Wednesday 7 August 2013

ታናሽነት


         እግዚአብሔር ሥራውን የሚሰራው እንደሰው ልማድ አይደለም፡፡ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በእኛ ታሪክ ውስጥ ለእኛው ቢሆንም የሥራው ዋና ባለቤት እግዚአብሔር  ሥራውን እንደፈቃዱ ብቻ እንደሰራ በመንፈስ ከሆንን ማስተዋል አያዳግተንም፡፡
         ታናሽነት በሰው ፊት ከማይፈለጉና  ከሚናቁ ነገሮች የመጀመርያ ተርታ ላይ ያለ ነገር ነው፡፡ እንደሰው ልማድ ታላቅና የመጀመርያ መባል የሚያስከብርና ቦታን የሚያሰጥ ሥፍራ ነው፡፡ ስለዚህም ታላቅና የመጀመርያ ለመባል የማያባሩ እልፍ እልቂቶችና የመጨካከን የጦርነት ዘመኖችን ምድራችን ከማተናገድ አላረፈችም፡፡
           ሁላችን የእጁ ፍጥረቶች ሆነን ተፈጥረን ሳለ (ሸክላ ሰሪው ጌታ የሚያድፍ የመሰላቸው በዝሙት የሰከሩ አንዳንዶች "እጁን ታጥቦ" የፈጠረሽ ሲሉ ባያፍሩም) በቁሳዊው ነገር ለመበላለጥ ህያው አካል ያለውን ነፍስ ለማጥፋት መሮጣችን ላስተዋለው ከነውር የከፋ ድርጊት ነው፡፡ በተቃራኒው በእግዚአብሔር ከተወደዱ መልካም ነገሮች  ያልተናቀን ፣ዝቅ ያለን ታናሽነት እንደሚመርጥ ስናይ "ሥራህ ግሩም" ጌታ ነህ ብለን እጅን በአፍ እንጭናለን፡፡


            መዝሙረኛው ባለበገና እንደተናገረ እግዚአብሔር ትልቅ ነው፡፡ ትልቁ ጌታ የሚፈልገውና ውዱ የምትወደው ታናናሾችን ነው፡፡ ይህን እውነት ለማረጋገጥ አንድምታ ማጥናት ፣ታላቁን መጽሐፍ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራዕይ  መዝለቅ አያሻም፡፡ ገና አንደኛው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት ላይ የበዙ አብነቶች አሉ፡፡
            ጌታ እግዚአብሔር ከታላቁ ቃየል ይልቅ የታናሽ ታናሽ ሴትን መረጠ፣ከያፌትም ይልቅ የሴምን ድንኳን ለማደርያነት ፣ ከእስማኤልም አብልጦ የሳቅን ልጅ ይስሐቅን ፣ ከብርቱውና ከአዳኙ ኤሳውም ይልቅ ያዕቆብን ወደደ፣ ከያዕቆብም አስራ ሁለቱ ልጆች መካከል ታላቁን ሮቤልንና ስምዖንን ትቶ ታናናሾቹን ይሁዳንና ዮሴፍን የመንግስትን በትር በእጃቸው አስጨበጠ፣ ከምናሴም ይልቅ ኤፍሬምን ፣ እጅግ አቀረበ፡፡
             እንኪያስ ተመልከቱ! እኒህ ሁሉ ምስክርነቶች ያሉት ገና በአንደኛው መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ ብንቀጥል ከሙሴ እስከዳዊት ከዳዊት እስከድንግል ማርያም ከድንግል ማርያም እስከደቀ መዛሙርቱ የተመረጡት ታናናሾችና በሰው ፊትም የተናቁ ሥፍራም ያልነበራቸው ናቸው፡፡ከሰው ልብ ተገፍትረን ካልወጣን ወደእግዚአብሔር አደባባይ በክብርና በድፍረት መውጣት አንችልም፡፡ሁለቱን ለማስማማት ማሰብም (በሰው ተወዶ በእግዚአብሔርም ላለመጠላት ማሰብን) ክርስቶስና ቤልሆርን የማስታረቅ ያህል ነው፡፡
            እግዚአብሔር ባዶነታቸውን  ለሚያምኑ ታናናሾች የፀጋውን ልብስ በምልዐት ያለብሳቸዋል፡፡ያለን ነገር የማይኖር ያለው ጌታ ግን በግርማ የሚያኖር ኃያል ነው፡፡እግዚአብሔር ታላላቆቹን ያልወደደው ስለልባቸው ትዕቢት እንጂ ታላቅነት ኃጢአት ስለሆነ አይደለም፡፡ታላቅነት እንደብኩርና በትር ለሚቆጠርባት ምድር የእግዚአብሔር ታናናሾችን መምረጥ የዝቅ በሉ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡
         ታላላቆች ብዙ ጊዜ ህይወታቸውን እንደአለቃ በማዘዝና የበላይነትን በማንጸባረቅ የሚኖሩ ስለሆነ ታናናሾቻቸውን ለማገልገል ይጨነቃሉ የሚናቁም ይመስላቸዋል፡፡ትልቁ ጌታ ኢየሱስ ፍጹም የታዘዘ ጻድቅ ባርያ መሆኑን  ሲገልጥ ከማዕድ በኋላ የሚደረገውን እግር ማጠብ ከእራት በፊት በመፈጸም ታላላቅ ነን የሚሉ ዝቅ ብለው በታናሽነት እንዲያገለግሉ በህይወት አሳይቷል፡፡ታናሽነት በሰው ፊት የሚናቅ ቢሆን እንኳ ህያው ጌታ እግዚአብሔር የሚከብርበት የህይወት ጥበብ ነው፡፡ሰው መልክ ያያል ጌታ ግን ልብ ፣ሰው ቁመት ያያል እግዚአብሔር ግን የልብን ማስተዋል፣ ሰው የበራ የቀላ ቆዳን ያያል ጌታ እግዚአብሔር ግን የመንፈስን ብሩህነት፣ ሰው ቁሳዊውን ትልቅነት(ቤት፣ መኪና፣ ማዕረግ፣ ስልጣን…)ያያል ጌታ ግን ክቡር ሰውነትን የከበረ ታናሽነትን ያያል፡፡
         የእኛ ታላቅነት የጌታን ድካም ስለማይረዳ ጌታ ታናናሾችን ለብርቱ ሰልፍ ያሰለጥናል፡፡የዛሬዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ሰው ያደነቃቸውንና ያተለቃቸውን "ሰባኪ፣ ቄስ፣መጋቢ፣ ዘማሪና ጳጳስ" ይዘው በእግዚአብሔር ፊት ታናሽ ነኝ ማለት ጭንቅ ሆኖባቸዋል፡፡ ሁሉም የሥልጣን በትር መጨበጥ ያምረዋል፡፡ እግር የምናጥበው በአመት አንዴ "ለመታሰቢያ" እንጂ አገልግሎት ነው ብለን አይደለም፡፡
       ሽብርክ ብሎ ዝቅ ማለት ከኢትዮጲያዊነት የሥጋዊነትና አለማዊነት ወኔ ጋር ተደባልቆብን ለመንፈሳዊ ነገር ዝቅ ማለትን ጠልተነዋል፡፡ስለዚህ ራሱን ፣ ስሜቱን ለአምላኩ ካስገዛው ይልቅ ለእኛ ትልቁ ጀግና አስሩን ደራርቦ የገደለው ነው፡፡በቤቱም ካሉ አገልጋዮች ይልቅ አሻግሮ ወዲያ እየቀላወጡ አርቲስትና ዘፋኝ መንደር የሚያቅበዘብዘው በታናሽ ላለመገልገል የሚሻ አመንዝራነት ነው፡፡
      ታላቅ፣ አንደበተ ርቱዕ ቀልጣፋ ተናጋሪ አሮንን የምትሹ ሆይ ጌታ የሚከብረውና ሥራውን መስራት የሚሻው በትንሹ በአፈ ትቡ ቋንቋ እንኳ በማይቀናለት ቅዱስ ሙሴ ነውና "ታላቅ" በመፈለግ ለተቅበዘበዛችሁበት ዘመን ዛሬ ንስሐ ግቡ፡፡ ቃሉም እንዲህ ይላል፦
                         "ይህን እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ፥ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው።"(1ጢሞ-4÷11-12)
                               ማንም ታናሽነትን አይናቅ፡፡
                    ተወዳጆች ሆይ! የክብር መንፈስ ይብዛላችሁ፡፡አሜን፡፡

2 comments:

  1. abu tebarek ehe tabotina xaot yitedebalekebet zemen wengelin bekedenu teretachewin zergitew kemiyalazinu yihe biyanekache tanashinet werdet ayimselachew ....amen

    ReplyDelete

  2. 8 ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።
    9 እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤

    10 ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።

    ReplyDelete