Monday 19 May 2014

አንደኛው መስቀል

Please Read in PDF
በህይወት የማይስማሙ በሞት ይጣመራሉ፡፡በክርስቶስ የሚካካዱ ለሰይጣን ሊገዙ በአንድ ያብራሉ፡፡በምድረ በዳ ሰው ለመግደል ፣የሰው ንብረት ለመዝረፍ የሚስማሙ ቀራንዮ ላይ መለያየት ይጀምራሉ፡፡በወንበዴነት ሚስማሙ የክርስቶስ በመባል ግን ይለያያሉ፡፡በኃጢአት የሚጣበቁ በጽድቅ ይነጣጠላሉ፡፡አይለያዩም የተባሉ የኃጢአት ባልንጀሮች ክርስቶስን በማመንና ባለማመን  እስከማይተዋወቁ ድረስ ይከፋፋሉ፡፡
       ቀራንዮ ድካማችን አይጸድቅባትም፡፡ድካማችንን በመስቀሉ ጠርቀን፤ ክፉ ምኞት አንቂ አሮጌውን ሰው ሰቅለን አዲሱን ሰው የምንለብስባት፤ ለአንዱ ጌታ መገዛታችንን በግልጥ ውሳኔያችንን የምንገልጥባት ስፍራ ናት፡፡ቀራንዮ ላይ ብዙ አማራጮች ብዙ መንገዶች የሉም፡፡ብዙ የመዳን ቀመሮች ፣ከሁለት የዘለሉ የድህነት ስሌቶችም የሉም፡፡ቀራንዮ ላይ ሁለት መንገዶች ብቻ አሉ፡፡አንዱ የሲዖል አንዱ ወደእግዚአብሔር ገነት፡፡ሦስተኛ ምርጫ የለም፡፡ብንፈልግም ፈጽሞ ማግኘት አይሆንልንም፡፡
        አንደኛው መስቀል ላይ ዘመኑን በውንብድና የጨረሰ፣ለክፋቱ ዳርቻ ሳያበጅ ከነክፋቱ የተገኘ ለጥፋቱም ተካካይ ፍርድ በህጉ የተሰጠው አንድ ደካማ ሰው አለ፡፡አለም ሞት ብትፈርድበትም ክርስቶስ ግን ዛሬም የርህራሔ እጁን ዘርግቶ እስከማታ "ልጄ ሆይ አትሙትብኝ እኔ ልሙትልህ!!!" እያለ ይለምነዋል፡፡ ከእግዚአብሔር መዝገብ ፍርድ እስካልወጣ አለም ሞት ፈርዳ ለፍርዱ መፈጸም ብትቻኮልም የህይወት ጥላችንን ማንም አያጥፈውም፡፡አለም ሞት ብትደግስም ክርስቶስ ግን የማይደክም የማዳን እጅ ዘርግቶለታል፡፡

         ይህ ሰው ግን የተዘረጋውን እጅ የማያይ ፣ሞቶ የሚያድን አፍቃሪ ጌታውን ማየት የተሳነው ሐኬተኛ ባርያ ነው፡፡የተከደነለትን ነውሩን ፣የበዛ ኃጢአቱን ሳይሆን በሌላው የሚሳለቅ ፌዘኛ ነው፡፡የገረጣ ፊት ፣የቆሰለ ሰውነት፣ የተጋጋጠ አጥንት እያየ ሌላውን ይከሳል፡፡ቁስል አይቶ የማይደነግጥ ፣የደማና የተከሰከሰ አጥንት ተመልክቶ የማይሰቀቅ ስብዕና ምን አይነት ስብዕና ነው?!
        ከሳሽ ሁል ጊዜ ዕውር ነው፡፡ነጩን ማጥቆር እንጂ ነጩን ነጭ ነው ማለት አይችልም፡፡የከሳሽ መንፈስ ያለባቸው ሰዎች የገዛ እናታቸው ነውር እንኳ ሲያወሩ ምንም ሐፍረት አይሳልባቸውም፡፡ይህ ወንበዴ የጌታ ኢየሱስን ደምና ቁስል አይቶ አልደነገጠም፡፡ይልቁን ይሳደብና ይሳለቅ ነበር፡፡ከሳሽነት በሰው ስቃይና ሰቆቃ እንደመዝናናት የሚያስቆጥር ክፉ አጋንንታዊ መንፈስ ነው፡፡
      የዛሬው ዘመን ከቀደሙት ዘመናት ይልቅ በፖለቲካው፣በማህበረሰቡ፣በሥራ ገበታው፣ከሁሉ ከሁሉ "ኃይማኖተኞች በሚባሉት" መካከል ለቁጥር የሚያሰለቹ ከሳሾች የፈሉበት ዘመን ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ጨብጠው ምለው ሰውን በሐሰት የሚከሱና በሰው ላይ በሐሰት የሚመሰክሩ "ታላላቅ" የተባሉና ለምድር የከበዱ በሰው ፊት የተፈሩ አባቶችንና "ወንጌል" የጨበጡ "ሰባክያንን" አውቃለሁ፡፡ከሳሽነት እንዴት ጎጆ እንደሰራብን ሳስብ የሚቀርበው የሽንገላ አምልኮ የቁስል ያህል ይጠዘጥዘኛል!!!! አምላካችን ምህረትን እንጂ መች መስዋዕትን መረጠ!!!!!??
         ባልንጀራችንን ከሰን በገዛ እጃችን የሰማዩን በር በራሳችን ዘግተን "እንደምህረትህ እንጂ እንደበደላችን አይደለም" የሚለው የመዘባበቻ ጸሎት አያዋጣንም፡፡እውነታው አንድ ነው፤ እግዚአብሔር የባልንጀራውን ድካም የሚያወራውን ከንፈር ይጠየፋል፡፡
       አዎ! ያ ወንበዴ የሌላውን ድካም እያወራ ወደመቃብር ወረደ፡፡በብዙ ትለምነው የነበረችውን የጌታን የምህረት እጅ ተጠየፈ፡፡ከሳሽ የሰውን እንጂ የራሱን ኃጢአት ማየት ስለማይቻለው የሰውን እንዳየ ፣ የሰውን እንዳወራ የተሰጠውን ዕድል ሳይጠቀም ሞቶ ተቀበረ፡፡የሰውን ነውር የሚገልጡ የራሳቸውን ነውር ሳይከድኑ ወደመቃብር ይወርዳሉ፡፡በሰው ሲፈርድ እርሱ በሚብስ ፍርድ ተወገደ፡፡   
         እኛ ኃጢአታችንን ብንናዘው ዲያብሎስ ፈንታ ያጣል፡፡እኛ ግን የራሳችንን ሸሽገን የሌላውን ነውር ብናወራ ዲያብሎስ አንዳች ሳይስት ያለመታከት ያወራዋል፡፡እኛ ብዙውን ኃጢአት ነው ይቅር የተባልነው፡፡ ታዲያ ትንሹን የባልንጀራችንን ኃጢአት እንገልጥ ፣እናወራ ዘንድ ማን ሾመን? መስቀላችንን ተሸክመን በዝምታ ካልታገስነው ተቸንክረን እንኳ ክብር የለንም፡፡መከራውንም ተቀብለን ዋጋና ሽልማት የለንም፡፡ያ ወንበዴ በመስቀል ተሰቅሏል ግን የመስቀሉን ቃል ክብር አይለብስም፡፡ደምቷል ፣አንብቷል እንባውን ግን ከአይኑ የሚያብስ የለም፡፡ከሳሽነት ዘላለማዊውን ክብራችንን እንኳ እንዳናይ ዓይናችንን በጨለማ ይጋርደዋል፡፡
       ወዳጆቼ! ለምን መከራውን ብቻ ትቀበላላችሁ? ለምንስ እየተሰቀላችሁ እየደማችሁ ዋጋችሁን ታጣላችሁ? በክርስቶስ ርህራሄ ልለምናችሁ … በመስቀላችሁ ላይ ዝም በሉና ታገሱ!!! የቁስላችሁን ጥዝጣዜ ሳይሆን የተተወላችሁን ኃጢአትና ያበዛላችሁን ይቅርታ እያሰባችሁ ስለባልንጀራችሁ ኃጢአት አንቡ ፤አልቅሱ እንጂ በአንዳች ማንንም አትክሰሱ!!!
        ጌታ ክብር ካለበት፣ስለወንጌሉ መዋረድን ከማይታገስ፤ ከከሳሽነት መስቀል ያውርደን፡፡አሜን፡፡



No comments:

Post a Comment