Sunday 18 January 2015

“የምወድህ ልጄ አንተ ነህ …” (ማር.1፥10)





እንኳን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት መታሠቢያ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡



    ጌታ የማስተማር አገልግሎቱን ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ሲሆን (ሉቃ.3፥23) በግልጥ ለማገልገልና ለመጠመቅ ከመውጣቱ በፊት ይኖር የነበረው ደግሞ በገሊላ ናዝሬት ነው፡፡ (ማቴ.2፥23) ናዝሬት በብሉይ ኪዳን በአንድም ሥፍራ ስሟ ያልተጠቀሰችና የማትታወቅ ከተማ ናት፡፡ ናዝሬት የማትታወቅና ያልተጠቀሰች ከተማ ብትሆንም፥ ለጌታ ኢየሱስ “ቅጥያ ስያሜ” ሆና “የናዝሬቱ ኢየሱስ” ለመባል የበቃች ከተማ ናት፡፡ ጌታ “የናዝሬቱ  ኢየሱስ” የተባለው ስለተወለደባትና ስላደገባት ብቻ እንጂ እንደነሶምሶን “ልዩ ናዝራዊ” ለመባል አይደለም፡፡

   የብሉይ ኪዳን ነቢያት በትንቢታቸው የሚወለደው አዳኝ መሲሕ ሊናቅ እንደሚችል “ … የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም።” በማለት ተናግረውለታል፡፡(ኢሳ.53፥3) በእርግጥም፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በነበረበት ዘመን “የናዝሬት ሰው” ማለት የተናቀ ፣ የተጠላ ፣ ፈጽሞ መልካም ነገር ሊገኝበት የማይችል አይነት ሰው እንደሆነ “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” (ዮሐ.1፥47) የሚል አስደናቂ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ጌታ እግዚአብሔር  በናዝራዊው ሳምሶን እጅ ከሞተ አንበሳ ውስጥ ጥፍጥ ማር አስገኝቷል፡፡ (መሣ.14፥8) ይህ የእግዚአብሔር ልዩ ባህርይ ነው፡፡ ከሚጠበቀው ሳይሆን ከማይጠበቀው ጋር ድንቅን መሥራት ፣ ከሚጠበበው ከሰው ጥበብ ይልቅ  ከሰው በሚበረታው ድካሙ መሥራት (1ቆሮ.1፥25) ፣ ከኢየሩሳሌም ሳይሆን ከናዝሬት ፣ ከካህናቱ መካከል ሳይሆን በጥብርያዶስ ዓሣ ዳርቻ ዓሣ ከሚያጠምዱ፤ በዓሣም ከሚተዳደሩ ወገኖችና ከቀራጮች መካከል ሐዋርያትን መምረጡ ይህ የጌታ ልዩ ባህርይው ነው!!! ጌታም ከማትጠበቀዋ ከናዝሬት ወጣ!!!
    ማንነትና ክብር ለሚያስጨንቀን የከበረው የናዝሬቱ ኢየሱስ በተዋረደችው ከተማ ስም ተጠርቶ ለእኛ የክብራችን ሰገነት ሆነ፡፡ ለክብራችሁ አትጨነቁ ፤ ክብሩን ጥሎ ከፍ ባደረጋችሁ ጌታ መከበርን ውደዱ እንጂ፡፡ እኛም እንደናዝሬት ከማይተበቁት ወገን ሆነን ሳለን በምህረቱ ባዕለጠጋ የሆነው ጌታ ግን እንዲሁ፤ ደግሜ እላለሁ እንዲሁ መረጠን፡፡
    ጌታ ኢየሱስ በሠላሳ ዓመቱ ከገሊላ ናዝሬት ወደዮርዳኖስ ከዮሐንስ ዘንድ ሊጠመቅ ሄደ፡፡ ትልቁ ጌታ ወደ አገልጋዩ ዮሐንስ ሄደ፡፡ ማርቆስ፥ ጌታና መጥምቁ ዮሐንስ የተነጋገሩትን ሳይዘግብ (ማቴ.3፥14-15) እንደልማዱ “ወዲያው” ወደሚል የችኰላ አዘጋገቡ ይሄዳል፡፡ ቅዱስ ማርቆስ የወንጌሉ ትልቅ ትኩረት ጌታ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መግለጥ ነውና፥ ስለዮሐንስ በመጠኑ በመተረክ ጌታ ወዳደረገውና የእግዚአብሔር ልጅነቱን ወደሚገልጠው ታሪካዊና ተአምራዊ እውነት ለመናገር ይቸኩላል፡፡
   ወዲያው ጌታ ኢየሱስ ከውኃው በወጣ ጊዜ ሰማያት ተቀደው አብ ተናገረ ፤ መንፈስ ቅዱስም በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ በርግብ አምሳል ወረደበት፡፡ አብ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል” አለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አብን ደስ ያሰኘውና አብም ደስ የተሰኘበት፥ ሥጋ ለብሶ ለእኛ ባሳየው የጽድቅ ሕይወቱና ስለሰው ልጆች ኃጢአት በከፈለው የመሥዋዕትነት ሕይወቱ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ ከኃጢአትና ከመርገም ሕይወቱ የተነሳ ሕግን በመፈጸም(በማድረግ) እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አልተቻለውም፡፡ ነቢያት ፣ ቅዱሳን አባቶችና እናቶች ፣ ጻድቃንም በሕጉ ተከሰዋልና (ሮሜ.3፥9) የእግዚአብሔር ክብር ስለጐደላቸው (ሮሜ.3፥23) ፈጽሞ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አልቻሉም፡፡
    ክርስቶስ ኢየሱስ ግን ነቢያትንና ሕግን ፈጽሞ ፤ ጠንቅቆ በማድረግ (ማቴ.5፥17) አብን ደስ ያሰኘ ነው፡፡ እርሱም ሕግን በሕይወቱ የፈጸመ ፤ ምንም የሕግ ስህተት ምክንያት ያልተገኘበት እውነተኛ ጻድቅ ነው፡፡ እኛ ሕግን ጠንቅቆ መፈጸም ስላልሆነልን የበቃን ሆነን አልተገኘንም ፤ የሁላችን ቤዛ ክርስቶስ ግን ሕጉን ፈጽሞ በመገኘቱ በምድርም በሰማይም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ጻድቅ ነው፡፡
    ስለዚህም ጌታ በዚህ የጽድቅ ሕይወቱ ትልቅ ምሳሌነትን ትቶልን ሄዷል፡፡ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።” (1ጴጥ.2፥21) እንደእርሱ በጽድቅ ሕይወት እንጂ ሕግን ስለመተላለፍና ስለኃጢአት ልንከሰስ ወይም ልንነቀፍ አልተጠራንም፡፡ (ማቴ.5፥11 ፤ 1ጴጥ.2፥20) እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው ራሳችንን የተቀደሰ መሥዋዕት አድርገን በማቅረብ (ሮሜ.12፥1-3) የእርሱን የቅድስናና የጽድቅ ሕይወት እኛም ስንካፈለው ነውና፡፡ (ዘሌ.19፥2 ፤ 1ጴጥ.1፥16) ጌታ ኢየሱስ ለእኛ አብነት ትቶልን በሄደው የጽድቅ ሕይወቱ አባቱን ደስ አሰኝቶታልና  “በአንተ ደስ ይለኛል” ብሎ መሰከረለት፡፡

