Friday 30 August 2013

"ነገር ሁሉ ለበጎ አይደለም !!! "

Please read in PDF
      የመጽሐፍ ቅዱስን ሙሉውን ሃሳብና መለኮት ለእኛ ያለውን ዘላለማዊ እቅድ ማወቅና ማመን የሚቻለን የተነገረውን ቃል በትክክል ማንበብና መረዳት ሲቻለን ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ እጅ ጠምዝዞ የመተርጎምና ከተነገረለት አላማ ውጪ አመሳስሎ ማቅረብ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን በእኛ ዘመን በሚያሳዝን መልኩ ይስተዋላል፡፡
         "እግዚአብሔርን እንወደዋለን እናመልከዋለን" የሚሉ ብዙ ሰዎች እርሱን መውደድና ማምለክ ማለት መነሻውና መድረሻው ለእርሱ ቃል መገዛትና ቃሉን ማክበር መሰረት እንደሆነ ቢያስተውሉ እንዴት የተወደደ ነበር!!! ለቃሉ ክብርን ሳይሰጡ "እግዚአብሔርን " እንወደዋለን ማለት በሌላ ትርጉም የአምልኮ መልክ ይዞ ሙሉ ኃይሉን ከመካድ እኩል ነው፡፡

        በትክክል ቃሉ ከተነገረለት አንጻር ከማይጠቀሱ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መካከል አንዱና በብዙ የመኪናና የተለያዩ ስቲከሮች ላይ ከተጻፉት ውስጥ "ነገር ሁሉ ለበጎ ነው" የሚለው ቃል ነው፡፡
      "ነገር" የሚለውን ቃል መዝገበ ቃላቱ (የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፤1948 ገጽ 626 ) "ወሬ፣ የቃል ፍሬ ከድምጽ ጋራ የሚሰማ፣ በጥፈት በአንደበት የሚገለጥ፣ ከልብና ከአፍ የሚወጣ፣ ክፉውም በጎውም ማናቸውም ኹሉ…" እያለ ይፈታዋል፡፡በዚህ አፈታት ቃሉ ለክፉም ለመልካምም መጠቀስ የሚቻልና የተነገረለትን መሰረታዊ አላማ ካልተገለጠ ሊተላለፍ የተፈለገውን ሐሳብ ከመሳቱም በላይ አሉታዊ ጎኑ ያመዝናል ማለት ነው፡፡
       አንድ ነገር ሲነገርም ሆነ ሲፈጸም የተነገረበት ወይም የተፈጸመበት መነሻ ነገሩ እንጂ ከውጤቱ ተነስቶ መደምደሚያ መስጠት አይቻልም፡፡ አንድ ሰው ትዳር እያማገጠ በሴሰኝነት ተይዞ ወደማረሚያ ቤት ቢወርድ፤ ወህኒ ቤት መውረዱ እንደመጽሐፍ ቃል"ነገሩ የሆነው ለበጎ አይደለም"፡፡ ዮሴፍ ግን ከጲጥፋራ ሚስት ጋር አላመነዝርም ብሎ ወደእስር ቤት ቢወርድ  "እግዚአብሔርን ስለመውደዱ እንደሐሳቡም  ተጠርቶ ኃጢአትንና ኃጢአተኝነትን በመጥላቱ ደርሶበታልና ነገሩ የሆነው ለበጎ ነው፡፡ሌላ ምሳሌ፦አንድ ሰካራም ማታ ጠጥቶ ሲረብሽ ፖሊስ ይዞት ማረፊያ ቤት ቢያቆውና በዚያው ተፈርዶበት ማረሚያ ቤት ቢወርድ "እንዴት ነገሩ ለበጎ ይሆናል?"፡፡ ቅዱሳኑ ጳውሎስና ሲላስ ግን ቃሉን በስብከት ፣በትምህርትና በዝማሬ እያገለገሉ ያለፍርድ ዘብጥያ ቢጣሉ እንደሀሳቡ ተጠርተው እግዚአብሔርን በመውደዳቸው ይህ ደርሶባቸዋልና ነገሩ በተወደደ መልኩ ለበጎ ሆኖላቸዋል፡፡
       እንግዲህ አስተውሉ!! ነገር የሚለው ቃል በራሱ ሙሉ አይደለም፡፡ነገር ሁሉ ሲል ደግሞ ክፉውንም ደጉንም ሊያካትት እንደሚችል ልብ በሉ፡፡ ቃሉ ግን እንዲህ ነው የሚለው፦
    “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም  ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን”፤ (ሮሜ.8÷28)
    እንዲህ ሲሆን ቃሉ ሙሉ ነው፡፡  ነገር ሁሉ ለበጎ የሚሆንላቸው ወይም በጎ የሆነውን ነገር ሁሉ ለማድረግ እግዚአብሔር አብሮ የሚሰራው እግዚአብሔርን  ለሚወዱትና እንደ አሳቡም ለተጠሩት ብቻ ነው፡፡ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው ማለት የሚቻለው ከእግዚአብሔርና ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ሲገናኝና ሲያያዝ ነው ማለት ነው፡፡ አልያ ግን ነገር ሁሉ ለበጎ አይደለም አይሆንምም፡፡
     እግዚአብሔርን የመውደድ የመጀመርያው መገለጫ  ለእርሱ መታዘዝ ነው፡፡ በእርሱ መታዘዝን ሳንለምድ በራሳችን አመጸኝነትና አለመታዘዝ ላገኘን ነገር "ለበጎ ነው" ብንል ቃሉም እግዚአብሔርም አላለንም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህንንና የተጠራንበትን ምክንያት ሲተነትን እንዲህ ይላል፦
          በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ምስጋና   ይገባዋልና። ኃጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል። የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና" (2ጴጥ.2÷19-21)፡፡
     እንደሐሳቡ ከተጠራን የምንከሰስበትም የሚያገኘንም ነገር ሁሉ በእግዚአብሔርና በስሙ ነው፡፡ይህ ደግሞ ክብር አለበትና ሁልጊዜ ለበጎ ሁሌም ለሽልማት ነው፡፡ ቅዱሳን ያገኛቸው የነበረው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔርና በስሙ ስለነበር ጌታ ከእነርሱ ጋር ሆኖ መከራውንም፣ እስራቱንም፣ ከእሳትና ለአንበሳ መጣሉንም፣ መሰደዱንም፣ በወኅኒ መወርወሩንም፣ መሰየፉንም፣ መሸለቱንም ለበጎ እንዲሆንላቸው አብሯቸው ሠርቷል፡፡
      የክፋትና የግፍ ነገራችንን ሁሉ የእግዚአብሔር ለማስመሰል "ነገር ሁሉ ለበጎ ነው" አንበል፡፡ እግዚአብሔር ከተደረገው ነገር ይልቅ የተደረገበትን ልብና ኩላሊት መንፈስንም የሚመዝን አምላክ ነውና ለቃሉ ክብርን እንስጥ፡፡  " … እግዚአብሔር ግን መንፈስን ይመዝናል" (ምሳ. 16÷2) ለቃሉ እንታዘዝ እንጂ ቃሉን ወደእኛ ሐሳብ አንጠምዝዘው፡፡ ቃሉ የተነገረው እንዲህ ነው፦ 
"እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም  ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።"(ሮሜ.8÷28)
      እግዚአብሔርን ለምትወዱ እንደሐሳቡም ለተጠራችሁ እግዚአብሔር በጎውን ነገር ሁሉ ከእናንተ ጋር ለማድረግ ይሰራልና ደስ ይበላችሁ!!! ስለዚህም እግዚአብሔርን ለሚወዱት ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡ አሜን፡፡


6 comments:

  1. ጌታ በብርታቱ ያበርታህ እይታዎችህ ደስ ይላሉ እንደቃሉ ብቻ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ያረካሉ፡፡በርታ በርታ በርታ…………….

    ReplyDelete
  2. kale heywet yasemalen tebarek

    ReplyDelete
  3. Ohhhhhh Endet yemitafet agelales new,egziabher tsegawen yabzaleh kale hiwot yasemalen erejim edeme ketena gar yisteh Berta egziabher kehulachin far yihun amen!!

    ReplyDelete
  4. Amen kale hywetn yasemaln edmena tsegawn yabzalh ye mistir balebet egziabher amlak mistrun ygletslh berta!!!

    ReplyDelete
  5. Ewnet new kale hiwot yasemah

    ReplyDelete
  6. አሜን በክርስቶስ ኢየሱስ በተጠራንበት መጠራት ወንድሜ የምትሆን አንተ ሆይ በእምነት እልሀለሁ፡፡ በሚያስፈልግን ነገርሁሉ አምላኬ በክርስቶስ ኢየሱስ በረከቱንና ፀጋውን ይሰጥህ፡፡ ደግሞም ፈቃዱን ለማገልገል ጌታ ይርዳህ፡፡ የአምላክህን ሀሳብ በዘመንህ ሁሉ በእውነት አገልግልህ በክብር ወደ እርሱ መጠቅለል ይሁንልን፡፡

    ReplyDelete