ጌታ እግዚአብሔር የነጻነት አምላክ ነው ፤ የወደድነውን ፣ ሕሊናችን የመረጠውን
ኃላፊነትን ከሚያስከትለው ውጤት ጋር የመቀበል ሙሉ ነጻነትን ሰጥቶናል፡፡ መንገዳችንን እንደእስራኤል ዘሥጋ ቀድመን ማጥራትና መምረጥ
ከእኛ ነው የሚጠበቀው፡፡ መንገዶቹም በረከትና መርገም የሚባሉ እንጂ ሌላ ሦስተኛ አማራጭ የለም፡፡ ይህንን እውነት ነቢዩ ቅዱስ ሙሴ ምድረ ርስትን
ሊወርስ ላለው ፥ ለአዲሱ ትውልድ ሕጉን ለማስተማር ፤ የምክርንም ቃል በተናገረበት አንቀጹ እንዲህ ብሏል፦
እንግዲህ ፥ ከዚህ ሁለቱ አንዱን በተሰጠን የሕሊናና የዕውቀት ሚዛን መዝነን
ምርጫችንን መወሰን የእኛ ድርሻ እንጂ፥ ይህንን ምርጫ ሳናስተካክል በሚሆነው ነገር በእግዚአብሔር መዘበት ወይም ከእግዚአብሔር ጋር
መካሰስ አመክንዮታዊ ወይም ሥነ አጠይቋዊ ወይም አዕምሯዊ ፍተሻን የሚያሟላ አይደለም፡፡ ምክንያም እኛ አህዛብ እንኳ “ሕሊናቸው
ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉና” (ሮሜ.2፥15) አህዛብ
ስለሆኑ ክፋትን ብቻ መምረጥ አይችሉም ፤ መልካሙንም መምረጥ የሚችል
ሕሊና አላቸውና ከፍረድ አያመልጡም፡፡ እንኪያስ፥ አህዛብ ከፍርድ
የማያመልጡና የሚጠየቁ ከሆነ እኛ አምነናል የምንል እንዴት በጽኑ አንጠየቅ!?
የክርስቶስ ወንጌል የምንሰብከው በአብዛኛው የሠላም ሰዎች ለሆኑ ፥ ማለትም
ሊሰሙን ልባቸውን ላዘነበሉት ነው፡፡ (ማቴ.10፥11) ሊሰሙ ላልወደዱና ፈቃዳቸውን በተለያየ መንገድ ላለመስጠት የሚያስቸግሩትን
ግን “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ
ግን እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን።” (ሐዋ.13፥45-46) በማለት ትቢያችንን በማራገፍ (ማቴ.10፥14) “ደማችሁ በራሳችሁ
ነው፤ እኔ ንጹሕ ነኝ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” (ሐዋ.18፥6) ልንል ይገባናል፡፡
አንዳንዶች ቃሉን ላለመስማት እንደሄሮድስ ያፌዛሉ (ሉቃ.23፥11) ፣
አንዳንዶቹ እንደጠንቋዩ ኤልማስ ቃሉን ለመስማት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በር ይዘጋሉ (ሐዋ.13፥8) ፣ አንዳንዶች እንደ ፊልክስ
ወንጌል ለመስማት ዘመናቸውን ሲቀጥሩ ይኖራሉ (ሐዋ.24፥25) ፣ አንዳንዶች እንደአግሪጳ በእልኸኝነት መንፈስ ተይዘው እውነትን
ለመቀበል ይዘገያሉ (ሐዋ.26፥28) ፣ አንዳንዶች እንደጌርጌሴኖን(ጌራሴኖን) ሰዎች ኢየሱስን በግልጥ ይቃወማሉ (ማቴ.8፥34)
፣ ሌሎች ደግሞ በወንጌል ምሳሌ እንደተነገረ “ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ” (ማቴ.22፥5) እንደተባለ
ለግል ነገሮቻቸው ልዩ ትኩረት በመስጠት ወደዘላለማዊ የመንግሥቱ ወንጌል ማዕድ መጥተው ላለመካፈል ምክንያትን በማበጀት ቃሉን ከመስማት
ይዘነጋሉ ፤ ይሸሻሉ ፤ ይርቃሉም፡፡ በእውኑ እኒህንና ሌሎችን ሰዎች ወንጌልን በማባበል ቃል ልንሰብክ ይገባናልን?
