“የሥጋ ሕግ
ያጠፋል፤ የነፍስ ሕግ ግን ያድነናልና”
(በግርማዊ ቀዳ. ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ
ነገስት ዘኢትዮጲያ
መልካም ፈቃድ
በአሜሪካ ከታተመው የ1938 ዓ.ም
መጽሐፍ ቅዱስ ከታተመ የተወሰደ፡፡
ገጽ. 386)
በማስጨነቅ ወይም እጅ በመጠምዘዝ ከሚተረጎሙ የመጽሐፍ
ቅዱስ ክፍሎች አንዱ ከላይ በርዕሳችን ያነሳነው ቃል በብዛት ይዘወተራል፡፡ ይህንን ቃል ብዙ ምዕመናን ብቻ ሳይሆኑ በሕዝብ ዘንድ
“ተቀባይነት ያላቸው” የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ሰባኪዎች ጭምር በመጽሐፎቻቸውና በስብከቶቻቸው መሐል ከመጽሐፉ ሐሳብ ውጪ በመውጣትና
ወደራስ ሃሳብ በመሳብ ሲተረጉሙት አይተናል፤ ሰምተናልም፡፡
ቃሉን የተናገረው
ተወዳጁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ፤ በቆሮንቶስ ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያንና በመላው አካያይ ለሚኖሩ ቅዱሳን ነው፡፡ ሐዋርያው ይህን
ለማለት ያነሳሳው የቆሮንቶስ ምዕመናንን ወደኦሪት ሕግ፥ ወደኋላ የሚመልሱ አንዳንድ “አስተማሪዎች” በመነሳታቸው ምክንያት ነው፡፡
ይህን አስረግጦ ለመናገር ሁለቱን ኪዳናት በማነጻጸር ያሳያል፡፡
ሐዋርያው የመጀመርያውን ኪዳን ማለትም ብሉይ ኪዳንን፦
·
በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት (2ቆሮ.3፥7)
·
የኲነኔ አገልግሎት (2ቆሮ.3፥8)
ሁለተኛውንና አዲሱን ኪዳን ደግሞ፦
† የመንፈስ አገልግሎት (2ቆሮ.3፥8)
† የጽድቅ አገልግሎት (2ቆሮ.3፥9)
በማለት ያስቀምጣቸዋል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ የብሉይ ኪዳንን አገልግሎት
የሞት አገልግሎት በማለት በግልጥ ያስቀመጠው “በሥጋዊ ጥበብ እንጂ በእግዚአብሔር ጸጋ የማይመኩትን” (1ቆሮ.1፥12) እንዲሁም
እውነተኛውን የክርስትናን እምነት ከይሁዲነት ትምህርት ጋር እየበረዙ የቆሮንቶስን አማኞች ያውኩ የነበሩትን በግልጥ ለመቃወም ነው፡፡
የምዕራፉንም ሃሳብ የሚጀምረው የቆሮንቶስ ምዕመናን ከክርስቶስ እንደተላከ
መልእክት መቆጠራቸውን በመመስከር ነው፡፡ ይህንንም ምስክርነት ሌሎች ሐሰተኛ መምህራን ጠማማና ክፋት የበዛበትን ትምህርታቸውን ለማስረጽ
በሽንገላ ምስጋና ለውሰው እንደሚያቀርቡት ያለ ሳይሆን “ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ
ናችሁ።” (3፥2) በማለት በተለወጠው ሕይወታቸው አማካይነት የሚሠራውን የወንጌሉን ጉልበት በጽናት ይናገርላቸዋል፡፡ ዛሬ ግን ሰባኪዎቻችን
ታቦት አስቁመው ጠቀም ያለ ገንዘብ ላዋጣ ምዕመን(ሕዝብ) የብጹዕና የቅዱስ ነህ ሽንገላ ማሽጎድጎድ እንጂ የንስሐ ጥሪ ጨክነው ሲያስተላልፉ
አይታይም፡፡
የቆሮንቶስ አማኞች በመጀመርያው መልዕክት ላይ በብዙ እንደተዘለፉትና እንደተገሰጹት
ሳይሆን ሕይወታቸውን ብርሃን አድርገው ለሌሎች በማቅረባቸው በዚህ መልዕክት ላይ እጅግ ተወድሰዋል፡፡ ስለዚህም የተጻፉት በብራና
ጥቅልል ላይ እንደተጻፈው ፤ ደብዝዞ እንደዋዛ እንደሚለቀው ባለ ቀለም የተጻፉ ሳይሆኑ ሕይወትን እንደሚሰጠውና ከቶም ሊጠፋ በማይችለው
ሕያው መንፈስ ቅዱስ አማካይነት የተጻፉ መሆናቸውን “እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም” በማለት ያስረግጣል፡፡(2ቆሮ.3፥3)
ይህንንም በደንብ ለማስረዳት የእናንተ መልእክትነት በሲና ተራራ በድንጋይ ጽላት ላይ እንደተጻፈው አይደለም ፤ ምክንያቱም እርሱም
ቢሆን እንኳ የሚጠፋና ሕይወት ያለው አይደለም፥ የሞት አገልግሎት ነውና ብሎ ፤ ነገር ግን በሰው ልብ ጽላት ላይ እንደተጻፈ ያለ
ነው ይላል፡፡
በአጭር ቃል ሐዋርያው በዚህ ክፍሉ ፊደል በማለት ያስቀመጠው ሕጉን ወይም
በመጀመርያ የተጻፈበትን የድንጋይ ጽላት ወይም የሞት አገልግሎት የተባለውን ኦሪትን ነው፡፡ ሕጉ ራሱ ከድንጋይ የሆነ ወይም የድንጋይ
ጽላት ተብሎ ተጽፏልና፡፡ (ዘጸ.24፥12 ፤ 31፥18) ይህን አገልግሎት የሞትና የኲነኔ አገልግሎት በማለት በግልጥ ሲጠራው ፤
የሚገርመውና የሚደነቀው ይህ አገልግሎት እንኳ የተገለገለው በክብር ነው ይለናል፡፡ በእርግጥም ያ ኃጢአትን አዳፋኝና አቀጣጣይ ፤
ገዳይ አገልግሎት በብዙ ፍርሃትና መንቀጥቀጥ የተገለገለ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ በድንጋይ ላይ የተጻፈው ፊደል አገልግሎት የሞት
አገልግሎት ፊደል የተባለው የሕጉ ሥራና አገልግሎት ተላላፊዎችን ሁሉ ኰናኝ ነውና ገዳይ ነው፡፡
በድንጋይ ጽላት ላይ የተጻፈው “ሕግ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት
በጎም” ናት እንጂ በራሷ ገዳይ አይደለችም (ሮሜ.7፥13)፤ ነገር ግን ህጉን ባለመፈጸማችንና ባለመታዘዛችን ፤ እንዲሁም በራሱ
ከክፋትና ከኃጢአት የሚያነጻም አይደለምና ገዳይ ሆኗል፡፡ ኃጢአት ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔር ሕግ ለዘለቄታው ቅዱስ ላልሆነ፣
ማለትም ለሞት ተጠቀመበት፡፡
እኛ ግን
“በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ … ” (2ቆሮ.2፥15) በመሆን እንድናገለግል የተጠራነው እንደፊደል
ላለው አገልግሎት ላይደለ በመንፈስ ለሆነው አገልግሎት ነው፡፡ ይህን አገልግሎት ለማገልገል ብቃትን ያገኘነው(2ቆሮ.2፥16) ከእግዚአብሔር
ነው እንጂ በራሳችን አይደለም፡፡ (2ቆሮ.3፥5) በመንፈስ ቅዱስ የሚገለገለው የመንፈስ አገልግሎት የሆነው አዲስ ኪዳን አገልግሎት
በነቢያት የተነገረና እጅጉን የተናፈቀ ነው፡፡ የሞቱ አገልግሎት በክብር ከተገለገለ የመንፈሱ ወይም የአዲስ ኪዳኑ አገልግሎትማ እንዴት
ይልቅ በክብር አይሆንም!? የተባለለት አገልግሎት የጽድቅ አገልግሎት በሚበልጥ ክብር አብዝቶ ከብሯል፡፡
በሙሴ ፊት ላይ የነበረው “የፊተኛው አገልግሎት የክብር ብርሐን” በጊዜው
ትልቅ ክብር ነበረው፤ (ዘጸ.34፥30) ነገር ግን ከጊዜ በኋላ ተሽሯል (በመጋረጃ ተከድኗል)፡፡ እንዲሁ ፊተኛው የሞት ኪዳን በጊዜው
በትልቅ ክብር ተገልግሏል፡፡ በኋላ ግን እንደሙሴ የፊት ክብር በክርስቶስ ብቻ ተሽሯል፡፡(2ቆሮ.3፥14) አሁን ግን በክርስቶስ
በኩል ባገኘነው እምነትና ብቃት የእግዚአብሔርን ክብር ባልተሸፈነ ፊት በክርስቶስ ብቃት አዲስ ኪዳንን ልናይና ልናገለግል ነው የተጠራነው፡፡
በጠቅላላ ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስ ስለሆነው የአዲስ ኪዳን አገልግሎት ፍጹም
በጥብቅና ይቆማል፡፡ በዋናነትም አዲሱን የክርስቶስን ኪዳንና የቀደመውን አሮጌውን ኪዳን ከተቀበለው ከሙሴ ኪዳን ጋር ያለውን ነገር
በማነጻጸር በሙሴ የተገለገለው አሮጌው ኪዳን ይገድላል፤ ነገር ግን በክርስቶስ የሆነው መንፈስ ወይም መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ሕይወትን
ይሰጣል በማለት ያጸናዋል፡፡
ይህ ሃሳብ
ግን ፈጽሞ ፊደል የተባለው ንባብ ይገድላል ፤ መንፈስ የተባለው ትርጓሜ ደግሞ ሕይወትን ይሰጣል የሚል ትርጉም የለውም፡፡ ስለዚህም
የሕይወት መንፈስ መንፈስ ቅዱስ በነቢያት የተነገረውን ተስፋ ይፈጽም ዘንድ በአማኙ የልብ ጽላት ላይ ያንኑ ሕግ ይፈጽም ዘንድ ኃይልን
ይሰጠዋል፤ እንዲወድም ያደርገዋል ምክንያቱም ሕጉ ያለመንፈስ ቅዱስ ኃይልና እገዛ ጠብቁኝ ይላል እንጂ እንጠብቀው ዘንድ ኃይልን
አይሰጠንም፤ ይልቁን ባልጠበቅነው መጠን አብዝቶ የሚከሰንና የሚኮንነን ነው፡፡ ስለዚህም ነው የሥጋ ሕግ የሚያጠፋ ፤ የሚገድል ፤
የመንፈስ ሕግ ግን ሕይወትን ይሰጣል የተባለው፡፡
አቤቱ
የሕዝብህን ልብ አብራ ፤ ያስተውልም ዘንድ የጽድቅ መንፈስህ ይምራው፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment