ለዚህች አጭር ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ የምወደው፤ በአክብሮትም የሚያስተምረኝ ወንድሜ ከነገረኝ ነገር በመነሳት ነው፡፡
“አየር መንገድ ላይ ነው፡፡ ወንድሜ ሰው ለመጠበቅ እዚያ ከተቀመጠበት ከጐኑ ‘የተፈራና የተከበረ’ አገልጋይ ተቀምጦ በኪሱ ስልክ
ያወራል፡፡ የሚደውልለት ለአገልግሎት ከኢትዮጲያ ውጪ እየጋበዘው ነው፡፡ ግና ሲጀምር ለአገልግሎት ከአንድ አገር ተጠርቶ በእርሱ
በኩል ሌላ አገልጋይ የጠየቀው ጥያቄ ‘በአሪፍ ይሸኛሉ ወይ?’ ብሎ ነው፡፡ … ቀጠለ በአሪፍ የማይሸኙ ከሆነ ላይመጣ እንደሚችል
በሚያቅማማ ድምጸት መለሰ፡፡ ወይ በአሪፍ መሸኘት!
ለነገሩ
እኔም በአይኔ ያየሁት አለ፡፡ በአንድ የገጠር አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ንግስ ታኮ በብዙ ድካም የሦስት ቀን ጉባኤ ይዘጋጃል፡፡
“ለጉባኤውም ለንግሱም ድምቀት” ለብዙዎች ጆሮ ቅርብ ሆነና “የገነነ ስም ያለው ሰባኪም” ተጠርቷል፡፡ በጉባኤው ማብቂያ “ታዋቂው
ሰባኪ” ከተሰበሰበው አንድ ሦስተኛው የእርሱ ድርሻ እንደሆነ ገለጠ፡፡ በእርሱ ጥረት ስለተገኘና ጉባኤው የደመቀው በእርሱ እንደሆነ
በማስረገጥ፡፡ “በአሪፍ ካልሸኙትም” ዳግም ላይመጣ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ እኒያ ምዕመናን እያዘኑ አንድ ሦስተኛውን ሲሰጡት፥
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሌላ “ታዋቂ ሰባኪ” ላይጠሩ መማላቸውን አልተጠራጠርኩም፡፡
አንድ
እውነት አለ፤ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” እንደተባለ የሚያገለግልም አገልጋይ በእውነት ስለአገልግሎቱ ሊበላ፣ ሊጠጣ፣ ሊለብስ፣
ሊከፈለው … መብት አለው፡፡(1ቆሮ.9፥8-11) አገልጋይ መንፈስ ወይም መልአክ አይደለምና እንደሠራተኛነቱ “ለሠራተኛ ምግብ፤ ደመወዝም
ይገባዋል፡፡ (ማቴ.10፥10 ፤ ሉቃ.10፥7) ለአገልጋይ ከዚህ የሚልቀውና እጅግ የሚበልጠው ደመወዙ ግን ምድራዊ መልክ የሌለው
ዋጋው እጅግ የከበረ፤ ሰማያዊ ነው፡፡ ሰማያዊውን የክርስቶስን መንግስት የምናገልግል ሰማያውያን አምባሳደሮች ከሆንን፥ የሚበልጠውን
የዘለዓለሙን ምግብና ደመወዝ ማሰብ ይገባናል፡፡
በእግዚአብሔር
አገልግሎት ምክንያት በሥጋዊ ድሎትና ቅንጦት ለመኖር ወንጌሉን የሚቸረችሩ፣ ጸሎቱን በገንዘብ የሚተምኑ፤ በከንቱ የተቀበልነውን ለማንም
ሸክም ሳንሆን በቅድስናና ጽድቅ፤ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ በመሄድ በከንቱ መስጠት ሲገባን ስለምን ነው “በአሪፍ አልተሸኘንም” ብለን
የምናኰርፈው? በጌታ ልቡን ያሳረፍነውና፤ አገልግለን ስንት ሰው ፊቱን ወደጌታ ዘወር አደረግን? ማለት ከተሳነንና የተሸኘንበትን
የገንዘብ መጠን፤ መስተንግዶና ምግቡን አድንቀን ከተመለስን ነገር በእርግጥ ተለዋውጦብናል፡፡
መዳናችን
በጸጋ(ያለክፍያ እንዲሁ) ነው፡፡ ክፍያው በላይ በሰማይ በአብ ፊት የሆነና የተከናወነ ነው፡፡ ይኸውም የእኛን ሞት ሊሞት የእርሱን
ህይወት ሊሰጠን መለኮት መዳናችንን በጽኑ ፍትህ ከእኛ ምንም ሳይታከልበት በነጻ አድሎናል፡፡ ይህን እውነት በማሰብ ስለዚህ ዘመን
አገልጋዮች ቃለ መጠይቅ የተደረገለት አንድ ብርቱ የእግዚአብሔር ወዳጅ እንዲህ ብሎ መልሷል፦ “ … መቼም ክርስቶስን በሰማያዊ ሥፍራ
የሚጠይቁት አንዳች የላቸውም፤ በወንጌሉ ስም ሁሉን ተድላና ቅንጦት ከዚሁ ተቀብለዋልና…”፡፡
በእርግጥም
እንድናገለግል የተጠራነው “የሚበልጠውን መንፈሳዊ ዘር ዘርተናልና ለሥጋ የሚሆነውን ብናጭድ ትልቅነትና ክብር ነው” የሚለውን የዚህን
ዘመን “መብትና ጥቅማችንን” በመተው (1ቆሮ.9፥12)፤ በከንቱ የተቀበልነውን በከንቱ በመስጠት (ማቴ.10፥8) አልያም ከምናገለግልበትም
ከዚያ መንደርና ወገን … ከእነርሱ ዘንድ ካለው(ቤታቸው ካፈራው)
እየበላንና እየጠጣን ሊሆን ይገባዋል እንጂ(ሉቃ.10፥7) ረብና ሥጋዊ ጥቅም፤ ምቾትም በመሻት የአገልግሎታችንን ክብር ልናዋርደው
አይገባንም፡፡
ስለዚህ
ነገር ቅዱስ ጳውሎስ እንደዚህ ይላል፦ “ወንድሞች ሆይ፥ ድካማችንና ጥረታችን ትዝ ይላችኋልና፤ ከእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት
ሌሊትና ቀን እየሠራን፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ሰበክን። በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም
በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤ …”(1ተሰ.2፥9-10) መቼም ከጸጋው ወንጌል ይልቅ ልባችን
ወደብልጥግናው ወንጌል ፈቀቅ ካላለ በቀር የዚህ ቃል ፍቺ ምንም ሐቲት፤ አንዳች አንድምታ አያስፈልገውም፡፡ የተሰሎንቄ አማንያን
በግሪክ አማልክት አስተምህሮ ሥር ወድቀው፤ ግሪካውያን ስለአማልክቱ ክብር በእጅ ሥራን አይሰሩም ነበርና ሐዋርያው የእጅ ሥራ የባርያ
ብቻ አይደለም፤ የአማኝ በተለይም የአገልጋይ መሆኑን ሠርቶ አሳያቸው፡፡
ለቤተ
ክርስቲያን አገልጋዮች መዝሙርና ስብከት በገንዘብ እንደመተመንና በዚህም ተንደላቆ በቅምጥልነት ለመኖር እንደማቀድ ያለ ውርደትና
ቅሌት የለም፡፡ በእውኑ የምግብና የትራንስፖርት ከተሸፈነልን ማበራየታችን ያልታሠረ፤ የሚበቃንስ አይደለምን? ዋጋችንን ስለምን እናረክሰዋለን?
አገልግለን የተጣልን ብንሆን በክርስቶስ ፊት ለእኛ አይሻለንምን? እንደተወደዱ አገልጋዮች ሥልጣን እያለን ያለሥልጣን መሆንን ስለምን
አልፈለግንም?(2ተሰ.3፥9) ስለምናገለግላቸው ምዕመናንና ምዕመናት ስለምን ነው የምንጠነቀቀው? ያለደመወዝ ማገልግል እኰ መዋረድ
ወይም ዝቅ ማለት አይደለም!!! “ … ወይስ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ስለ ሰበክሁላችሁ፥ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን
እያዋረድሁ ኃጢአት አድርጌ ይሆንን?” (2ቆሮ.11፥7)
አዎ!
እውነተኛው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “… በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና
በራቁትነት ነበርሁ።” (2ቆሮ.11፥27) ካለንና በህይወቱ ካስተማረን እኛ ያልለፋንበትን መሰብሰብ፣ ያልዘራውን ማጨድ፣ ያላከማቸነውንም
መጐምጀት ነውርና ኃጢአት አመጸኝነትም ነውና … እናንተ አገልጋዮች ሆይ! በጌታ መክበር ማለት በዚህ ምድር ቅምጥልነት፣ በጌታ ስም
መበልጠግ፣ በአገልግሎት ሰበብ ሀብት ማካበት … አይደለምና ደግሜ እላለሁ “የገዛ እንጀራችሁን እየበላችሁ” (2ተሰ.3፥12) ጸጋውን
ወንጌል ለፍጥረት አድርሱ፡፡
ጌታ
ልባችንን ወደጸጋው ወንጌል ያዘንብልልን፡፡ አሜን፡፡
God bless you brother. it is important message to all
ReplyDelete