የክርስቶስ
የመንግሥት ወንጌል ቃል የመጀመርያው አዋጅ፥ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” (ማቴ.3፥1 ፤ 4፥17) እና “በጌታ በኢየሱስ
ክርስቶስ እመን[ን] አንተና [እናንተ] ቤተ ሰዎቻችሁ ትድናለህ[ላችሁ]”
(ሐዋ.2፥38 ፤ 10፥47 ፤ 16፥31) የሚል ግልጥና የታወቀ ነገር እንጂ ምንም የሚያባብል ቃል የለውም፡፡
የክርስቶስ ወንጌል እውነት ብቻ ነው፡፡ (2ሳሙ.7፥28 ፤ 1ነገ.17፥24
፤ ዮሐ.17፥17) ከሐሰት ጋርም ምንም መስማማት የለውም፡፡ ጌታ ኢየሱስን ጻድቅ ነው ስንል አንድም ስህተት አድርጎ አያውቅም ፤
ስህተትንም አያውቅም ማለታችን ነው፡፡ ቅድስና የባህርይ ገንዘቡ ስለሆነ ኃጢአትን ፈጽሞ መሥራት አይቻለውም፡፡ (ዘሌዋ.11፥44-45
፤ 19፥2 ፤ 20፥7 ፤ 1ጴጥ.1፥15-16) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ጌታ እግዚአብሔር የራሱን ጠባይ የገለጠ ብቻ አይደለም ፤
እንዲሁ የእርሱ የሆኑትም ጭምር ከእግዚአብሔር ጋር በመስማማት ኃጢአትንና ኃጢአተኝነትን እንዲጠየፉና ከዚህም እንዲርቁ እንጂ፡፡
እኛም ዛሬ በእርሱ ልናምን የተጠራን ሁላችን፦ “ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና።” (1ተሰ.4፥7)
በእርግጥም “ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ
ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር
ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና …” (2ቆሮ.6፥14-16) የሚለው
ቃልም የሚያሳየን በሁለቱ መካከል የሠፋ ልዩነትን ሳይሆን ፍጹም ተቃራኒነትን ነው፡፡ መለኪያችን ቅዱስ ቃሉ ከሆነ ልንቆም የሚገባን
በዚህ ቅዱስ ሚዛንነት ላይ ብቻ ነው፡፡ እኒህ ሁለቱን መቀላቀልም ሆነ ማቀራረብ ፤ በማስማማትም ለመተርጎም አይቻልም ፤ አንችልም፡፡
ይህንን ገሃድ ግን ብዙ ጊዜ በትርጉምና በቀደመው ሰው አዳማዊ ጠባይ ውስጥ ሆነን በማመቻመች ለመተርጎም ስንጥር እንታያለን፡፡
ለውርደት የማንሆነው፥ ዳሩ ለክብርና ለምርጥ የእግዘአብሔር ልጅነት
የምንበቃው ራሳችንን ከክፋት ሁሉ በማንጻት “ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ” ስንሆን
ነው፡፡ (2ጢሞ.2፥21) ምክንያቱም ለቅድስናና ለምርጥ ዕቃነት የምንበቃበት የመጀመርያው መንገድ እግዚአብሔር መፍራት ከሆነ፥ እግዚአብሔርን
መፍራት ደግሞ ክፋትንና ርኩሰትን በመጥላት ከእርሱ ጋር ብቻ መቆምን ይጠይቃልና፡፡ (ዘጸ.20፥20 ፤ ኢዮ.28፥28 ፤ ምሳ.8፥13
፤ ኤር.44፥4) ከዚህ የተነሳ የዓለምን ምኞትና ኃጢአተኝነትን በግልጥ
ልንክድ ፤ ልንቃወምም ፤ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነን ትዕዛዙን መጠበቅ ይገባናል ማለት ነው፡፡ (1ጢሞ.6፥14 ፤ ቲቶ.2፥13-14)
በዚህ ክፍል ሁለት ነገርን በአንድ ጊዜ መናገርን እወዳለሁ፡፡
ይቀጥላል …
ወንድማችን! ከይቅርታ ጋር ይህንን በዳግም ም11 ላይ የተናገረው እግዚአብሔር ሳይሆን ሙሴ ለወገኖቹ ለእስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይጣሉ ሕይወትን በመምረጥ በቃል ኪዳኑ እንዲጓዙ ከመሞቱ በፊት የመከራቸው ምክር ነው።
ReplyDeleteወንድማችን ትክክል ነው የወንጌል ዓላማዋ እኛ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድንወርስ ንስሐ አድርገን ሕይወት የሚሰጠውን ቃሉን በመመገብ የዘላለም ሕይወትን እንድናገኝ ወንጌል ሁልጊዜም ትመክረናለች። እንዲህ የሚል ቃል በመጽሀፉ ተመዝግቦ ይገኛል። " 47 የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤" (ሉቃ. ም12) ይላል። ስለዚህ እግዚአብሔር በመጽሀፉ የእኔ ፈቃድ እንዲህ ነው ብሎ ይመክረናል። " 2፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። የተቀደሰ ጉባኤ ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ፥ የእግዚአብሔር በዓላት፥ እነዚህ ናቸው።" (ዘሌ. ም23) ብሎ የእርሱ የተቀደሱ ሰንብቶች እንደሆኑ ነግሮአቸዋል። ስለዚህ እኛ ዛሬ በቤተ ክርስትያን በጥምቀት ከእስራኤል ጋር አንድ የሆን እንዚህን ሰንበቶች ማክበር አይገባንም??? ምክንያቱም "14 ስለዚህ። አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል።15 እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤16 ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።17 ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ።" (ኤፌ. ም5) ይላል። በዚህም ይህንን ጥያቄ ልጠይቅበት የፈልጉት ምክንያት ወንጌል የምትመክረን እኛ ሁሉ "12 በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።13 አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል።................19 እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም።20 በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤" (ኤፌ. ም2)። ይላል። ስለዚህ ነቢያት ደግሞ ሰንበትን ቅዳሜን አክብሩ የፋሲካውን የበዓለ ሃምሳን የዳስ በዓልን አክብሩ ብሎ እግዚአብሔር የእርሱ ፈቃዱ እርሱ መሆኑን በነቢያቱ መዝግቦ ያስተምረናል። እኛ ግን በዘመናችን ከእርሱ ፈቃድ ውጭ የራስችን ፋሲካ አለን በጭራሽ የዳስ በዓል ምን እንድሆነ አናውቀውም። ነገር ግን ከእስራኤልል ጋር አብረን በቅርንጫፍ በግንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ የተተክልን ነን። ምን ይሆን ይህ ሁሉ ጥበብ? ይህንን ምክንያት አስረዱ ብንባልም ብዙዎቻችን በራሳችን ጥብብ የምናወራው ብዙ ነው። ስለዚህ በቤተ ክርስትያናችን ያሉት ጠቢባን ምን ነው ማስተዋል ጠፋባቸው? ብዙ ሊቃውንት ምን ነው ተኙ? ወንጌልን ያስተዋለ ማን ነው? ምሥጥሩ የገባው ማን ነው? ዝም ብሎ የመጽሀፍ ቁጥር በመቁጠር ሳይሆን ቅዱስ ሰለሞን እንዳለው ጥበብ ያስፈልገናል። "1 ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥2 ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ።3 ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥4 እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤5 የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።6 እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤7 እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል፤ ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፤8 የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፤ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል።9 የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ።10 ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፥ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤11 ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥" (ምሳ. ም2)። ስለዚህ ሁላችንንም ማስተዋል ይስጠን!
ReplyDelete