Tuesday 6 January 2015

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ልዩ ነው!

       
                                  Please read in PDF



             እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት 
               መታሠቢያ በዓል በሰላም  አደረሳችሁ!!!!

        ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዷል፡፡ መወለዱም “ልደተ አዳም እምድር ፤ ልደተ ሔዋን እምገቦ ፤ ልደተ አቤል እምከርሥ ፤ ልደተ በግዕ እምዕፅ ፤ ልደተ ሙታን እመቃብር” እንደሆነው ያይደለ የእርሱ ከዚህ የተለየ ልዩ ልደት ነው፡፡ (ወንጌል አንድምታ፤ ከቀድሞ አባቶች ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ንባብና ትርጓሜው ፤ 1997፤ በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት የታተመ፤ ገጽ.44) እርሱ የተወለደው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ፤ ከሰው ነው፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው “ቃል ሥጋ ሆነ” ብሎ ሳያበቃ ፤ “ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ” ሲል የእኛን ሥጋ መዋሐዱን በማስረገጥ የተናገረው፡፡(ዮሐ.1፥1 ፤ 14)

   የሰው ልጅ ከቀደመው አዳም በመወለዱ ምክንያት ብቻ ፍጹም ኃጢአተኛ ሆነ፡፡ ከዚህ የተነሳም ሁላችን ከአዳም የተወለድን በመሆናችን ደግሞ በአንድ ጊዜ ኃጢአተኞች ሆነን ተገኘን፡፡(ሮሜ.5፥14) ስለዚህ ኃጢአት በመሥራት ያይደለ ከአዳም የተወለደ ፍጥረት ሁሉ በኃጢአት ከተበከለ ዘር ተከፍሏልና ከእርሱ በመወለዱ ብቻ የኃጢአት ደመወዝ ሞት ተፈረደበት፡፡ ኃጢአት የባህርይ ዕድፈት ነውና በባህርያችን በእግዚአብሔር ፊት የምንቆምበትን ትምክህት (መመኪያ) አጣን፡፡
   የአብ የባህርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድምና ከአባቱ ያለእናት እንደተወለደ (መዝ.2፥7  ፤ማቴ.3፥17) እንዲሁ ከእኛም ያለአባት ፍጹም መወለድን ተወለደ፡፡ በቀደመው ሰው በአዳም ምትክ ልዩ ልደትን ይዞልን መጣ፡፡ የቀደመው ሰው ከመሬት እንደተፈጠረ(እንደተወለደ) ባለ ልደት ያይደለ፥ እርሱ በገዛ ሥልጣኑ ከቅድስት ድንግል ማርያም በኤፍራታ ክፍል በቤተ ልሔም አውራጃ ተወለደ፡፡ ከቀደመው ሰው በመወለዳችን ኃጢአተኞችና ርኩሳን ስለሆንን አሁን ደግሞ በሁለተኛው አዳም በክርስቶስ ኢየሱስ ልደትነት ልጆች ተብለን፤ ያለጽድቃችን ጻድቃን እንባል ዘንድ ሰው ሆነ፡፡
     ከቀደመው ሰው አዳም በመወለዳችን ብቻ ኃጢአተኞች ሆነን ሞት ተፈረደብን ወይም በመርገመ ሥጋ ላይ መርገመ ነፍስ ፤ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲዖል አገኘን፡፡ ዕድፈት ላለበት ባህርይም ተላልፈን ተሰጠን፡፡ “ጽድቅ” እየሠራን ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ የሆነው፥ ባህርያችን በማደፉ ምክንያት ነው፡፡ ሁለተኛው አዳም ሰው የሆነው ክርስቶስ የመጣበት ዋናው ዓላማ ከእርሱ ዳግመኛ በመወለድ ሕይወት እንድናገኝና እንዲበዛልንም ነው፡፡ (ዮሐ.3፥5 ፤ 10፥10 ፤ 20፥31) ከክርስቶስ በመወለዳችን ብቻ ደግሞ ጻድቃን እንባላለን፡፡ ከፊተኛው አዳም የተነሳ ኃጢአተኞች ለመባል ድርሻችን መወለድ ነበር ፤ እንዲሁ በኋለኛው አዳም በክርስቶስ ጻድቃንና ቅዱሳን ለመባልም ድርሻችን መወለድ ነው፡፡
     ጌታ ሰው በመሆኑ ምክንያት ለእኛ የባህርያችን መመኪያ ሆኗል ማት ነው፡፡ በባህርይ እድፈት ስለነበረብን በጌታ መቆም ያልተቻለን አሁን ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ከኃጢአት ዕድፈትና ነውር ነጽተን በፊቱ ያለፊት መጨማደድ እንቆም ዘንድ አበቃን፡፡(ኤፌ.5፥27) በክርስቶስ ኢየሱስ ልደት የባህርያችን ዕድፈት ተወገደልን፡፡ የተወገደልን ብቻ አይደለም ኃጢአትና የኃጢአት ደመወዝ ዳግመኛ በእኛ ላይ ሥልጣን የሌለውና ድልም የማይነሳን ሆነ እንጂ፡፡(ሮሜ.8፥1 ፤ 1ቆሮ.15፥55)
    የቀደመው አዳም የተወለደው በእግዚአብሔር መልክና አርአያ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን መልክና አርኣያውን በገዛ መንገዱ ኃጢአትን በመምረጡ ምክንያት አበላሸው፡፡ የእግዚአብሔር መልክ ቅድስናና ንጽዕና ሆኖ ሳለ የቅድስናውንና የንጽዕናውን ሕግ ተላልፎ (ዘፍ.3፥17) ፊተኛው ሰው በኃጢአት ምክንያት ወደርኩሰትና ዕድፈት መልክ ቀየረው፡፡ (ዘፍ.3፥22) ስለዚህም በእግዚአብሔር መልክ የተወለደው የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ሕግ ባለመታዘዙ ምክንያት እንደእግዚአብሔር መልክ ያለ ትውልድ መውለድ ሲገባው ከእግዚአብሔር በመራቁና በኃጢአት በመበከሉ፥ የእግዚአብሔር መልክ ያለውን ያይደለ የራሱን መልክ የሚመስለውን ትውልድ ወለደ፡፡ “አዳምም ሁለት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ልጅንም በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ ስሙንም ሴት ብሎ ጠራው።” (ዘፍ.5፥3)
   የባህርያችን መመኪያ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ የተወለደው የቀደመው ሰው በኃጢአቱ ምክንያት ያጣውን ፤ እግዚአብሔርን የሚመስልበትን ያንን መልክ ሊመልስለት ፤ “በእውነት ቃል አስቦም”(ያዕ.1፥8) ይወልደው ዘንድ ተወለደ! ድንቅ ልደት !!! የእግዚአብሔር መልክ ቅድስና ከሆነ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ያንን መልክ ማሳየት የሚቻለው (ሉቃ.2፥52) እርሱ ብቻ ስለሆነና ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቶ፥ የሕይወት መንፈስ ሕግ መስጠት የሚቻለው አንድ ጌታ ፤ ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነውና ስለዚህም ተወለደ፡፡(ሮሜ.8፥2) ከእርሱ ወመለዳችን የእርሱ ነጻ ሥጦታ እንጂ የእኛ ምርጫ አይደለም፡፡
     የጌታ ልደት በቤተ መንግሥትና በቤተ መቅደስ ሲጠበቅ በከብቶች ግርግም ፣ ከቀዳማይ እመቤቶችና ከልዕልታት ሲጠበቅ ከአንዲት ገሊላዊት ድንግል ሴት ፣ በኢየሩሳሌም ሲጠበቅ በታናሿ ግዛት በቤተ ልሄም ፣ ካህናትና የካህናት አለቆች ያጅቡታል ሲባል እረኞች ፣ የቅርብ ነገሥታትና ገዢዎች ያከብሩታል ሲባል እንኳን ሊያከብሩት ንቀውት ሳለ፥ የሩቅ አህዛብ ነገሥታት የሰገዱለት ፣ በብዙ ዕልልታ ይወለዳል ሲባል ዓለም ፊቷን አዙራ ቦታ ሳትሰጠው  … ይህ ጌታ በድንቅ ልደት ተወለደ!
    በጌታ ልደት ቤተ ልሄም ከኢየሩሳሌም ይልቅ ክብሯ በዛ፤  ከካህናትና ከመቅደሱ አገልጋዮች እጅግ በሚበልጥ ክብር እረኞች ገነኑ፤ ድንግል ማርያም በመቅደሱ ከሚያገለግሉ ሴቶችና ቀዳማይ እመቤቶች ይልቅ ለሚበዛ ሥራ፥ ለትልቅ ባለሟልነት ተመረጠች ፤ ከተወደደው ቤተ መንግሥትና ከሚፈራው ቤተ መቅደስ የከብቶች ግርግም የመላዕክትን ዕልልታና ዝማሬ አስተናገደ!!! ቦታ የሚለዋውጥ ድንቅ የሆነ ይህ ልደት ክብሩ እንዴት ይበዛ ይሆን!?
    በእውነት!  እናንተስ መላዕክት ሆይ! ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ያህል ወደቤተ መቅደሱ ትወርዱ አልነበረምን? … ዛሬ ስለምን በክብር ብርሃን ላይ ሆናችሁ ወደበረቱ በመውረድ ከእረኞች ጋር በአንድነት ትዘምራላችሁ?! … በውኑ ልደቱ ድንቅ የሆነ ኢየሱስ ተወልዶ አይደለምን?

     ጌታ ሆይ! እኛም በልደትህ ነውና የተመረጥነው! እናመሠግንሃለን፡፡ አሜን፡፡   

3 comments: