Sunday 4 August 2013

እረግጣለሁ ገና



የአሸዋ ላይ ሕንፃ ለነፋስ እስክስታ
የነፋስ ላይ ጐጆ ለእሳት ተሰጥታ
የውኃ ላይ ኩበት ዝም ብሎ ጉዞ
ዕረፍት አልባ ትጋት ፈዞና ደንግዞ

ቦግ ብሎ ድርግም ብልጭ ብሎ ጠፊ
ገደቡን የጣሰ እጅግ በጣም ሰፊ …
     ቢሆንም ይህ ዓለም
     ድንግዝግዝ ጭልምልም
     አያረገርግም ቤቴ ድምድማቱ
     ዐለቴ አንተ ሆነህ ሥነ- መሠረቱ፡፡ 
የላመ የጣመ ፍርጥምጥም ሰውነት
ሕዋን ያስጨበጠ የመጠቀ ዕውቀት
እንደሰም አቅልጦ
እንደገል ቀጥቅጦ
ሁሉን ቢያስገዛልኝ  ሥልጣኔ 'ረግጦ
ሊያኖረኝ አይችልም አኑሮኝም አያውቅ
መሠረተ ሕይወት አንተ ነህ የ’ኔ አባት::
         የእምነት ምሰሶ የገርነት ወለል
         የትህትና ጣሪያ የየዋሃት ጉበን
         እራስን የመግዛት ሌላንም የቻለ ውብ ብርቱ ማዕዘን
         የነፍሴ አዕማዳት ቤቴ የቆመበት
         እኒህና ሌሎች ደገኛ ምግባራት
        በፍፁም አይደሉም እኔን ያስጠለሉ
        መሠረቴ አንተ ነህ አንተ ካለህ ብቻ እኒህ ሁሉ አሉ፡፡
እርፌን አልጨብጥም የኋሊት ለማረስ
አንተን ትቼ ሌላ ልመሠርት አዲስ
በደም ዋጋ ቤቴን ያነጽክ ኢየሱስ ሆይ
ፍፁም አልታወክ የለም አልናወጥ የስምህ አገልጋይ
ገና በእግሮቼ እረግጣለሁ ደግሞ ከደመናት በላይ፡፡



1 comment:


  1. " … ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።" እንዲል ቃሉ አዎን ገና ክብራችንን ከደመና በላይ በመርገጥ እናየዋለን፡፡ተባረክ ወንድሜ፡፡

    ReplyDelete