Monday 26 May 2014

የትንሣኤው ምስክሮች

    የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል ሙስና መቃብርን አጥፍቶ መነሣት የክርስትና መሠረት የቆመበት ጽኑ ዐለት ነው፡፡ አሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ደም በጸጋ ድነናል፤ ወደፊት ደግሞ ፍጹም እንድናለን፤ (ኤፌ.2፥8) ብለን ደፍረንና ጨክነን ጮኸን የምንናገረውና ቤተ ክርስቲያንም አሰምታ የምትሰብከው እርሱ ዝጉን መቃብር ሳይከፍት፤ የታተመው ድንጋይ ሕትመቱ ሳይፈታ፤ ሞትን ድል አድርጎ ከሙታን መካከል ስለተነሣ ነው፡፡
     የጌታ ትንሣኤ የስብከቶች ሁሉ ዋናውና የመጀመርያው፤ ትልቁም ርዕስ ነው፡፡ አንድ ሰባኪ የእግዚአብሔርን ቃል ሊናገር በወጣበት አውደ ምሕረት ላይ “ብዙ ቃል” ሰብኮ የጌታን ትንሳኤ ሳይናገር ቢወርድ፤ በእውነት! እውነተኛ ሰባኪ መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ ምንም እንኳ ጥቂት እንከኖች ቢኖርባትም ያቺ በተራራ ላይ የተሠራችውና ታበራ የነበረችው የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን በአስቆሮቱ ይሁዳ ፈንታ ሌላ ሐዋርያ ሊመርጡ ባሉ ጊዜ ያስቀመጡት የመጀመርያው መስፈርት “ … ከእነዚህ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል”(ሐዋ.1፥22) የሚል ነው፡፡
    ደቀ መዛሙርቱ ያልተደራደሩበት እውነት “ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር” የሚሆን ብቻ እርሱ እውነተኛ የጌታ ሐዋርያ ነው ብለው ማመናቸው ነው፡፡ ጌታ ከሙታን መካከል መነሣቱን የሚያምኑና የሚያውቁ ብዙ ሰዎች በዚያን ጊዜ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ የተፈለገው፤ ጌታ “እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ ”(ሮሜ.1፥4) መሆኑን ሳይፈራ ሳያፍር በአደባባይ የሚመሰክር ሐዋርያ ነው፡፡

     የዛሬ ዘመን አገልጋዮች ትልቁ ፈተና ይህን አለመረዳት ነው፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ የዛሬ ዘመን አገልጋይ ነውና የቀደመ ዘመን የራሱን ስብከት ዕድፍና ጉድፉን ያውቀዋል፤ አውደ ምሕረት ላይ በወጣ ጊዜ ከሞቱና ከትንሣኤው ርቀው ይሰብካቸው፤ ያስተምራቸው የነበሩት ርዕስና ሐሳቦች በፍጹም አይዘነጉትም፡፡ ዛሬም ላይ በግብዝነት ራሱን ከፍ ከፍ አያደርግም (አያጸድቅም፤ አያመጻድቅም)፤ “እንደጲላጦሳዊ ጽድቅ” እጄን ታጥቤያለሁ በደል የለብኝም ለራሳችሁ ተጠንቀቁ አልልም፡፡ የስህተቱ አንድ አካል ነኝና፡፡ ግና “እንደአጋንንታዊ ንስሐ” ስህተት በስህተት ይጥራ አልልም፡፡ አዎ! እንድንታረም፤ ወደእውነተኛ መልካችን እንድንመለስ እንጂ፡፡
      በወጡበት አውደ ምሕረት ላይ የራሳቸውን የወየበና የቸካ “ትምህርት”፣ የሚጎረብጥ፤ ለነፍስና ለመንፈስ የማይለደልድ የትንቢት(የምክር ቃል)፣ በነገር ማርዘምና መደጋገም ፍሬ አልባ እንቶ ፈንቶ ብልሐታዊ ተረት … እየሰበኩ የክርስቶስን የደም ዋጋና የትንሣኤውን ዋና ነገር ዘንግተው ህዝብ አሰልችተው መቅበዝበዙን ሳያሳርፉ፣ ማዘኑን ሳያጽናኑ፣ ተስፋውን ሳይቀጥሉ፣ ከእረኛው ሳያገናኙ፣ ባዛኙን በግ ይብስ ለተኩላ የሚያደላድሉ ለሆዳቸውና ለጎጇቸው ትንሳኤ እንጂ ለክርስቶስ ትንሣኤ የማይተጉትን በብርቱ ቃል መውቀስ ይገባናል፡፡
    አንድ አገልጋይ በሁል ጊዜ አገልግሎቱ የማይዘነጋው የምስክርነት ቃል “መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ”(1ቆሮ.15፥3-5) የሚለው ቃል ነው፡፡ጌታ በዘመነ ሥጋዌው ለሁል ጊዜ የተናገረው ሞቱንና ትንሠሣኤውን ነበር፡፡ ይህን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በመጣ ጊዜ ሁሉን ገልጦ ለሐዋርያት እንደሚነግራቸው “ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ”(ዮሐ.15፥26-27) ብሏቸዋል፡፡ የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ስናጠና ሐዋርያቱ ጌታ እንደተናገራቸው በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ ያልዘነጉትና ቢደጋግሙ ያልሰለቹት “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን”(ሐዋ.2፥32)፤ “ … የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤ እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፥ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን”(ሐዋ.3፥15) … የሚለው ድንቅ የምስክርነት ቃላቸው ነው፤ (4፥2 ፤ 10 ፤ 33 ፤ 5፥30… ጥቂት ማሳያ ጥቅሶች ናቸው፡፡)
   የጌታ ትንሳኤ በሐዋርያቱ ስብከት ለአንድም ቀን ያልተዘነጋ ዋና ርዕስ ነው፡፡ መከራ የተቀበሉበት፣ ወህኒ የተጣሉበት፣ ከሰው መካከል የተወገዱበት፣ መናፍቃን ተብለው ፍጹም የተወገዙበት … የጌታን ትንሣኤ ደፍረውና ጮኸው በመስበካቸው ምክንያት ነው፡፡ ሐዋርያት በስብከታቸው ሁሉ መዳናችን የተረጋገጠበትን እውነተኛውን ይህንን ርዕስ በዋናነት ከሰበኩ የዛሬ ዘመን አገልጋዮች ምነው ከዚህ ከዋናው ርዕስ ፈቀቅ አሉ? መድረኩንና አውደ ምሕረቱን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆነ ትምህርትና ፌዝ፤ ሳቅና ስላቅ መሙላትን ከየት ይሆን ያመጡት?
    አዎ! ሕዝቡ እንዲያርፍ፤ ከመቅበዝበዙ እንዲመለስ የሞተለትንና የተነሳለትን ጌታ እንስበከው፡፡ ያለትንሣኤውም ምስክር ስብከታችን ከንቱ መሆኑን ልብ ልንል ይገባናል፡፡ በአንድ ወቅት ቅዱስ ጳውሎስ ጠርጠሉስ በሚባል ዋና ጠበቃ በአገረ ገዢው ፊልክስ ፊት በሙታን ትንሣኤና በብዙ ክስ ተከሰሰ፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጳውሎስ ስለክሱ ሲመልስ እንዲህ አለ፦ “… ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ…”(ሐዋ.24፥14-16)፡፡
  አሜን፡፡ ዛሬም ብዙዎች መናፍቅነት በሚሉት በጌታ መንገድ የአባቶቻንን አምላክ እንዲህ እናመልካለን፤ እንሰብካለን፤ እንመሰክራለንንም፡፡


No comments:

Post a Comment