   በሌላ በኩል ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በከፈለው የኃጢአት መሥዋዕትነቱ ፍጹም አብንም እኛንም ያረካ ነው፡፡ ስለኃጢአት ክፍያ የእንሰሳቱ መሥዋዕትና የእህሉ ቁርባን ፣ የሰው ትጋትና ጸሎት አብን ፈጽሞ ደስ ሊያሰኘው አልቻለም፡፡ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በመስቀል ላይ የከፈለው የማዳን ዋጋ ፍጹም አብ የረካበትና ደስ የተሰኘበት ነው፡፡
   አብ ኃጢአትን ፈጽሞ የቀጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ጫንቃ ላይ ነው፡፡ የአለምን ኃጢአት ሁሉ ሊያስወግድ (ዮሐ.1፥47) ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሰውን ልጅ ኃጢአት ሁሉ ተሸክሞ ነበርና፡፡ (ኢሳ.53፥4) ጌታ ስለኃጢአት ለሰው ልጅ መከፈል ያለበትን ዕዳ ሁሉ ከፍሎ “ተፈጸመ” ባለ ጊዜ (ዮሐ.19፥30) አብ፤ መልድ በፈጸመው መሥዋዕትነት ሥራ ፈጽሞ ረክቷል፡፡ ስለዚህም “ … በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ” (ሮሜ.3፥26) እንዲል የእርሱን ጽድቅ የምንወርስ እኛ ክርስቶስ መስቀል ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ መሞቱን፥ እርሱ ራሱን ክርስቶስ ኢየሱስን ትምክህት ባደረገ እምነት ልንታመን ይገባናል፡፡

   እንኪያ ፦ አብ በጌታ ኢየሱስ ለሠላሳ ሦስት ዓመታት በኖረው በጽድቅ ሕይወቱም ፤ ለኃጢአት በከፈለው የመሥዋዕትነት ሕይወት ረክቷል፡፡ የጽድቅ ሕይወቱን እንመስለው ዘንድ ተጠርተናል ፤ ተጋብዘናልም፡፡ ለኃጢአት በከፈለው የመሥዋዕትነት ሕይወት ግን አምነን እንድን ዘንድ ብቻ ነው የተጠራውና፥ በዚህ እኛም ደስ ሊለን ይገባናል፡፡ ስለኃጢአት አብ ከረካበት ከክርስቶስ የመስቀል ሥራ በቀር ሌላ ምንም ምን የሥርየት መንገድ የለም፤ አብ በወደደውና ፤ በረካበት በዚያ በልጁ የጽድቅ ሕይወትና  ስለኃጢአት በከፈለው የመስቀል ቤዛነት ሥራ ሁላችን ደስ ይበለን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment