Sunday 7 July 2013

አንድ ሰው


please read in PDF

     አገልግሎት የሚጀምረው ከአንድ ሰው ነው፡፡ ከአንደ ሰው የማይጀምር ፣ አንድ ሰው የማያከብር አገልግሎት ደጋፊ እንጂ አማኝ አያፈራም፡፡ ይህን እውነት ያስተማረን ትልቅ ሰው መድኃኒአለም ነው፡፡ ጌታ በአደባባይ ካገለገለው አገልግሎት ይልቅ ብዙ አንድ ሰዎችን ያገለገለው አገልግሎት ይበዛል፡፡ ሁል ጊዜ ከአንድ የሚጀመር ማንኛውም ነገር ጤናማና የስኬት እውነተኛ መንገድ ነው፡፡

     እውነተኛ ሰባኪ ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም ብዙ ኪሎ ሜትር ወደምትርቀው የሰማርያ ከተማ በእግሩ ተጉዞ ደክሞ እንደደረሰ ታላቁን የሕይወት ቃል የያዘው መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ ይህች ሴት ውኃ ቀጂ በንግግሯ ደግሞ አሷፊ፣ አስሟጣጭ፣ አሽሙረኛ … ነበረች፡፡ ጌታ ግን ታግሶ ብዙ አደመጣት፡፡ ማድመጡ እንድታደምጥ ፣የፍቅር አይኖቹ ራሷን እንድታይ ፣ ትዕግስቱ ወደንስሐ … መራት፡፡ ማንም አያውቅብኝም ያለችው ገመና በእርሱ ፊት የተገለጠ መሆኑን አስተዋለች፡፡ ገመና አዋቂ ብቻ ሳይሆን ብቸኛውና አንዱ ገመና ሸፋኝ የተናፈቀው ነቢይ መሢሕ መሆኑን አመነች፡፡ ያመነችውን በአንደበቷ ተናገረች፤ ልሷ ሰማችውን ለከተማይቱ ሰዎች ሄዳ ጮኻ ሰበከች … አንዲቱ የሰማርያ ሴት የከተማውን ሕዝብ ነቅላ ወደጌታ አመጣች፡፡
      አንድ ሰው ላይ ስንለፋ እግዚአብሔር በዚያ ሰው ውስጥ ሚሊዮኖችን አማኞች ያያል፡፡ የጌርጌሴኖኑ እብድ፣ የኢያሪኮው አይናማ፣ የመግደሎሟ ምርጥ ሴት፣ ሽቱ ቀቢዋ ሴት፣ አጭሩ የኢያሪኮ ባዕለጠጋ፣ አሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችው ሴት፣ ብዙ አንዶች …. ቤተ ክርስቲያን የተሠራችው፣ የተሰበሰበችው በእነዚህ ምርጥ ምርጥ (ካህል) በወንጌሉ ጥሪ በተጠሩ (አክሌስያ) አንድ አንድ አማኞች ነው፡፡
     ጌታ ብዙ ጊዜውን ያሳለፈው ከበጣም ጥቂት ሰዎች ጋር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በብዜት ለመሥራት “ሠሪዎቹን” በብዙ መሥራት ፣ መቅረጽ፣ መሳል፣ ለመንፈስ ቅዱስም አደራ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አሥራ ሁለት ሰዎች ለአለሙ ይበቃሉ ብሎ (ያውም ሁሉ ነገራቸው የማይገጥም አስቸጋሪ ሰዎች) ሥልጠኛ መጀመር በአለሙ ፊት እብድት ወይም ሞኝነት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን አሻግሮ በክርስቶስ የተጠቀለለችውን ቅድስት ሕብረት ቀድሞ አይቷል፡፡ ስለዚህ ጌታ ረዥሙን ጊዜ አንድ እያለ ከጠራቸው ደቀ መዛሙርት ጋር አሳለፈ፡፡
     በክርስትና አንድ ሰው ብዙ ነው፡፡ አንድ ሰው ከጨከነ ምድሪቱን ለክፋትም ለበጐነትም ያሰለጥናል፡፡ (በአንድ ወቅት አዶልፍ ሒትለርና ኦሳማ ቢላደን የአልም ሥጋት ነበሩ) አንድ ሰው ሊናቅ አይገባም፡፡ አንድ ሰው እግዚአብሔር ቢሰለጥንብት ድንቅ የሚሠራውን ያህል ሰይጣንም ቢሰለጥንበት የሚሠራውን በማሰብ በአገልግሎታችን ማንንም ላለመናቅ መጠንቀቅ አለብን፡፡
     በአንድ ወቅት “ትልቅ ጉባኤ” (ትልቅ ጉባኤ እስከ የሌላ ጊዜ ርዕስ ይሁን) ተዘጋጀና “ታላላቅ” መምህራንን ተጋበዙ ተባለ፡፡ በአጋጣሚ ጉባኤውን ከሚታደሙ አንዱ ነበርኩ፡፡ ለአይን ባንመላም ሰው ሁሉ ይመጣሉ ብሎ ተስፋ አድርጐ በመጠበቅ ሳለ ድንገት የመቅረታቸው ዜና ተሰማ፡፡ ምክንያት ሲባል ሌላ ሌላ ነገር ቢባልም ለአዘጋጆቹ ቅርብ የሆንን በደንብ እናውቅ ነበር፡፡ (ገጠር ላይ ያውም “ለጥቂት” ምዕመናን ምን ዕዳ በሉ?¡ አይ ታላላቅ?¡)
    አንዱን የጠፋውን በግ ጌታው ፈልጐ ደክሞ ሲያገኝና አቅፎ ሲያመጣው ሎሌው መናቅና መገፍተር ከጀመረ ፍርዱ ምን ይሆን? … አንድ ሰው አዳም ነው … አንድ ሰው እኔ ነኝ … አንድ ሰው አንተ ነህ … አንድ ሰው እርሷ ናት … አንድ ሰው እርሱ ነው … በተዋሕዶ የከበረው ጌታ ኢየሱስ ፈልጐ ያገኘን ቤተ ክርስቲያን እኰ እኛ ነን፡፡ አንዱን ለሕይወት የማይሰራ አገልጋይ የክርስቶስን ሕንጻ ያፈርሳል፤ ከእርሱ ደግሞ የሟቹን ሞት የማይፈቅድ ጌታ ደሙን ከእኛ ይፈልጋል፡፡
    እናንተ አገልጋዮች! ምንድር ነው “በደመቀ” ጉባኤ ላይ የደመቁ ቀሚሶች ለብሶ መንጎራደድ? ሺህ እንጂ አንድ አለማገልገል ከየት ተማራችሁ? ጌታችን የምትሉት እኮ አንድ ሰውን በጽሙና የሚያደምጥ ነው፡፡ በማስተዋል አንጂ ጉባኤ ሰብስቦ በአበጠ ጥፈንዳ ማገልገል አያለማም፡፡ አንድ ሰው ትልቅ ነው፣ አንድ ሰው ብዙ ነው ፣ አንድ ሰው … አንድ ሰው … አገልግሎት መነሻው ጌታ የሞተለትን አንድ ሰው ከማገልገል መጀመር ነው፡፡ ይህን ያላስተዋለ ባያገለግል እጅግ ይሻለዋል፡፡ የምናመልከው አምላክ ጸጉራችን እንኳ በፊቱ የተቆጠረ፣ አንድ ሰው ከብዙ ድንቢጦች የሚበልጡበት ጻድቅ ነው … እናም አገልጋዮች ሆይ! ደጋፊና አድናቂ ሳይሆን አማኝ ለማፍራት አገልግሎታችሁን  እንደጌታ ከአንድ ሰው ጀምሩ … ከአንድ ሰው … ከአንድ … አዎ ከአንድ ሰው …
በነገር ሁሉ ጌታ ማስተዋልን ይስጠን፡፡ አሜን፡፡


2 comments: