Thursday 16 October 2014

የአብያተ ክርስቲያናት ሐሳብ ያስጨንቀናል?



     የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ለተነገረለት ሳይሆን ላልተነገረለት ነገር በግድ በማስጨነቅ ከሚተረጐሙት ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ የመጻህፍትና የእግዚአብሔርን ኃይል ስለማናስተውል ብዙ ጊዜ በስህተት ወጥመድ እንያዛለን፡፡(ማቴ.22፥29) ቤተ ክርስቲያን በመመስረት ከሌሎች ሐዋርያት ግንባር ቀደሙ ሐዋርያ፥ ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ ለዚህም አገልግሎቱ ሦስት በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ አንድ ደግሞ በታሪክ የተረዳ በድምሩ አራት ታላላቅ ሐዋርያዊ ጉዞዎችን አድርጓል፡፡ በእነዚህ ጉዞዎቹ እጅግ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት መሥርቷል፡፡  (አንደኛው ሐዋርያዊ ጉዞ ሐዋ.13፥4-18፥28 ፤ ሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ 15፥39-18፥22 ፤ ሦስተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ 18፥23-21፥17 ያለው ነው፡፡)

     ሐዋርያው እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት ሲመሠርት በብልጠትና በሚያባብል ቃል፤ በሥጋዊ ጥበብ በመናገር ሳይሆን (2ቆሮ.1፥12 ፤ 1ተሰ.2፥5) የጸጋውን ወንጌል በድፍረት በመመስከር ነው፡፡(ሮሜ.15፥16) ምክንያቱም “የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና።”(1ቆሮ.4፥20) ስለዚህም ለህይወቱ አስጊና ከባድ የሆኑ መከራዎችን በመቀበል አገልግሏል፡፡(2ቆሮ.11፥23-27) ወንጌልን ሰብከን ከሰዎች መከበርና መወደድን መጠበቅ የወንጌሉን ጠባይ አለማወቅ ነው፡፡ እንኳን ወንጌልን “ሙሉ ስብዕና” ኖሯቸው ስለሰው እኩልነትና ነጻነት የተጋደሉትን የዚህን አለም ሰዎች እጅግ ብዙዎች አልተቀበሏቸውም፡፡
   ወንጌልን ሰብከን በብዙ ከተገፋንና ከተነቀፍን በእርግጥ እኛ የጌታ ልጆች ፤ የሐዋርያትም ባልንጀሮች ነን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የሐሰተኛ መምህራንን ጠባይ በሚገባ ከገለጠ በኋላ፥ የደረሰበትን መከራ በመጥቀስ ሐሰተኞችን ሊያሳፍር ይወዳል፡፡ ራሱን እንደክርስቶስ አገልጋይ እንጂ “የክርስቶስ አገልጋይ ነን” እንደሚሉት አይቆጥርም፡፡ እንደእነርሱ በቃል በመናገር አይደክምም፤ በህይወት ምስክርነት ያስረግጣል እንጂ፡፡
   ከዚህ ይልቅ ጳውሎስን የሚያስጨንቀው፤ የሚከብደውና ዕረፍት የማይሰጠው ብርቱ ነገር አለ፤ እርሱም የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ነው፡፡ “አብያተ ክርስቲያናት” የሚለውን ቃል ብዙዎቻችን የወሰድነው(የተረጎምነው) በሲሚንቶ በአፈር፣ በብረት በእንጨት፣ በሳር በቆርቆሮ፣ በድንጋይ በሸክላ … ስለተሠሩ የሰው እጅ ሥራ ገዳማት ፣ ካቴድራሎችና አድባራት ፤ ደብራት እንጂ ሌላውና ዋናው ምስጢር ወደህሊናችን የሚመጣው በብዙ ምጥና ጣዕር ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህ አስፈላጊዎች ቢሆኑም የቃሉ ዋና ሐሳብ ግን ይህን አይመለከትም፡፡

     አብያተ ክርስቲያናት የተባሉት በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ አምነው የተሰበሰቡ ምዕመናንን ለማመልከት የተነገረ ቃል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚለው በአንድ ቦታ (በአንድ ሐገር) ያሉትን ሲሆን አብያተ ክርስቲያናት የሚለው ደግሞ በመላው ዓለም የሚገኙትን የክርስቶስ ምዕመናንን ለመናገር የተፈለገ ሐሳብ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያንና ለአብያተ ክርስቲያናት አብዝቶ ሲጨነቅ ፤ ሲተጋ እናየዋለን፡፡ ሁለት ምሳሌ ብናነሳ፦
1.     ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን፦ ሐዋርያው ይህችን ቤተ ክርስቲያን ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን ከእንባ ጋር በማስተማርና በመገሰጽ ተግቶላታል፡፡ ለኤፌሶን ሽማግሌዎችም የተናገረው እውነትም ይኸው ነው፡፡(ሐዋ.20፥31)
2.    ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ያሉ አማኞች ደግሞ እያንዳንዳቸው እግዚአብሔር እንደከፈላቸው እንደጠራቸውም እንዲመላለሱ ይደነግጋል፡፡(1ቆሮ.7፥17)
    በእግሩ ተጉዞ ላልደረሰባቸውና ላላስተማራቸው አብያተ ክርስቲያናት የእምነታቸውን ጥንካሬ ሰምቶ፤ ጽፎላቸዋል፡፡ (ሮሜ.1፥8) ተምረው ወደኋላ ላፈገፈጉ ደግሞ የተግሳጽና የትምህርት መልዕክት፤ የተጣሉ አማኞች(ቤተ ክርስቲያኖች) ደግሞ እንዲታረቁ መልዕክት ጽፏል፡፡(ገላ.1፥6 ፤ ፊሊ.12)
    ቅዱስ ጳውሎስ “ይከብደኛል፤ ያስጨንቀኛል” የሚለው በእርግጥም ከብዶት፤ እውነትም ጨንቆት ነው፡፡ ተጨንቆ ደግሞ ግራ ገብቶት ወይም ምን ማድረግ እችላለሁ? ብሎ ተዘልሎ የተቀመጠ አይደለም፡፡ ከእርሱ እንደጌታ መንፈስ ቅዱስ ሐሳብ የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደረገ ነው እንጂ፡፡
     ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን እንድትሞት አይፈልግም፡፡ የሞተ ነገር ይሸታል፤ የሚሸት ነገር አፍንጫን ይሰነፍጣል፤ እንዲህ ለአፍንጫ ጠር ከሆነ ነገር ደግሞ ብዙ ሰው ይሸሻል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ስትለይ ትሞታለች ወይም የአለማውያንና የአህዛብን ፈቃድ ፈጻሚ ትሆናለች፤ ልጆቿንም ለእነርሱ ትገብራለች፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያን ያልተገባና እንግዳ ነገር ነውና ብዙዎች ከዚህ ነገሯ የተነሳ ይሸሻሉ፡፡
    ቤተ ክርስቲያን ከቃሉ እየራቀች ስትሄድ አለማዊነትን ከመካድ ይልቅ አለማዊነት በመካከሏ ይነግሳል፡፡ የክርስቶስም መልክ ሳይጠፋት ኃይሉን ግን ትክዳለችና ብዙዎች እንደመልኳ በህይወቷ ስላለላማረች ከእርሷ ይሸሻሉ፡፡ አለማውያንም ርዕስ አድርገው በጋዜጣ በመጽሔት በነውሯ ያላግጣሉ፡፡ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ነውር በግልጥ ወደአደባባይ ወጥቶ ነበር፤ መከፋፈሉ(1፥12)፣ ቅንአት ክርክሩ(3፥3) ፣ትዕቢቱ(4፥8) ፣ ዝሙቱ(5፥1)፣ ከአማኝ ባልንጀራ ጋር መከራከሩ(6፥1) … ጳውሎስ ግን ሳይሸፋፍን በግልጥ ወቀሳቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ዳነች፡፡(2ቆሮ.1፥24)
    በቅርቡ የቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የቤተ ክርስቲያናችን አማኞች ቁጥር መቀነሱን “ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫቸው” አሳውቀዋል፡፡ ቁጥሩ መቀነሱ ብቻ ተነገረ እንጂ የመቀነሱ ምክንያት ጥልቅ ጥናት የተደረገበት አይመስልም፡፡ ይሁንና ይህንንም እንደችግር መረዳቱ ጥሩ ነው፡፡ ግን የሚያሳዝነው ይህንን የፈጠጠ እውነትና አስጊ ነገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካባ አልብሰው “ድሮም የጻድቃን ቁጥር ጥቂት ነው፣ ከእኛ ስላልሆኑ ሄዱ ፣ አብ ያልተከለው ተክል  ይነቀላል …” የሚሉ ብዙ ነገሮችን ከብዙ ገጾች አንብቤያለሁ፡፡
    እውነቱን እንናገር ከተባለ፦ ክርስቶስን በሕይወቷ የምትሰብክ ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ስላላት “ጌታ የሚድኑትን ነፍሳት ዕለት ዕለት በእርሷ ላይ ይጨምርላታል እንጂ አያጎድልባትም፡፡”(ሐዋ.2፥47) እርሷም ኃጢአተኞችን እየቀጣች ስለእግዚአብሔር ቃል ማደግና መብዛት የምትተጋ ናት፡፡(ሐዋ.12፥24)
   እንኳን ያለበደሉ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተገፍቶ  የሚወጣ ይቅርና፥ ቅዱስ ጳውሎስ “በግልጥ ኃጢአት የሠራ ሰው” እንዲወገዝ፤ እንዲገለል(ውግዘት አያስፈልግም አልተባለም!) ሳይሆን እንዲመለስ ነው ትልቁ ጭንቀቱ፡፡(1ቆሮ.5፥5) ለአንድ አዳም ሊሞት ከመጣ ጌታ ተምረን በሚሊየንና በመቶ ሺህ ቁጥር እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን ለጣሉ ፤ ያዳናቸውን አምላክና ቤዛ ክደው ወደ አማሌቅ ምድር ለገቡቱ፥ እንዲሁም ባሳደገቻቸው ቤተ ክርስቲያን ላይ የጥፋት ጦር ለሚስሉ ልንራራላቸው ፤ ልንጨነቅላቸው ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ለመሆናቸው በብዙም ይሁን በጥቂቱ የእኛ ስህተት አለበትና፡፡
       ደግሞስ እኛ ለእነርሱ የሚገባውንስ ሁሉ አድርገናል? ከዘረኝነት የጸዳ አገልግሎትና ፍትህ ሰጥተን ይሆን? ከቤተ ክርስቲያን አንድነት በቀሩ ጊዜ ጳጳሱ፣ ቄሱ፣ መነኩሴው “ምነው ልጄ የት ቀረህ?” ብለው በአድራሻው ፈልገውታል? ለእርሱ እንደሚጨነቁለት እስኪገባው ድረስ ቤቱ ተመላልሰው በወንጌል ቃል ጎብኝተውታል?
     ሰባኪዎችስ ለአብያተ ክርስቲያናት(ላመኑ ሁሉ አማንያን) መጨነቃችን እስከምን ድረስ ነው? አማኞች ለገዳምና ለካቴድራል የምንጨነቀውን ያህል ከጎናችን ላለው ትልቁ የሥላሴ ህንጻ(የሰው ልጅ) ተጨንቀንስ እናውቃለን? ጌታ ማስተዋልን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡
እንኪያስ ሐዋርያው ግን እንዲህ ይላል፦
      “ለምዕመናን ሳስብ ከዚህ ሌላ ዕለት ዕለት ያገኘኝ መከራ ብዙ ነው፡፡”(1ቆሮ.11፥28)( በግርማዊ ቀዳ. ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጲያ መልካም ፈቃድ በአሜሪካ ከታተመው የ1938 ዓ.ም መጽሐፍ ቅዱስ ከታተመ የተወሰደ፡፡)
የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሠላም ይብዛላችሁ፡፡ አሜን፡፡


1 comment: