Sunday 18 August 2013

የምስክርነታችን ማህተም

   Please read in PDF
     ከገሊላ ባህር በስተሰሜን ከሔርሞን ተራራ ተዳፋት ሥር ባለችው የፊሊጶስ ቂሳርያ በምትሆነው ከተማ ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ ቀላል ግን ሰማያዊ መገለጥ ከሌለበት የማይመለስ ጥያቄ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው ፡፡(ማቴ.16÷13)፡፡ደቀመዛሙርቱ ሰዎች የሚሉትን ብዙውን ተናገሩ፡፡ዋናው የተፈለገው የእነርሱ ሐሳብና መልስ ነበር፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ከሁሉም ቀድሞ በሰማያዊ መገለጥ በሥጋ ተገልጠህ ያየንህ ፍጹም ሰው የእግዚአብሔር ልጅም የሆንክ ፍጹም አምላክ ነህ ብሎ መሰከረ፡፡
https://4.bp.blogspot.com/-1XkOSpo4--8/UhEIMtDa9QI/AAAAAAAAAGY/Cu_cjOdlz3A/s320/life-of-jesus-pic-08.jpg

      ይህ የጴጥሮስ ምስክርነት ለፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሳቸው ዋና መፍትሔ መሲሁ እንደሆነ ለሚያስቡ አይሁድ እንዲሁ በቀላሉ የሚታመን ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እነርሱ መሲሁን በልዩ ክብር እንጂ እንዲህ ከድኃ ቤተሰብና ከዝቅተኞች ጋር ይኖራል ብሎ የጠበቀው እጅግ በጣም በጣም ጥቂቱ ነው፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ምስክርነት ለደቀ መዛሙርቱ ለራሳቸው አጠራጣሪ የሆነበት አንዱ ምክንያት ይህም ነበር፡፡ ሰገነት ላይ ሲጠብቁት በበረት፣ ከእቴጌዎቹ ሲጠበቅ በናዝሬት ካለች ትንሽ ብላቴና፣ ከልዑላኑ ተርታ ሲገመት ከድሆች ጋር መዋሉ ለብዙዎች አልተዋጠላቸውም፡፡ ዛሬም ትልቁ ችግር ይኸው ነው ወንጌሉ ትልልቅ በተባሉት በኩል ቢደርሰን እንጂ የሰውን ዓይን ያልሳቡት ሲነግሩን ጆሮዎቻችንን ያሳክከናል፡፡ እንኳን ልንሰማ ገና ከአቀማመጣችን እንበላሻለን፡፡
      የጴጥሮስ ምስክርነት ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ (ብቃት ያለው አዳኝ) መሆኑን ገለጠ (ማቴ. 17÷20) ይህንንም ለማንም እንዳይገልጡ (የመስቀሉ ጉዞ እንዳይደናቀፍና አለጊዜው እንዳይሆን) እንዳይናገሩም አስጠነቀቃቸው፡፡ ዋናውን ነገር ሞቱንና መከራውን ግን ከዚያን ቀን ጀምሮ መናገር ለእነርሱም መግለጥ ጀመረ፡፡የመጣበት ትልቁ አላማ ሞቱ ነው መሆን ያለበትም በጊዜው ነው፡፡ ክርስቶስ በመምጣቱና ከእኛ እንደአንዱ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በሞቱም ጭምር የአባቱን ጊዜና ፈቃድም የጠበቀ ነው፡፡ በአገልግሎታችን፣ በመልካምነታችን ብቻ ሳይሆን በመከራችንና በሐዘናችን ሁሉ አባት አብን እናከብር ዘንድ ኢየሱስ በህይወት አስተማረን፡፡
      ከስድስት ቀን በፊት በፊሊጶስ ቂሳርያ የተነሳው ጥያቄና የተሰጠው መልስ የክርስትናው ማዕከላዊ መሰረት ነው፡፡ይህን ህያው እውነት ያልተረዱና የተጠራጠሩ ነበሩ፡፡ይህን ህያው እውነት ሊያስረግጥና ምስክርነቱ የታተመ የጸናም እንዲሆን ከፊሊጶስ ቂሳርያ በሰሜን ምስራቅ በኩል በሚገኘው የአርሞንዔም ተራራ (በተለምዶ የታቦር ተራራ) እየተባለ በሚጠራው እርሱ ሊጸልይ ሲወጣ (ሉቃ.9÷28) ከአንድ መቶ ሐያ ቤተሰብ በጣም ለይቶ ካቀረባቸው አስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካካል ሦስቱን አዕማድ (ዋና) ሐዋርያት ጴጥሮስን ያዕቆብንና ዮሐንስን መርጦ በመያዝ ወደተራራው ወጣ፡፡ እነዚህ ብርቅዬ አገልጋይ ሐዋርያት ለቅዱስ ጳውሎስና ለቅዱስ በርናባስ ወደአሕዛብ ሄደው እንዲያገልግሉ ቀኝ እጃቸውን ሰጥተዋቸዋል (ገላ.2÷9)፡፡ አገልግሎት በተሾምንበት ጸጋችንና በየድርሻችን ሲሆን ሁሌም የምናተርፍ ምርኮም የምናበዛ ነን፡፡ አንዱ የሌላውን ጸጋና ድርሻ ካላከበረ ወደፊት የሚደረግ ጉዞ ይቀርና ባለንበት መገፋፋት እንጀምራለን፡፡
      ይህ የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን የከሰረችበት አንዱ መልክ ነው፡፡ስንገፋፋ ብዙ እድሎች አምልጠውናል፡፡ ድርሻችንን እንደጸጋችን መጠን ስላልተከፋፈልን ሁሉንም ለመያዝ ስንሮጥ እኛው ተናጋሪ፣ እኛው መካሪ፣ እኛው ላኪ፣ እኛው ተላኪ፣ እኛው መምህርና ተማሪ ሆነን የቱን ከምን መለየት እስኪያቅተን ተደባልቆብናል፡፡ ዛሬ አህዛብ የሚፈነጩባቸውና ማዕከላቸው የሆኑባቸው ቦታዎች "አጥምቁን አስተምሩን ልጆቻችሁ እንሁን " ብለው ይለምኑ የነበሩ ወገኖቻችን መሆናቸውን በቅርብ የምናስታውሰው ትዝታችን ነው፡፡እርስ በእርስ ስንነካከስ ግን ሊያመልጠን የማይገባ ትልቅ የወንጌል እድል አምልጦናል፡፡
     ስለዚህም በዚያ ለሦስቱ ደቀመዛሙርት በግርማው ታየ፣በፊታቸውም ተለወጠ፣እንደብርሐን ነጭ እንደፀሐይም አበራ በክብሩም በፊታቸው ተገለጠ፡፡ በዳግም ምጽአቱ የሚገለጠው ፍጹም ክብሩ በፊታቸውም በተገለጠ ጊዜ በብሩህ ደመና ቃል መጣ፡፡" በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል" (ማቴ.17÷5)፡፡ አብ በሕይወቱም፣ በሞቱም፣ መስዋዕት ሆኖ ዓለምን በማዳኑ ደስ የተሰኘበት ብቸኛና ውድ ልጁ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና በመታዘዝ እንሰማው ዘንድም ለእኛም ተነገረን፡፡
         ይህን ታላቅ ምስጢር ጌታ ከሙታና እስኪነሳ ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው፡፡ ከሙታን እስክነሠ አለ እንጂ አትናገሩ አላለም፡፡ ከሙታን መካከል በኃይልና በሥልጣን በተነሳ ጊዜ ግን በቃል የሰሙትን እንዲሁ በዓይኖቻችን አይተዋልና ሌላ ምስክርነት አላስፈለጋቸውም፡፡ የእርሱን ግርማ በአይናችው ማየታቸውንም ጮኸው ሰበኩ፤ (2ጴጥ.1÷16)፡፡ ይህ ያዩት ክብር ለሚመሰክሩለት የወንጌል እውነት እንደማሕተም ያለ ማስረገጫ ነው፤ እናም በሰው ብልሐት የተፈጠረ ተራ ድርሰትና ልብወለድ ነክ ተረታ ተረት ሳይሆን በዚያ በቅዱሱ ተራራ ላይ በነበሩ ጊዜ ያዩትን ግርማዊ መለኮታዊ ክብርን መሰከሩ እንጂ፡፡
     እነርሱ እርግጠኞች ሆነው ያልጨበጡትንና ያላመኑትን ለሌላው መስጠትና ማስጨበጥ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ጌታ እነርሱ ሙሉ ለሙሉ ለሚመሰክሩለት ምስክርነት እርግጠኞች እስኪሆኑ ብዙ ነገርን አስተማራቸው አሳያቸውም፡፡ 
       ክብሩንና ግርማውን በዚያ በቅዱሱ ተራራ ያየኸው ሆይ!!! የእውነቱን ወንጌል ጨክነህ ተናገረው፤ ክብሩን እንዳየኸው ብቻ የምትቀር አይደለህም ገናም ትለብሰዋለህና በርታ፡፡ ውዱ የጌታን ወንጌል የምታገለግለውና የምትኖርለት ወንድሜና ቤተሰቤ ሆይ! ልትመሰክር አንደበትህን ከማላቀቅህ በፊት አንተው የምትናገረውን ቀድመህ እመነው፡፡ ያላመነ አያሳምንም፣ ያልተማረከ አይማርክም ፣ያልደቀቀ አያደቅቅምለዚህ ዓለም ነገር ያልሞተ የክርስቶስ ህይወት በእርሱ አይሰራም፡፡
            አቤቱ ግርማዬ ሆይ! ነፍሴ ትታመንብሐለች፡፡አሜን፡፡


4 comments:

  1. wendme tsegawun yabzalh. dinkina astemari tsihuf new.berta berta atakumew.achir gn batadergew tiru new.

    ReplyDelete
  2. Can I say this the bible as the final authority for our faith and practice.I never log in UR blog before here I got some thanks God.awesome job GOD BLESS YOU bra.

    ReplyDelete