Thursday, 9 October 2014

“ታይታኒክን ራሱ እግዚአብሔር እንኳ አያሰጥማትም!!!”

   

                                               



 በሰው እጅ ተንቀሳቃሽ ሆነው ከተሠሩ ነገሮች ተወዳዳሪ ያልተገኘላትን ኤም. ኤስ ታይታኒክ መርከብን በባለቤትነት የያዛት ጆን ፒርፖንት በ1912 ዓ.ም ስለታይታኒክ መርከብ የተናገረውን ቃል ነው በርዕስነት የወሰድኩት፡፡ ስለመርከቢቱ ብዙ የተባለ ስለሆነ እኔ ስለዚያ የምለው ነገር የለኝም፤ ይሁንና የመርከቢቱ ባለቤት የተናገረው ቃል እጅግ ድፍረትና “መዓት አውርድ” መሆኑን መርከቢቱ ያሰጠመቻቸውን 1522 ሰዎችን በሞት፤ በንብረትም ላይ ካደረሰችው ጥፋት መረዳት ይቻላል፡፡

    በተወሰነ መልኩ ከዚህ ታሪክ ጋር ዝምድና ያለው ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለይግባኝ ከብዙ እስረኞች ጋር ወደሮም ሊጓዙ በተነሱ ጊዜ፥ ሊመጣ ያለውን ጥፋት ሐዋርያው ከመንፈስ ቅዱስ እንደተረዳ ለሰዎቹ ቢናገርም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል የእስረኞቹ ጠባቂ የመቶ አለቃ “… ጳውሎስ ከተናገረው ይልቅ የመርከብ መሪውንና የመርከቡን ባለቤት ያምን ነበር፡፡”(ሐዋ.27፥11) ይለናል፡፡ በፍጡር “መልካምነትና ብቃት” በመመካት እግዚአብሔርን መዘንጋት የማያባራ ጥፋት አለበት፡፡
    አብያተ ክርስቲያናት ዛሬ ላይ እግዚአብሔር በመናኛና በሰው ፊት ሞገስ በሌለው ነገር ድንቅን እንደሚሠራ መተዋቸው፤ የሚታየውን እንጂ የማይታየውን ነገር ሲሠራ የምናየውን ታማኝ የሆነችውን የእግዚአብሔርን እጅ ያላስተዋሉበት ምክንያታቸው የአገልግሎቱን መድረክና አውደ ምህረቱን የያዙት እንደጆን ፒርፖርት ያሉ ቅምጥል በመሆናቸው ነው፡፡ የቤት መኪናና ሞባይል፤ ስለሚኖሩበት ቤትና ግጥግጥ ዕቃቸው እንጂ ክርስቶስ ስለሞተለት አንዲት ነፍስ የማይጨነቁ አድርጓቸዋል፡፡
   የቀደመው እባብ የወደቀበት ትልቁ ስህተት ትዕቢት ነው፡፡ “ሊጋርድ የተቀባውና በእግዚአብሔር ተራራ ላይ የነበረው ኪሩብ”(ሕዝ.28፥14) የወደቀው በእግዚአብሔር ላይ ከኰራው ኲራቱ፤ በተቀማጠለው መቀማጠሉ፤ በተመካው ትምክህቱ ነው፡፡ ከፍታን እየሻተ ቁልቁል ወደውርደት የወረደው ስለትዕቢቱ ነው፡፡
     ትዕቢት የሰይጣን የልብ መዝገቡ፤ መመላለሻ ሠገነቱም ነው፡፡ ተከታዮቹም የዚያኑ ያህል “በእግዚአብሔር የለሽ” እምነታቸው ላይ የደረቡት ትምክህት ትዕቢት ነው፡፡ የታይታኒክ መርከብ ባለቤት ያደረገው ይኸንኑ ነው፡፡ የእርሱን መርከብ ሊያቆም የሚችል ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ኃይል እንደሌለ በድፍረት ተናገረ፡፡ ግና ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነገር ሳይዘገይ ተሰማ፡፡ ከጥቂቶች ታሪክ ነጋሪ ሰዎች በቀር ነገሮች ወዳለመኖር ተቀየሩ፡፡
   እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል (1ጴጥ.5፥5) ብቻ ሳይሆን ይጠላልም፡፡(ምሳ.8፥13) ትዕቢት ክፉ ነውና፡፡(ያዕ.4፥16) እግዚአብሔር “የትዕቢተኞችን የጌጥና የበገና ድምጽ ወደሲዖል ያወርዳል፤ ዜመኞችም፦ በበታቾቻችሁ ብል ተነጥፎአል፥ ትልም መደረቢያ ሆኖአል ብለው ይመልሱላቸዋል”(ኢሳ.13፥11) እግዚአብሔር በትዕቢት ራሳቸውንና ሥራቸውን የሚያገኑትንም ይቃወማል፡፡ ከፈርዖን እስከናቡከደነጾር፤ ጌታን ካሳደደው ሄሮድስ እስከበትል ተበልቶ እስከሞተው ሄሮድስ(ዘጸ.5፥2 ፤ ዳን.4፥30 ፤ ማቴ.2፥16 ፤ ሐዋ.12፥23) እግዚአብሔር የተቃወማቸውና በብርቱ ቅጣት ያዘመናቸው (ያሳለፋቸው) ራሳቸውን በማክበርና በማመስገን ተይዘው እርሱን ስለተገዳደሩት ፤ ከክብራቸውም ውጪ ስለተመኩ ነው፡፡ ትዕቢት ውድቀትና ጥፋትንና ከቀደመች ፤ለመጥፋትና ወድቀው ለመሰበር የሚሹ ይታበያሉ(ምሳ.16፥28) ማለት ነው፡፡
  ትዕቢት የትህትና ተቃራኒ ነው፡፡ በሐገራችንና በዓለም ዙርያ ያሉ እጅግ ብዙ መሪዎችና ባዕለጠጎች እንዲሁም አገልጋዮች ልባቸውና መንፈሳቸው በፈትል የተገመደ ያህል ከትዕቢት ጋር የተዛመደ ነው፡፡ የህዝባቸውን ረሃብና ስደት ስለመከበራቸው፤ የድኃውን እንባና ጩኸት ስለዙፋናቸው መጽናት ፤ የአማኙን በመንፈስ መራቆት ለመጠጥና ለእንጀራቸው በትዕቢት የሚሠዉ መሪና ባዕለጠጋ፤ ሰባኪና የደብር አለቃ ቁጥራቸው ያስደነግጣል፡፡ ባዕለጠጋ ወደመንግስተ ሰማያት መግባት ጭንቅ የሚሆንበት ባዕለጠጋ በመሆኑ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ሠጪውን ባለማስተዋሉ በባዕለጠግነት ሀሳብ በመታለል በእሾህ መካከል እንዳለ ተክል አንቆ ይዞት የወንጌሉን ቃል ፍሬ የማያፈራ ያደርገዋልና ነው፡፡(ማቴ.13፥23፤ 19፥23)  
  የታይታኒኳ መርከብ “መሪ የሌላት በሚመስል ጥፋት የጠፋችው” ባለቤቷ ህሊናውን በመጣሉና በእምነት ነገር በመጥፋቱ ነው፡፡(1ጢሞ.1፥19) የአገልግሎት መሪና መርሕ ትሁት ልብ ከሆነ፤ ትዕቢት አገልግሎት ለማፍረስ ከክፉ ልብ ላይ ይበቅላል ማለት ነው፡፡ በአገልግሎት ህይወት ብዙ አገልጋዮች በጣም ትዕቢተኞች የሚሆኑት አገልግሎቱን ከሰው እንጂ ከእግዚአብሔር ስላልተቀበሉት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ያልተቀበልነው አገልግሎትና አለጊዜው የተሰጠን አገልግሎት ብዙ ጊዜ በትዕቢት ይነፋናል፡፡ ከዚያም የምንናገረው ከትዕቢት የተነፈስነውን ነው፡፡(1ጢሞ.3፥7)
   በህግና በሥርዓት በእግዚአብሔርም ፈቃድ ሀብት ያከማቹ፤ ያለደም ማፍሰስና በአገባቡ ሥልጣን የያዙ፤ አገልግሎቱን በፍርሃተ እግዚአብሔር ያገለገሉ ወገኖች ምድርን ወደ መልካም የዕረፍት ሥፍራ ወስደዋታል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በግፍና በደም ሀብት ያከማቹና  ሥልጣን የያዙ ግን ዕብሪተኞችና ትዕቢተኞች ሆነው ምድርን በመከራና በሰቆቃ እሳት ውስጥ ማግደዋታል፡፡ ከሌላው የተሻልን እንደሆን ማሰባችን፤ ድኃውን ተጠይፈን ራሳችንን “የሰማይ ስባሪ” ላይ ማስቀመጣችን፤ ለአላዋቂው ከመጸለይና በቃሉ ከመርዳት ይልቅ በአላዋቂነቱ ላይ መዘባነናችን … የዘመን ስብራታችን ነው፡፡
    ወላዲቱ ደክማ መካኒቱ የመጽናናቷ ምስጢር ሰባት የወለደችው በትዕቢት በመናገሯ ነው፡፡ “ለምድር የከበደው” ጦረኛውና በሁሉ የተፈራው  ጎልያድ ወድቆ አባቱ እንኳ የረሳው እረኛው ብላቴናው ዳዊት በጠጠር የጣለው፤ የጌት ጎልያድ የትዕቢት ቃል ከአፉ ስለወጣ ነው፡፡ ትዕቢት ብርቱዎችን አድክማለች፤ አለን ያሉትን ህልውናቸውን አሳጥታለች፤ እንደተራራ ከፍ ያሉትን እንደደልዳላ ሜዳ ደልድላ ዝቅ አድርጋለች፡፡ ትሁታን ግን ከፍ ከፍ ብለዋል፤ ጸጋም በዝቶላቸዋል፡፡(ሉቃ.1፥52፤1ጴጥ.5፥5)
    ስለዚህ፦ “አትታበዩ፥ በኲራትም አትናገሩ፤
              እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ …
              ከአፋችሁ የኲራት ነገር አይውጣ፡፡” (1ሳሙ.2፥3)

በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅርና ሰላም ይብዛላችሁ፡፡ አሜን፡፡  

3 comments: