3. መጠራጠር ፦ ደቀ መዛሙርቱ ነገረ ትንሳኤውን ሲሰሙ የተነገራቸው “ … ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑም፡፡”(ሉቃ.24፥11) ደቀ መዛሙርት አርብ ዕለት በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነውን መከራ አይተነዋል፡፡ስለዚህ ሁሉም “ተሰብስበው … አይሁድን ስለፈሩ ደጅ ዘግተው … ” በፍርሐት ቆፈን ውስጥ ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ (ዮሐ.20፥19) እግዚአብሔርን የማይፈራ ፍርሃት ጥበብ የጎደለው ፍርሃት ነው፡፡እግዚአብሔርን እስከመካድ ያደርሳልና፡፡
ጴጥሮስ “አንተ
ክርስቶስ የህያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ”(ማቴ.16፥16) ብሎ የመሰከረለትን ጌታ ከሥጋዊ ፍርሃት የተነሳ በአንዲት “ነጻነት በሌላት”ሴት
ፊት በተጠየቀ ጊዜ “የምትይውን … ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ ካደ፡፡(ማቴ.26፥70፤72) “መለኮታችን” መለኮትን ፤ፍርሃታችን
እግዚአብሔርን መፍራት ካልቻለ ፍርሃታችን የራሱን መለኮት ፈጥሮ መካዳችን የማይቀር ነው፡፡ጌዴዎን የመፍራቱና የመጠራጠሩ ምንጭ የምድያማውያን
ጥቃትና እግዚአብሔርም እንደተዋቸውና እንደጣላቸው ማሰቡ ነበር፡፡(መሳ.6፥11-13)
አይሁድ ሁሉንም ሰው በክርስቶስ ሞት እንዲተባበር ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉት
ወይም እንዲገድሉት ህዝቡን እጅግ አባብለዋል፡፡ስለዚህም ሁሉም ይሰቀል እያሉ ጩኸት አብዝተዋል፡፡(ማቴ.27፥20፤23) ይህም በራሱ
ለደቀ መዛሙርቱ ከባድ የፍርሃትና የጥርጥር ምንጭ ነው፡፡ አለሙ የተስማማበት ብዙዎች የተከተሉት ውሸት በእርግጥ ለዘመናት ብዙዎችን
በጥርጣሬ መንፈስ ወደኋላ ስቧል፡፡ ዛሬም ወንጌልን በድፍረት እንዳንመሰክር የሚያደርገንና የፍርሃታችን አንዱ ዋናው ምንጭ ስህተት
የሆነውን ነገር የተቀበለው ህዝብና ወገን በፍጥራዊው አይናችን ፊት በዝቶ ስለታየንና ትልቁን የጌታ ክንድ መዘንጋታችን ወይም መጠራጠራችን
ነው፡፡ በመጠራጠር ወደኋላ መመለስ ደግሞ ውጤቱ ካለማመን ይበልጥ ሊከፋ ይችላል፡፡ስለዚህም “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም
የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና”(2ጢሞ.1፥7) በመንፈስ አካለ መጠን ልንጎለምስ ይገባል፡፡
ጠላት ክንዱ በበዛና ክንዱም በበረታ ጊዜ ይህ ፍጥረታዊው ሰው በፍርሃትና
በጥርጣሬ ካልቀለጥሁ ይላል፡፡የዚያን ጊዜ ግን ጠላትን ሁሉ እንደአንድ ሰው መምታት እንዲቻለን ኃይልና ጥበብን የሚሰጠንንና ለእጆቻችንም
ሰልፍን የሚያስተምረውን ጌታ በብዙ ልንታመንበት ይገባናል፡፡በእርግጥ እርሱ ሳይታዘብ ደካማውን ይረዳልና፡፡
4.
የመጻህፍትን ኃይል መሳት
፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ያለማስተዋላችን ትልቁ ምስጢር “መጻህፍቱንና ኃይሉን ባለማወቅ መሳታችን” ነው፡፡(ማቴ.22፥29)
ደቀ መዛሙርቱ ጌታ ገና ከእነርሱ ጋር ሳለ “በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም …” ስለእርሱ የተጻፈውን ሁሉ በጆሮአቸው ነግሯቸው
ነበር፡፡(ማቴ.16፥21፤ማር.10፥32፤ሉቃ.4፥21፤24፥44) መላዕክቱ እንኳ በተገለጡ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገሩት “የሰው
ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሳ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደተናገረ አስቡ፡፡”(ሉቃ.24፥7)
እያሉ ነበር፡፡ደቀ መዛሙርቱ ግን ከማስተዋል የዘገዩ ይመስላል፡፡
ሰፊው የክህደት በር እግዚአብሔር የተናገረው ቃሉን ችላ ከማለትና ካለማስተዋል
ይጀምራል፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱንና ሃሳቡን የገለጠልን በቅዱስ ቃሉ አማካይነት ነው፡፡እግዚአብሔር የተናገረን እንደአባት ልጆች ለምንሆን
ለእኛ ነው፡፡የሚናገረንም እንዳንጠፋና እንዳንቅበዘበዝ በዕረፍቱ ጥላ ሥር እንድንሆን ነው፡፡(ምሳ.1፥33፤ኢሳ.48፥16)እረኛ እንደሌለን
በጎች ተጨንቀን ተጥለንም ባየን ጊዜም ያዝንልናል፤ ቃሉንም በየመንደራችን ዞሮ ያስተምረናል፡፡(ማቴ.9፥31) በፊቱም በመታዘዝ በቀረብን
ጊዜ ቃሉን እናደምጥ ዘንድ ልባችንን ይከፍትልናል፡፡ (ሐዋ.16፥15)
ቃሉን በጸሎትና በማጉተምተም ማንበብና ማጥናት ከምንም በላይ የአንድ ብርቱ
ክርስቲያን ትልቅ መገለጫ ነው፡፡ ህይወት አልባ ክርስቲያን ያፈራነው፣ዘፋኝና ጨፋሪ አማኝ ያበዛነው፣ቃሉን ሳያጠኑ በድፍረት የሚሰብኩ
አገልጋዮችን በጉያችን ያፈላነው፣ቃሉንና ኃይሉን የማያውቁ በቤቱ ላይ
በሰበካ መንፈሳዊ፤ስብከተ ወንጌል ክፍልና ሰንበት ትምህርት ቤት ላይ የሾምነው ቃሉን ከማጥናትና ከማንበብ ባዕዳን ስለሆንን ነው፡፡
በዘመናችን ከምንም ጊዜ በላይ የእግዚአብሔር መጻህፍትና ኃይላቸው የተዘነጋበት
ዘመን ነው፡፡የእግዚአብሔር ቃል ወደርና የሚመስለው የለም፡፡መጽሐፍ ቅዱስ እርሱን የሚመስል የሌለው ድንቅና ትልቅ መጽሐፍ ነው፡፡ነገር
ግን ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ከመጽሐፍ ቅዱስ እኩል የሚታዩ ወይም በላይ የሆኑ ጥቂት ያይደሉ መጻህፍት አሏቸው፡፡እንደውም ቃሎቻቸው
ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃልና እውነት በላይ ይታያሉም፡፡ ይህ ነው እንግዲህ መጻህፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል መሳትና አለማወቅ ማለት፡፡
እናም ደቀ መዛሙርቱ ይህን ቃሉን ፈጽሞ ማስተዋል አልተቻላቸውም፡፡ስለዚህም
ጌታ “እናንተ የማታስተውሉ ፥ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ…” (ሉቃ.24፥25) በማለት አብዝቶ ወቀሳቸው፡፡አዎ!
ከጌታ ክርስቶስ ኢየሱስ ቃል በምናስበልጠው በማናቸውም ቃላችንና ድርጊታችን ይህ ተግሳጽና ወቀሳ ያገኘናል፡፡አለማስተዋል ያደነዝዛልና
ካላስተዋልንበት ዘመናችን ዛሬ በቃሉ እውነትና ኃይል እንንቃ፡፡
ጌታ በጉልበቱ ይርዳን፡፡አሜን፡፡
ይቆየን፡፡
TEBAREK WENDME! BERTA AGELGILOTIHN YIBARKILH!!
ReplyDeleteEgziabher yistelen
ReplyDelete