅ ወሲብነት ወደግብረ ሰዶማዊነት ለመሸጋገር “የተከፈተ በር” ሲያዘጋጁ “ዝም ማለታችን” የልብ ልብ እንዳይሰጥ ደግመን ማጤኑ በጎ ይመስለኛል፡፡
    አስተውሉ! የተቀጣጠለ እሳት ላይ ቤንዚን አርክፍክፎ የባሰ ማጋጋም ሊኖር እንደሚችል አየርላንድ ምሳሌ ትሆነናለች ብሎ ማንሳት ይቻላል፡፡ ቀጣዩ ትውልድ ለቅዱስ ጋብቻና እሴቱ እንግዳ ትውልድ ሆኖ ልቡ ወደግብረ ሰዶም እንዳያደላ ዛሬ ላይ በብዙ መሥራት እንዳለብን የሚጮህ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው፡፡  ጎዳናዎቻችን ነገ እንደአየርላንድ የሰዶማውያንን ጩኸት እንዳታስተናግድና እንደእስራኤል ልጆች በመልካምና ቅዱስ ለቃሉ በመታዘዝ በሚገኝ ደስታ የእግዚአብሔር በዓልን በማክበር በልዩ መዓዛ ለማወድ ገና ያልተጀመረ የቤት ሥራችንን ሳይረፍድ መጀመሩ ይረባናል፡፡
ጌታ ሆይ! እባክህን ወደልባችን መልሰን፡፡ አሜን፡፡

    

2 comments:

  1. መቸም ይሔው የመጣው ከፕሮቴስታንቶች አካባቢ ነው።አሜሪካም ቢሆን አንዳነድ ቸርቾች ፈቅደው ወንድና ወንድ ያጋባሉ።

    ReplyDelete
  2. እመብርሃን ሀገራችንን ከምንሰማው ከምናየው ትጠብቅልን፡፡ ልጆቻችንን ባሪያህ አድርገህ በሀይማኖታችን እንድንጸና በጐናችን አትራቅ፡፡

    እመብርሀን ትጠብቀን

    ReplyDelete