Wednesday 10 June 2015

ቅዱስ ሲኖዶስና የመሰብሰቡ ዓላማ (የመጨረሻ ክፍል)



3. በግፍና ያለሥራው የሚወገዝ እንዳይኖር ለመከላከል

      “ … ወደጌታችን ወደኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ንጽሕና በሚቀርቡ ገንዘብ፡፡ ከካህናት ወገን ወይም ከሕዝቡ ወገን ቢሆን ኤጲስ ቆጶስ አውግዞ የለየውን ሰው ፍርድ ይመረምሩ ቸልታ እንዳይሆን ወይም ይህን በሚመስል ነገር ሁሉ እንደተገለጠላቸው ይፈርዱ ዘንድ፡፡” የሚለው የፍትሐ ነገሥቱ አንቀጽ አድሎዐዊነት እንዳይከሰት በውስጡ ማሳሰቢያ አዘል መልዕክት አለው፡፡ የቱም ጤናማ አባወራ ወይም የቷም ጤናማ እማወራ ልጆቿም የምታሳድገው ባለማበላለጥ በእኩልነት ነው፡፡ ኤጲስ ቆጶስም አማኞችን ሲመራ ልክ ቤተሰቡን እንደሚመራው አይነት ምንም አድሎ በማይኖርበት መልኩ ሊሆን ይገባዋል፡፡ (1ጢሞ.3፥4)

      ይህ ግን አንዳንዴ ይጣስ ይሆናል ፤ ምክንያቱም ኤጲስ ቆጶስ ሥጋን እንደመልበሱ ይበድላል ፣ ይስታልም፡፡ ስለዚህ ሲኖዶሳውያን ኤጲስ ቆጶሳት እንዲህ ያለውን ነገር ባዩ ጊዜ፥ “አውግዞ የለየውን ሰው ፍርድ ይመርምሩ ዘንድ ቸል ማለት” የለባቸውም፡፡ ይህም አንድ ኤጲስ ቆጶስ ሥራው እንደቃሉ መሆን አለመሆኑ ሊፈተሽ እንደሚገባ ሲያመለክት “ወደጌታችን ወደኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ንጽሕና በሚቀርቡ ገንዘብ፡፡” በማለት ፍትሐ ነገሥቱ ይቀንናል፡፡
      ሥራችንና ሕይወታችን ሁል ጊዜ “በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ታይቶ እንደሚወደድና እንደሚሻተት ቅዱስ መሥዋዕት” (ኤፌ.5፥1-2) ተወዳጅ መሆን መቻል አለበት፡፡ ከካህንም ሆነ ከሕዝብ መካከል ኤጲስ ቆጶስ ያወገዘውን ያለቸልታ ሲኖዶሳውያን በጌታ ቃል መለኪያነት ሊለኩ ፣ በቃሉ መነጽርነት እያዩም ሊመረምሩ ይገባቸዋል፡፡ በተለይም ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ላይ ከተያዘችባቸው ወጥመዶች አንዱ፥ ጥቂት የማይባሉ ኤጲስ ቆጶሳት በዘረኝነት ፤ በጥቅመኝነት ተጠምደው ከእነርሱ ዘርና ጥቅመኛ፥ ጠባቂና አስጠባቂ ውጪ የሆነውን ካህን ፣ ዲያቆንና ሕዝብን እያደረሱበት ያለውን በደል ማየት አለመቻሏ ነው፡፡ ሲኖዶሳውያኑ ችግሩ መኖሩን በግማሽ ቢያምኑም ነገር ግን ለማስተካከልና መልክ ለማስያዝ ከሚደረገው ጥረት ግን በዝምታ ማለፍን የመረጡ ይመስላል፡፡
        ቤተ ክርስቲያን እንኳን በመካከሏ በዓለም ላይ ኢ ፍትሐዊ የሆነ አካሄድን ፍጹም ነው መቃወም ያለባት፡፡ በመካከሏ ሲሆን ደግሞ አምልኮዋ በጌታ ፊት ዋጋ ቢስ እንዳይሆን (ማቴ.5፥23) ፈጥና ነው ማስተካከል ያለባት፡፡ እንግዲህ ቅዱስ ሲኖዶስ እንደተቀነነው ቀኖና እኒህን በማሟላት ለአምልኮ ራሱን ሊያቀርብ ይገባዋል እንጂ ሲኖዶስ ስለሆነ በሲኖዶስነቱ ብቻ መቅረብ የለበትም እንላለን፡፡ ከሁሉ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን በዚህ በአንዳንድ ኤጲስ ቆጶሳት ፍትሕ ነሺነት ምክንያት የፍርድ ቤት መዝግብ ቤቶችን ያጣበቡትን፥ የምትካሰስበትን ስፍር ቁጥር የሌለውን መዝገብ ፈጥና ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን የበደለቻቸውን ልጆቿን ይቅርታ በመጠየቅ በዓለም ፊት የተገለጠ ነውሯን ከድና ፍጹም በሆነ ቅድስና ፤ ሙሽራዋን ለመቀበል እንደተዘጋጀች ሴት ብታጌጥ እጅግ ውብና መልካም ነው፡፡ አልያ በዓለም የከፈተችውን የራሷን የክስ መዝገብ በምህረትና በይቅርታ ሳትዘጋ ዓለሙንና የኤጲስ ቆጶሳቱን ድካምና ስህተት ለመውቀስና ለማስተካከል እጅግ ይከብዳታል፡፡ የሌላን እንከን ከማጥራት የራስን ቀድሞ ማጥራት ያሻልና፡፡ (ማቴ.23፥24 ፤ ሉቃ.11፥39) 
     ይህም ብቻ ሳይሆን ዛሬ ላይ “በዕውር ድንብር” ግለሳባዊ ጥላቻና ከማህበራት ጋር ስላልተስማሙ ብቻ በየቦታው “የሚወገዙ” ብቻ ያይደለ ተደብድበው ከእንጀራቸው የሚፈናቀሉ ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው የገዛ ልጆቿ ቤተ ክርስቲያን ቅንነት የበዛበትን ፍርድ በመፍረድ ልትራራላቸው ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ እየተሰጡ ያሉ ፍርዶችንና ሆደ ሰፊ ሆኖ ክሶችንና በደሎችን የማድመጥ ነገር የምናያቸው ጥረቶች “ይበል ፤ መልካም ነው” የሚያሰኝ ነገር ቢኖረውም ከችግሩ መብዛትና ከነገሩ አሳሳቢነት አንጻር ፤ እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያን የቅድስና ሕይወት አንጻር የሚገባውን ያህል አልተሠራም ማለት ያስደፍራል፡፡
ጸጋ ይብዛላችሁ፡፡ አሜን፡፡

ተፈጸመ፡፡

No comments:

Post a Comment