Tuesday 6 May 2014

ደቀ መዛሙርት የጌታን ትንሳኤ ለምን ተጠራጠሩ? (ክፍል - 2)

     ደቀ መዛሙርቱ የተወራውን ወሬ በማመናቸው ሲጠራጠሩ ታይተዋል፡፡የመግደሎሟ ሴት “ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም … አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርከው ንገረኝ”(ዮሐ.20፥13-16) ማለቷ መሰረቁንና መወሰዱን ያመነች ይመስላል፡፡ጌታ ስለዚህ አለማመኗ “አትንኪኝ” በማለት ወቅሷታል፡፡ማርያም መግደላዊት ቀድሞ የት እንዳኖሩት ወይም እንደቀበሩት ቆማ ተመልክታ ነበር ግና ከመነሳቱ መሰረቁን ተቀበለች፡፡(ማር.15፥47)፡፡የጠላት ወሬ ምን ያህል ልብ እንደሚለውጥ አስቡ! ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ እነሳለሁ ያላቸውን ጌታ ረስተው፤ ቃሉን ዘንግተው ግን የተወራውን አብልጠው ተቀበሉ፡፡ደቀ መዛሙርቱ ከወንጌሉ ይልቅ ለጊዜውም ቢሆን የጠላትን ወሬ ማመናቸው እጅግ ይደንቃል!
   በእርግጥም የዛሬ ዘመን እልፍ አገልጋዮችና አማኞች የሚፈሩት ነገር ከሌላ ወገን የሚወራን ወሬ ነው፡፡ከሁሉ ይልቅ በተለይ ብዙዎች አገልጋይና አማኞች በኢየሱስና በስሙ መታማት አንፈልግም፡፡ምክንያቱም ስሙን ከደጋገምን አንድ ከባድ የሚለጠፍብን ታርጋ አለ፡፡“ጴንጤ ፣ተሐድሶ፣ጸረ ማርያም፣ጸረ ቅዱሳን፣መናፍቅ … ”የሚሉና ሌሎችም፡፡ ብዙ ጊዜ የክርስቶስ ስሙን ለሆዳቸው የሚቸረችሩ አገልጋይና አማኞችን በማየቴ ብዙም አልደነቅም፡፡ነገር ግን ለእውነት ሳንቆም በገና ለገና የሰው ወሬ የምንፈራ ከሆንን እውነተኛ ምስክር መሆናችን አይገለጥም፡፡
   ወሬው በጊዜው ቀላል አይደለም፡፡ማቴዎስ ወንጌሉን ይጽፍ በነበረበት ዘመን እንኳ ተሰርቋል የሚለው ወሬ በአይሁድ ዘንድ በጣም ይወራ ነበር፡፡(ማቴ.28፥15) አዎ! ታርጋ ከተለጠፈብን በኋላ ስለምንናገረው እውነት ሰሚ ማግኘት በጣም ከባድ ነው፡፡ለልባችን ቅርብ የነበሩቱ እንኳ በወሬው ብቻ በጠላትነት ጎራ ሊሰለፉብን ፣የማያውቁን አይናቸውን ጨፍነውና በጨው አጥበው ስማችንን ጥላሸት ሲቀቡት ተለምዶ፣ተዋህዶ፣ሥርዓት ሆኖ ይኸው እያየን ነውና በእርግጥም ያማል፡፡
     በተለይ መገናኛ ብዙሃን ለእውነት ሳይቆሙና ሳይቀኑ በእንቶፈንቶ ቋታቸውን ሲሞሉ ለሀገርና ለወገን የሚረባውን ትተው ተራ ወሬና ያልተባለን እየቀጣጠሉ ሲያወሩና እንደመቃኞ በሬ ሰዎችን ሲነዱ ማየት የበለጠ ልብ ይሰብራል፡፡ ብናስተውል ፖለቲካችን ያልተፈወሰው፣ስብከታችን የጠነዛው፣ክህነታችን የገረጀፈው፣ድቁናችን የነቀዘው፣ ቅስናችን የተናቀው፣ጵጵስናችን የተነቀፈው፣ ንግግራችን የተጠላው … ወሬን ማለፍ ስላልቻለና ከተግባራችን ጋር ፍጹም ዝምድና ስለሌለው ነው፡፡

    ደስ የሚለው፤ ጠላት ቀድሞ  የሚያወራው የጨበጥነው የክርስቶስ እውነት ህያውና የማይሻር ሰለሆነ ውሸቱ እንዳይገለጥበት ፈርቶ ነው፡፡ነገር እስኪገለጥ ሐሰት ከእውነት ጋር ተደባልቆ ይኖራል፤ክርስቶስ ሲነሳ ግን ሐሰትና ሰይጣን ለዘላለም ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡አዎ! ልንጨክን ይገባናል እንጂ የሰው አፍና ወሬ ፈርተን ከመጨከን ወደኋላ በማለት ትጥቃችንን ልንፈታ አይገባንም፡፡ገና ለገና ከሚለጠፍብን ታርጋ የተነሳ “እንጀራችንንና ቤተሰባችንን እንዳናጣ” ፈርተን ጥግ የቆምን ቀኑ ድንገት መሽቶ መቅረዛችን እንዳይወሰድ መጠንቀቁ ይበጀናል፡፡ በንጉስ ክርስቶስ የንጉስ ወገን ተብሎ መታማት ክብር እንጂ ውርደት የለበትምና፤ ጌታም እንደተነገረበት ሳይሆን እንደተናገረው ቃሉ ተነስቷልና ጠላቴ ሆይ ደስ አይበልህ!
    2.  የስህተት ትምህርት ፦ የጌታ ደቀ መዛሙርት የተጠሩት ከተለያየ ሥፍራና ሙያ ነው፡፡ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያ ደቀ መዛሙርት መካከል ማቴዎስ ከቀራጭነት (ማቴ.9፥9) ሲጠራ ከብዙዎቹ ረዳት ደቀ መዛሙርት ደግሞ ሉቃስ ከህክምና ሙያው የተጠራ ነው፡፡(ቆላ.4፥14) አገልግሎት ጥሪ ነው እንጂ ሙያ አይደለም፡፡ ጌታ ሙያተኛ እረኞችን አብዝቶ ወቅሷል፡፡“ … ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? ጮማውን ትበላላችሁ ጠጉሩንም ትለብሳላችሁ፣የወፈሩትን ታርዳላችሁ በጎቹን ግን አታሰማሩም፡፡ … ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ ፣በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና … ” (ህዝ.34፥2-3፤9) የሚለውን ቃል ስናስብ የዛሬዎቹ በላተኛ (በልተው የሚተኙ) አገልጋዮች ከመታዘብ አልፈን ሙያተኞች እንጂ የተጠሩ አለመሆናቸውን እንረዳለን፡፡ለዚህ ነው ጌታ “እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል …” በማለት (ዮሐ.10፥12) የተናገረው፡፡በእርግጥም ቅዳሴውና ኪዳኑ፤ ስብከቱና ጉባኤው ገቢ ማግኛ ሙያ እንጂ ለብዙ አገልጋዮች በቅድስና የሚደረግ መንፈሳዊ ተግባር መሆኑ የተካደና የሚታይ እውነት ነው፡፡
    ጌታ ደቀ መዛሙርቱን ከጠራ በኋላ ደጋግሞ ያስጠነቀቃቸው “ከፈሪሳውያን እርሾ” ማለት “ከሐሰተኛና ግብዝ ትምህርታቸው” እንዲርቁ ነው፡፡(ማቴ.16፥6፤12፤ሉቃ.12፥1) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመልዕክታቱ ትልቅና ዋና ሃሳብ የመናፍቃንን ትምህርት በመቃወም መልስ በመስጠት ላይ በማተኮር የጻፈ ሐዋርያ ነው፡፡አንዱ የአገልግሎት ዘርፍ የመናፍቃንን ትምህርትና አስተምህሮ በሚገባ ነቅሶ በእውነተኛው የመዳን ወንጌል በየዋህነትና በፍርሃት መልስ መስጠትና መቃወም እንጂ(1ጴጥ.3፥15) አይን ጨፍኖ መሳደብ አይደለም፡፡ መሳደቡና ማንጓጠጡ የትም አላደረሰንም፤ ወጣቶቻችንን ለኦሾና ለራንባ ከንቱ ፍልስፍና አሳልፎ ከመስጠት ውጪ፡፡
 ጌታ ኢየሱስ ከሙታን ተነስቶ ለሐዋርያትና ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠበት በመጀመርያዎቹና በሁለተኛው መገለጥ ቶማስ የተባለው ዲዲሞስ ከመካከላቸው አልነበረም፡፡ስለዚህም ያዩትን በነገሩት ጊዜ እርሱ “ካላየሁ አላምንም” ብሎ ተከራከረ፡፡(ዮሐ.20፥24) በእምነት አለም እያዩ ማመን ያደክማል፡፡እያመኑ ማየት ግን ነፍስን ያለመልማል፡፡የፈሪሳውያን ትልቁ  ችግር እያዩ “ማመን” ነበር፡፡ ስለዚህ ሁል ጊዜ ለማመን የሚታይ ነገር ይፈልጋሉ፡፡(ማቴ.12፥38)የዛሬዋም ቤተ ክርስቲያን አማኞች ትልቁ ችግራቸው ማመንን ሳይሆን ተአምራትን ለማየት ፍለጋ ከአንዱ ቤተ ክርስቲያን ወደሌላ ቤተ ክርስቲያን ፣ከአንዱ ጸበል ወደሌላ ጸበል፣ከአንዱ አጥማቂ ወደሌላ አጥማቂ ፣ከአንድ “ፈዋሽ” ወደሌላ “ፈዋሽ” … ሲንከራተቱ እናያለን፡፡ያመነች ነፍስ ግን ያመነችውን በሩቅ አይታለችና በተስፋ እየተጽናናች ትጠባበቃለች፡፡(1ተሰ.4፥8)
   ቶማስ “ካላየሁ አላምንም” የማለት ምክንያቱ የተጠራው ከሰዱቃውያን መካከል ነው ይላሉ መተርጉማነ መጻህፍት፡፡ሰዱቃውያን ደግሞ ትንሳኤ ሙታንን አይቀበሉም፡፡(ማቴ.22፥23) ስለዚህም ቶማስ ምንም እንኳ ከጌታ ዘንድ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ቢማርም “ያ ቅሪት” አልወጣለትምና፤ ተጠራጠረ፡፡የቀደመው ዘመን የመጀመርያው መናፍቃን የሚባሉት የግኖስቲካውያን መሥራቾች ሁሉም የጌታን ወንጌል የተማሩና ያጠኑ ናቸው፡፡ግና ወደገዛ ህሊናቸው ስላዘነበሉ ከእውነተኛይቱ ወንጌል ተለዩ፡፡
   ጌታ ግን “ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን … ሳያዩ የሚያምኑም ብፁዓን ናቸው” ብሎ ወቀሰው፡፡”(ዮሐ.20፥27-28) የሚያምኑ ብፁዓን የተባሉት ስለማያዩ አይደለም፤ በአይን ከማየት ይልቅ በእምነት ስለሚያዩ ነው እንጂ፡፡ለቁሳዊው ዓለም ያላመነ ሰው ግን ብዙዎች ለሚጋደሉበት ለዚህ ቁሳዊ ዓለም አይን የለውም፡፡ስለማያስፈልግ ሆኖ አይደለም ከያዘው ነገር ፈጽሞ የማይነጻጸር መናኛ ስለሚሆንበት እንጂ፡፡
በወሬ ከመፈታት በማመን ማየት ይሁንልን፡፡አሜን፡፡

ይቀጥላል …

1 comment:

  1. ያመነች ነፍስ ግን ያመነችውን በሩቅ አየይታለችና በተስፋ እየፀናች ትጠባበቃለች 1ተሰ4:8

    ReplyDelete